የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ | በቤት ውስጥ ሰላም እንዲሰፍን ማድረግ
በቤት ውስጥ ግጭት እንዳይፈጠር ምን ማድረግ ይቻላል?
ከቤታችሁ ግጭት የማይጠፋ ከሆነስ? ምናልባትም ግጭቶቹ እየተደጋገሙና እየከረሩ ሄደው ይሆናል። አንዳንድ ጊዜ አለመግባባቱ እንዴት እንደተፈጠረ እንኳ ላታውቁ ትችላላችሁ። ይሁንና እርስ በርስ እንደምትዋደዱና አንዳችሁ ሌላውን መጉዳት እንደማትፈልጉ የታወቀ ነው።
የሐሳብ ልዩነት ተፈጠረ ማለት ቤተሰባችሁ አለቀለት ማለት እንዳልሆነ ምንጊዜም አስታውሱ። ቤታችሁ ጠብ የነገሠበት እንዲሆን የሚያደርገው የተፈጠረው አለመግባባት ሳይሆን አለመግባባቱን ለመፍታት የምትሞክሩበት መንገድ ነው። ግጭት እንዳይፈጠር ለማድረግ የሚረዷችሁን አንዳንድ እርምጃዎች እስቲ እንመልከት።
1. አጸፋ አትመልሱ።
ጭቅጭቅ የሚፈጠረው ቢያንስ በሁለት ሰዎች መካከል ነው፤ አንዱ ሲናገር ሌላው ጸጥ ብሎ ካዳመጠ ግን ጠቡ እየረገበ ይሄዳል። በመሆኑም የሚያስቆጣ ነገር ሲያጋጥማችሁ አጸፋ ከመመለስ ተቆጠቡ። ራሳችሁን በመቆጣጠር ክብራችሁን ለመጠበቅ ጥረት አድርጉ። በቤታችሁ ውስጥ ሰላም መስፈኑ ተከራክሮ ከመርታት የበለጠ ዋጋ እንዳለው አስታውሱ።
“እንጨት ከሌለ እሳት ይጠፋል፤ ስም አጥፊ ከሌለ ደግሞ ጭቅጭቅ ይበርዳል።”—ምሳሌ 26:20
2. የቤተሰባችሁን አባላት ስሜት ተረዱ።
አንድ ሰው ጣልቃ ሳይገባ ወይም ለመፍረድ ሳይቸኩል በትኩረትና በርኅራኄ ማዳመጡ ቁጣን ለማብረድና ሰላም እንዲሰፍን ለማድረግ ያስችላል። በሌላው ሰው ላይ ለመፍረድ ከመቸኮል ይልቅ ስሜቱን ለመረዳት ጥረት አድርጉ። በአለፍጽምና ምክንያት ያደረገውን ነገር በክፋት ተነሳስቶ እንደፈጸመው አድርጋችሁ አትደምድሙ። አብዛኛውን ጊዜ አንድ ሰው ጎጂ ንግግር የሚናገረው በክፋት ተነሳስቶ ሳይሆን በግድየለሽነት ወይም ስሜቱ በመጎዳቱ ሊሆን ይችላል።
“ከአንጀት የመነጨ ርኅራኄን፣ ደግነትን፣ ትሕትናን፣ ገርነትንና ትዕግሥትን ልበሱ።”—ቆላስይስ 3:12
3. ጊዜ ወስዳችሁ ተረጋጉ።
በቀላሉ የምትቆጡ ከሆነ እስክትረጋጉ ድረስ በዘዴ ከአካባቢው ዞር ማለታችሁ ጥሩ ሊሆን ይችላል። ስሜታችሁ እስኪረጋጋ ድረስ ወደ ሌላ ክፍል ልትገቡ ወይም ወጣ ብላችሁ በእግር ልትንሸራሸሩ ትችላላችሁ። አንድ ሰው እንዲህ ማድረጉ ከችግሩ ለመሸሽ እንደሞከረ ወይም በጉዳዩ ላይ ለመወያየት ፍላጎት እንደሌለው አሊያም እንዳኮረፈ የሚያሳይ አይደለም። ከዚህ ይልቅ ይህን አጋጣሚ ይሖዋ ትዕግሥትና ማስተዋል እንዲሰጠው ለመጠየቅ ሊጠቀምበት ይችላል።
“ጥል ከመነሳቱ በፊት ከአካባቢው ራቅ።”—ምሳሌ 17:14
