በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

 የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ | መከራ ሲደርስብህ—መቋቋም የምትችለው እንዴት ነው?

ጤና ማጣት

ጤና ማጣት

በአርጀንቲና የምትኖረው ማቤል የፊዚዮቴራፒ ባለሙያ ሆና ትሠራ የነበረ ሲሆን እንቅስቃሴ የበዛበት ሕይወት ትመራ ነበር። ሆኖም በ2007 በጣም ይደክማትና በየቀኑ ከባድ ራስ ምታት ያስቸግራት ጀመር። እንዲህ ብላለች፦ “ወደ ተለያዩ ሐኪሞች የሄድኩ ሲሆን ብዙ ዓይነት መድኃኒቶችንም ሞከርኩ፤ ግን አንዱም አልረዳኝም።” በመጨረሻ ኤም አር አይ በተባለ መሣሪያ አማካኝነት ምርመራ ተደረገላት፤ ምርመራውም የአንጎል ዕጢ እንዳለባት አሳየ። ማቤል እንዲህ ብላለች፦ “በድንጋጤ ክው ብዬ ቀረሁ! እንዲህ ያለውን ጠላት ተሸክሜ እኖር እንደነበር ማመን አልቻልኩም።”

“በሽታው ምን ያህል ከባድ እንደሆነ በደንብ የገባኝ ግን ቀዶ ጥገና ካደረግሁ በኋላ ነው። ከቀዶ ጥገናው ስነቃ ልዩ ክትትል የሚደረግበት ክፍል ውስጥ ነበርኩ፤ አልጋዬ ላይ ተንጋልዬ ጣሪያ ጣሪያውን ከማየት ሌላ ሰውነቴን ጨርሶ ማንቀሳቀስ እንደማልችል ተገነዘብኩ። ቀዶ ጥገና ከማድረጌ በፊት እንደ ልቤ መንቀሳቀስና የፈለግሁትን ማድረግ የምችል ሰው ነበርኩ። ከሕክምናው በኋላ ግን ምንም ነገር ማድረግ የማልችል ሰው ሆንኩ። ልዩ ክትትል በሚደረግበት ክፍል ውስጥ የሕክምና መሣሪያዎችና የድንገተኛ ጥሪዎች ድምፅ እንዲሁም ሌሎች ሕመምተኞች ሲያቃስቱ ይሰማ ነበር። በግራ መጋባት የተዋጥኩ ሲሆን በሥቃይና በመከራ እንደተከበብኩ ሆኖ ይሰማኝ ነበር።

“አሁን በመጠኑም ቢሆን አገግሜያለሁ። ማንም ሳይደግፈኝ መራመድና አልፎ አልፎም ራሴን ችዬ ወደ ውጭ መውጣት ችያለሁ። ይሁን እንጂ ነገሮች ሁለት ሆነው ይታዩኛል፤ እንዲሁም አሁንም ሰውነቴን ማቀናጀት ያቅተኛል።”

መከራውን መቋቋም

አዎንታዊ አመለካከት ይኑርህ። መጽሐፍ ቅዱስ በምሳሌ 17:22 ላይ “ደስተኛ ልብ ጥሩ መድኀኒት ነው፤ የተሰበረ መንፈስ ግን ዐጥንትን ያደርቃል” ይላል። ማቤል እንዲህ ብላለች፦ “እኔ ጋ የሚታከሙ ሰዎች ፈታኝ ይሆንባቸው የነበረው ነገር እኔም እያገገምኩ በነበረበት ወቅት አጋጥሞኛል። የሰውነት እንቅስቃሴዎቹ በጣም ያሳምሙኝ ስለነበረ ተስፋ ቆርጬ ለማቋረጥ ያሰብኩባቸው ጊዜያት ነበሩ። ሆኖም የማደርገው ጥረት ውሎ አድሮ ጥሩ ውጤት እንደሚኖረው ስለማውቅ እንደነዚህ ያሉትን አሉታዊ አስተሳሰቦች ለማስወገድ እታገል ነበር።”

መጽናት እንድትችል ተስፋ በሚሰጥህ ነገር ላይ አተኩር። ማቤል እንዲህ ብላለች፦ “በሰዎች ላይ መከራ የሚደርስበትን ምክንያት ከመጽሐፍ ቅዱስ ተምሬያለሁ። እያንዳንዷ ቀን ባለፈች ቁጥር ደግሞ ሥቃይ ጨርሶ ወደሚወገድበት ጊዜ ይበልጥ እየተቃረብን እንደሆነ አውቃለሁ።” *

አምላክ በግለሰብ ደረጃ ለአንተ እንደሚያስብልህ አስታውስ። (1 ጴጥሮስ 5:7) ማቤል ይህን ማሰቧ እንዴት እንደረዳት ታስታውሳለች፦ “ለቀዶ ጥገና በሚወስዱኝ ጊዜ አምላክ ‘እኔ ከአንተ ጋር ነኝና አትፍራ’ በማለት በኢሳይያስ 41:10 ላይ የተናገረው ሐሳብ እውነት መሆኑን ማየት ችያለሁ። እኔ ስለሚያጋጥመኝ ነገር ይሖዋ አምላክ እንደሚያስብ ማወቄ ይህ ነው የማይባል ሰላም እንዳገኝ ረድቶኝ ነበር።”

ይህን ታውቅ ነበር? መጽሐፍ ቅዱስ የሰው ልጅ በጤና ችግሮች የማይሠቃይበት ጊዜ እንደሚመጣ ያስተምራል።—ኢሳይያስ 33:24፤ 35:5, 6