መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?
የብልግና ምስሎችና ጽሑፎች
መጽሐፍ ቅዱስ የብልግና ምስሎችንና ጽሑፎችን ያወግዛል?
“የፆታ ስሜቱ እስኪቀሰቀስ ድረስ አንዲትን ሴት በምኞት የሚመለከት ሁሉ በዚያን ጊዜ በልቡ ከእሷ ጋር አመንዝሯል።”—ማቴዎስ 5:28
ይህን ማወቅ ለምን አስፈለገ?
በዛሬው ጊዜ የብልግና ምስሎችና ጽሑፎች ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ በጣም ተወዳጅ አልፎ ተርፎም በቀላሉ የሚገኙ ሆነዋል። አምላክን ማስደሰትና ደስተኛ ሕይወት መኖር የምትፈልግ ከሆነ አምላክ ስለ ብልግና ምስሎችና ጽሑፎች ምን እንደሚሰማው ማወቅ ይኖርብሃል።
መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?
መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ብልግና ምስሎችና ጽሑፎች በቀጥታ አይናገርም። ያም ሆኖ የብልግና ምስሎችና ጽሑፎች ከብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎች ጋር በቀጥታ ይጋጫሉ።
ለምሳሌ ያህል፣ አንድ ያገባ ሰው የትዳር ጓደኛው ያልሆነችን ሴት ‘በምኞት በመመልከት’ ከእሷ ጋር የፆታ ግንኙነት የመፈጸም ፍላጎት በውስጡ እንዲያድግ የሚፈቅድ ከሆነ ምንዝር ወደመፈጸም ሊያደርሰው እንደሚችል መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ ይናገራል። አንድ ሰው ያገባም ይሁን ያላገባ፣ የብልግና ምስሎችን ‘የሚመለከት’ ከሆነ እንዲህ ያለው ድርጊት የፆታ ብልግና ስለመፈጸም እንዲያውጠነጥን ስለሚያደርገው ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ በእሱ ላይ ይሠራል። እንግዲያው አምላክ እንዲህ ዓይነቱን ምግባር እንደሚጸየፈው ግልጽ ነው።
አንድ ሰው ዝሙት እስካልፈጸመ ድረስ የብልግና ምስሎችን ቢመለከት ምን ችግር አለው?
“በምድራዊ የአካል ክፍሎቻችሁ ውስጥ ያሉትን ዝንባሌዎች ግደሉ፤ እነሱም ዝሙት፣ ርኩሰት፣ የፆታ ምኞት፣ መጥፎ ፍላጎትና ጣዖት አምልኮ የሆነው መጎምጀት ናቸው።”—ቆላስይስ 3:5
ሰዎች ምን ይላሉ?
አንዳንድ ተመራማሪዎች፣ ሰዎች የብልግና ምስሎችን መመልከታቸው አስነዋሪ የፆታ ድርጊቶችን ከመፈጸማቸው ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት እንደሌለው ይሰማቸዋል። ሆኖም የብልግና ምስሎችን መመልከት በራሱ ሥነ ምግባር የጎደለው ድርጊት ነው?
መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?
