የመካከለኛው ዘመን የሕክምና ሊቃውንት
ብዙዎቹ ዘመናዊ የሕክምና ዘዴዎች አንዳንዶች እንደሚያስቡት በዘመናችን የተገኙ ላይሆኑ ይችላሉ። እንዲያውም በአሁኑ ጊዜ ካሉት የተለመዱ የሕክምና ዘዴዎች መካከል በርካታዎቹ በአንዳንድ አገሮች በመቶዎች ከሚቆጠሩ ዓመታት በፊት ይሠራባቸው ነበር። በመካከለኛው መቶ ዘመን በመካከለኛው ምሥራቅ ይሠራበት የነበረውን ሕክምና እንደ ምሳሌ እንመልከት።
ከሊፋ ሐሩን አልራሺድ መዲናው በሆነችው በባግዳድ በ805 ዓ.ም. አንድ ሆስፒታል አቋቋመ። ከ9ኛው እስከ 13ኛው መቶ ዘመን በነበሩት ዓመታትም ሌሎች ገዥዎች ከስፔን እስከ ሕንድ በሚገኙት የእስልምና ግዛቶች ውስጥ ሆስፒታሎች እንዲገነቡና አገልግሎት መስጠታቸውን እንዲቀጥሉ አድርገዋል።
በእነዚህ ሆስፒታሎች ውስጥ ሀብታሞችም ሆኑ ድሆች እንዲሁም የማንኛውም ሃይማኖት አባል የሆኑ ሰዎች ሕክምና ያገኙ ነበር። በሙያቸው የላቀ ችሎታ ያላቸው ሐኪሞች፣ ታካሚዎችን ከማከም ባለፈ ጥናታዊ ምርምር ያካሂዱና አዳዲስ ሐኪሞችን ያሠለጥኑ ነበር። በሆስፒታሎቹ ውስጥ የዓይን፣ የአጥንትና የውስጥ ደዌ ሕክምና የሚሰጥባቸው እንዲሁም ቀዶ ሕክምና የሚደረግባቸው ብሎም ተላላፊ በሽታ እና የአእምሮ ሕመም ያለባቸው ሰዎች እርዳታ የሚያገኙባቸው የተለያዩ ክፍሎች ተዘጋጅተው ነበር። በየጠዋቱ ሐኪሞች ከተማሪዎቻቸው ጋር ሆነው ሕመምተኞችን ይጎበኛሉ፤ እንዲሁም ሕመምተኞቹ ሊወስዱ የሚገባቸውን ምግብና መድኃኒት ያዙላቸዋል። በሆስፒታሉ ውስጥ የሚሠሩ የፋርማሲ ባለሙያዎች ደግሞ መድኃኒቶችን ይሰጣሉ። በተጨማሪም ልክ በዛሬው ጊዜ እንደሚደረገው በሆስፒታሎቹ ውስጥ መዛግብትን የሚይዝ፣ ወጪዎችን የሚቆጣጠር፣ የምግብ ዝግጅቱን የሚከታተልና ሌሎች የአስተዳደር ሥራዎችን የሚያከናውን የአስተዳደር ክፍልም ነበር።
የታሪክ ምሁራን እነዚህ ሆስፒታሎች “የመካከለኛው ዘመን እስላማዊ ማኅበረሰብ ካበረከታቸው ታላላቅ ሥራዎች” መካከል የሚጠቀሱ እንደሆኑ ይናገራሉ። ደራሲና የታሪክ ምሁር የሆኑት ሃዋርድ ተርነር እንደተናገሩት በመላው እስላማዊ ዓለም “በጤና ሳይንስና በጤና ጥበቃ ረገድ እስከ ዘመናችን የሚደርስ ተጽዕኖ በሚያሳድር መልኩ በሆስፒታሎች ውስጥ ከፍተኛ የሆነ እድገት በመታየት ላይ ነበር።”
ራዚዝ የተወለደው በጥንታዊቷ ሬይ (በአሁኗ ቴህራን ዳርቻ) በዘጠነኛው መቶ ዘመን አጋማሽ ላይ ሲሆን “በእስልምናው ዓለም እንዲያውም በመካከለኛው ዘመን በሙሉ ተወዳዳሪ ያልተገኘለት ሐኪም” የሚል እውቅና አግኝቷል። ይህ የሳይንስ ሊቅ፣ ሙከራውን ሲያደርግ የተጠቀመባቸውን ዘዴዎችና መሣሪያዎች እንዲሁም የነበሩትን ሁኔታዎችና ያገኛቸውን ውጤቶች ሌሎች ባለሙያዎች እንዲገለገሉባቸው በማሰብ መዝግቦ አስቀምጧቸዋል። ሁሉም ሐኪሞች በተሰማሩባቸው መስኮች ከተደረሰባቸው ግኝቶች ጋር እኩል እንዲሄዱ ይመክር ነበር።
