በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ጥሩ የሐሳብ ልውውጥ የማድረግ ልማድ ይኑራችሁ

ጥሩ የሐሳብ ልውውጥ የማድረግ ልማድ ይኑራችሁ

“የቱንም ያህል ቢደክመኝ ሁልጊዜ ጥሩ አዳማጭ መሆን እንዳለብኝ ተምሬያለሁ።”—ሚራንዳ፣ ደቡብ አፍሪካ

ተፈታታኝ ሁኔታ፦

“ከልጄ ጋር የማሳልፈውን ጊዜ ማመቻቸት ብቻ ሳይሆን ከእሷ ጋር ስሆን ስለ ሌሎች ኃላፊነቶቼና ስለ ድካሜ ሳላስብ አእምሮዬ ሳይከፋፈል ማዳመጥ ተፈታታኝ ይሆንብኛል” በማለት ክርስቲና የተባለች እናት ተናግራለች።

የመፍትሔ ሐሳቦች፦

ስሜታቸውን ሳይደብቁ በግልጽ ሊነግሯችሁ እንደሚችሉ እንዲሰማቸው አድርጉ። የአምስት ልጆች እናት የሆነችው ኢሊዛቤት እንዲህ ብላለች፦ “በዚህ ረገድ ምሳሌ ለመሆን ጥረት አደርጋለሁ፤ ልጆቼም የተሰማቸውን በነፃነት ይነግሩኛል። እርስ በርሳቸው የሐሳብ ልውውጥ እንዲያደርጉ የማበረታታቸው ከመሆኑም ሌላ ማናቸውም ተኮራርፈው ማደር እንደማይችሉ እነግራቸዋለሁ። ከዚህም በላይ ‘ተኮራርፎ እርስ በርስ መዘጋጋት’ ፈጽሞ የተከለከለ እንደሆነ ያውቃሉ።”

ልጆቻችሁ ሲያዋሯችሁ ችላ አትበሏቸው። ሊያን እንዲህ ስትል ጽፋለች፦ “ልጄ ትንሽ እያለ አውርቶ አይጠግብም ነበር፤ በመሆኑም ብዙ ጊዜ ችላ እለው ነበር። በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ ሲገባ ግን ማውራት አቆመ፤ ትልቅ ስህተት እንደሠራሁ የተገነዘብኩት ያኔ ነበር። እንዲያዋራኝ ለማድረግ ያልሞከርኩት ነገር የለም ማለት ይችላል። በጉባኤዬ ያለን አንድ ሽማግሌ ስለ ጉዳዩ አማከርኩት። እሱም ልጄ እንዲያዋራኝ ከመጫን ይልቅ ከእሱ ጋር ቀስ በቀስ ጭውውት ለመጀመር እንድሞክር መከረኝ። ይህን ምክር ተግባራዊ ሳደርግ ሁኔታዎች ቀስ በቀስ መሻሻል ጀመሩ።”

ትዕግሥተኞች ሁኑ። መክብብ 3:7 “ለዝምታ ጊዜ አለው፤ ለመናገርም ጊዜ አለው” ይላል። የሦስት ልጆች እናት የሆነችው ደልሲ “ልጆቼ ማውራት ካልፈለጉ እነሱ በሚፈልጉበት ጊዜ ሊያዋሩኝ እንደሚችሉ እንዲያውቁ አደርግ ነበር” በማለት ተናግራለች። አዎ፣ ሐሳባቸውን እንዲገልጹ ከመጫን ይልቅ ስሜታቸውን አውጥተው እንዲናገሩ መንገድ መክፈትና ታጋሽ መሆን የተሻለ ነው። መጽሐፍ ቅዱስም ቢሆን እንዲህ ማድረግን ያበረታታል። “የሰው ልብ ሐሳብ እንደ ጥልቅ ውሃ ነው፤ አስተዋይ ሰው ግን ከዚያ ቀድቶ ያወጣዋል።”—ምሳሌ 20:5

‘ለመስማት የፈጠናችሁ፣ ለመናገር የዘገያችሁ ሁኑ።’ (ያዕቆብ 1:19) ከዚህ በፊት ባለው ርዕስ ላይ የተጠቀሰችው ሊዛን እንዲህ ትላለች፦ “ልጆቼ የገጠማቸውን ችግር ሲነግሩኝ አፌ ላይ የመጣውን ነገር ላለመናገር ራሴን መቆጣጠር አስፈልጎኛል። በተጨማሪም የሚያበሳጭ ነገር ሲነግሩኝ ምክር ለመስጠት ከመቸኮል ይልቅ ረጋ ብዬ መናገርን መልመድ ነበረብኝ።” የሁለት ወንዶች ልጆች እናት የሆነችው ሊሳ እንደሚከተለው በማለት ጽፋለች፦ “ጥሩ አዳማጭ በመሆን ረገድ ሁልጊዜ ምሳሌ የምሆን ሰው ነኝ ማለት አልችልም። ልጆቼ የሚያጋጥማቸው ችግር አንዳንድ ጊዜ ለእኔ ያን ያህል ቁም ነገር ሆኖ አይታየኝም፤ ሆኖም ስሜታቸውን በመረዳት ረገድ ማሻሻያ ማድረግ እንዳለብኝ ተገንዝቤያለሁ።”

