በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከመጠን ባለፈ ውፍረት የሚሠቃዩ ወጣቶች ምን መፍትሔ አላቸው?

ከመጠን ባለፈ ውፍረት የሚሠቃዩ ወጣቶች ምን መፍትሔ አላቸው?

የዩናይትድ ስቴትስ የጤና እና ሰብዓዊ አገልግሎት ቢሮ እንደገለጸው ከሆነ ከ1980 እስከ 2002 ባሉት ዓመታት፣ ከመጠን ያለፈ ውፍረት ያላቸው በጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኙ ወጣቶች ቁጥር በሦስት እጥፍ ያደገ ሲሆን ለዚህ ችግር የተጋለጡ ታዳጊዎች ቁጥር ደግሞ ከሁለት እጥፍ በላይ ጨምሯል። በልጅነት የሚመጣ ከመጠን ያለፈ ውፍረት ከሚያስከትላቸው የረጅም ጊዜ የጤና ችግሮች መካከል ከፍተኛ የደም ግፊት፣ የስኳር በሽታ፣ የልብ ሕመምና የተለያዩ የካንሰር ዓይነቶች ይገኙባቸዋል። *

ልጆች ከመጠን ያለፈ ውፍረት እንዲኖራቸው የሚያደርጉት ምክንያቶች በርካታ ሲሆኑ ከእነዚህም መካከል የዕለት ተዕለት ልማዳቸው እምብዛም እንቅስቃሴ የሚጠይቅ አለመሆኑ፣ ወጣቶችን ዒላማ የሚያደርጉ ማስታወቂያዎች እንዲሁም ጤናማ ያልሆኑ ምግቦች በብዛትና በርካሽ መገኘታቸው ተጠቃሽ ናቸው። የዩናይትድ ስቴትስ የበሽታ መቆጣጠሪያና መከላከያ ማዕከል እንዲህ ብሏል፦ “ልጆች ከመጠን ያለፈ ውፍረት የሚኖራቸው ኃይል ሰጪ ምግቦችን ከተገቢው በላይ በመመገባቸውና በቂ የአካል እንቅስቃሴ ባለማድረጋቸው ነው።”

ሕፃናት፣ በጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኙ ልጆች ብሎም አዋቂዎች የአመጋገብ ልማዳቸውን በቁም ነገር መመርመራቸው አስፈላጊ ነው። ከባድ እርምጃዎችን መውሰድ ሳያስፈልግ ጥቂት ማስተካከያዎችን ማድረግ ብቻውን ትልቅ ለውጥ ሊያመጣ ይችላል። የአመጋገብ ልማዱን በማስተካከሉ ከጤና ጋር በተያያዘ ከፍተኛ ጥቅም ያገኘውን ማርክ የተባለ ወጣት እንደ ምሳሌ እንውሰድ። “በፍጥነት የሚዘጋጁ ለጤና ጠቃሚ ያልሆኑ ምግቦችን የማግበስበስ ልማድ ነበረኝ” በማለት ማርክ ይናገራል። ማርክ እንዴት ለውጥ ሊያደርግ እንደቻለ ንቁ! መጽሔት አነጋግሮታል።

በአመጋገብ ረገድ ችግር ያጋጠመህ ከመቼ ጀምሮ ነው?

የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን ሳጠናቅቅ ነው። በዚያ ወቅት አዘውትሬ ከቤት ውጭ መብላት ጀመርኩ። በምሠራበት አካባቢ በፍጥነት የሚዘጋጁ ምግቦችን የሚሠሩ ሁለት ምግብ ቤቶች ስለነበሩ በየቀኑ ማለት ይቻላል አንዱ ጋ ምሳ እበላ ነበር። ምሳዬን ራሴ ከማዘጋጀት ይልቅ በፍጥነት የሚዘጋጁ ምግቦችን የሚሠሩ ምግብ ቤቶች ውስጥ መመገቡን ይበልጥ ቀላል ሆኖ አገኘሁት።

ራስህን ችለህ መኖር ስትጀምርስ?

ያኔማ እንዲያውም ባሰብኝ። ምግብ ማብሰል አልችልም፤ በዚያ ላይ ደግሞ ብዙ ገንዘብ አልነበረኝም። ከቤቴ ብዙም ሳይርቅ በፍጥነት የሚዘጋጁ ምግቦችን የሚሠራ በጣም የምወደው ምግብ ቤት ይገኝ ስለነበር እዚያ መብላት፣ በጣም ቀላልና ወጪ ቆጣቢ እንደሆነ ተሰማኝ። ለጤና ተስማሚ ያልሆነ ምግብ መመገቤ ሳያንስ ከመጠን በላይ መብላት ጀመርኩ። የተለመደው የምግብ መጠን ምንም ስለማያረካኝ ተጨማሪ ድንች ጥብስ፣ በትልቁ መጠጫ የሚቀርበውን የለስላሳ መጠጥ እንዲሁም ኪሴ እስከፈቀደልኝ ድረስ አለ የተባለውን ትልቅ ሃምበርገር ከአንድ በላይ አዝዝ ነበር።

በሕይወትህ ውስጥ ለውጥ እንድታደርግ ያነሳሳህ ምንድን ነው?

በ20ዎቹ ዕድሜ መጀመሪያ ላይ ስሆን ስለ ጤንነቴ በቁም ነገር ማሰብ ጀመርኩ። ከመጠን በላይ ወፍሬ ነበር። ሁልጊዜ የድካም ስሜት ይሰማኝ ነበር፤ በራሴ መተማመንም እያቃተኝ መጣ። በመሆኑም ለውጥ ማድረግ እንደሚኖርብኝ ተሰማኝ።

የአመጋገብ ልማድህን መቆጣጠር የቻልከው እንዴት ነው?

