የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ
የዜና ማሰራጫዎችን ማመን ይቻላል?
ብዙ ሰዎች በዜና ማሰራጫዎች የሚሰሟቸውንና የሚያነቧቸውን ነገሮች ይጠራጠራሉ። ለምሳሌ በዩናይትድ ስቴትስ በ2012 በተደረገ የጋለፕ ጥናት ሰዎች በጋዜጣ፣ በቴሌቪዥንና በሬዲዮ የሚተላለፈው ዜና ትክክለኛ፣ ሚዛናዊና የተሟላ በመሆኑ ላይ “ምን ያህል እምነት እንዳላቸው” ተጠይቀው ነበር። ከ10 ሰዎች 6ቱ የሰጡት መልስ “እምብዛም እምነት አንጥልበትም” ወይም “ምንም እምነት አንጥልበትም” የሚል ነበር። እንዲህ ያለው ጥርጣሬ ተገቢ ነው?
ብዙ ጋዜጠኞችና ጋዜጠኞቹ የሚሠሩላቸው ድርጅቶች ትክክለኛና የተሟላ መረጃ የማስተላለፍ ቁርጠኝነት እንዳላቸው ይናገራሉ። ይሁን እንጂ ሰዎች ጥርጣሬ እንዲያድርባቸው የሚያደርጉ ነገሮች አሉ። እስቲ የሚከተሉትን ሁኔታዎች አጢን፦
-
የመገናኛ ብዙኃን ባለቤት የሆኑ ትላልቅ ድርጅቶች ዋነኞቹን የዜና ማሰራጫዎች በባለቤትነት የሚያስተዳድሩት በጣም ከፍተኛ አቅም ያላቸው ጥቂት ድርጅቶች ናቸው። እነዚህ የዜና ማሰራጫዎች የትኞቹ ክንውኖች እንደሚዘገቡ፣ በምን መንገድ እንደሚዘገቡና ምን ያህል ሽፋን ሊያገኙ እንደሚገባ በመወሰን ረገድ ከፍተኛ ተጽዕኖ ያሳድራሉ። አብዛኞቹ ድርጅቶች ለትርፍ የተቋቋሙ በመሆናቸው የዜና ማሰራጫዎቹ የሚያደርጉት ውሳኔ ከሚያገኙት የገንዘብ ጥቅም ጋር የተያያዘ ሊሆን ይችላል። አንድ ዜና፣ የዜና ማሰራጫ ድርጅቱን ባለቤቶች ትርፍ የሚነካ ከሆነ ሳይተላለፍ ሊቀር ይችላል።
-
መንግሥታት በዜና የምንሰማቸው አብዛኞቹ ነገሮች ከሕዝብና ከመንግሥታት ጋር የተያያዙ ናቸው። መንግሥታት፣ ሕዝባቸው ላወጡት ፖሊሲና ለባለሥልጣናት ድጋፍ እንዲሰጥ ለማሳመን ይፈልጋሉ። መገናኛ ብዙኃን የሚያስተላልፉት መረጃ ከመንግሥት ያገኙትን በመሆኑ ጋዜጠኞችና የመንግሥት የመረጃ ምንጮች እርስ በርስ የሚተባበሩባቸው ጊዜያት አሉ።
-
ማስታወቂያ በአብዛኞቹ አገሮች ውስጥ ያሉ የዜና ማሰራጫዎች ሕልውናቸው የተመካው ከማስታወቂያ በሚያገኙት ገቢ ላይ ነው። በዩናይትድ ስቴትስ መጽሔቶች ከ50 እስከ 60 በመቶ፣ ጋዜጦች 80 በመቶ፣ ለትርፍ የተቋቋሙ የቴሌቪዥን ድርጅቶች ደግሞ 100 በመቶ የሚሆነውን ገቢያቸውን የሚያገኙት ከማስታወቂያ ነው። ማስታወቂያ እንዲተላለፍላቸው የሚፈልጉ ድርጅቶች በምርቶቻቸው ወይም በአስተዳደራቸው ላይ ጥላሸት የሚቀባ ፕሮግራም ስፖንሰር ማድረግ እንደማይፈልጉ የታወቀ ነው። አንድ የዜና ማሰራጫ የሚያስተላልፈው ነገር ካልጣማቸው ማስታወቂያቸው በሌላ የመገናኛ ብዙኃን ድርጅት እንዲቀርብ ሊያደርጉ ይችላሉ። የዜና አርታኢዎች ይህን ስለሚያውቁ ሰዎች በስፖንሰሮቻቸው ላይ አሉታዊ ስሜት እንዲያሳድሩ የሚያደርጉ ዜናዎችን አፍነው ሊያስቀሩ ይችላሉ።
-