ራዚዝ በርካታ ነገሮችን ማከናወን ችሏል። ለምሳሌ፣ የሕክምና ጽሑፎቹ አል ሃዊ (አጠቃላይ መጽሐፍ) በተባለው ባለ 23 ጥራዝ መጽሐፍ ውስጥ የተካተቱ ሲሆን ይህ መጽሐፍ በሕክምና ዘርፍ ትልቅ ቦታ ከሚሰጣቸው ጽሑፎች ውስጥ ይመደባል። ስለ ማህፀንና ሥነ ተዋልዶ እንዲሁም ስለ ዓይን ቀዶ ሕክምና የሚገልጹ ሐሳቦች ለመጀመሪያ ጊዜ የሰፈሩት በዚህ መጽሐፍ ላይ እንደሆነ ይታሰባል። ስለ ፈንጣጣና ኩፍኝ የሚገልጽ እምነት የሚጣልበት ጥንታዊ መረጃ የተገኘው ራዚዝ በሕክምና ዙሪያ ካዘጋጃቸው 56 ጽሑፎች መካከል ነው። በተጨማሪም ራዚዝ፣ ሰውነት በሽታ አምጪ ተህዋስያንን ከሚዋጋባቸው መንገዶች አንዱ ትኩሳት እንደሆነ ተገንዝቦ ነበር።
ከዚህም በላይ በሬይና በባግዳድ ሆስፒታሎችን በመክፈት የአእምሮ ሕሙማንን ያክም የነበረ ሲሆን በዚህም ምክንያት የአእምሮ ሕክምና እና የሥነ ልቦና አባት የሚል ስያሜ አግኝቷል። ራዚዝ ከሕክምና በተጨማሪ የኬሚስትሪ፣ የሥነ ፈለክ፣ የሒሳብ፣ የፍልስፍናና የሥነ መለኮት መጻሕፍትን ጽፏል።
አቨሴና ሌላው እውቅ የሕክምና ሊቅ ሲሆን በዘመናችን ኡዝቤኪስታን ውስጥ የምትገኘው የቡክሃራ ተወላጅ ነው። አቨሴና በ11ኛው መቶ ዘመን ከኖሩ ታላላቅ የሕክምና፣ የፍልስፍና፣ የሥነ ፈለክና የሒሳብ ሊቃውንት አንዱ ሊሆን ችሏል። አቨሴና በወቅቱ በሕክምናው መስክ የሚታወቀውን ነገር በሙሉ ያካተተ ዘ ካነን ኦቭ ሜዲስን የተባለ ኢንሳይክሎፒዲያ አዘጋጅቷል።
አቨሴና በዚህ ኢንሳይክሎፒዲያ ላይ ሳንባ ነቀርሳ ተላላፊ በሽታ እንደሆነ፣ በሽታ በውኃና በአፈር አማካኝነት ሊተላለፍ
እንደሚችል፣ የስሜት ለውጥ በአካላዊ ጤንነት ላይ ተጽዕኖ እንደሚያሳድር እንዲሁም ነርቮች የሕመም ስሜትንና ጡንቻዎች እንዲኮማተሩ የሚያዝዝ መልእክትን እንደሚያስተላልፉ ጽፏል። ይህ ኢንሳይክሎፒዲያ 760 የሚያህሉ መድኃኒቶችንና የእነዚህን መድኃኒቶች ባሕርያት፣ በሰውነት ውስጥ የሚሠሩበትን መንገድ እንዲሁም አገልግሎታቸውን የሚገልጽ ከመሆኑም ሌላ አዳዲስ መድኃኒቶችን መሞከር የሚቻልበትን መንገድ ያብራራል። ይህ ጽሑፍ ወደ ላቲን ከተተረጎመ በኋላ በአውሮፓ የሕክምና ትምህርት ቤቶች ውስጥ በመቶዎች ለሚቆጠሩ ዓመታት ተሠርቶበታል።