ለቤተሰብ | የወላጅ ሚና
ስለ ሴክስቲንግ ከልጃችሁ ጋር መነጋገር የምትችሉት እንዴት ነው?
ተፈታታኙ ነገር
ሴክስቲንግ በወጣቶች መካከል በጣም የተለመደ እንደሆነ ሰምተህ ሊሆን ይችላል። ‘የእኔ ልጅ እንዲህ ያደርግ ይሆን?’ ብለህ ራስህን ትጠይቅ ይሆናል።
ስለ ጉዳዩ ከልጅህ ጋር መነጋገር ብትፈልግም ‘ይህን ማድረግ የምችለው እንዴት ነው?’ የሚለው ነገር ያስጨንቅህ ይሆናል። የዚህን ጥያቄ መልስ ከመመለሳችን በፊት ሴክስቲንግ በአንዳንድ ወጣቶች ዘንድ በጣም እየተለመደ የመጣው ለምን እንደሆነና ይህ አንተን ሊያሳስብህ የሚገባው ለምን እንደሆነ እንመልከት። *
ምክንያቱ ምንድን ነው?
አንዳንድ ወጣቶች የሚወዱትን ሰው ለማሽኮርመም ሲሉ የፆታ ብልግና የሚንጸባረቅባቸው መልእክቶችን ይልካሉ።
አንዲት ወጣት የራሷን እርቃን የሚያሳዩ ፎቶዎች የምትልከው አንድ ወንድ እንዲህ እንድታደርግ ተጽዕኖ ስላደረገባት ሊሆን ይችላል።
አንድ ወንድ ጓደኞቹን ለማዝናናት ወይም ከአንዲት ሴት ጋር የነበረው ጓደኝነት በመቋረጡ የበቀል ስሜቱን ለማርካት ሲል የእሷን እርቃን የሚያሳዩ ፎቶዎችን ለብዙዎች የሚልክበት ጊዜ አለ።
ምክንያቱ ምንም ይሁን ምን ሞባይል ስልክ የያዘ አንድ ወጣት ብዙ ችግር ውስጥ ሊገባ ይችላል። “አንድ ቁልፍ በመጫን ብቻ የብዙዎች ሕይወት ለዘለቄታው ተለውጧል” በማለት ሳይበርሴፍ የተባለው መጽሐፍ ተናግሯል።
አንድ ፎቶ አንዴ በኢንተርኔት መረብ ውስጥ ከገባ፣ ሌሎች የሚጠቀሙበትን መንገድ መቆጣጠር እንደማይቻል ብዙ ሰዎች አይረዱም። ከዩናይትድ ስቴትስ የፌዴራል የወንጀል ምርመራ ቢሮ (ኤፍ ቢ አይ) የወጣ አንድ ሪፖርት እንዳመለከተው አንዲት የ18 ዓመት ወጣት፣ የወንድ ጓደኛዋ በሞባይል ስልኳ የላከችለትን እርቃኗን የሚያሳይ ፎቶ በመቶዎች ለሚቆጠሩ አብረዋት ለሚማሩ ልጆች በመላኩ ምክንያት ራሷን ልታጠፋ ችላለች። ፎቶውን በማሰራጨት ረገድ አስተዋጽኦ ያደረጉት ልጆች ይህች ልጅ በኀፍረት እንድትሸማቀቅ አድርገዋል።
በሌላ በኩል ደግሞ ሴክስቲንግ፣ አንድን ሰው ከሕግ አንጻር ተጠያቂ ሊያደርገው ይችላል። ለምሳሌ በአንዳንድ ቦታዎች እርቃንን የሚያሳዩ ፎቶዎችን በእነሱ የዕድሜ ክልል ለሚገኙ ልጆች የሚልኩ ለአካለ መጠን ያልደረሱ ወጣቶች፣ ልጆችን ለብልግና ምስሎች መጠቀሚያ በማድረግ ሊከሰሱ ብሎም ከፆታ ጋር በተያያዘ እንደ ወንጀለኛ ተቆጥረው ስማቸው በመንግሥት መዝገብ ላይ ሊጻፍ ይችላል። ወላጆች፣ የሞባይል ስልኩ በእናንተ ስም የወጣ ከሆነ ወይም ልጃችሁ ከዚህ ድርጊት እንዲቆጠብ ጥረት ካላደረጋችሁ እናንተም ብትሆኑ ልትጠየቁ ትችላላችሁ።
ምን ማድረግ ይቻላል?
