የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ
ሥራ ሲታክትህ መፍትሔው ምንድን ነው?
አኒል የሚሰማው ስሜት ከመዛልም ያለፈ ነው። አዲስ ሥራ ጀምሮ የነበረ ሲሆን ይህን ሥራ የመረጠው በደረጃውም ሆነ በደሞዙ ከፍ ያለ እንደሆነ ስለተሰማው ነው። አሁን ግን በጣም አምሽቶ የሚሠራ ከመሆኑም ሌላ ቅዳሜና እሁድንም ሥራ ይገባል፤ እንዲያውም አንዳንድ ጊዜ በሳምንት እስከ 80 ሰዓት ድረስ ይሠራል። እንዲህ ብሏል፦ “ሥራው ወከባ የበዛበት ነው፤ ደግሞም ኃላፊነቱ ሁሉ የወደቀው በእኔ ላይ ነው። ‘ምን ማድረጌ ነው? ለውጥ ካላደረግሁ እኮ መሞቴ ነው’ ብዬ አሰብኩ።” አኒል ሥራው በጣም ታክቶታል!
የሥራ መታከት እንዲሁ ድካም ብቻ ሳይሆን ከዚያ ያለፈ ነገር ነው፤ ደግሞም በየዕለቱ የምናከናውነው ሥራ ከሚፈጥረው ውጥረት የባሰ ነው። የሥራ መታከት ከሚገለጽባቸው መንገዶች አንዳንዶቹ ሥር የሰደደ የመዛል ስሜት፣ ኃይለኛ የሆነ መሰላቸትና አቅም ማጣት ናቸው። ሰዎች በሥራቸው ሲታክቱ ሥራውን በስሜት አያከናውኑም፤ የሥራ ተነሳሽነት ያጣሉ፤ እንዲሁም ውጤታማነታቸው እየቀነሰ ይመጣል። የተለያዩ ጥናቶች እንዳሳዩት መታከት ከበርካታ ስሜታዊና አካላዊ የጤና ችግሮች ጋር ይያያዛል።
የሥራ መታከት መንስኤው ምንድን ነው? በአብዛኛው ለዚህ ምክንያቱ ከባድ የሥራ ጫና ነው። አንዳንድ አሠሪዎች በኢኮኖሚው ጫና የተነሳ ሠራተኞቻቸውን ረጅም ሰዓት ያሠራሉ፤ አንዳንድ ጊዜም ይህን የሚያደርጉት በአነስተኛ ክፍያ ነው። ቴክኖሎጂ አንዳንድ ሰዎች ከሥራቸው እንዳይላቀቁ ስለሚያደርግ ሥራቸው ቤታቸው ድረስ ተከትሏቸው ይመጣል፤ በመሆኑም ሥራንና የግል ሕይወትን መለየት አስቸጋሪ ሆኗል። አንዳንዶች ደግሞ የሥራው ዓለም አስተማማኝ ባለመሆኑ፣ ሥራቸውን በሚፈልጉት መንገድ መሥራት ባለመቻላቸው ወይም ፍትሐዊ ያልሆነ ነገር እንደተደረገባቸው ሲሰማቸው ይታክታሉ። በተጨማሪም ቅድሚያ የሚሰጣቸውን ነገሮች በግልጽ አለማወቅ ወይም ከሥራ ባልደረቦች ጋር የሚፈጠር ግጭት ለመታከት መንስኤ ሊሆን ይችላል።
መታከት በገዛ እጅም ሊመጣ ይችላል። አንዳንዶች በሙያቸው አንቱ ለመባል ወይም ከፍተኛ ገቢ ለማግኘት ሲሉ በሥራ ላይ ሥራ ይደራርባሉ። እንዲህ ዓይነቶቹ ሰዎች ከአቅማቸው በላይ ስለሚሠሩ ሳይታወቃቸው ወደ መታከት የሚወስደውን ጎዳና ይያያዙታል።
አንተስ ሥራ ታክቶሃል? ከሆነ ያለህበትን ሁኔታ ማስተካከል የምትችለው እንዴት ነው? እርግጥ ነው፣ ከገባህበት ወጥመድ መውጣት እንደማትችል ከተሰማህ ለውጥ ማድረጉ ከባድ መስሎ ሊታይህ ይችላል። እስቲ የመታከትን ስሜት ለማሸነፍ የሚረዱህን አራት እርምጃዎች እንመልከት። ከምታስበው በላይ ብዙ አማራጮች ሊኖሩህ ይችላሉ።
1. ቅድሚያ የምትሰጣቸውን ነገሮች መርምር።
ከሁሉ በላይ አስፈላጊ እንደሆነ የሚሰማህ ነገር ምንድን ነው? ብዙ ሰዎች ትልቅ ቦታ ከሚሰጧቸው ነገሮች መካከል ቤተሰባቸውና ጤንነታቸው እንደሚገኝበት ጥያቄ የለውም። በሥራ መታከትህ ደግሞ በእነዚህ ነገሮች ላይ ተጽዕኖ ማሳደሩ አይቀርም።
ቅድሚያ የምትሰጣቸውን ነገሮች በግልጽ ማወቅህ ከባድ ውሳኔዎችንና ለውጦችን ለማድረግ ዝግጁ እንድትሆን ያስችልሃል። ለምሳሌ ያህል፣ ሥራህ ወደ መታከት እያመራህ እንደሆነ ትገነዘብ እንበል። ያም ሆኖ እንዲህ ብለህ ታስብ ይሆናል፦ ‘ገንዘቡ ስለሚያስፈልገኝ ሥራዬን መለወጥም ሆነ መቀነስ አልችልም!’ እውነት ነው፣ ሁሉም ሰው ገንዘብ ያስፈልገዋል፤ ይሁን እንጂ የሚያስፈልገው ምን ያህል ነው? ደግሞስ ይህን ገንዘብ ለማግኘት ከሁሉ ይበልጥ ከፍ ያለ ቦታ የምትሰጣቸውን ነገሮች መሥዋዕት ማድረግ ይኖርብሃል?
