በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ለቤተሰብ | ወጣቶች

የእኩዮችን ተጽዕኖ መቋቋም የሚቻልበት መንገድ

የእኩዮችን ተጽዕኖ መቋቋም የሚቻልበት መንገድ

ተፈታታኙ ነገር

“በመለስተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ሳለሁ አብዛኞቹ ልጆች አይቀርቡኝም ነበር፤ ይህ ደግሞ ስሜቴን ጎድቶታል። ስለሆነም ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ስገባ በቁመናዬና በአመለካከቴ ላይ ለውጥ አደረግኩ። ጓደኞች የማግኘት ከፍተኛ ፍላጎት ስለነበረኝ የክፍል ጓደኞቼ እንዲወዱኝ ስል ብቻ በእኩዮች ተጽዕኖ ተሸነፍኩ።”—የ16 ዓመቷ ጄኒፈር *

አንተስ የእኩዮች ተጽዕኖ ይደርስብሃል? ከሆነ ይህ ርዕስ ተጽዕኖውን እንድትቋቋም ይረዳሃል።

ለእኩዮች ተጽዕኖ በምትሸነፍበት ጊዜ ሌሎች ሰዎች እንዲቆጣጠሩህ መፍቀድህ ነው፤ በመሆኑም ማሰብ እንደማይችል ሮቦት ትሆናለህ። ለምን በአንተ ላይ እንዲሠለጥኑ ትፈቅዳለህ?—ሮም 6:16

ማወቅ የሚኖርብህ ነገር

የእኩዮች ተጽዕኖ ጥሩ ሰዎችን መጥፎ ነገር እንዲያደርጉ ሊገፋፋቸው ይችላል።

“መጥፎ ጓደኝነት መልካሙን አመል ያበላሻል።”—1 ቆሮንቶስ 15:33

“አንድ ዓይነት አካሄድ ወይም ድርጊት መጥፎ እንደሆነ እናውቅ ይሆናል፤ ነገር ግን ከሁኔታው ጋር ስንፋጠጥ ስሜታችን ያሸንፈንና ሰውን የማስደሰት ዝንባሌ ይቆጣጠረናል!”—ዳና

የእኩዮች ተጽዕኖ እኩዮችህ በሚያሳድሩብህ ተጽዕኖ ብቻ የተወሰነ አይደለም።

“ትክክል የሆነውን ነገር ማድረግ ስፈልግ ከእኔ ጋር ያለው ግን መጥፎ ነገር ነው።”—ሮም 7:21

“የሚሰማኝ ተጽዕኖ አብዛኛውን ጊዜ የሚመጣው ከራሴ ነው፤ እኩዮቼ የሚያወሩትን ነገር ለማግኘት የምመኘው እኔው ራሴ ነኝ። እነሱ ደግሞ በጣም የሚያስደስት ነገር እንደሆነ አድርገው ያቀርቡታል።”—ዳያና

የእኩዮችን ተጽዕኖ መቋቋም ልትኮራበት የሚገባ ስኬት ነው።

“ጥሩ ሕሊና ይኑራችሁ።”—1 ጴጥሮስ 3:16

“በአንድ ወቅት የእኩዮችን ተጽዕኖ መቋቋም በጣም ይከብደኝ ነበር፤ አሁን ግን ከእኩዮቼ የተለየሁ ሆኜ መታየት አያስፈራኝም። ካደረግኩት ውሳኔ ንቅንቅ አልልም። ንጹሕ ሕሊና ይዞ እንደመተኛት የሚያስደስት ነገር የለም።”—ካርላ

ምን ማድረግ ትችላለህ?

