በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የዓለማችን ትልቁ አበባ

የዓለማችን ትልቁ አበባ

የዓለማችን ትልቁ አበባ

“ጌታዬ ይምጡ፣ በጣም ትልቅ፣ የሚያምርና አስደናቂ የሆነ አበባ ላሳይዎት” በማለት ጆሴፍ አርኖልድን የሚያስጎበኘው ሰው ተናገረ፤ አስጎብኚው አበባውን ለአርኖልድ ለማሳየት በጣም እንደጓጓ ከአኳኋኑ ያስታውቃል። እነዚህ ሰዎች የኢንዶኔዥያ ክፍል በሆነችው በሱማትራ ደሴት ዕፅዋት እየሰበሰቡ ነበር። የሥነ ዕፅዋት ተመራማሪ የሆነው ብሪታኒያዊው አርኖልድ የተመለከተው ነገር “በእርግጥም እጅግ አስደናቂ” እንደሆነ ገልጿል። በጣም የሚያስገርም አበባ ነበር። ይህ ከሆነ 200 ዓመት ያለፈ ቢሆንም አርኖልድ በ1818 የተመለከተው የአበባ ዝርያ ይኸውም አስደናቂ የሆነው ራፍሊዢያ ዛሬም ቢሆን የዓለማችን ትልቁ አበባ ነው።

በደርዘን የሚቆጠሩ የራፍሊዢያ ዝርያዎች ያሉ ሲሆን ሁሉም የሚበቅሉት በደቡብ ምሥራቅ እስያ በሚገኙ ደኖች ብቻ ነው። ዛሬም ድረስ የዚህ ተክል አዳዲስ ዝርያዎች ይገኛሉ። በትልቅነቱ የአንደኛነት ደረጃ የያዘውን አበባ የሚያስገኘው ተክል ራፍሊዢያ አርኖልዲ ሲሆን ይህ ተክል የተሰየመው በጆሴፍ አርኖልድና በጉዞ ጓደኛው በሰር ቶማስ ስታምፎርድ ራፍልስ ስም ነው፤ ሲንጋፖርን ያገኛት ሰር ቶማስ ሲሆን የዚህች አገር ገዥም ነበር። ይህ አበባ አስደናቂ ውበት ቢኖረውም እቅፍ አበባ ለማዘጋጀት ግን ልትጠቀሙበት አትችሉም።

እንዲህ የምንልበት የመጀመሪያው ምክንያት መጠኑ ነው። ራፍሊዢያ እስከ 1 ሜትር የሚደርስ ይኸውም የአውቶቡስ ጎማ የሚያህል ስፋት ሲኖረው 11 ኪሎ ግራም * ገደማ ይመዝናል። አበባው ሲፈካ የቀይ ቡኒ ቀለም ያላቸው አምስት መልካበባዎች (ፔታልስ) ይዘረጋሉ፤ እነዚህ ወፋፍራም መልካበባዎች በትናንሽ ነጠብጣቦች የተሸፈኑ ናቸው። መሃላቸው ላይ ደግሞ እስከ 6 ሊትር ውኃ መያዝ የሚችል ድስት የሚመስል ሰፊ ቀዳዳ አለ።

በሁለተኛ ደረጃ ልታስቡበት የሚገባው ነገር ደግሞ ጠረኑ ነው። አንድ አሳሽ የራፍሊዢያን ጠረን “ከጠነባ የጎሽ በድን” ጋር አመሳስሎታል፤ ይህ አባባል የዚህን አበባ ጠረን ጥሩ አድርጎ የሚገልጸው ሲሆን ራፍሊዢያ ሬሳው አበባ እንዲሁም የገማው በድን አበባ ተብሎ መጠራቱም የተገባ ነው። * ይህ አበባ እንዲዳቀል በዋነኝነት አስተዋጽኦ የሚያደርጉት ጠረኑ የሚማርካቸው ጥንብ ተመጋቢ ዝንቦች ናቸው።

