የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ | መከራ ሲደርስብህ
የሚወዱትን ሰው በሞት ማጣት
በብራዚል የሚኖረው ሮናልዱ፣ እናቱንና አባቱን ጨምሮ ለአምስት የቤተሰቡ አባላት ሞት ምክንያት የሆነ የመኪና አደጋ አጋጥሞት ነበር። “ቤተሰቦቼ በአደጋው እንደሞቱ የተነገረኝ ሁለት ወር ያህል ሆስፒታል ከቆየሁ በኋላ ነው” ይላል።
“መጀመሪያ ላይ ሁሉንም እንዳጣሁ ማመን አቅቶኝ ነበር። እንዴት ሁሉም ሊሞቱ ይችላሉ? ነገሩ እውነት መሆኑን ስገነዘብ በከፍተኛ ድንጋጤ ተዋጥኩ። እንደዚያ ያለ ሥቃይ ተሰምቶኝ አያውቅም። ከዚያ በኋላ ባሉት ቀናት፣ እነሱ ከሌሉ ሕይወት ምንም ትርጉም እንደሌለው ተሰማኝ። ለበርካታ ወራት በየቀኑ አለቅስ ነበር! መኪናዋን ሌላ ሰው እንዲነዳ በመፍቀዴ ራሴን ወቀስኩ። እኔ ብነዳ ኖሮ ቤተሰቦቼ አሁን በሕይወት ይኖሩ ነበር ብዬ አሰብኩ።
“ይህ ከሆነ አሥራ ስድስት ዓመታት አልፈዋል፤ እኔም ወደተለመደው ሕይወቴ መመለስ ችያለሁ። ይሁን እንጂ የቤተሰቦቼ አሳዛኝ ሞት ዛሬም ድረስ ሊሽር ያልቻለ ትልቅ ጠባሳ በሕይወቴ ውስጥ ጥሎ አልፏል።”
መከራውን መቋቋም
ሐዘንህ አምቀህ አትያዝ። መጽሐፍ ቅዱስ “ለማልቀስ ጊዜ አለው” ይላል። (መክብብ 3:1, 4) ሮናልዱ እንዲህ ብሏል፦ “ማልቀስ ባሰኘኝ ቁጥር አለቅሳለሁ። እንባዬን ለመቆጣጠር መታገል ምንም ጥቅም አልነበረውም፤ ደግሞም ካለቀስኩ በኋላ ቀለል ይለኛል።” እርግጥ ነው፣ ሰዎች ሐዘናቸውን የሚገልጹበት መንገድ ይለያያል። ስለዚህ ሐዘንህን የምትገልጸው ሌሎች በሚያዩት መንገድ ስላልሆነ ብቻ ስሜትህን አምቀህ ይዘኸዋል ወይም ደግሞ ራስህን አስገድደህ ማልቀስ አለብህ ማለት አይደለም።
ራስህን አታግልል። (ምሳሌ 18:1) ሮናልዱ እንዲህ ብሏል፦ “ከሌሎች እንድርቅ የሚታገለኝን ስሜት ለማሸነፍ ጥረት ማድረግ ነበረብኝ። ሰዎች ሊጠይቁኝ ሲመጡ በደስታ እቀበላቸዋለሁ። በተጨማሪም ለባለቤቴና ለቅርብ ወዳጆቼ የውስጥ ስሜቴን አውጥቼ እናገራለሁ።”
ሰዎች የሚጎዳ ነገር ቢናገሩህ አትረበሽ። “ሁሉ ለበጎ ነው” እንደሚሉ ያሉ አነጋገሮችን ትሰማ ይሆናል። ሮናልዱ “እኔን ለማጽናናት ተብለው የሚሰነዘሩ አንዳንድ ሐሳቦች ይጎዱኝ ነበር” ብሏል። ጎጂ በሆኑ ቃላት ላይ ከማብሰልሰል ይልቅ “የሚነገረውን ቃል ሁሉ ለማዳመጥ አትሞክር” የሚለውን ጥበብ ያዘለ የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር ተከተል።—መክብብ 7:21
ሙታን ስለሚገኙበት ሁኔታ እውነቱን ተማር። ሮናልዱ እንዲህ ብሏል፦ “መጽሐፍ ቅዱስ መክብብ 9:5 ላይ የሞቱ ሰዎች እየተሠቃዩ እንዳልሆኑ ይናገራል፤ ይህን ማወቄ ውስጣዊ ሰላም እንዲኖረኝ ረድቶኛል። በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ የሙታን ትንሣኤ እንደሚኖርና የሞቱ ሁሉ እንደገና በሕይወት እንደሚኖሩ ይገልጻል። ስለሆነም በሞት ያጣኋቸውን ቤተሰቦቼን ሩቅ አገር እንደሄዱ አድርጌ አስባለሁ።”—የሐዋርያት ሥራ 24:15
ይህን ታውቅ ነበር? መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ ‘ሞትን ለዘላለም የሚውጥበት’ ጊዜ እንደሚመጣ ይናገራል። *—ኢሳይያስ 25:8
^ አን.11 ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? የተባለውን መጽሐፍ ምዕራፍ 7 ተመልከት።