ለቤተሰብ | የወላጅ ሚና
“አይሆንም” ማለት የምትችሉት እንዴት ነው?
ተፈታታኙ ነገር
ልጃችሁ “አይሆንም” ስትሉት * ፈጽሞ አይሰማም። እንዲያውም በዚህ ጊዜ የሚያሳየው ተገቢ ያልሆነ ባሕርይ ትዕግሥታችሁን ይፈታተነዋል። ምንም ብታደርጉ ወይም ብትናገሩ ዝም ስለማይል በመጨረሻ እሱ ያለውን ከማድረግ ሌላ አማራጭ እንደሌላችሁ ይሰማችኋል። አሁንም እንደገና ሳትወዱ በግዳችሁ ሐሳባችሁን ቀይራችሁ እሺ ትሉታላችሁ።
እንዲህ ያለው እልህ አስጨራሽ ልማድ እንዲቆም ማድረግ ትችላላችሁ። በመጀመሪያ ግን “አይሆንም” ከማለት ጋር የተያያዙ አንዳንድ ነጥቦችን እንመልከት።
ማወቅ የሚኖርባችሁ ነገር
“አይሆንም” ማለት ጭካኔ አይደለም። አንዳንድ ወላጆች በዚህ ላይስማሙ ይችላሉ፤ ‘ልጅህን ማሳመን፣ ምክንያትህን ማስረዳት አልፎ ተርፎም መደራደር አለብህ’ ይሉ ይሆናል። እንዲያውም ለልጅ “አይሆንም” የሚል መልስ መስጠት ተገቢ እንዳልሆነ ይመክራሉ፤ ምክንያቱም እንዲህ ዓይነቱ መልስ ልጁን ቅር እንደሚያሰኘው ይሰማቸዋል።
እርግጥ ነው፣ “አይሆንም” የሚል መልስ መስጠታችሁ መጀመሪያ ላይ ልጃችሁን ሊያበሳጨው ይችላል። ይሁን እንጂ ለልጁ አንድ በጣም አስፈላጊ ትምህርት ይኸውም በገሃዱ ዓለም ሰዎች የፈለጉትን ሁሉ ማግኘት እንደማይችሉ ያስተምረዋል። በሌላ በኩል ደግሞ ሁሌ እሱ የሚፈልገውን የምታደርጉለት ከሆነ ለሥልጣናችሁ ያለው አክብሮት ይቀንሳል፤ በተጨማሪም በመነጫነጭ የሚፈልገውን ሁሉ እንደሚያገኝ እንዲሁም እናንተን እንደፈለገው ሊያሽከረክራችሁ እንደሚችል እንዲሰማው ያደርጋል። ውሎ አድሮ በምትሰጡት መልስ መቆጣት ሊጀምር ይችላል። ደግሞስ አንድ ልጅ ወላጁን እንደፈለገ እንደሚያሽከረክረው ከተሰማው እንዴት ሊያከብረው ይችላል?
“አይሆንም” ማለታችሁ ልጁን በጉርምስና ዕድሜው ብሎም አዋቂ ሲሆን ይጠቅመዋል። ስሜትን መቆጣጠር ምን ጥቅሞች እንዳሉት እንዲገነዘብ ያደርገዋል። እንዲህ ያለ ጠቃሚ ሥልጠና ያገኘ ልጅ የጉርምስና ዕድሜ ላይ ሲደርስ ዕፅ እንዲወስድ ወይም ከጋብቻ በፊት የፆታ ግንኙነት እንዲፈጽም ጫና ሲደረግበት ለተጽዕኖው አይሸነፍም።
በተጨማሪም “አይሆንም” ማለታችሁ ልጁ አዋቂ ሲሆን የሚጠቅመውን ሥልጠና ይሰጠዋል። ዶክተር ዴቪድ ዎልሽ “እንደ እውነቱ ከሆነ፣ እኛ [አዋቂዎችም] የምንፈልገውን ነገር የምናገኘው ሁልጊዜ አይደለም” በማለት ጽፈዋል። “ዓለም ሁልጊዜ እነሱ የፈለጉትን ነገር በብር ሳህን ላይ አድርጎ እንደሚያቀርብላቸው ለልጆቻችን ማስተማራችን አይጠቅማቸውም።” *
ምን ማድረግ ትችላላችሁ?