ለውጥ ማድረግ የጀመርኩት ቀስ በቀስ ነበር። በመጀመሪያ የምበላውን ምግብ መጠን ቀነስኩ። ራሴን እንዲህ እለው ነበር፦ “የምበላው ለመጨረሻ ጊዜ አይደለም፤ ከፈለኩ በማንኛውም ሰዓት መብላት እችላለሁ።” ከገበታ ላይ ተነስቼ ለመሄድ የተገደድኩባቸው ጊዜያት አሉ። እንዲህ ያለ እርምጃ ከወሰድኩ በኋላ ግን ትልቅ ድል ያገኘሁ ያህል ደስ ይለኛል።

ከባድ ማስተካከያዎች ማድረግ አስፈልጎህ ነበር?

አንዳንድ ነገሮችን ሙሉ በሙሉ ትቻለሁ። ለምሳሌ ለስላሳ መጠጦችን አቁሜ ውኃ ብቻ መጠጣት ጀምሬያለሁ። እንዲህ ማድረግ ከባድ ነበር። ምክንያቱም ለስላሳ መጠጦችን በጣም እወድ ነበር፤ ውኃ መጠጣት ደግሞ ያስጠላኝ ነበር። አንድ ብርጭቆ ውኃ ከጠጣሁ በኋላ አፌ ላይ ጥሩ ጣዕም እንዲቀር አንድ ሁለት ጊዜ ጭማቂ ፉት እላለሁ። ብዙም ሳይቆይ ግን ውኃ መጠጣት እየለመድኩ መጣሁ።

ጤናማ ካልሆኑ ምግቦች ከመራቅ በተጨማሪ ምን ሌላ ነገር አደረግክ?

በእነሱ ምትክ ጤናማ የሆኑ ምግቦችን መመገብ ጀመርኩ። መጀመሪያ ላይ ፖም፣ ሙዝ፣ የተለያዩ ዓይነት እንጆሪዎችንና ሌሎች ፍራፍሬዎችን መብላት ጀመርኩ። በተጨማሪም እንደ ዶሮና ቱና ያሉ ስብ ያልበዛባቸውን ምግቦች መመገብ ጀመርኩ። ውሎ አድሮ እነዚህ ምግቦች በጣም እየወደድኳቸው መጣሁ። አትክልቶችን በብዛት ለመመገብና ሌሎቹን ደግሞ ቀነስ ለማድረግ እሞክራለሁ። በየመሃሉ ጤናማ መክሰስ ከበላሁ ምሳና እራት ላይ ብዙ እንደማልበላ ተገነዘብኩ። ውሎ አድሮ በፍጥነት ለሚዘጋጁ ምግቦች መንሰፍሰፍ አቆምኩ።

ከቤት ውጭ መብላት ሙሉ በሙሉ ትተሃል ማለት ነው?

አልተውኩም፤ አልፎ አልፎ ውጭ እበላለሁ። በዚህ ጊዜ ግን የምበላውን መጠን እቆጣጠራለሁ። የቀረበልኝ ምግብ ብዙ እንደሆነ ከተሰማኝ የምግብ መጠቅለያ ዕቃ እንዲሰጡኝ እጠይቃለሁ። ከዚያም መብላት ከመጀመሬ በፊት ግማሹን ምግብ በዕቃው ውስጥ እጨምረዋለሁ። በዚህ መንገድ፣ ምግቡ ተርፎ ይጣላል ብዬ በማሰብ ብዙ ከመብላት ይልቅ የሚበቃኝን ያህል ብቻ እበላለሁ።

ማስተካከያዎችን በማድረግህ ምን ጥቅም አግኝተሃል?

ክብደት ቀንሻለሁ፤ አሁን እንደ በፊቱ አይደክመኝም። ስለ ራሴ ጥሩ ስሜት ይሰማኛል። ከሁሉ በላይ ደግሞ ጤንነቴን መንከባከቤ ሕይወት ለሰጠኝ አምላክ አክብሮት እንዳለኝ የሚያሳይ እንደሆነ ስለማውቅ ደስ ይለኛል። (መዝሙር 36:9) ጤናማ የሆነ የአመጋገብ ሥርዓት መከተል አሰልቺ እንደሆነ ይሰማኝ ነበር። አመጋገቤን ካስተካከልኩ በኋላ ግን ይህን የአኗኗር ዘይቤ በምንም ነገር መለወጥ አልፈልግም! *

^ አን.2 ከመጠን ያለፈ ውፍረት ያላቸው ልጆች አዋቂ ሲሆኑም ወፍራም የመሆን አጋጣሚያቸው 70 በመቶ ገደማ እንደሚሆን ባለሙያዎች ይናገራሉ።

^ አን.20 ንቁ! አንድን ዓይነት የአመጋገብ ልማድ ለይቶ በመጥቀስ የተሻለ እንደሆነ የሚገልጽ ሐሳብ አያቀርብም። እያንዳንዱ ግለሰብ ከአመጋገብ ጋር የተያያዘ ውሳኔ ከማድረጉ በፊት፣ ያሉትን አማራጮች በጥንቃቄ መመዘንና ሐኪም ማማከር ይኖርበታል። ጉዳት ሊያስከትሉ ከሚችሉ ዘመን አመጣሽ የአመጋገብ ልማዶች ራሳችሁን ጠብቁ።