ለቤተሰብ | የወላጅ ሚና
በአሥራዎቹ ዕድሜ ከሚገኝ ልጃችሁ ጋር የሐሳብ ልውውጥ ማድረግ
ተፈታታኙ ነገር
ልጃችሁ ትንሽ እያለ ሁሉንም ነገር ይነግራችሁ ነበር። ከጎረመሰ በኋላ ግን ምንም ነገር ሊነግራችሁ አይፈልግም። ልታነጋግሩት ስትሞክሩ አጫጭር መልሶችን ይሰጣችኋል፤ አሊያም ወደ ጦፈ ክርክር የሚመራ ነገር ይናገራል።
ደስ የሚለው ግን በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ ከሚገኘው ልጃችሁ ጋር የሐሳብ ልውውጥ ማድረግን ልትማሩ ትችላላችሁ። በመጀመሪያ ግን ለዚህ ተፈታታኝ ሁኔታ ምክንያት ሊሆኑ የሚችሉ ሁለት ነገሮችን እንመልከት። *
ምክንያቱ ምንድን ነው?
ነፃነት መፈለግ። በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ የሚገኘው ልጃችሁ ኃላፊነት የሚሰማው አዋቂ የሚሆነው በአንድ ጀንበር አይደለም፤ በምሳሌያዊ አገላለጽ ልጃችሁ ከተሳፋሪ መቀመጫ ተነስቶ ሾፌሩ ወንበር ላይ በመቀመጥ አስቸጋሪ በሆነው የሕይወት ጎዳና ላይ መንዳትን ቀስ በቀስ መማር ይኖርበታል። እርግጥ ነው፣ አንዳንድ ልጆች ሊሰጣቸው ከሚገባው በላይ ነፃነት ይፈልጋሉ፤ በሌላ በኩል ደግሞ አንዳንድ ወላጆች የሚሰጡት ነፃነት መስጠት ከሚገባቸው ያነሰ ነው። በዚህ ምክንያት የሚፈጠረው አለመግባባት ደግሞ በወላጆች እና በልጆች መካከል ከፍተኛ ጦርነት ሊያስነሳ ይችላል። የ16 ዓመቱ ብራድ * እንዲህ በማለት ያማርራል፦ “ወላጆቼ እያንዳንዱን የሕይወቴን እንቅስቃሴ ለመቆጣጠር ጥረት ያደርጋሉ። አሥራ ስምንት ዓመት እስኪሆነኝ ድረስ ተጨማሪ ነፃነት የማይሰጡኝ ከሆነ ቤቱን ለቅቄ እወጣለሁ!”
የማመዛዘን ችሎታ። ትናንሽ ልጆች ነገሮችን የሚያስቡት ቀጥተኛ በሆነ መንገድ ይኸውም አንድ ነገር ወይ ትክክል አሊያም ስህተት ነው ከሚለው አንጻር ብቻ ነው። በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ የሚገኙ ብዙዎቹ ወጣቶች ግን ፊት ለፊት ከሚታዩት ነገሮች በስተጀርባ ያለውን ሁኔታ ማጤን ይችላሉ። ይህም የማመዛዘን ችሎታቸው እንደዳበረ የሚያሳይ ሲሆን ብስለት በሚንጸባረቅበት መንገድ ለማሰብም ይረዳቸዋል። እስቲ አንድ ምሳሌ እንመልከት፤ አንድ ትንሽ ልጅ አለማዳላት ሲባል ወደ አእምሮው የሚመጣው እናቱ አንድን ብስኩት ለሁለት ከፍላ ግማሹን ለእሱ፣ ግማሹን ደግሞ ለወንድሙ በመስጠት ማካፈሏ ሊሆን ይችላል። ለዚህ ልጅ አለማዳላት ወይም ፍትሕ በቀላሉ በሒሳብ ስሌት ሊቀመጥ የሚችል ነገር ነው። በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ የሚገኙ ወጣቶች ግን ፍትሕ ከዚህ በላይ ውስብስብ እንደሆነ ይገነዘባሉ። ምክንያቱም አለማዳላት ወይም ፍትሐዊ መሆን ሲባል ሁሉንም ሰው በተመሳሳይ መንገድ መያዝ ማለት እንዳልሆነና ሁሉንም ሰው በተመሳሳይ መንገድ መያዝ ደግሞ ሁልጊዜ ፍትሐዊ እንደማይሆን ያውቃሉ። በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ የሚገኝ ልጃችሁ የማመዛዘን ችሎታውን ማዳበሩ እንዲህ ያሉ ውስብስብ ነገሮችን ከተለያየ አቅጣጫ እንዲመለከት ያደርገዋል። በእርግጥ ይህ ሌላም ውጤት አለው። የማመዛዘን ችሎታውን ማዳበሩ በአንዳንድ ጉዳዮች ከእናንተ የተለየ አመለካከት እንዲኖረው ሊያደርገው ይችላል።
ምን ማድረግ ትችላላችሁ?