ራፍሊዢያ ግንድ፣ ቅጠል ወይም ሥር የሌለው አበባ ሲሆን የሚያድገውም በደን ውስጥ መሬት ለመሬት የሚበቅሉ አንዳንድ ተክሎች ጥገኛ ሆኖ ነው። የራፍሊዢያ እምቡጥ ጥገኛ የሆነበትን ተክል ቅርፊት ሰንጥቆ ከወጣ በኋላ አድጎ ትልቅ ጥቅል ጎመን የሚያህል መጠን እስኪኖረው ድረስ አሥር ወር ገደማ ይፈጅበታል። ከዚያም ለመፍካት በርካታ ሰዓታት የሚወስድ ሲሆን መልካበባዎቹ ሲዘረጉ አስደናቂ የሆነው ውበታቸው ይገለጣል። መልካበባዎቹ መሃል ያለው ቀዳዳ ውስጥ እሾህ የመሰሉ በርካታ ጉጦች አሉ። የእነዚህ ጉጦች ሥራ ምን እንደሆነ ገና ያልታወቀ ቢሆንም አንዳንድ ተመራማሪዎች ሙቀት ለማሰራጨትና መጥፎውን ጠረን ለማባባስ እንደሚያገለግሉ ያስባሉ።

ይሁን እንጂ ይህ አበባ እንዳማረበት ብዙ አይቆይም። ከጥቂት ቀናት በኋላ ጠውልጎ መበስበስ ስለሚጀምር በቦታው የሚቀረው ዝልግልግ ያለ ጥቁር ነገር ይሆናል።

ራፍሊዢያ አርኖልዲ ብርቅዬና ከምድር ገጽ ለመጥፋት የተቃረበ ተክል ነው። ለምን? ወንዴና ሴቴ አበቦች የሚዳቀሉት አጠገብ ለአጠገብ ካበቡ ብቻ ነው፤ አብዛኞቹ እምቡጦች ሳይፈኩ ወይም እድገታቸውን ሳይጨርሱ ይሞታሉ። ይህም የሆነው ብዙዎቹ እምቡጦች ተለቅመው ለባሕላዊ መድኃኒትነት ወይም ለምግብነት ስለሚውሉ ነው። በዚህ የተነሳ በዱር የሚበቅሉት አበቦች ብዛት በእጅጉ ተመናምኗል። የአበባው የተፈጥሮ መኖሪያ የሆነው ደናማ አካባቢ እየተራቆተ መሄዱም ይህ ተክል ከምድር ገጽ የመጥፋት አደጋ እንዲጋረጥበት አስተዋጽኦ አድርጓል።

ራፍሊዢያን ማየት ለየት ያለ ስሜት ይፈጥራል። መጠኑ አስገራሚ ጠረኑም የማይረሳ ነው። ቀለሙና ቅርጹም ቢሆን ያስደንቃል። እርግጥ ነው፣ የዓለማችን ትልቁ አበባ ፈጣሪያችን ከሠራቸው ስፍር ቁጥር የሌላቸው አስደናቂ ነገሮች አንዱ ብቻ ነው። መዝሙር 104:24 “እግዚአብሔር ሆይ፤ ሥራህ እንዴት ብዙ ነው! ሁሉን በጥበብ ሠራህ፤ ምድርም በፍጥረትህ ተሞላች” ይላል።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.4 አንዳንድ የራፍሊዢያ ዝርያዎች የአበባቸው ስፋት ከ10 ሴንቲ ሜትር አይበልጥም።

^ አን.5 ቲታን አሩም (አሞርፎፋሉስ ቲታኑም) በመባል የሚታወቀው አበባም ሬሳው አበባ የሚል ቅጽል ስም የተሰጠው ሲሆን ከራፍሊዢያ ጋር የሚምታታበት ጊዜ አለ።​—የመስከረም 2000 ንቁ! ገጽ 26⁠ን ተመልከት።

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ካርታ]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

ማሌዥያ

ሱማትራ

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

“የራፍሊዢያ” እምቡጥ ሊፈካ ሲል