ቅድሚያ የሚሰጣቸውን ነገሮች በመለየት ረገድ በዙሪያህ ያሉ ሰዎች ጫና እንዳያሳድሩብህ ተጠንቀቅ። አሠሪህና አንተ ቅድሚያ የምትሰጧቸው ነገሮች የተለያዩ ሊሆኑ ይችላሉ። ሌሎች በሕይወታቸው ውስጥ ለሥራ አንደኛውን ቦታ ይሰጡ ይሆናል፤ ይህ ማለት ግን አንተም እንደዚህ ማድረግ አለብህ ማለት አይደለም።
የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር፦ “አንድ ሰው ሀብታም ቢሆንም እንኳ ሕይወቱ በንብረቱ ላይ የተመካ ስላልሆነ ተጠንቀቁ።”—ሉቃስ 12:15
2. ኑሮህን ቀላል አድርግ።
ውጥረትን ለመቀነስና ትልቅ ቦታ ለምትሰጣቸው ነገሮች ጊዜ ለማግኘት ስትል የሥራ ሰዓትህን መቀነስ፣ አሠሪህ በአሁኑ ጊዜ ያለብህን የሥራ ጫና እንዲቀንስልህ ማሳመን አለዚያም ሥራ መቀየር ይኖርብህ ይሆናል። ውሳኔህ ምንም ይሁን ምን፣ የገንዘብ አቅምህን ግምት ውስጥ በማስገባት በአኗኗርህ ላይ ለውጥ ማድረግ ሊያስፈልግህ ይችላል። ይህን ማድረግ ግን የማይቻል ነገር አይደለም፤ እንዲሁም የምታስበውን ያህል ከባድ ላይሆን ይችላል።
በብዙ አገሮች ውስጥ የኅብረተሰቡ ሕይወት በመግዛትና በመሸጥ ላይ ያተኮረ ነው፤ ይህ ሁኔታ አንድ ሰው ደስታው የተመካው ባለው ገቢ ወይም በንብረቱ መጠን ነው የሚል አስተሳሰብ እንዲሰፍን አድርጓል። ይሁን እንጂ እውነታው ከዚህ የተለየ ነው። ኑሮን ቀላል ማድረግ የበለጠ ነፃነትና እርካታ ሊያስገኝ ይችላል። እንዲህ ዓይነቱን ለውጥ ማድረግ እንድትችል ወጪህን በመቀነስ ገንዘብህን ቆጥብ። ዕዳህን ለመቀነስ ወይም ከፍለህ ለመጨረስ ጥረት አድርግ። በተጨማሪም የአኗኗር ለውጥ ማድረጉ አስፈላጊ መሆኑን ከቤተሰብህ አባላት ጋር በመወያየት የእነሱን ድጋፍ ማግኘት ይኖርብሃል።
የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር፦ “ምግብ እንዲሁም ልብስና መጠለያ ካለን በእነዚህ ነገሮች ረክተን መኖር ይገባናል።”—1 ጢሞቴዎስ 6:8
3. መቼ አልችልም ማለት እንዳለብህ እወቅ።
የሥራው ጫና ከአቅምህ በላይ ከሆነብህ ወይም ሊወገድ ያልቻለ ሌላ ዓይነት ችግር ካጋጠመህ ሁኔታውን ከአሠሪህ ጋር ተወያይበት። የሚቻል ከሆነ የአንተንም ሆነ የአሠሪህን ፍላጎት ግምት ውስጥ ያስገባ የመፍትሔ ሐሳብ አቅርብ። ኃላፊነትህን እንደምትወጣ ለአሠሪህ አረጋግጥለት፤ እንዲሁም ለመሥራት የምትስማማውን ነገር ግለጽለት፤ ይሁን እንጂ ልትሠራ የማትችለውን ነገር በግልጽና ቁርጥ ባለ መንገድ ንገረው።
አርቀህ የምታስተውልና እውነታውን የምታገናዝብ ሁን። ሥራ እንዲቀነስልህ የምትፈልግ ከሆነ አሠሪህም የምታገኘውን ጥቅም ሊቀንስብህ እንደሚችል መጠበቅ ይኖርብሃል። ሥራህን ልታጣ እንደምትችል በማሰብ ራስህን አዘጋጅ። ሥራ ከመልቀቅህ በፊት ሌላ ሥራ መፈለግህ የተሻለ እንደሆነ አትዘንጋ፤ ምክንያቱም ሌላ ሥራ የማግኘት አጋጣሚህ ሰፊ የሚሆነው ሥራ ላይ ሆነህ የምትፈልግ ከሆነ ነው።
