በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከዓለም አካባቢ

ከዓለም አካባቢ

“[በዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ] በየዓመቱ በሐኪም ምርመራ ከሚረጋገጡት የካንሰር በሽታዎች መካከል ግማሹ ማለትም ከ130,000 የሚበልጡት የሚከሰቱት እንደ ማጨስ፣ መጠጣትና ጤናማ ያልሆኑ ምግቦችን እንደ መመገብ ባሉ ሊወገዱ በሚችሉ የአኗኗር ዘይቤዎች ነው።”—ቢቢሲ የዜና አገልግሎት፣ ብሪታንያ

“በተደራጁ ወንጀለኞች የሚመራውና ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተወሳሰበና እየተባባሰ የመጣው የዱር አራዊት የአካል ክፍሎች ሕገ ወጥ ንግድ . . . የዓለምን ተወዳጅ የእንስሳት ዝርያዎች ከዚህ በፊት ታይቶ በማያውቅ መጠን እንዲመናመኑ እያደረጋቸው ነው።”—የዱር አራዊት ጥበቃ ማኅበር፣ ዩናይትድ ስቴትስ

በየቀኑ በአማካይ ለስድስት ሰዓት ቴሌቪዥን በመመልከት የሚያሳልፉ ሰዎች ቴሌቪዥን ከማይመለከቱት ሰዎች በ4.8 ዓመት ያነሰ ዕድሜ ይኖራሉ። በሌላ አነጋገር፣ እምብዛም መንቀሳቀስ የማይጠይቅ የአኗኗር ዘይቤ ያለው አዋቂ ሰው ቴሌቪዥን በመመልከት የሚያሳልፈው እያንዳንዱ ሰዓት ዕድሜውን በ22 ደቂቃ ያሳጥረዋል።—ብሪትሽ ጆርናል ኦቭ ስፖርትስ ሜዲስን፣ ብሪታንያ

ጀርመን ውስጥ በማህፀናቸው ያለ ጽንስ ዳውን ሲንድሮም የተባለ የአእምሮ ችግር እንዳለበት በሐኪም ምርመራ ከሚገለጽላቸው ሴቶች መካከል ከ90 በመቶ በላይ የሚሆኑት ማስወረድ ይመርጣሉ።—ደር ታገሽፒገል፣ ጀርመን

የከተማ ኑሮ የሚፈጥረው ውጥረት

“በትላልቅ ከተሞች የሚኖሩ ሰዎች ውጥረት ሲያጋጥማቸው የሚሰጡት ምላሽ በትናንሽ ከተሞች የሚኖሩ ሰዎች ከሚሰጡት ምላሽ ይበልጥ ኃይል የተንጸባረቀበት” መሆኑን ጥናቶች እንዳመለከቱ ሼክሩይ የተሰኘ የፖላንድ መጽሔት ዘግቧል። በዋርሶ የሥነ ልቦና ትምህርት ላቦራቶሪ ውስጥ የሥነ ልቦና ሐኪም የሆኑት ሚዬኪስዋቭ ያስኩልስኪ “ትላልቅ ከተሞች ለሚያስቆጡ በርካታ ነገሮች ያጋልጣሉ” በማለት ገልጸዋል። “በትላልቅ ከተሞች የሚኖሩ ሰዎች በገጠር አካባቢ ከሚኖሩት ይልቅ ከልክ ላለፈ ጭንቀት የመዳረግ አጋጣሚያቸው 21 በመቶ የሚበልጥ ሲሆን በስሜት መለዋወጥ ችግር የመያዝ አጋጣሚያቸው ደግሞ 39 በመቶ ከፍ ያለ ነው።” ታዲያ በትላልቅ ከተሞች ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች ሁኔታውን መቋቋም የሚችሉት እንዴት ነው? “ከቁጥጥርህ ውጪ በሆኑ ነገሮች አትበሳጭ፣” “ከሥራ ስትወጣ ጭንቀትህን እዚያው ትተህ ውጣ፣” “በእግርህ ተንሸራሸር” እንዲሁም “እረፍት ከመውጣት ወደኋላ አትበል” በማለት ሼክሩይ ይመክራል።

ፌስቡክ ምን ያህል መረጃ ያስቀምጣል?

አንድ አውስትራሊያዊ የሕግ ተማሪ የዓለማችን ትልቁ ማኅበራዊ ድረ ገጽ በሆነው በፌስቡክ ላይ አባል ሆኖ በቆየባቸው ሦስት ዓመታት ውስጥ ድርጅቱ ስለ እሱ ምን ያህል መረጃ እንዳለው ማወቅ ስለፈለገ የመረጃው ቅጂ እንዲላክለት ጠየቀ። ፌስቡክም 1,222 ገጾችን የያዘ መረጃ በሲዲ ላከለት። ደር ታገሽፒገል የተሰኘው የጀርመን ጋዜጣ እንደዘገበው ተማሪው “ጓደኞቼን የሚመለከቱ ሚስጥራዊ መረጃዎችን ጨምሮ ሁሉም ነገር ማለትም እያንዳንዱ መልእክትና እያንዳንዱ ወሬ ተቀምጧል” በማለት ተናግሯል። በተላከለት መረጃ ውስጥ እንደሰረዛቸው እርግጠኛ የሆናቸው ነገሮች ይገኙበታል!