በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

 መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

ምድር

ምድር

አምላክ ለምድር ያለው ዓላማ ምንድን ነው?

“ምድርን . . . የሠራት . . . የሰው መኖሪያ እንጂ፣ ባዶ እንድትሆን ያልፈጠራት፣ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል።”—ኢሳይያስ 45:18

ሰዎች ምን ይላሉ?

ብዙ ሰዎች፣ ምድር በአጋጣሚ እንደተገኘች ይናገራሉ። አንዳንድ ሃይማኖቶች፣ አምላክ በሰማይ ለዘላለም የሚኖሩትን ሰዎች፣ በእሳታማ ሲኦል ውስጥ ከሚጣሉት ሰዎች ለመለየት ምድርን ጊዜያዊ የመፈተኛ ቦታ አድርጎ እንደሚጠቀምባት ያስተምራሉ።

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ “ሰማያትንና ምድርን ፈጠረ” በማለት ይናገራል። (ዘፍጥረት 1:1) አምላክ ለመጀመሪያዎቹ ባልና ሚስት “ብዙ ተባዙ፤ ምድርን ሙሏት፤ ግዟትም፤ . . . በምድር ላይ የሚንቀሳቀሱትን ሕያዋን ፍጡራንን ሁሉ ግዟቸው” በማለት ነግሯቸዋል። (ዘፍጥረት 1:28) በሌላ በኩል ግን ሞት የተጠቀሰው ካለመታዘዝ ጋር ተያይዞ ነው። (ዘፍጥረት 2:17) በመሆኑም አምላክ ምድርን የፈጠራት ለሰው ዘር ዘላለማዊ መኖሪያ እንድትሆን ነው። የአምላክ ዓላማ ታዛዥ የሆኑ ሰዎች ምድርን እየተንከባከቡ ለዘላለም እንዲኖሩባት ነው።

 ምድር ትጠፋለች?

“ለዘላለም እንዳትናወጥ፣ ምድርን በመሠረቷ ላይ አጸናሃት።” —መዝሙር 104:5

ሰዎች ምን ይላሉ?

የሳይንስ ሊቃውንት፣ ምድር እንድትጠፋ ወይም ለመኖሪያነት የማትመች እንድትሆን የሚያደርጉ የተለያዩ ነገሮች ሊከሰቱ እንደሚችሉ ይናገራሉ። ከንዑሳን ፕላኔቶች ወይም ከጅራታም ከዋክብት ጋር መላተም፣ ከፍተኛ ኃይል ያላቸው እሳተ ገሞራዎች፣ የፀሐይ መሞት፣ የምድር ሙቀት መጨመር እንዲሁም የኑክሌር ጦርነትና በባዮሎጂያዊ መሣሪያዎች የሚደረግ የሽብር ጥቃት የሰውን ዘር ሕልውና አደጋ ላይ እንደሚጥሉ ከሚታሰቡት የተፈጥሮና ሰው ሠራሽ አደጋዎች መካከል ተጠቃሽ ናቸው።

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

አምላክ ለምድር ያለው ዓላማ አልተለወጠም። የአምላክ ቃል “ምድር . . . ለዘላለም ጸንታ ትኖራለች” በማለት በግልጽ ይናገራል። (መክብብ 1:4) ከዚህም በላይ መጽሐፍ ቅዱስ “ጻድቃን ምድርን ይወርሳሉ፤ በእርሷም ለዘላለም ይኖራሉ” በማለት ስለሚናገር ምድር ለዘላለም የሰው ልጆች መኖሪያ ትሆናለች።—መዝሙር 37:29

ይህን ማወቅ ለምን አስፈለገ?

አንዳንዶች ምድር እንደምትጠፋ ማመናቸው ውድ የሆኑ የተፈጥሮ ሀብቶችን እንዲበዘብዙ ምክንያት ሆኗል። ሌሎች ደግሞ ስለ ወደፊቱ ጊዜ ብሩሕ አመለካከት ስለሌላቸው የሚኖሩት ለዛሬ ብቻ ነው። ይህ ደግሞ ሕይወት ትርጉም ወይም ዓላማ እንዳይኖረው ያደርጋል። በአንጻሩ ግን በምድር ላይ ለዘላለም እንደምንኖር የምናምን ከሆነ የምናደርጋቸው ውሳኔዎች ዛሬ ብቻ ሳይሆን ወደፊትም ጭምር ራሳችንንም ሆነ ቤተሰቦቻችንን የሚጠቅሙ ይሆናሉ።

የሰው ልጆች ሁሉ ወደ ሰማይ ይሄዳሉ?

“ሰማየ ሰማያት የእግዚአብሔር ናቸው፤ ምድርን ግን ለሰው ልጆች ሰጣት።”—መዝሙር 115:16

ሰዎች ምን ይላሉ?

ብዙዎች፣ ጥሩ ሰዎች ሁሉ ወደ ሰማይ እንደሚሄዱ ያምናሉ።

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

ሰማይ የአምላክ መኖሪያ ሲሆን ምድር ግን የተፈጠረችው ለሰው ዘሮች ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ‘መጪው ዓለም’ ይናገራል። (ዕብራውያን 2:5) በተጨማሪም ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ሰማይ የሄደው ኢየሱስ እንደሆነ እንዲሁም የተመረጡ ጥቂት ሰዎች ለአንድ ዓላማ ወደ ሰማይ እንደሚሄዱ ይገልጻል። እነሱም ከኢየሱስ ጋር በምድር ላይ “ነገሥታት ሆነው ይገዛሉ።”—ራእይ 5:9, 10፤ ሉቃስ 12:32፤ ዮሐንስ 3:13

ይህን ማወቅ ለምን አስፈለገ?

ጥሩ ሰዎች ሁሉ ወደ ሰማይ ይሄዳሉ ብሎ ማመን ከመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ጋር ይጋጫል። አምላክ ጥሩ ሰዎችን ሁሉ ወደ ሰማይ የሚወስድ ቢሆን ኖሮ እንዲህ ማድረጉ ለምድር የነበረውን ዓላማ መፈጸም እንዳቃተው የሚያሳይ ከመሆኑም በላይ በምድር ላይ ለዘላለም ስለ መኖር የሰጠው ተስፋ ውሸት ይሆን ነበር። በአንጻሩ ግን የአምላክ ቃል “እግዚአብሔርን ደጅ ጥና፤ መንገዱንም ጠብቅ፤ ምድሪቱን ትወርስ ዘንድ ከፍ ከፍ ያደርግሃል” የሚል ተስፋ ይሰጣል።—መዝሙር 37:34