ስለ ሥራህ ሁኔታ ከአሠሪህ ጋር መግባባት ላይ ብትደርሱም እንኳ ተጨማሪ ሥራ እንድትሠራ በድጋሚ ጫና ሊደረግብህ ይችላል። ታዲያ በአቋምህ ለመጽናት ምን ሊረዳህ ይችላል? የገባኸውን ቃል ማክበር ይኖርብሃል። ይህ ደግሞ የሥራው ጫና ከተነጋገራችሁት እንዳያልፍ ማድረግን ጨምሮ የአንተም መብት እንዲከበር ለመጠየቅ ነፃነት ይሰጥሃል።
የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር፦ “ቃላችሁ አዎ ከሆነ አዎ ይሁን፣ አይደለም ከሆነ አይደለም ይሁን።”—ማቴዎስ 5:37
4. ራስህን አድስ።
ከሥራህ ጋር በተያያዘ ከበድ ያሉ ችግሮች ባያጋጥሙህም እንኳ ውጥረት የሚፈጥሩብህ ነገሮች ሊኖሩ ይችላሉ፤ አሊያም አስቸጋሪ ባሕርይ ያላቸው ሰዎችና ደስ የማይሉ ሁኔታዎች ያጋጥሙህ ይሆናል። ስለዚህ በቂ እረፍት ለማድረግና ሚዛኑን በጠበቀ መንገድ ለመዝናናት ጊዜ መድብ። የምትመርጠው መዝናኛ የአንተንም ሆነ የቤተሰብህን መንፈስ የሚያድስ እንዲሆን ለማድረግ የግድ ብዙ ወጪ የሚጠይቅ መሆን እንደሌለበት አስታውስ።
ከሥራህ ውጪ ልታከናውናቸው የምትችላቸው አስደሳች እንቅስቃሴዎች እንዲኖሩህ አድርግ፤ ወይም ደግሞ ከወዳጆችህ ጋር ጊዜ ለማሳለፍ ጥረት አድርግ። እንዲሁም ማንነትህን በምትሠራው የሥራ ዓይነትና መጠን ከመመዘን ተቆጠብ። ለምን? ገንዘብህ ወይስ ሕይወትህ (እንግሊዝኛ) የተሰኘው መጽሐፍ “ማንነትህ ገንዘብ ለማግኘት ብለህ ከምትሠራው ሥራ በእጅጉ የላቀ ነው” በማለት ይገልጻል። ማንነትህና ለራስህ የምትሰጠው ግምት በዋነኝነት የተመካው በሥራህ ላይ ከሆነ በሕይወትህ ውስጥ ለሥራ የምትሰጠውን ቦታ አሳንሰህ ማየት ከባድ ሊሆንብህ ይችላል።
የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር፦ “በድካምና ነፋስን በመከተል ከሁለት እጅ ሙሉ ይልቅ አንድ እጅ ሙሉ በዕረፍት ይሻላል።”—መክብብ 4:6 የ1954 ትርጉም
ታዲያ የሥራ መታከትን በተሳካ ሁኔታ ለመቋቋም የሚያስችሉህን ለውጦች ማድረግ በእርግጥ ትችላለህ? አዎ፣ ትችላለህ። በዚህ ርዕስ መግቢያ ላይ የተጠቀሰው አኒል በዚህ ረገድ ተሳክቶለታል። እንዲህ ይላል፦ “ወደ ቀድሞ አሠሪዬ በመሄድ መልሶ ይቀጥረኝ እንደሆነ ጠየቅሁት፤ እሱም ወደ ሥራዬ መለሰኝ። የቀድሞ የሥራ ባልደረቦቼን ተሰናብቻቸው ስሄድ የተሻለ ሥራ እንዳገኘሁ ተናግሬ ስለነበረ እነሱን ማየት አሳፈረኝ። ደሞዜም ቢሆን ከቀድሞው በጣም ያነሰ ነው። ያም ቢሆን አሁን የአእምሮ ሰላም አለኝ፤ እንዲሁም ለቤተሰቤና ትልቅ ቦታ ለምሰጣቸው ነገሮች ተጨማሪ ጊዜ አግኝቻለሁ።”