በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ | ልጆችን መቅጣት ቀረ እንዴ?

ጠቃሚ የሆነ ተግሣጽ

ጠቃሚ የሆነ ተግሣጽ

የወላጅ ኃላፊነት ከባድ እንደሆነ አይካድም። ይሁን እንጂ ወላጆች ተግሣጽ መስጠት ሲኖርባቸው ይህን ሳያደርጉ መቅረታቸው ሁኔታውን ይበልጥ ያከብደዋል። ለምን? ምክንያቱም ልጆች ተግሣጽ ካልተሰጣቸው (1) ከስህተታቸው አይታረሙም፤ ይህ ደግሞ ወላጆች እንዲሰለቻቸው ያደርጋል፤ እንዲሁም (2) ወላጆች ወጥ የሆነ መመሪያ ስለማይሰጡ ልጆቹ ግራ ይጋባሉ።

በሌላ በኩል ደግሞ በፍቅር የተሰጠ ሚዛናዊ ተግሣጽ የአንድን ልጅ አስተሳሰብ እንዲሁም ሥነ ምግባር ለመቅረጽ ያስችላል። በተጨማሪም ልጆቹ አድገው ትልቅ ሰው ሲሆኑ በራሳቸው የሚተማመኑ እንዲሆኑ ይረዳቸዋል። ይሁን እንጂ ለልጆችህ ተግሣጽ በመስጠት ረገድ የሚጠቅምህ አስተማማኝ የሆነ መመሪያ ከየት ማግኘት ትችላለህ?

የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎች ያላቸው ጥቅም

የዚህ መጽሔት አዘጋጆች የሆኑት የይሖዋ ምሥክሮች መጽሐፍ ቅዱስ፣ ስለ ራሱ እንደሚናገረው “ለማስተማር፣ ለመውቀስ፣ ለማረምና በጽድቅ ለመገሠጽ” የሚጠቅም መጽሐፍ እንደሆነ ያምናሉ። (2 ጢሞቴዎስ 3:16 የግርጌ ማስታወሻ) መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ልጅ አስተዳደግ ብቻ ሳይሆን ለመላው ቤተሰብ የሚጠቅሙ መመሪያዎችን ይዟል። እስቲ ከእነዚህ መካከል አንዳንዶቹን እንመልከት።

መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “ሞኝነት በልጅ ልብ ውስጥ ታስሯል።”—ምሳሌ 22:15

ልጆች አሳቢና ደግ ቢሆኑም በአብዛኛው የሞኝነት ድርጊት ይፈጽማሉ። በመሆኑም ልጆች ተግሣጽ ያስፈልጋቸዋል። (ምሳሌ 13:24) ይህን ሐቅ አምነህ መቀበልህ የወላጅነት ኃላፊነትህን እንድትወጣ ይረዳሃል።

መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “ልጅን ከመገሠጽ ወደኋላ አትበል።”—ምሳሌ 23:13

ሚዛናዊ በሆነ መንገድ ተግሣጽ መስጠትህ የልጆችህን ስሜት እንደሚጎዳው ወይም ካደጉ በኋላ እንዲጠሉህ እንደሚያደርግ በማሰብ መፍራት የለብህም። ተግሣጽ የምትሰጠው በፍቅር ከሆነ ልጆችህ የሚሰጣቸውን እርማት በትሕትና መቀበልን ይማራሉ፤ ይህ ደግሞ ትልቅ ሰው ሲሆኑ የሚጠቅማቸው ችሎታ ነው።—ዕብራውያን 12:11

መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “አንድ ሰው ምንም ዘራ ምን ያንኑ መልሶ ያጭዳል።”—ገላትያ 6:7

ወላጆች ልጆቻቸውን ከችግር ለመጠበቅ መፈለጋቸው ተፈጥሯዊ እንዲሁም ተገቢ ነው። ይሁን እንጂ በዚህ ረገድም ቢሆን ሚዛናዊ መሆን ያስፈልጋል። ልጆችህ፣ የፈጸሙት ስህተት የሚያስከትለው መዘዝ እንዳይነካቸው ለማድረግ ብትሞክር ወይም መምህራቸው አሊያም ሌላ ትልቅ ሰው፣ የፈጸሙትን ጥፋት ሲነግርህ ጥብቅና ብትቆምላቸው አትጠቅማቸውም። ከዚህ ይልቅ እንዲህ ዓይነቱን ሰው እንደ አጋርህ አድርገህ ተመልከተው። እንዲህ ስታደርግ ልጅህ የአንተንም ሆነ የሌሎችን ሥልጣን ማክበርን ይማራል።—ቆላስይስ 3:20

መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “መረን የተለቀቀ ልጅ . . . እናቱን ያሳፍራል።”—ምሳሌ 29:15

አፍቃሪ እና ምክንያታዊ ሁን፤ እንዲሁም ተግሣጽ አሰጣጥህ ወጥ ይሁን

ወላጆች ከልጆቻቸው ጋር በተያያዘ በጣም ጥብቅ መሆን የሌለባቸው ቢሆንም ወደ ተቃራኒው ጽንፍ በማድላት መረን የሚለቁ መሆንም የለባቸውም። “ወላጆች ልጆቻቸውን መረን የሚለቅቋቸው ከሆነ ልጆቹ በቤቱ ውስጥ ሥልጣን ያላቸው አዋቂዎቹ እንደሆኑ አይገነዘቡም” በማለት ዘ ፕራይስ ኦቭ ፕሪቭሌጅ የተሰኘው መጽሐፍ ተናግሯል። ሥልጣኑ የእናንተ መሆኑን ካላሳያችሁ ልጃችሁ በቤቱ ውስጥ ሥልጣን ያለው እሱ እንደሆነ ሊሰማው ይችላል። በዚህም የተነሳ በራሱም ሆነ በእናንተ ላይ ሐዘን የሚያስከትል ጥበብ የጎደለው ውሳኔ ማድረጉ አይቀርም።—ምሳሌ 17:25፤ 29:21

መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ ‘ሰው ከሚስቱ ጋር ይጣበቃል፤ ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ።’—ማቴዎስ 19:5

በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረት ልጆች የሚወለዱት አንድ ወንድና አንዲት ሴት ከተጋቡ በኋላ ሲሆን ልጆቹ አድገው ራሳቸውን ከቻሉ በኋላም ባልና ሚስቱ አብረው መኖራቸውን ይቀጥላሉ። (ማቴዎስ 19:5 6) በዚህ ምክንያት ወላጆች፣ ቅድሚያ መስጠት ያለባቸው ለትዳር ጓደኛቸው እንጂ ለልጆቻቸው አይደለም። ቅድሚያ የምትሰጠው ነገር የተገላቢጦሽ ከሆነ ግን ልጅህ ‘ስለ ራሱ ከሚገባው በላይ ማሰብ’ ሊጀምር ይችላል። (ሮም 12:3) ከትዳር ጓደኛቸው የበለጠ ለልጃቸው ቅድሚያ የሚሰጡ ወላጆች ትዳራቸው ጠንካራ አይሆንም።

ለወላጆች የሚጠቅም ምክር

የወላጅነት ኃላፊነትህን ስትወጣ እንዲሳካልህ ከፈለግክ ለልጆችህ የምትሰጠው ተግሣጽ ቀጥሎ ከተጠቀሱት መመሪያዎች ጋር የሚስማማ መሆን አለበት።

እርማቱን በፍቅር ስጥ። “አባቶች ሆይ፣ ቅስማቸው እንዳይሰበር ልጆቻችሁን አታበሳጯቸው።”—ቆላስይስ 3:21

ተግሣጽ አሰጣጥህ ወጥ ይሁን። “ቃላችሁ ‘አዎ’ ከሆነ አዎ ይሁን፤ ‘አይደለም’ ከሆነ አይደለም ይሁን።”—ማቴዎስ 5:37

ምክንያታዊ ሁን። “በተገቢው መጠን እገሥጽሃለሁ።”—ኤርምያስ 30:11 *

^ አን.21 ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት jw.orgን ተመልከት። በድረ ገጹ ላይ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች > ባለትዳሮች እና ወላጆች በሚለው ሥር የሚከተሉትን ርዕሶች ማግኘት ይቻላል፦ “ለልጆች ተግሣጽ መስጠት” “ልጆች እልኸኛ ሲሆኑ ምን ማድረግ ይቻላል?” “በልጆቻችሁ ልብ ውስጥ የሥነ ምግባር እሴቶችን ትከሉ” እና “በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ ለሚገኙ ልጆቻችሁ ተግሣጽ መስጠት የምትችሉት እንዴት ነው?