ባገኛችሁት አጋጣሚ ሁሉ ተጨዋወቱ። የተገኙትን አጋጣሚዎች በሙሉ ለመጨዋወት ተጠቀሙባቸው። ለምሳሌ ያህል፣ በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ የሚገኙ ወጣቶች ከወላጆቻቸው ጋር ፊት ለፊት ሳይሆን ጎን ለጎን ሆነው ሲሠሩ ወይም በመኪና ሲሄዱ ማውራት እንደሚቀላቸው አንዳንዶች ተገንዝበዋል።—የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓት፦ ዘዳግም 6:6, 7
ብዙ አትናገሩ። በእያንዳንዱ ጉዳይ ላይ እስክትካረሩ ድረስ መከራከር የለባችሁም። ከዚህ ይልቅ ነጥቡን ተናገሩና አቁሙ። ልጃችሁ ከተናገራችሁት ነገር ውስጥ አብዛኛውን “የሚሰማው” በኋላ ላይ ብቻውን ሆኖ ሲያሰላስልበት ነው። እንዲህ እንዲያደርግ አጋጣሚውን ስጡት።—የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓት፦ ምሳሌ 1:1-4
አዳምጡ፤ እንዲሁም ግትር አትሁኑ። ልጃችሁ የገጠመውን ችግር በደንብ መረዳት እንድትችሉ ሲናገር አታቋርጡት፤ እንዲሁም በጥሞና አዳምጡት። መልስ በምትሰጡበት ጊዜ ምክንያታዊ ሁኑ። ያወጣችሁትን ደንብ በግትርነት ለማስከበር የምትጥሩ ከሆነ ልጃችሁ ማምለጫ ቀዳዳ መፈለጉ አይቀርም። ስቴይንግ ኮኔክትድ ቱ ዩር ቲኔጀር የተባለው መጽሐፍ እንዲህ በማለት ያስጠነቅቃል፦ “ልጆች ሁለት ዓይነት ኑሮ መኖር የሚጀምሩት በዚህ ጊዜ ነው። በአንድ በኩል ወላጆቻቸው መስማት የሚፈልጉትን ነገር የሚናገሩ ሲሆን ከወላጆቻቸው እይታ ሲሰወሩ ደግሞ ደስ የሚያሰኛቸውን ነገር ያደርጋሉ።”—የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓት፦ ፊልጵስዩስ 4:5
ተረጋጉ። ካሪ የተባለች በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ የምትገኝ ልጅ “ከእናቴ ጋር በአንድ ጉዳይ ካልተስማማን የምናገረው ነገር ሁሉ ያናድዳታል” በማለት ተናግራለች። አክላም “ይህ ደግሞ እኔን ስለሚያበሳጨኝ ንግግራችን ወዲያውኑ ወደ ጦፈ ክርክር ይቀየራል” ብላለች። እንግዲያው ልጃችሁን ከመቆጣት ይልቅ ስሜቱን እንደተረዳችሁ በሚያሳይ መንገድ ተናገሩ። ለምሳሌ “ይህ ምንም የሚያሳስብ ነገር አይደለም!” ከማለት ይልቅ “ጉዳዩ አንተን ምን ያህል እንዳሳሰበህ ይገባኛል” ብትሉ የተሻለ ነው።—የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓት፦ ምሳሌ 10:19
በተቻለ መጠን ከማስገደድ ይልቅ ለመምራት ሞክሩ። የልጃችሁ የማመዛዘን ችሎታ፣ መዳበር ከሚያስፈልገው ጡንቻ ጋር ሊመሳሰል ይችላል። በመሆኑም ልጃችሁ አጣብቂኝ የሆነ ሁኔታ ሲያጋጥመው የእሱ ጡንቻ እንዲፍታታ እናንተ “የአካል ብቃት እንቅስቃሴ” አትሥሩለት፤ በሌላ አባባል ውሳኔ ልታደርጉለት አይገባም። በጉዳዩ ላይ ስትወያዩ የመፍትሔ ሐሳብ እንዲያፈልቅ ዕድል ስጡት። ከዚያም ሐሳቡን ከገለጸ በኋላ እናንተ እንደሚከተለው ማለት ትችላላችሁ፦ “እነዚህ አማራጮችም አሉ። ለአንድ ለሁለት ቀን አስብባቸው፤ ከዚያም የመረጥከውን የመፍትሔ ሐሳብና የመረጥክበትን ምክንያት እንደገና እንወያይበታለን።”—የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓት፦ ዕብራውያን 5:14
^ စာပိုဒ်၊ 5 በዚህ ርዕስ ውስጥ በአሥራዎቹ ዕድሜ ስለሚገኙ ወጣቶች ስንናገር በወንድ ፆታ የተጠቀምን ቢሆንም የቀረቡት ነጥቦች ለሁለቱም ፆታዎች ይሠራሉ።
^ စာပိုဒ်၊ 7 በዚህ ርዕስ ውስጥ የተጠቀሱት ስሞች ተቀይረዋል።