በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የካውካሰስ ተራሮች—የቋንቋዎች መናኸሪያ

የካውካሰስ ተራሮች—የቋንቋዎች መናኸሪያ

ሰፊና ተራራማ በሆነ አንድ አካባቢ እንደምትገኝ አድርገህ አስብ። በዚህ አካባቢ እያንዳንዳቸው የራሳቸው ቋንቋ ያላቸው በደርዘን የሚቆጠሩ ብሔረሰቦች እንደሚኖሩ ስታውቅ ትገረም ይሆናል። በዚያ ላይ ደግሞ ቅርብ ለቅርብ ባሉ መንደሮች የሚኖሩ ሰዎች እንኳ በቋንቋ ምክንያት ላይግባቡ ይችላሉ! የመካከለኛው ዘመን የጂኦግራፊ ሊቃውንትም ይህ ሁኔታ ሳይገርማቸው አልቀረም፤ ምክንያቱም ከመካከላቸው አንዱ ይህን የካውካሰስ አካባቢ “የልሳናት ተራራ” ሲል ሰይሞታል።

በጥቁር ባሕርና በካስፒያን ባሕር መካከል የሚገኙት የካውካሰስ ተራሮች፣ የአህጉራት መሸጋገሪያና የታላላቅ ሥልጣኔዎች ማዕከል በመሆናቸው የረጅም ጊዜ ታሪክና የተለያዩ ባሕሎች ሊኖራቸው ችሏል። የአካባቢው ሕዝቦች ለአረጋውያን ባላቸው አክብሮት፣ ለጭፈራ ባላቸው ፍቅርና ሞቅ ባለ የእንግዳ ተቀባይነታቸው ይታወቃሉ። ብዙ ጎብኚዎች የሚደነቁት ግን በካውካሰስ ባለው የጎሳዎችና ቋንቋዎች ብዛት ነው፤ በአውሮፓ ተመሳሳይ ስፋት ካላቸው ሌሎች ቦታዎች የበለጠ በዚህ አካባቢ ብዛት ያላቸው ቋንቋዎች ይነገራሉ።

ጉራማይሌ ሕዝብ

በአምስተኛው ክፍለ ዘመን ዓ.ዓ. የኖረው ሄሮዶተስ የተባለው ግሪካዊ የታሪክ ምሁር “የተለያየ ባሕል ያላቸው በርካታ ሕዝቦች በካውካሰስ ይኖራሉ” ሲል ጽፏል። በአንደኛው መቶ ዘመን ዓ.ም. ገደማ ደግሞ ስትራቦ የተባለ ሌላ ግሪካዊ የታሪክ ምሁር በዚህ አካባቢ ስለሚኖሩ 70 የሚያክሉ ነገዶች ጽፏል። እያንዳንዱ ነገድ የራሱ ቋንቋ የነበረው ሲሆን ሁሉም ዳዮስኪዩሪየስ ትባል በነበረ ቦታ መጥተው ይገበያዩ ነበር፤ በጥቁር ባሕር ዳርቻ ላይ የምትገኘው ይህች ከተማ በአሁኑ ጊዜ ሱኩሚ ትባላለች። ከበርካታ አሥርተ ዓመታት በኋላ ሮማዊ ምሁር የሆነው ትልቁ ፕሊኒ፣ ሮማውያን በዳዮስኪዩሪየስ ለመነገድ 130 አስተርጓሚዎች እንደሚያስፈልጓቸው ጽፏል።

በዛሬው ጊዜ በካውካሰስ የሚኖሩ ከ50 የሚበልጡ ጎሳዎች አሉ። እያንዳንዱ ጎሳ በራሱ ባሕል፣ አብዛኛውን ጊዜ ደግሞ በራሱ አለባበስ፣ ሥነ ጥበብና ሥነ ሕንፃ ይኮራል። በዚህ አካባቢ በትንሹ 37 የሚያክሉ ቋንቋዎች ይነገራሉ፤ አንዳንዶቹ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ተናጋሪዎች ያሏቸው ሲሆን ሌሎቹ ቋንቋዎች ደግሞ በጥቂት መንደሮች ብቻ የሚነገሩ ናቸው። በቋንቋዎች ብዛት የበላይነቱን የያዘው በሩስያ የሚገኘው የዳግስታን ሪፑብሊክ ሲሆን 30 የሚያክሉ ጎሳዎች ይኖሩበታል። በእነዚህ ቋንቋዎች መካከል ያለው መወራረስ እንዲሁም ከሌሎች የቋንቋ ቡድኖች ጋር ያላቸው ዝምድና እስካሁን ድረስ በውል አይታወቅም።

የይሖዋ ምሥክሮች በካውካሰስ መጽሐፍ ቅዱስን ሲያስተምሩ

በካውካሰስ አካባቢ የሚነገሩት የኮውኬዢያ ቋንቋዎች የትኞቹ እንደሆኑ ማወቅ ትፈልጋለህ? www.pr418.com የተባለውን የይሖዋ ምሥክሮች ሕጋዊ ድረ ገጽ ከ400 በሚበልጡ ቋንቋዎች መመልከት ይቻላል። ከእነዚህ መካከል የቋንቋዎች መናኸሪያ በሆነው በዚህ ተራራማ አካባቢ የሚነገሩ አንዳንድ ቋንቋዎች ይገኙበታል።