ሐቀኛ አለመሆን ሁሉም ዘጋቢዎች ሐቀኞች ናቸው ማለት አይቻልም። አንዳንድ ጋዜጠኞች ታሪክ ፈጥረው ሊያወሩ ይችላሉ። ለምሳሌ ከጥቂት ዓመታት በፊት በጃፓን የሚገኝ አንድ ሪፖርተር ባሕር ጠላቂዎች በኦኪናዋ በሚገኙ ኮራሎች ላይ ምን ያህል ጉዳት እያስከተሉ እንዳሉ የሚያሳይ ዘገባ ለማቅረብ ፈልጎ ነበር። በዚህ መንገድ ጉዳት የደረሰበት ኮራል ፈልጎ ማግኘት ሳይችል ሲቀር ራሱ የተወሰኑ ኮራሎችን ካበላሸ በኋላ ያን ፎቶግራፍ በማንሳት ማስረጃ አድርጎ አቀረበ። በተጨማሪም ተመልካቾችን ለማሳሳት ሲባል ፎቶግራፎችን አሻሽሎና ለውጦ ማቅረብ ይቻላል። በፎቶግራፎች ላይ ማሻሻያና ለውጥ ለማድረግ የሚያስችለው ቴክኖሎጂ በጣም ከመራቀቁ የተነሳ አንዳንዶቹን ለውጦች ፈጽሞ መለየት አይቻልም።
-
አቀራረብ የሚቀርበው ዘገባ ምንም ያህል እውነተኝነቱ የተረጋገጠ ቢሆንም ዘገባው የሚቀርብበት መንገድ በጋዜጠኛው አመለካከት ላይ የተመካ ነው። በአንድ ዘገባ ውስጥ መካተት ያለባቸው መረጃዎች የትኞቹ ናቸው? መቅረት ያለባቸውስ? ለምሳሌ አንድ የእግር ኳስ ቡድን ሁለት ግቦች ተቆጥረውበት ተሸንፎ ይሆናል። እውነታው ይህ ሆኖ ሳለ፣ ቡድኑ የተሸነፈበትን ምክንያት አስመልክቶ የሚቀርበው ዘገባ ግን እንደየጋዜጠኛው ሊለያይ ይችላል።
-
ማስቀረት ጋዜጠኞች ትኩረት የሚስብ ዘገባ ለማቅረብ መረጃዎቻቸውን በሚያደራጁበት ጊዜ ጉዳዩን ሊያወሳስቡ ወይም ውዝግብ ሊያስነሱ የሚችሉ ዝርዝር ሐሳቦችን ከማካተት ብዙጊዜ ይቆጠባሉ። ይህም አንዳንዶቹ መረጃዎች ተጋነው እንዲቀርቡ ሌሎቹ ደግሞ እንዲድበሰበሱ ያደርጋል። አንዳንድ ጊዜ የቴሌቪዥን ዜና አቅራቢዎችና ሪፖርተሮች አንድን ውስብስብ ርዕሰ ጉዳይ በአንድ ደቂቃ ወይም ከዚያ ብዙ በማይበልጥ ጊዜ ውስጥ ማቅረብ ስለሚጠበቅባቸው አስፈላጊ የሆኑ ዝርዝር ሐሳቦችን ሳይጠቅሱ ሊያልፉ ይችላሉ።
-
ፉክክር ከቅርብ አሥርተ ዓመታት ወዲህ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ቁጥራቸው በመበራከቱ ምክንያት ተመልካቾች አንድን ጣቢያ ብቻ በመመልከት የሚያሳልፉት ጊዜ በጣም እየቀነሰ ሄዷል። የዜና ማሰራጫ ጣቢያዎች የተመልካቾቻቸውን ትኩረት ይዘው ለመቆየት ሲሉ ለየት ያለ ወይም አዝናኝ የሆነ ነገር ለማቅረብ ይገደዳሉ። ሚድያ ባያስ የተባለው መጽሐፍ ይህን አስመልክቶ አስተያየት ሲሰጥ “[በቴሌቪዥን የሚቀርቡ] ዜናዎች አስደንጋጭ ወይም ስሜት ቀስቃሽ በሆኑ ምስሎች የተሞሉ ሲሆኑ የዜና ዘገባዎቹም ተመልካቾች ካላቸው አጭር የትኩረት ጊዜ ጋር እንዲመጣጠኑ ሲባል ተቀነጫጭበው ይቀርባሉ” ብሏል።
-
ስህተቶች ጋዜጠኞች፣ ሰዎች እንደመሆናቸው መጠን ያልታሰበ ስህተት የሚሠሩበት ጊዜ ይኖራል። የሆሄያት ግድፈት፣ አለቦታው የገባ ሥርዓተ ነጥብና የሰዋስው ስህተት የመሳሰሉ ነገሮች የአንድን ዓረፍተ ነገር ትርጉም ሊያዛቡ ይችላሉ። መረጃዎቹ በጥንቃቄ ላይጣሩ ይችላሉ። ቁጥሮችም አንድን ጋዜጠኛ በቀላሉ ሊያሳስቱ ይችላሉ፤ የተሰጠው የጊዜ ገደብ ሳያልፍ ዘገባውን ለማቅረብ እየተጣደፈ ያለ አንድ ጋዜጠኛ 100,000 ብሎ ከመጻፍ ይልቅ 10,000 ብሎ ሊጽፍ ይችላል።
