መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?
ጋብቻ
ጋብቻ እንዲሁ አብሮ ለመኖር የሚደረግ ማኅበራዊ ዝግጅት ነው?
“አምላክ ያጣመረውን ማንም ሰው አይለያየው።”—ማቴዎስ 19:6
መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?
ጋብቻ በአምላክ ዘንድ ማኅበራዊ ዝግጅት ከመሆን የበለጠ ትርጉም አለው። ጋብቻ በአንድ ወንድና በአንዲት ሴት መካከል የሚመሠረት ቅዱስ ጥምረት ነው። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “በፍጥረት መጀመሪያ ‘አምላክ ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው። ከዚህም የተነሳ ሰው ከአባቱና ከእናቱ ይለያል፤ ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ’፤ . . . ስለዚህ አምላክ ያጣመረውን ማንም ሰው አይለያየው።” *—ማርቆስ 10:6-9፤ ዘፍጥረት 2:24
“አምላክ ያጣመረው” የሚለው አባባል ጋብቻ የሚመሠረተው በሰማይ መሆኑን አያመለክትም። ከዚህ ይልቅ የጋብቻን ዝግጅት ያስጀመረው ፈጣሪያችን መሆኑን ያመለክታል፤ ይህ ደግሞ ጥምረቱ በቁም ነገር መታየት የሚገባው መሆኑን ያጎላል። አንድ ባልና ሚስት ለጋብቻ እንዲህ ዓይነት አመለካከት የሚኖራቸው ከሆነ ትዳራቸውን ቅዱስና ዘላቂ ጥምረት እንደሆነ አድርገው ይመለከቱታል፤ ይህም ትዳራቸው እንዲሳካ ያላቸውን ቁርጠኝነት ያጠናክርላቸዋል። በተጨማሪም ባልና ሚስት የሥራ ድርሻቸውን በሚወጡበት ጊዜ መመሪያ ለማግኘት ወደ መጽሐፍ ቅዱስ ዘወር የሚሉ ከሆነ በትዳራቸው ስኬታማ የመሆናቸው አጋጣሚ ከፍ ይላል።
የወንዱ ድርሻ ምንድን ነው?
“ባልም የሚስቱ ራስ ነው።”—ኤፌሶን 5:23
መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?
ቤተሰብ ሥርዓት ባለው መንገድ እንዲመራ ከተፈለገ የመጨረሻውን ውሳኔ የሚያደርግ ሰው መኖር አለበት። መጽሐፍ ቅዱስ ይህን ኃላፊነት የሰጠው ለባልየው ነው። ይሁን እንጂ ይህ መሆኑ እሱን አምባገነን ወይም ፈላጭ ቆራጭ እንዲሆን ሥልጣን አይሰጠውም። ወይም ደግሞ ከኃላፊነቱ በመሸሽ ሚስቱ ለእሱ ያላት አክብሮት እንዲጠፋ አያደርግም፤ አሊያም የእሱንም ኃላፊነት ደርባ እንድትሠራ በማድረግ አላስፈላጊ ሸክም አይጭንባትም። ከዚህ ይልቅ ሚስቱን ለመንከባከብ ጠንክሮ እንዲሠራና እሷን ከማንም ይበልጥ የሚቀርባትና እምነት የሚጥልባት አጋሩ እንደሆነች አድርጎ በማየት እንዲያከብራት አምላክ ይጠብቅበታል። (1 ጢሞቴዎስ 5:8፤ 1 ጴጥሮስ 3:7) “ባሎች ሚስቶቻቸውን እንደ ገዛ አካላቸው አድርገው ሊወዷቸው ይገባል” በማለት ኤፌሶን 5:28 ይናገራል።
ሚስቱን የሚወድ ባል ችሎታዋንና ተሰጥኦዋን ከፍ አድርጎ ይመለከታል፤ በተለይ ቤተሰቡን በሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ አመለካከቷን ከግምት በማስገባት ለእሷ ያለውን አክብሮት ይገልጻል። የቤተሰቡ ራስ ስለሆነ ብቻ የእኔ ሐሳብ ተቀባይነት ካላገኘ ብሎ ድርቅ ማለት የለበትም። ፈሪሃ አምላክ የነበረው አብርሃም፣ ሚስቱ ቤተሰቡን በሚመለከት አንድ ጉዳይ ላይ ያቀረበችውን ጥሩ ምክር ለመቀበል እምቢ ባለ ጊዜ ይሖዋ አምላክ “ሣራ የምትልህን ሁሉ ስማ” ብሎታል። (ዘፍጥረት 21:9-12) አብርሃም አምላክ የነገረውን በትሕትና በመፈጸሙ ቤተሰቡ ሰላምና አንድነት አልፎ ተርፎም የአምላክን በረከት ማግኘት ችሏል።
የሴቲቱ ድርሻ ምንድን ነው?
“እናንተ ሚስቶች፣ . . . ለገዛ ባሎቻችሁ ተገዙ።”—1 ጴጥሮስ 3:1
መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?
አምላክ ለመጀመሪያው ሰው ሚስት ከመፍጠሩ በፊት “ሰው ብቻውን መሆኑ መልካም አይደለምና የሚስማማውን ረዳት አበጅለታለሁ” ብሎ ነበር። (ዘፍጥረት 2:18) ረዳት የሚለው ቃል ማሟያ ወይም ፍጹም የሚያደርግ የሚል ትርጉም ያስተላልፋል። በመሆኑም አምላክ ሴቲቱን የፈጠራት ከወንዱ ጋር አንድ ዓይነት እንድትሆን ወይም እንድትፎካከረው ሳይሆን የእሱ ማሟያ እንድትሆንለት ነበር። ሁለቱም አንድ ላይ በመሆን ልጆች እንዲወልዱና ምድርን በዘሮቻቸው እንዲሞሉ አምላክ የሰጣቸውን ተልእኮ መፈጸም ይችሉ ነበር።—ዘፍጥረት 1:28
ሴቲቱ የራሷን ድርሻ መወጣት እንድትችል አምላክ በአካል፣ በአእምሮና በስሜት ተስማሚ የሆነ ተፈጥሮ እንዲኖራት አድርጓል። እነዚህን ስጦታዎቿን በጥበብና በፍቅር ስትጠቀምባቸው ለትዳሯ መሳካት ከፍተኛ አስተዋጽኦ የምታበረክት ከመሆኗም በላይ ባሏ ረክቶና ተረጋግቶ እንዲኖር ትረዳዋለች። እንዲህ ዓይነቷ መልካም ሴት በአምላክ ዘንድ የተመሰገነች ናት። *—ምሳሌ 31:28, 31