አልብዩኬሲስ በሕክምና ታሪክ ውስጥ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ሌላ ሰው ነው። በዘመናዊቷ ስፔን የምትገኘው የአንዳሉዣ ተወላጅ የሆነው ይህ የአሥረኛው መቶ ዘመን ሊቅ፣ 300 ገጾች ያሉትን የቀዶ ሕክምና መመሪያ ጨምሮ በ30 ጥራዞች የተዘጋጀ መጽሐፍ አውጥቷል። በዚህ የቀዶ ሕክምና መመሪያ ላይ የውስጥ አካል ክፍሎችን በጅማት ስለመስፋት፣ በሽንት መተላለፊያ ቱቦ የሚገባ መሣሪያ በመጠቀም የፊኛ ጠጠርን ስለማውጣት፣ የታይሮይድ ዕጢን ስለማውጣት፣ የዓይን ሞራ ስለመግፈፍና ስለመሳሰሉት የተራቀቁ የሕክምና ዘዴዎች ገልጿል።
አልብዩኬሲስ በወሊድ ወቅት የሚያጋጥሙ አስቸጋሪ ሁኔታዎችን ለመቅረፍ እንዲሁም የትከሻ ውልቃትን ለማስተካከል የሚረዱ “ከዘመኑ አንጻር የተራቀቁ” እንደሆኑ የሚነገርላቸው ዘዴዎችን ይጠቀም ነበር። በቀዶ ሕክምና ወቅት በጥጥ የመጠቀምንና የአጥንት ስብራትን በጄሶ የማሰርን ዘዴ ያስጀመረው አልብዩኬሲስ ነው። በተጨማሪም ቦታውን የሳተ ጥርስን ለማስተካከል፣ ሰው ሠራሽ ጥርስ ለመትከል፣ የተወላገደ የጥርስ አበቃቀልን ለማስተካከልና ጥርስ ላይ የሚጋገር ሻክላን ለማስወገድ የሚያስችሉ ዘዴዎችን ገልጿል።
የቀዶ ሕክምና መሣሪያዎች ለመጀመሪያ ጊዜ በሥዕል የቀረቡት አልብዩኬሲስ ባዘጋጀው የቀዶ ሕክምና መመሪያ ላይ ነው። ሁለት መቶ የሚያህሉ የቀዶ ሕክምና መሣሪያዎችን ግልጽ በሆነ መንገድ በሥዕል ያስቀመጠ ከመሆኑም በላይ በእነዚህ መሣሪያዎች እንዴትና መቼ መጠቀም እንደሚቻል መመሪያ ሰጥቷል። አንዳንዶቹ መሣሪያዎች በሺህ ዓመት ጊዜ ውስጥም እንኳ ብዙም ለውጥ አልተደረገባቸውም።
የሕክምና እውቀት ወደ ምዕራቡ ዓለም ደረሰ
በ11ኛውና በ12ኛው መቶ ዘመን በተለይ በቶሌዶ፣ ስፔን እንዲሁም በሞንቴ ካሲኖና በሳሌርኖ፣ ጣሊያን የሚገኙ ምሁራን የአረብኛ የሕክምና ጽሑፎችን ወደ ላቲን መተርጎም ጀመሩ። እነዚህ ጽሑፎች፣ ላቲን ተናጋሪ በሆኑ የአውሮፓ አገሮች ውስጥ በሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ሐኪሞችን ለማስተማር አገልግለዋል። ኤሳን ማሱድ የተባሉት የሳይንስ ጸሐፊ እንደገለጹት በዚህ መንገድ የመካከለኛው ምሥራቅ የሕክምና እውቀት “በቀጣዮቹ ምዕተ ዓመታት ወደ አውሮፓ ዘልቆ ገባ፤ [ይህ ሳይንስ] በእስልምናው ዓለም ከነበረ ከማንኛውም የሳይንስ እውቀት ይበልጥ በአውሮፓ ሳይስፋፋ አልቀረም።”
እንደ ራዚዝ፣ አቨሴና፣ አልብዩኬሲስ ያሉና በዚያ ዘመን የኖሩ ሌሎች የመካከለኛው ዘመን ሊቃውንት የደረሱባቸው ግኝቶችና አዳዲስ እውቀቶች በዛሬው ጊዜ ዘመናዊ ሕክምና ለምንለው የእውቀት ዘርፍ መሠረት እንደሆኑ ተደርገው መገለጻቸው ተገቢ እንደሆነ ጥያቄ የለውም።