ንድፍ አውጪ አለው?
የኤምፐረር ፔንግዊን ባለ ላባ ልብስ
ኤምፐረር ፔንግዊን በሚያስደንቅ ፍጥነት በውኃ ውስጥ መዋኘትና በበረዶ ግግር ላይ ዘልሎ ፊጥ ማለት ይችላል። ይህ ሊሆን የቻለው እንዴት ነው?
እስቲ የሚከተለውን አስብ፦ ኤምፐረር ፔንግዊን በላባው ውስጥ አየር አምቆ መያዝ ይችላል። ይህ መሆኑ የሰውነቱን ሙቀት በመጠበቅ በቅዝቃዜ እንዳይጠቃ የሚረዳው ከመሆኑም አልፎ አየር መያዝ ባይችል ኖሮ ሊሄድ ከሚችለው ፍጥነት ሁለት ወይም ሦስት እጥፍ በላይ እንዲጓዝ ይረዳዋል። ይህ ሊሆን የቻለው እንዴት ነው? የባሕር ውስጥ የሥነ ሕይወት ተመራማሪዎች፣ ይህ ወፍ እንዲህ ባለ ፍጥነት ሊጓዝ የቻለው በላባው ውስጥ የያዛቸውን ጥቃቅን የአየር አረፋዎች በመልቀቅ እንደሆነ ይናገራሉ። እነዚህ አረፋዎች በሚለቀቁበት ጊዜ በፔንግዊኑ ሰውነት ዙሪያ ያለው ሰበቃ ስለሚቀንስ ፍጥነቱን መጨመር ይችላል።
የምሕንድስና ባለሙያዎች በመርከብ አካል ዙሪያ የሚፈጠረውን ሰበቃ በአረፋ አማካኝነት እንዲቀንስ በማድረግ መርከቦቹ የበለጠ ፍጥነት እንዲኖራቸው ለማድረግ ጥናት ሲያካሄዱ ቆይተዋል። ይሁን እንጂ “በላባ የተሸፈነው የፔንግዊን ሰውነት እጅግ ውስብስብ መሆኑ ከዚህ ጋር የሚመሳሰል ባለ ቀዳዳ ልባስ ወይም ወንፊት መሥራት አስቸጋሪ እንዳደረገባቸው” ተመራማሪዎቹ ይናገራሉ።
ታዲያ ምን ይመስልሃል? የኤምፐረር ፔንግዊን ባለ ላባ ልብስ በዝግመተ ለውጥ የተገኘ ነው? ወይስ ንድፍ አውጪ አለው?