በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ

እውነተኛ ስኬት ምንድን ነው?

እውነተኛ ስኬት ምንድን ነው?

እውነተኛ ያልሆነ ስኬት ካገኘ ሰው ጨርሶ ያልተሳካለት ሰው ይሻላል። ምክንያቱም አንድ ነገር ሞክሮ ያልተሳካለት ሰው ሁኔታውን ለማስተካከል አንዳንድ እርምጃዎችን መውሰድ ይችላል። ሌላው ቢቀር ከውድቀቱ ትምህርት የሚያገኝ ከመሆኑም ሌላ በሚቀጥለው ጊዜ ስህተቱን ላለመድገም ያለው ቁርጠኝነት ይጠናከራል።

እውነተኛ ያልሆነ ስኬት ግን ከዚህ ይለያል። አንተ ተሳክቶልኛል ብለህ ታስብ ይሆናል፤ እውነታው ግን ከዚህ የተለየ ነው። ለውጥ ማድረግ እንደሚኖርብህ የምትገነዘበው ደግሞ ጊዜው ካለፈ በኋላ ሊሆን ይችላል።

አንድ ምሳሌ እንመልከት። ኢየሱስ ክርስቶስ በአንድ ወቅት “አንድ ሰው ዓለሙን ሁሉ የራሱ ቢያደርግ፣ ነፍሱን ግን ቢያጣ ምን ይጠቅመዋል?” ሲል ጠይቆ ነበር። (ማቴዎስ 16:26) ይህ ሐሳብ መላ ሕይወታቸውን ገንዘብንና ገንዘብ ሊገዛ የሚችላቸውን ነገሮች ለማሳደድ ባዋሉ ሰዎች ላይ ይሠራል፤ እነዚህ ሰዎች የሚያገኙት ስኬት፣ እውነተኛ ላልሆነ ስኬት እንደ ምሳሌ ሊጠቀስ ይችላል። የሥራ መስክ ምርጫ አማካሪ የሆኑት ቶም ዴናም እንዲህ ብለዋል፦ “ነጋ ጠባ ስለ ሥራ እድገት፣ ተጨማሪ ገንዘብ ስለ ማግኘት ወይም ብዙ ንብረት ስለ ማካበት ብቻ ማሰብ ለነፍስ እርካታን አያስገኝም። ስኬትን ከገንዘብ አንጻር ብቻ መለካት ብስለት እንደሌለን የሚያሳይ ከመሆኑም በላይ የኋላ ኋላ የባዶነት ስሜት እንዲሰማን ያደርጋል።”

በአሁኑ ጊዜ ያሉ ብዙ ሰዎች በዚህ እንደሚስማሙ መረጃዎች ያመለክታሉ። በዩናይትድ ስቴትስ የተደረገ አንድ ጥናት እንዳመለከተው “ለተሳካ ሕይወት አስተዋጽኦ የሚያደርጉ” ተብለው ከተዘረዘሩ 22 ነገሮች መካከል “ብዙ ገንዘብ ማግኘት” 20ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። ጤንነት፣ ከሰዎች ጋር ጥሩ ግንኙነት መመሥረት እና በሚወዱት የሥራ መስክ ላይ መሰማራት ግን መጀመሪያ አካባቢ ከተቀመጡት ነገሮች መካከል ይገኙበታል።

ከዚህ በግልጽ መረዳት እንደሚቻለው፣ ብዙ ሰዎች በሕይወታቸው ተግባራዊ ባያደርጉትም እንኳ እውነተኛ የሆነን ስኬት እውነተኛ ካልሆነው መለየት አይከብዳቸውም። ይበልጥ ከባድ የሚሆነው ግን ስለ ስኬት ትክክለኛ አመለካከት እንዳለን የሚያሳይ ውሳኔ ማድረግ ነው።