“ንግግራችሁ ምንጊዜም ለዛ ያለው . . . ይሁን።” (ቆላስይስ 4:6) ሊያን እንዲህ ብላለች፦ “ያለ ምንም እንቅፋት የሐሳብ ልውውጥ ማድረግ እንድንችል ስል ከበድ የሚሉ ጉዳዮች በሚነሱበት ጊዜም በተቻለ መጠን ለመረጋጋትና ላለመረበሽ የታሰበበት ጥረት ማድረግ አስፈልጎኛል።”

ተረጋግታችሁ ማዳመጥ ካቃታችሁ በቁጣ ገንፍላችሁ ኃይለ ቃል ልትናገሩ ትችላላችሁ፤ ይህ ደግሞ ችግሩን ይበልጥ ያባብሰዋል! (ኤፌሶን 4:31) ለምሳሌ ያህል፣ በልጃችሁ ላይ ብትጮኹበት ሐሳቡን መግለጹን ሊያቆምና አስቸጋሪ ባሕርይ ሊያዳብር ይችላል። በአሥራዎቹ ዕድሜ የምትገኝ ልጅ ያለቻት ሃይዲ እንዲህ ብላለች፦ ‘ልጆችን በደግነትና በፍቅር የምታናግሯቸው ከሆነ ሐሳባቸውን በነፃነት ይገልጻሉ። የምትጮሁባቸውና የምታንቋሽሿቸው ከሆነ ግን ሐሳባቸውን መግለጽ ያቆማሉ።’

የልጆቻችሁን ባሕርይ እወቁ። ቀደም ሲል የተጠቀሰችው ያስሚን “ሁለቱ ወንዶች ልጆቼ በጣም የተለያዩ ናቸው” ብላለች። “አንደኛው ለፍላፊ ሲሆን ሌላው ግን ዝምተኛ ነው። ዝምተኛ የሆነውን ልጄን ፊት ለፊት አለማፋጠጥ የተሻለ እንደሆነ ተገንዝቤያለሁ። ከዚህ ይልቅ እንደ ዳማ ወይም ቼዝ የመሰለ ጨዋታ ስንጫወት ወይም ስለሚወደው ርዕስ አንስቶ በሚያወራበት ጊዜ ከእሱ ጋር ለመጨዋወት እሞክራለሁ። በእነዚህ ጊዜያት ስለ አንድ ጉዳይ ምን እንደሚሰማው በዘዴ እጠይቀዋለሁ።”

ይሁንና አንድ ልጅ ስለ አንዳንድ የግል ጉዳዮቹ ለእናቱ ማውራት የሚጨንቀው ቢሆንስ? በጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኘው የሚሳኦ ልጅ እንዲህ ተሰምቶት ነበር። እናቱን “ስሜቴን ልትረጂልኝ አትችይም” አላት። ሚሳኦ በጉባኤዋ ያለ አንድ የጎለመሰና እምነት የሚጣልበት ወንድም እንዲረዳት ጠየቀች። “ይህ ወንድም ለልጄ መካሪ ስለሆነለት አሁን ልጄ መረጋጋት ችሏል” ብላለች።

ወላጅ እንደመሆናችሁ መጠን ልጆቻችሁን ሚስጥረኞቻችሁ አታድርጓቸው። የሁለት ልጆች እናት የሆነችው ኢዎና “በአሥራዎቹ ዕድሜ የምትገኘውን ልጄን ሚስጥረኛዬ አድርጌያት ነበር” በማለት ተናግራለች። “በእርግጥ እንዲህ ማድረግ ትክክል እንዳልሆነ አውቅ ነበር፤ በመሆኑም ስህተቴን ማረም አስፈልጎኛል።” ከልጃችሁ ጋር በጣም ብትቀራረቡም እንኳ ወላጅ እንደሆናችሁና በቤቱ ውስጥ ሥልጣን ያላችሁ እናንተ መሆናችሁን አትዘንጉ። ለእናንተ ያላቸው አክብሮት እንዲቀንስ የሚያደርግ ነገር የማታደርጉ እንዲሁም ጎልማሳና የተረጋጋችሁ እንደሆናችሁ የምታሳዩ ከሆነ ልጆቻችሁ እናንተን ማክበርና “ልጆች ሆይ፣ . . . ለወላጆቻችሁ ታዘዙ” የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ትእዛዝ መፈጸም ቀላል ይሆንላቸዋል።—ኤፌሶን 6:1, 2

‘ልጆቻችሁን ውደዱ።’ (ቲቶ 2:4) ልጆች ምግብና ውኃ የሚያስፈልጋቸውን ያህል ፍቅርም ያስፈልጋቸዋል! ስለዚህ በቃልም ሆነ በተግባር ሁልጊዜ ፍቅራችሁን ግለጹላቸው! እንዲህ ካደረጋችሁ እነሱም የመረጋጋትና የመተማመን ስሜት የሚሰማቸው ከመሆኑም በላይ ሐሳባቸውን ለእናንተ መግለጽም ሆነ መታዘዝ ይበልጥ ይቀላቸዋል።