ግልጽ ደንብ አውጡ። የልጃችሁን የስልክ አጠቃቀም ሙሉ በሙሉ መቆጣጠር ባትችሉም ልጃችሁ ያወጣችሁትን ደንብና ይህን ደንብ ቢጥስ ምን ቅጣት እንደሚጠብቀው ማሳወቅ ትችላላችሁ። በተጨማሪም ወላጅ እንደመሆናችሁ መጠን የልጃችሁን ሞባይል ስልክ የመቆጣጠር መብት እንዳላችሁ አስታውሱ።—የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓት፦ ኤፌሶን 6:1
ልጃችሁ ድርጊቱ በሚያስከትለው ጉዳት ላይ እንዲያስብ አድርጉ። እንዲህ ማለት ትችላላችሁ፦ “ወጣቶች ስለ ሴክስቲንግ ያላቸው አመለካከት የተለያየ ነው። ሴክስቲንግ የሚለው ቃል ምን ትርጉም ይሰጥሃል?” “ተገቢ እንዳልሆኑ የሚሰሙህ ምን ዓይነት ፎቶዎች ናቸው?” “በአንዳንድ ቦታዎች ለአካለ መጠን ያልደረሰ አንድ ልጅ በእሱ የዕድሜ ክልል ላለ ሌላ ልጅ እርቃንን የሚያሳይ ፎቶ ቢልክ በወንጀል ሊጠየቅ ይችላል። ሴክስቲንግ ይህን ያህል መጥፎ ድርጊት እንደሆነ ይሰማሃል?” “ሴክስቲንግ ከሥነ ምግባር አኳያ ስህተት የሆነው ለምንድን ነው?” ልጃችሁ ሐሳቡን ሲገልጽ ልብ ብላችሁ አዳምጡ፤ የመላኪያውን ቁልፍ ከተጫነ በኋላ የሚመጣውን ጣጣ እንዲያስብ አድርጉ።—የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓት፦ ዕብራውያን 5:14
የመላኪያውን ቁልፍ ከተጫናችሁ በኋላ የሚመጣውን ጣጣ አስቡ
ሊያጋጥሙ የሚችሉ ሁኔታዎችን በማንሳት ተወያዩ። ለሴት ልጃችሁ እንዲህ ልትሏት ትችላላችሁ፦ “ለምሳሌ አንዲት ልጅ የወንድ ጓደኛዋ ‘ሴክስት’ እንድታደርግለት ተጫናት እንበል። ይህች ልጅ ምን ማድረግ ይኖርባታል? ጓደኝነቷን ላለማጣት ስትል እሺ ትበል? ጥያቄውን ባትቀበልም በሌላ መንገድ ማሽኮርመሟን ትቀጥል? ጓደኝነቷን ታቋርጥ? ወይስ ለትልቅ ሰው ትናገር?” ልጃችሁ ጉዳዩን በጥሞና እንድታስብበት እርዷት። እርግጥ ነው፣ ለወንድ ልጃችሁም ተመሳሳይ ዘዴ ልትጠቀሙ ትችላላችሁ።—የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓት፦ ገላትያ 6:7
ጥሩ ስም ማትረፍ ያለውን ጥቅም እንዲገነዘብ እርዱት። እንደሚከተለው ያሉ ጥያቄዎችን ተጠቀሙ፦ ጥሩ ስም መያዝህ ምን ያህል አስፈላጊ ነው? በየትኛው ባሕርይ ብትታወቅ ደስ ይልሃል? መጥፎ ፎቶ በመላክ ሌላን ሰው ለኀፍረት ብትዳርግ ምን ይሰማሃል? ትክክል ለሆነ ነገር አቋም ብትወስድስ ምን ይሰማሃል? ልጃችሁ “ጥሩ ሕሊና” እንዲኖረው እርዱት።—1 ጴጥሮስ 3:16
ራሳችሁ ጥሩ ምሳሌ ሁኑ። መጽሐፍ ቅዱስ አምላካዊ ጥበብ ንጹሕና ከግብዝነት የጸዳ እንደሆነ ይናገራል። (ያዕቆብ 3:17) እናንተ ያሏችሁ የሥነ ምግባር እሴቶች ይህን ጥቅስ ያንጸባርቃሉ? “እኛ ራሳችን ጥሩ ምሳሌ መሆን አለብን፤ መጥፎ ወይም ሕገ ወጥ ተደርገው የሚቆጠሩ ምስሎችን ወይም ድረ ገጾችን መመልከት የለብንም” በማለት ሳይበርሴፍ የተባለው መጽሐፍ ተናግሯል።
^ አን.5 “ሴክስቲንግ” የሚለው ቃል የብልግና መልእክቶችን፣ ፎቶዎችንና ቪዲዮዎችን በሞባይል ስልክ መላላክን ያመለክታል። ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት jw.org ከተባለው ድረ ገጽ ላይ “የወጣቶች ጥያቄ—ስለ ሴክስቲንግ ምን ማወቅ ይኖርብኛል?” የሚለውን ርዕስ አንብብ፤ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች > ወጣቶች በሚለው ሥር ይገኛል።