ቃለ ምልልስ | ዴቪ ሎስ
የባዮኬሚስትሪ ባለሙያ ስለሚያምንበት ነገር ምን ይላል?
ዶክተር ዴቪ ሎስ በቤልጅየም የሚኖር የባዮኬሚስትሪ ባለሙያ ነው። የፈጣሪን መኖር የሚጠራጠርበትና በዝግመተ ለውጥ የሚያምንበት ወቅት ነበር። ከጊዜ በኋላ ግን አመለካከቱን ቀየረ። ይህ ተመራማሪ ስለ ሕይወት አመጣጥ የነበረውን አመለካከት እንዲለውጥ ያደረገው ምንድን ነው? ንቁ! ዶክተር ሎስን ስለ ሙያውና ስለ እምነቱ አነጋግሮታል።
በሳይንሳዊ ምርምርና ጥናት ላይ እንድትሰማራ ያነሳሳህ ምንድን ነው?
ዩኒቨርሲቲ ሳለሁ ኬሚስትሪ ለማጥናት ወሰንኩ። በተለይ ፕሮቲኖችና ኑክሊክ አሲዶች አስደነቁኝ፤ እነዚህ ሞለኪውሎች በፕላኔታችን ላይ ከሚገኙት ሞለኪውሎች ሁሉ የበለጠ ውስብስብ ናቸው። ከጊዜ በኋላ ደግሞ አንዳንድ ሞለኪውሎች የፀሐይ ብርሃንን የሚጠቀሙበት መንገድ ትኩረቴን ሳበው።
በአምላክ ታምን ነበር?
ትንሽ ልጅ ሳለሁ አምን ነበር። በሌቨን የካቶሊክ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ በነበርኩበት ወቅት ግን ሕይወት ያላቸው ነገሮች ወደ ሕልውና የመጡት በዝግመተ ለውጥ እንደሆነ ተማርኩ። አስተማሪዎቹ ስለዚህ ሂደት የሚያብራሩበት መንገድ አሳማኝ ይመስል ነበር። እነዚህ ሰዎች የብዙ ዓመት ተሞክሮ ያላቸው የሳይንስ ሊቃውንት ስለሆኑ የተናገሩትን በሙሉ አመንኩ። ከጊዜ በኋላ፣ አምላክ መኖሩን ማመን እየከበደኝ መጣ።
ስለ ሕይወት አመጣጥ የነበረህን አመለካከት እንድትለውጥ ያደረገህ ምንድን ነው?
በ1999 አንድ የትምህርት ቤት ጓደኛዬን አገኘሁ፤ ይህ ጓደኛዬ የይሖዋ ምሥክር ሆኖ ነበር፤ አንድ ቀን በስብሰባቸው ላይ ተገኘሁ። በዚያው ጊዜ አካባቢ ደግሞ አንድ የይሖዋ ምሥክር ቤታችን መጥቶ ስለ አንተ የሚያስብ ፈጣሪ ይኖር ይሆን? * (እንግሊዝኛ) የተባለውን መጽሐፍ ትቶልኝ ሄደ።
መጽሐፉን ስታነብበው ምን ተሰማህ?
በመጽሐፉ ላይ ያለው ጥልቅ ምርምር የተደረገበት ሐሳብ አስገረመኝ። ሕይወት ባላቸው ነገሮች ላይ የሚታየው ንድፍ በዝግመተ ለውጥ የተገኘ መሆኑን መጠራጠር ጀመርኩ።
በፍጥረት ሥራዎች ላይ ከሚታየው ንድፍ መካከል አንተን ያስደነቀህ የትኛው ነው?
የባዮኬሚስትሪ ባለሙያ ሆኜ በማደርገው ምርምር፣ በውቅያኖስ በሚኖሩ ሳይኖባክቴሪያዎች ውስጥ ያሉትን አንዳንድ ሞለኪውሎች ንድፍ አጥንቻለሁ፤ ሳይኖባክቴሪያዎች በዓይን የማይታዩ ሕዋሳት ሲሆኑ ምግባቸውን የሚያዘጋጁት ራሳቸው ናቸው። አንዳንድ ተመራማሪዎች፣ በፕላኔታችን ላይ መኖር የጀመሩት የመጀመሪያዎቹ ሕያዋን ፍጥረታት እነዚህ ባክቴሪያዎች እንደሆኑ ያስባሉ። እነዚህ ረቂቅ ባክቴሪያዎች ከፀሐይ ብርሃን የሚያገኙትን ኃይል በመጠቀም ውኃንና ካርቦን ዳይኦክሳይድን ወደ ምግብነት ይለውጣሉ፤ ይህን የሚያደርጉበትን እጅግ ውስብስብ የሆነ ኬሚካላዊ ሂደት ተመራማሪዎች ዛሬም ድረስ ሙሉ በሙሉ ሊረዱት አልቻሉም። በተጨማሪም ሳይኖባክቴሪያዎች የፀሐይን ብርሃን የሚሰበስቡበት መንገድ በጣም ውጤታማ መሆኑ አስደነቀኝ።
ቅጠሎችም የፀሐይ ብርሃንን ተጠቅመው ምግብ ያዘጋጃሉ። ታዲያ እነዚህን ባክቴሪያዎች ልዩ የሚያደርጋቸው ምንድን ነው?