በግባችሁ ላይ አተኩሩ። ልጃችሁ አድጎ ትልቅ ሰው ሲሆን ብቃት ያለው፣ ስሜቱን መቆጣጠር የሚችልና ስኬታማ ሰው እንዲሆን ትፈልጋላችሁ። ይሁን እንጂ የጠየቃችሁን ነገር ሁሉ የምታደርጉለት ከሆነ እዚህ ግብ ላይ መድረስ አትችሉም። መጽሐፍ ቅዱስ፣ አንድ ሰው “ከልጅነቱ ጀምሮ ከተሞላቀቀ፣ የኋላ ኋላ ምስጋና ቢስ” እንደሚሆን ይናገራል። (ምሳሌ 29:21 NW) በመሆኑም ልጅን ለማሠልጠን ውጤታማ ከሆኑት መንገዶች አንዱ “አይሆንም” ማለት ነው። እንዲህ ያለው ሥልጠና ልጃችሁን ይጠቅመዋል እንጂ አይጎዳውም።—የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ ምሳሌ 19:18
በውሳኔያችሁ እንደቆረጣችሁ በሚያሳይ መንገድ ተናገሩ። ልጃችሁ እኩያችሁ አይደለም። ስለዚህ “አይሆንም” ያላችሁበትን ምክንያት ሊያጸድቅላችሁ የሚገባ ይመስል ከእሱ ጋር መከራከር አያስፈልጋችሁም። እርግጥ ነው፣ ልጆች እያደጉ ሲሄዱ “ትክክልና ስህተት የሆነውን ነገር መለየት እንዲችሉ የማስተዋል ችሎታቸውን” ማሠልጠን አለባቸው። (ዕብራውያን 5:14) በመሆኑም ስለ ጉዳዩ ልጃችሁን ለማስረዳት ጥረት ማድረጋችሁ በራሱ ስህተት አይደለም። ይሁን እንጂ “አይሆንም” ያላችሁት ለምን እንደሆነ ለማስረዳት ስትሉ ከትናንሽ ልጆቻችሁ ጋር ማቆሚያ የሌለው ክርክር ውስጥ አትግቡ። ከልጃችሁ ጋር ብዙ የምትከራከሩ ከሆነ “አይሆንም” ያላችሁት ነገር ቁርጥ ያለ ውሳኔ መሆኑ ቀርቶ ለድርድር የቀረበ ነገር እንደሆነ ሊያስብ ይችላል።—የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ ኤፌሶን 6:1
በውሳኔያችሁ ጽኑ። ልጃችሁ በማልቀስ ወይም በመለማመጥ ውሳኔያችሁን እንድትቀይሩ ተጽዕኖ ሊያደርግባችሁ ይችላል። ይህ የሆነው ቤት ውስጥ ሳላችሁ ከሆነ ምን ማድረግ ትችላላችሁ? ላቪንግ ዊዛውት ስፖይሊንግ የተሰኘው መጽሐፍ “ልጁ ካለበት አካባቢ ራቁ” በማለት ይመክራል። “ልጃችሁን እንዲህ በሉት፦ ‘ማልቀስ ከፈለግክ ትችላለህ፤ እኔ ግን የአንተን ለቅሶ መስማት አልፈልግም። ስለዚህ ክፍልህ ገብተህ እስኪበቃህ ድረስ ማልቀስ ትችላለህ።’” መጀመሪያ ላይ በልጃችሁ ላይ እንዲህ ዓይነት ቆራጥ እርምጃ መውሰድ ሊከብዳችሁ ይችላል፤ ልጁም ቢሆን ውሳኔውን ለመቀበል ይቸገር ይሆናል። ይሁን እንጂ ቃላችሁን እንደማትለውጡ ሲገነዘብ እሱም መወትወቱን እየቀነሰ ይሄዳል።—የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ ያዕቆብ 5:12
ሥልጣናችሁን ለማሳየት ስትሉ ብቻ “አይሆንም” አትበሉ
ምክንያታዊ ሁኑ። ሥልጣናችሁን ለማሳየት ስትሉ ብቻ “አይሆንም” አትበሉ። ከዚህ ይልቅ “ምክንያታዊነታችሁ በሰው ሁሉ ዘንድ የታወቀ ይሁን።” (ፊልጵስዩስ 4:5) በልጁ ለቅሶ ተሸንፋችሁ እስካልሆነና የልጃችሁ ጥያቄ ተገቢ እስከሆነ ድረስ እሺ ብትሉት ምንም ችግር የለውም።—የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ ቆላስይስ 3:21