መጥፎ ነገር እንድታደርግ እኩዮችህ ተጽዕኖ ሲያደርጉብህ እንዲህ ለማድረግ ሞክር፦

መዘዙን ቆም ብለህ አስብ። ራስህን እንዲህ እያልክ ጠይቅ፦ ‘ለተጽዕኖው ብሸነፍና ያደረግኩት ነገር ቢታወቅብኝስ? ወላጆቼ ስለ እኔ ምን ይሰማቸዋል? እኔስ ስለ ራሴ ምን ይሰማኛል?’—የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓት፦ ገላትያ 6:7

“ወላጆቼ ‘በተጽዕኖው ብትሸነፊ ምን ሊደርስብሽ ይችላል?’ ብለው ይጠይቁኛል። የእኩዮች ተጽዕኖ ወደተሳሳተ ጎዳና እንዴት ሊመራኝ እንደሚችል እንድገነዘብ ይረዱኛል።”—ኦሊቭያ

እምነትህን አጠናክር። ‘ይህ አካሄድ እኔንም ሆነ ሌሎችን ይጎዳል ብዬ የማምነው ለምንድን ነው?’ ብለህ ራስህን ጠይቅ።—የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓት፦ ዕብራውያን 5:14

“ትንሽ ልጅ ሳለሁ እምቢ እል ነበር ወይም አጭር መልስ ብቻ እሰጥ ነበር፤ አሁን ግን አንድን ነገር ለምን እንደማደርግና እንደማላደርግ ጥሩ ማብራሪያ መስጠት እችላለሁ። ትክክልና ስህተት ነው ብዬ የማምንበትን ነገር በተመለከተ ጥብቅ አቋም አለኝ። መልስ የምሰጠው እኔው ራሴ እንጂ ሌሎች አይደሉም።”—አኒታ

ስለ ማንነትህ አስብ። ‘ምን ዓይነት ሰው መሆን እፈልጋለሁ?’ ብለህ ራስህን ጠይቅ። ከዚያም እየደረሰብህ ስላለው ተጽዕኖ አስብና ‘ታዲያ እንዲህ ያለ ሰው ይህ ሁኔታ ቢያጋጥመው ምን ያደርጋል?’ ብለህ ራስህን ለመጠየቅ ሞክር።—የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓት፦ 2 ቆሮንቶስ 13:5

“በማንነቴ አላፍርም፤ በመሆኑም ሌሎች ስለ እኔ የሚያስቡት ነገር አያስጨንቀኝም። ከዚህ በላይ ደግሞ እኔን በማንነቴ የሚወዱኝ ብዙ ሰዎች አሉ።”—አሊስያ

የወደፊቱን ጊዜ አሻግረህ ተመልከት። ተማሪ ከሆንክ በዛሬው ጊዜ በአድናቆት እንዲያዩህ የምትፈልጋቸውን ልጆች ከጥቂት ዓመታት፣ እንዲያውም ከወራት በኋላ ፈጽሞ ላታገኛቸው ትችላለህ።

“ተማሪ ሳለን የተነሳነውን ፎቶ ሳይ ከክፍል ጓደኞቼ መካከል የአንዳንዶቹን ስም እንኳ ማስታወስ አልቻልኩም። አብሬያቸው እማር በነበረበት ጊዜ ግን የማምንበትን ነገር አጥብቄ ከመከተል ይልቅ የእነሱን አመለካከት አስበልጬ እመለከት ነበር። እንዴት ያለ ሞኝነት ነው!”—የ22 ዓመቷ ዶውን

አስቀድመህ ተዘጋጅ። መጽሐፍ ቅዱስ “ለእያንዳንዱ ሰው እንዴት መልስ መስጠት እንደሚገባችሁ [እወቁ]” ይላል።—ቆላስይስ 4:6

“ወላጆቼ እኔና እህቴ በገሃዱ ዓለም ሊያጋጥሙን የሚችሉ ሁኔታዎችን አስቀድመን በማሰብ ምን ምላሽ እንደምንሰጥ ከወዲሁ እንድንለማመድ ይረዱን ነበር።”—ክርስቲን

^ አን.4 በዚህ ርዕስ ውስጥ የተጠቀሱት አንዳንዶቹ ስሞች ተቀይረዋል።