-
አመለካከት ትክክለኛ የሆነ ሪፖርት ማቅረብ ብዙዎች እንደሚያስቡት ቀላል አይደለም። ዛሬ እውነት የሆነ ነገር ነገ ስህተት ሆኖ ሊገኝ ይችላል። ለምሳሌ ምድር የሥርዓተ ፀሐይ እምብርት እንደሆነች የሚታመንበት ጊዜ ነበር። አሁን ግን ምድር በፀሐይ ዙሪያ እንደምትዞር እናውቃለን።
ሚዛናዊ መሆን ያስፈልጋል
በዜና የሚቀርበውን ሁሉ አምነን መቀበል ጥበብ ባይሆንም ተአማኒነት ያለው ምንም ነገር አይቀርብም ብሎ መደምደምም ቢሆን ተገቢ አይደለም። ስለሆነም አንድን ዜና አእምሯችንን ክፍት አድርገን የምንከታተል ቢሆንም ጤናማ የሆነ ጥርጣሬ ቢያድርብን ክፋት የለውም።
መጽሐፍ ቅዱስ “ምላስ የምግብን ጣዕም እንደሚለይ፣ ጆሮ ቃላትን አይለይምን?” ይላል። (ኢዮብ 12:11) በመሆኑም የምንሰማቸውንና የምናነባቸውን ነገሮች ለመመዘን የሚያስችሉ ዘዴዎች ከዚህ ቀጥሎ ቀርበዋል፦
-
መረጃውን የሰጠው አካል፦ መረጃው የተገኘው እምነት ከሚጣልበትና ጉዳዩ ከሚመለከተው ኣካል ነው? ፕሮግራሙ ወይም ጽሑፉ የሚታወቀው ቁም ነገር ያለባቸውን ነገሮች በመመዝገብ ነው ወይስ ስሜታዊነት የሚንጸባረቅባቸውን መረጃዎች በማቅረብ? የዜናው ምንጭ የገንዘብ ድጋፍ የሚያገኘው ከማን ነው?
-
ምንጮች፦ ጥልቅ ምርምር እንደተደረገበት የሚያሳይ ማስረጃ አለ? ዘገባው በአንድ ምንጭ ላይ ብቻ የተመሠረተ ነው? ምንጮቹስ አስተማማኝ፣ ፍትሐዊና አድሏዊነት የማይንጸባረቅባቸው ናቸው? ሚዛናዊ ናቸው ወይስ የአንዱን ወገን አመለካከት ብቻ የሚያስተላልፉ?
-
ዓላማ፦ ራስህን እንዲህ ብለህ ጠይቅ፦ ‘ዜናው የቀረበበት ዋነኛ ዓላማ መረጃ ለማስተላለፍ ነው ወይስ ለማዝናናት? አንድን ነገር ለማሳመን እየሞከረ ነው ወይስ ለመደገፍ?’
-
ቃና፦ አንድ ዜና የቀረበበት ቃና ቁጣ፣ ጥላቻ ወይም ትችት የሚንጸባረቅበት ከሆነ የሚተላለፈው ነገር ምክንያታዊ ከመሆን ይልቅ ጥቃት ለመሰንዘር የታለመ እንደሆነ መገመት ይቻላል።
-
ከሌሎች መረጃዎች ጋር የማይጋጭ፦ መረጃዎቹ በሌሎች ዘገባዎች ላይ ከወጡት ጋር ይስማማሉ? የሚቀርቡት የዜና ዘገባዎች እርስ በርሳቸው የሚጋጩ ከሆነ ተጠንቀቅ።
-
ወቅታዊነት፦ መረጃው ወቅታዊ ነው? ከ20 ዓመት በፊት ትክክለኛ እንደሆነ ተደርጎ ይታሰብ የነበረ ነገር ዛሬ ተቀባይነት ሊያጣ ይችላል። በሌላ በኩል ደግሞ ገና ትኩስ ዜና ከሆነ ያልተሟላና ሁሉን አቀፍ መረጃ ያልያዘ ሊሆን ይችላል።
ታዲያ የዜና ማሰራጫዎችን ማመን ይቻላል? ሰለሞን “ተላላ ሰው ሁሉን ያምናል፤ አስተዋይ ግን ርምጃውን ያስተውላል” ሲል ጥበብ ያዘለ ምክር አስፍሯል።—ምሳሌ 14:15