4. ምን እና እንዴት መናገር እንዳለባችሁ ቆም ብላችሁ አስቡ።
የቤተሰባችሁን አባል ስሜት ሊጎዳ የሚችል መልስ መስጠታችሁ ምንም ፋይዳ የለውም። ከዚህ ይልቅ የተጎዳውን ሰው ስሜት ሊፈውስ የሚችል ነገር ለመናገር ሞክሩ። በተጨማሪም ምን ዓይነት ስሜት ሊያድርበት እንደሚገባ ከምትነግሩት ይልቅ የተሰማውን ስሜት በግልጽ እንዲነግራችሁ ለስለስ ባለ መንገድ ጠይቁት፤ ከዚያም የልቡን አውጥቶ ሲናገር አመስግኑት።
“ሳይታሰብበት የሚነገር ቃል እንደ ሰይፍ ይወጋል፤ የጥበበኞች ምላስ ግን ፈውስ ነው።”—ምሳሌ 12:18
5. አትጩኹ፤ እርቅ ለማውረድ እንደምትፈልጉ የሚያሳይ የድምፅ ቃና ይኑራችሁ።
አንደኛው የቤተሰብ አባል ትዕግሥት ማጣቱ ሌላኛውም በቀላሉ እንዲቆጣ ሊያደርገው ይችላል። በጣም ቅር ብትሰኙም እንኳ በአሽሙር ወይም በንቀት ላለመናገር አሊያም ላለመጮኽ ጥረት አድርጉ። “ለእኔ ግድ የለህም” ወይም “አንድ ቀን እንኳ በሥርዓት አዳምጠሽኝ አታውቂም” እንደሚሉት ያሉ ጎጂ ንግግሮችን አስወግዱ። ከዚህ ይልቅ የትዳር ጓደኛችሁ ባደረገው ነገር የተነሳ ምን እንደተሰማችሁ ረጋ ባለ መንፈስ ተናገሩ (“. . . ስታደርግ ይከፋኛል”)። መገፍተርንና በጥፊ ወይም በእርግጫ መምታትን ጨምሮ በትዳር ጓደኛችሁ ላይ ማንኛውንም ዓይነት አካላዊ ጥቃት መሰንዘር ፈጽሞ ተገቢ አይደለም። መሳደብ፣ መዝለፍና መዛትም ቢሆን ተቀባይነት የለውም።
“የመረረ ጥላቻ፣ ቁጣ፣ ንዴት፣ ጩኸትና ስድብ ሁሉ እንዲሁም ክፋት ሁሉ ከእናንተ መካከል ይወገድ።”—ኤፌሶን 4:31
6. ይቅርታ ለመጠየቅ ፈጣን ሁኑ፤ ችግሩን ለመፍታት ምን ለማድረግ እንደወሰናችሁ ተናገሩ።
አሉታዊ ስሜቶች ግባችሁን እንድትዘነጉ ሊያደርጓችሁ አይገባም፤ ግባችሁ ሰላም መፍጠር ነው። ከአንድ ሰው ጋር ከተጣላችሁ ሁለታችሁም ተሸናፊ ናችሁ። ሰላም ከፈጠራችሁ ግን ሁለታችሁም ታሸንፋላችሁ። በመሆኑም ለተፈጠረው ግጭት የእናንተም ጥፋት እንዳለበት አምናችሁ ተቀበሉ። ምንም ጥፋት እንደሌለባችሁ ቢሰማችሁም እንኳ ስለተቆጣችሁ፣ ጥሩ ያልሆነ ምላሽ ስለሰጣችሁ ወይም ሆን ብላችሁ ባይሆንም ሌላኛውን ግለሰብ ስላበሳጫችሁት ይቅርታ ልትጠይቁ ትችላላችሁ። በኩራት የተነሳ ከማኩረፍ ወይም ተከራክሮ ከማሸነፍ ይልቅ አስፈላጊ የሆነው ሰላም መፍጠር እንደሆነ አትዘንጉ። በሌላ በኩል ደግሞ አንድ ሰው ይቅርታ ከጠየቃችሁ ይቅር ለማለት ፈጣን ሁኑ።
“ሂድና ባልንጀራህን በትሕትና አጥብቀህ ለምነው።”—ምሳሌ 6:3
ክርክሩ ካበቃ በኋላ በቤታችሁ ውስጥ ሰላም እንዲሰፍን ምን ማድረግ ትችላላችሁ? የዚህን ጥያቄ መልስ በሚቀጥለው ርዕስ ላይ እንመረምራለን።