መጽሐፍ ቅዱስ “ጸያፍ ቀልድ” አስነዋሪ ምግባር እንደሆነ ይገልጻል። (ኤፌሶን 5:3, 4) ታዲያ የብልግና ምስሎችና ጽሑፎች ከጸያፍ ቀልድ የበለጠ አስነዋሪ አይደሉም? በአብዛኛው በዛሬው ጊዜ ያሉት የብልግና ምስሎች ምንዝር፣ ግብረ ሰዶምና ሌሎች የዝሙት ድርጊቶች በገሃድ ሲፈጸሙ ያሳያሉ። በእርግጥም አምላክ የፆታ ስሜትን የሚቀሰቅሱ እንዲህ ያሉ የብልግና ድርጊቶችን መመልከትን ከጸያፍ ንግግር የበለጠ እንደሚጠላው ጥርጥር የለውም።
ሰዎች የብልግና ምስሎችን መመልከታቸው የፆታ ድርጊቶችን እንዲፈጽሙ ሊያነሳሳቸው ይችላል የሚለው ጉዳይ አሁንም ተመራማሪዎችን እያወዛገበ ነው። ይሁን እንጂ የብልግና ምስሎችና ጽሑፎች መንፈሳዊ ጥፋት እንደሚያስከትሉ እንዲሁም አምላክ በጣም እንደሚጸየፋቸው መጽሐፍ ቅዱስ በማያሻማ መንገድ ይጠቁማል። መጽሐፍ ቅዱስ “የአካል ክፍሎቻችሁ ውስጥ ያሉትን ዝንባሌዎች ግደሉ፤ እነሱም ዝሙት [እና] የፆታ ምኞት . . . ናቸው” የሚል ምክር ይሰጣል። (ቆላስይስ 3:5) የብልግና ምስሎችን የሚመለከቱ ሰዎች ከዚህ ሐሳብ ተቃራኒ የሆነ ነገር እያደረጉ ነው፤ ይኸውም እንዲህ ያሉ ምኞቶችን ከመግደል ይልቅ እያሳደጓቸውና እያቀጣጠሏቸው ነው።
ከብልግና ምስሎችና ጽሑፎች ለመራቅ ምን ሊረዳህ ይችላል?
“መልካሙን እንጂ ክፉውን አትፈልጉ፤ . . . ክፉውን ጥሉ፤ መልካሙንም ውደዱ።”—አሞጽ 5:14, 15
መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?
መጽሐፍ ቅዱስ ሴሰኞች፣ ሰካራሞችና ሌቦች ስለነበሩ ሆኖም መጥፎ ምግባራቸውን መተው ስለቻሉ ሰዎች ይናገራል። (1 ቆሮንቶስ 6:9-11) እንዴት ተሳካላቸው? በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኘውን ጥበብ ሥራ ላይ በማዋል መጥፎ የሆነውን ነገር መጥላት ስለተማሩ ነው።
የብልግና ምስሎችና ጽሑፎች የሚያስከትሉትን አሠቃቂ መዘዝ በጥንቃቄ በማሰብ እነዚህን ድርጊቶች መጥላትን መማር ይቻላል። በዩታ የሚገኝ አንድ ዩኒቨርሲቲ በቅርቡ ተደርጎ ስለነበር አንድ ጥናት ያሳተመው ሪፖርት ይፋ እንዳደረገው የብልግና ምስሎችን የሚመለከቱ አንዳንድ ሰዎች “የመንፈስ ጭንቀት ይይዛቸዋል፤ ራሳቸውን ከኅብረተሰቡ ያገላሉ እንዲሁም ከሌሎች ጋር ያላቸው ግንኙነት ይበላሻል።” አልፎ ተርፎም ሌሎች አሳዛኝ ጉዳቶች ይደርሱባቸዋል። ከዚህም በላይ ቀደም ሲል እንደተገለጸው የብልግና ምስሎችን መመልከት አምላክ የሚጸየፈው ድርጊት ስለሆነ ከዚያም የበለጠ ጉዳት አለው። ሰዎች ከፈጣሪያቸው ጋር እንዲራራቁ ያደርጋቸዋል።
መጽሐፍ ቅዱስ መልካም የሆነውን መውደድን እንድንማር ሊረዳን ይችላል። መጽሐፍ ቅዱስን ይበልጥ ባነበብን መጠን በውስጡ ለያዛቸው የሥነ ምግባር መሥፈርቶች ያለን ፍቅርም እያደገ ይሄዳል። ይህ ፍቅር ደግሞ የብልግና ምስሎችንና ጽሑፎችን አጥብቀን እንድንጠላ እንዲሁም “በዐይኔ ፊት፣ ክፉ ነገር አላኖርም” በማለት የጻፈው መዝሙራዊ የተሰማው ዓይነት ስሜት እንዲኖረን ይረዳናል።—መዝሙር 101:3