ወደ ባሕር ጠልቀህ በገባህ መጠን የምታገኘው ብርሃን እያነሰ ይሄዳል። ስለሆነም ጠለቅ ባለው የባሕር ክፍል ውስጥ የሚኖሩት ሳይኖባክቴሪያዎች፣ ወደ እነሱ የሚደርሰውን አነስተኛ ብርሃን በሙሉ መሰብሰብ ይኖርባቸዋል፤ እነዚህ ባክቴሪያዎች ይህን ለማድረግ የሚያስችሏቸው በጣም የተራቀቁ አንቴናዎች አሏቸው። በዚህ መንገድ የሰበሰቡት ከብርሃን የሚገኝ ኃይል ምንም ሳይባክን ምግብ አምራች ወደሆነው ክፍል ይተላለፋል። እነዚህ ባክቴሪያዎች ብርሃን የሚሰበስቡበት ይህ ሂደት፣ ከፀሐይ ብርሃን ኃይል ለማመንጨት የሚረዱ ሰሌዳዎችን የሚያመርቱ ድርጅቶችን ትኩረት ስቧል። እርግጥ ነው፣ በፋብሪካ የሚመረቱት እነዚህ ሰሌዳዎች፣ ውጤታማነታቸው ከባክቴሪያዎቹ ጋር ሊወዳደር የሚችል አይደለም።
ይህ ምን ድምዳሜ ላይ እንድትደርስ አደረገህ?
መሐንዲሶች፣ ሕይወት ባላቸው ነገሮች ውስጥ ያሉትን አስደናቂ ሂደቶች ለመኮረጅ ስለሚያደርጉት ጥረት ሳስብ፣ ሕይወት የተገኘው ከአምላክ መሆን አለበት የሚል ድምዳሜ ላይ ደረስኩ
መሐንዲሶች፣ ሕይወት ባላቸው ነገሮች ውስጥ ያሉትን አስደናቂ ሂደቶች ለመኮረጅ ስለሚያደርጉት ጥረት ሳስብ፣ ሕይወት የተገኘው ከአምላክ መሆን አለበት የሚል ድምዳሜ ላይ ደረስኩ። ይሁን እንጂ እምነት እንዳዳብር ያደረገኝ በሳይንሱ መስክ ያደረግሁት ጥናት ብቻ አይደለም። መጽሐፍ ቅዱስን በጥልቀት ማጥናቴም ጠቅሞኛል።
መጽሐፍ ቅዱስን ያስጻፈው አምላክ እንደሆነ ያሳመነህ ምንድን ነው?
ይህን እንዳምን ካደረጉኝ በርካታ ምክንያቶች አንዱ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች በዝርዝር ፍጻሜ ማግኘታቸው ነው። ለምሳሌ፣ ነቢዩ ኢሳይያስ ስለ ኢየሱስ አሟሟትና ስለሚቀበርበት መንገድ በመቶዎች ከሚቆጠሩ ዓመታት በፊት በዝርዝር ገልጾ ነበር። በኩምራን የተገኘው የኢሳይያስ ጥቅልል፣ የተገለበጠው ኢየሱስ ከመወለዱ ከመቶ ዓመት በፊት ስለሆነ ትንቢቱ የተጻፈው ኢየሱስ ከመሞቱ በፊት እንደሆነ እርግጠኞች መሆን እንችላለን።
ትንቢቱ “አሟሟቱ ከክፉዎች፣ መቃብሩም ከባለጠጎች ጋር ሆነ” በማለት ይናገራል። (ኢሳይያስ 53:9, 12) ልክ በትንቢቱ እንደተነገረው ኢየሱስ የተገደለው ከወንጀለኞች ጋር ሲሆን የተቀበረው ግን በአንድ ሀብታም ቤተሰብ መቃብር ቦታ መሆኑ የሚያስደንቅ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ በአምላክ መንፈስ መሪነት እንደተጻፈ ካሳመኑኝ ፍጻሜያቸውን ያገኙ በርካታ ትንቢቶች መካከል ይህ አንዱ ብቻ ነው። (2 ጢሞቴዎስ 3:16) ከጊዜ በኋላ የይሖዋ ምሥክር ሆንኩ።
የይሖዋ ምሥክር መሆንህ የሚያስደስትህ ለምንድን ነው?
እምነታችን በጭፍን አመለካከት ላይ የተመሠረተ አይደለም፤ በሳይንስ የተረጋገጡ እውነታዎችን አምነን እንቀበላለን
እምነታችን በጭፍን አመለካከት ላይ የተመሠረተ አይደለም፤ በሳይንስ የተረጋገጡ እውነታዎችን አምነን እንቀበላለን። በተጨማሪም በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ያሉትን መመሪያዎች በጥብቅ እንከተላለን። የይሖዋ ምሥክር እንደመሆኔ የመጽሐፍ ቅዱስን የሚያጽናና መልእክት ለሰዎች ማካፈልና ለሚነሱባቸው ጥያቄዎች መልስ እንዲያገኙ መርዳት ያስደስተኛል።
^ አን.9 በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀ።