በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

 የታሪክ መስኮት

ጆሴፍ ፕሪስትሊ

ጆሴፍ ፕሪስትሊ

“ሁለገብነቱ፣ ጉጉቱ፣ ያደረጋቸው ነገሮችና ሰብዓዊነቱ፤ ከቁሳዊ፣ ከሥነ ምግባራዊና ከማኅበራዊ ጉዳዮች አኳያ ስለ በርካታ ነገሮች ለማወቅ ያለው ፍላጎት፤ በሳይንስ፣ በሥነ መለኮት፣ በፍልስፍናና በፖለቲካ ረገድ ያበረከተው አስተዋጽኦ፤ ለፈረንሳይ አብዮት ያደረገው ድጋፍ እንዲሁም ያለ ጥፋቱ የደረሰበት ሥቃይና መከራ [ፕሪስትሊን] የአሥራ ስምንተኛው መቶ ዘመን ታላቅ ሰው ያደርገዋል።”—ፍሬደሪክ ሃሪሰን፣ ፈላስፋ

ጆሴፍ ፕሪስትሊ ይህን ያህል ከፍተኛ ቦታ የተሰጠው ምን ነገር ቢያከናውን ነው? ግኝቶቹና የሥነ ጽሑፍ ሥራዎቹ የመንግሥትን ሚና፣ የአምላክን ማንነት እንዲሁም የምንተነፍሰውን አየር በተመለከተ በሰዎች አስተሳሰብ ላይ ተጽዕኖ አሳድረዋል።

ፕሪስትሊ ስለ ሳይንስም ሆነ ስለ ሃይማኖት በሚጽፍበት ጊዜ ለእውነትና ለሐቅ ለመቆም ሲል መሠረት የሌላቸው ጽንሰ ሐሳቦችንና ሲወርድ ሲዋረድ የመጡ ወጎችን ይቃወም ነበር። ይህን እንዴት እንዳደረገ እስቲ እንመልከት።

ሳይንሳዊ እውነቶችን ለማግኘት ያደረገው ፍለጋ

ቀደም ሲል ሳይንሳዊ ምርምሮችን በትርፍ ጊዜው ያከናውን የነበረው ጆሴፍ ፕሪስትሊ በ1765 ቤንጃሚን ፍራንክሊን ከተባለው አሜሪካዊ የሳይንስ ሊቅ ጋር ከተገናኘ በኋላ በኤሌክትሪክ መስክ ምርምር ማድረግ ጀመረ። በቀጣዩ ዓመት ሌሎች የሳይንስ ሊቃውንት ጆሴፍ ፕሪስትሊ በደረሰባቸው ሳይንሳዊ ግኝቶች በመደነቃቸው ሮያል ሶሳይቲ ኦቭ ለንደን በተባለ ስመ ጥር ማኅበር ውስጥ አባል እንዲሆን መረጡት።

ቀጥሎ ፕሪስትሊ ትኩረቱን ወደ ኬሚስትሪ አዞረ። በአጭር ጊዜ ውስጥ አሞንያን እና ናይትረስ ኦክሳይድን (የሚያስቅ ጋዝ) ጨምሮ በርካታ አዳዲስ ጋዞችን አገኘ። ካርቦን ዳይኦክሳይድ ከውሃ ጋር እንዲቀላቀል በማድረግ ጋዝ ያለው ውኃ መፍጠርም ችሏል።

ፕሪስትሊ በ1774 በደቡባዊ እንግሊዝ ሙከራ በሚያደርግበት ወቅት ሻማ ደምቆ እንዲበራ የሚያደርግ አስደናቂ ጋዝ አገኘ። በኋላም በመስተዋት ዕቃ ውስጥ አንዲት አይጥ በማስቀመጥ ይህንን ጋዝ (60 ሚሊ ሊትር)  ጨመረበት። አይጧ እንዲሁ በአየር በተሞላ የመስታወት ዕቃ ውስጥ ብትቀመጥ ኖሮ ከምትቆይበት በእጥፍ የሚበልጥ ጊዜ መቆየት ቻለች። ፕሪስትሊ ራሱ ይህን ጋዝ ወደ ውስጥ እንደሳበና ከዚያ በኋላ ለመተንፈስ እንደቀለለው ተናግሯል።

ጆሴፍ ፕሪስትሊ ያገኘው ጋዝ ኦክስጅን * ነበር። ሆኖም ፍሎጂስተን የሌለው አየር እንዳገኘ ስለተሰማው ይህንን ጋዝ ዲፍሎጂስቲኬትድ አየር በማለት ጠራው፤ ፍሎጂስተን የሚባለው ነገር አየር ተቀጣጣይ እንዳይሆን የሚያግድ ንጥረ ነገር እንደሆነ በመላምት ደረጃ ይታሰብ ነበር። ፕሪስትሊ የደረሰበት ድምዳሜ ስህተት ቢሆንም ይህ ግኝት ፕሪስትሊ “በሕይወቱ ካከናወናቸው ሥራዎች ሁሉ ቁንጮው” እንደሆነ ብዙዎች ይናገራሉ።

ሃይማኖታዊ እውነቶችን ለማግኘት ያደረገው ፍለጋ

ፕሪስትሊ፣ ስለ አንድ ጉዳይ በቂ ማስረጃ ሳይኖር አስቀድሞ መደምደም ሳይንሳዊ እውነት እንዳይታወቅ እንቅፋት ይሆናል የሚል እምነት ነበረው፤ በመሆኑም ሲወርድ ሲዋረድ የመጡ ወጎችና ቀኖናዎች ሃይማኖታዊ እውነቶች እንዳይታወቁ ጋሬጣ ሆነዋል ከሚል መደምደሚያ ደርሷል። የሚገርመው ግን ፕሪስትሊ የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት ለማግኘት ፍለጋ ባደረገባቸው የሕይወቱ ዘመናት፣ መጽሐፍ ቅዱስ ከሚያስተምረው ትክክለኛ ትምህርት ጋር የሚጋጩ አንዳንድ ሐሳቦችን ተቀብሎ ነበር። ለምሳሌ፣ በአንድ ወቅት አምላክ መጽሐፍ ቅዱስን በመንፈሱ እንዳስጻፈው አያምንም ነበር። በተጨማሪም ኢየሱስ ሰው ከመሆኑ በፊት በሰማይ ይኖር እንደነበረ የሚገልጸውን የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት አይቀበልም።

“ሳይንስ እውነትን ለማግኘት የሚደረግ ፍለጋ ነው ከተባለ ፕሪስትሊ እውነተኛ ሳይንቲስት ነበር ማለት እንችላለን።”—ካትረን ከለን፣ የባዮሎጂ ባለሙያ

በሌላ በኩል ግን ፕሪስትሊ በእሱ ዘመንም ሆነ እስከ አሁን ድረስ በትላልቅ ሃይማኖቶች ውስጥ ሰፊ ተቀባይነት ያገኙ ሐሰት የሆኑ ሃይማኖታዊ ትምህርቶችን አጋልጧል። ኢየሱስና ተከታዮቹ ያስተማሩት እውነት ከጊዜ በኋላ ሐሰት በሆኑ ትምህርቶች እንደተበረዘ ጽፏል፤ ከእነዚህ መካከል ሐሰት የሆነው የሥላሴ ትምህርት፣ ነፍስ አትሞትም የሚለው የተሳሳተ እምነትና በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተወገዘው የምስሎች አምልኮ እንደሚገኙበት ጽፏል።

የፕሪስትሊ ሃይማኖታዊ አመለካከቶች እንዲሁም ለአሜሪካና ለፈረንሳይ አብዮቶች ይሰጥ የነበረው ድጋፍ የአገሩ ተወላጆች በሆኑት እንግሊዛውያን ዘንድ ቁጣን አስነስቶበታል። በ1791 ረብሸኞች መኖሪያ ቤቱንና ቤተ ሙከራውን አወደሙበት፤ በዚህ ጊዜ ፕሪስትሊ ወደ ዩናይትድ ስቴትስ ለመሸሽ ተገደደ። ጆሴፍ ፕሪስትሊ በይበልጥ የሚታወሰው በሳይንሳዊ ግኝቶቹ ነው፤ ያም ቢሆን ፕሪስትሊ ስለ አምላክና ስለ ዓላማው መማር “ከሁሉ የላቀ ክብር የሚሰጠውና አስፈላጊ ነገር” እንደሆነ ያምን ነበር።

^ አን.10 ካርል ሼለ የተባለው ስዊድናዊ የኬሚስትሪ ባለሙያ ቀደም ሲል ኦክስጅንን አግኝቶ የነበረ ቢሆንም ግኝቱን በጽሑፍ ለማሳተም አልበቃም። በኋላ ላይ አንቷን ሎራን ለቩዋዝዬይ የተባለው ፈረንሳዊ የኬሚስትሪ ባለሙያ ለዚህ ጋዝ ኦክስጅን የሚለውን ስያሜ ሰጠው።