በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

‘ለሃይማኖት ቤተሰቦች’ የተደረገ የፍቅር መግለጫ

‘ለሃይማኖት ቤተሰቦች’ የተደረገ የፍቅር መግለጫ

‘ለሃይማኖት ቤተሰቦች’ የተደረገ የፍቅር መግለጫ

እውነተኛ ክርስቲያኖች እርስ በርሳቸው የቤተሰብ ዓይነት ትስስር አላቸው። በእርግጥም ከመጀመሪያው መቶ ዘመን እዘአ አንስቶ እርስ በርሳቸው “ወንድም” እና “እህት” በማለት ይጠራራሉ። (ማርቆስ 3:​31-35፤ ፊልሞና 1, 2) ይህ እንዲሁ አፋዊ ብቻ አይደለም፤ የአምላክ አገልጋዮች አንዳቸው ለሌላው ያላቸውን ስሜት በትክክል የሚገልጽ ነው። (ከ1 ዮሐንስ 4:​7, 8 ጋር አወዳድር።) ኢየሱስ “እርስ በርሳችሁ ፍቅር ቢኖራችሁ፣ ደቀ መዛሙርቴ እንደ ሆናችሁ ሰዎች ሁሉ በዚህ ያውቃሉ” ብሏል።​—⁠ዮሐንስ 13:​35

ቺሊ ውስጥ ለረጅም ጊዜ የዘለቀ ድርቅ አብቅቶ በሐምሌ 1997 ኃይለኛ ዝናብና ጎርፍ በተከሰተ ጊዜ እንዲህ ዓይነቱ ፍቅር በግልጽ ታይቷል። ወዲያውኑ ብዙዎች የምግብ፣ የአልባሳትና የሌሎች ቁሳዊ ነገሮች ችግር ገጠማቸው። የተፈጥሮ አደጋዎች በሚከሰቱበት ጊዜ የይሖዋ ምሥክሮች ጳውሎስ ለገላትያ ክርስቲያኖች የሰጣቸውን ምክር በሥራ ለማዋል ይጥራሉ:- “እንግዲያስ ጊዜ ካገኘን ዘንድ ለሰው ሁሉ ይልቁንም ለሃይማኖት ቤተ ሰዎች መልካም እናድርግ።”​—⁠ገላትያ 6:​10

ስለሆነም የይሖዋ ምሥክሮች እርዳታ ለመስጠት ወዲያው ተደራጁ። ምግብ፣ አልባሳትና የመሳሰሉት ነገሮች ከተሰባሰቡ በኋላ በዓይነት በዓይነታቸው ታሽገው አደጋው ወደ ደረሰበት አካባቢ ተላኩ። ሌላው ቀርቶ ሕፃናት እንኳ አሻንጉሊቶቻቸውን ለግሰዋል! አንዲት እህት የመንግሥት አዳራሹ በእርዳታ ቁሳ ቁሶች ተሞልቶ ስታይ በጣም ተደነቀች። “የምለው ጠፍቶኝ በመገረም ቆሜ ቀረሁ” ስትል ተናግራለች። “የሚያስፈልገን ነገር ሁሉ መጥቶልን ነበር።”

ከዚያም በጎርፍ የተጥለቀለቀው አካባቢ የተወሰነ ክፍል በድንገት በመሬት መንቀጥቀጥ ተመታ። በርካታ ቤቶች ወደሙ። ወንድሞች የሚያስፈልጋቸውን ለማሟላት ተጨማሪ የመልሶ ማቋቋም ኮሚቴዎች ተቋቋሙ። የይሖዋ ምሥክሮችን የመሰብሰቢያ አዳራሾች ግንባታ የሚከታተሉት የአካባቢ የሕንፃ ሥራ ኮሚቴዎች ድጋፍ በመስጠት ተባበሩ። ምን ውጤት ተገኘ? ቤታቸው ለወደመባቸው ወንድሞች ኮሚቴው ባዘጋጀው ንድፍ የተገነቡ አነስ አነስ ያሉ ቤቶች በእርዳታ ተሰጧቸው። ምንም እንኳ እነዚህ ቤቶች ምርጥ ናቸው ባይባሉም በመንግሥት የመልሶ ማቋቋም ግንባታ ተሠርተው በብድር ከተሰጡት የወለል ንጣፍና መስኮቶች ከሌላቸው እንዲሁም ቀለም ካልተቀቡት ቤቶች በጣም የተሻሉ ናቸው።

አንዳንድ ወንድሞች ሥራውን ለመደገፍ ረጅም ርቀት ተጉዘው መጥተዋል። አንድ የአካባቢ የሕንፃ ሥራ ኮሚቴ ሊቀመንበር ምንም እንኳ የሚንቀሳቀሰው በተሽከርካሪ ወንበር ቢሆንም ለሁለት ተከታታይ ቀናት አካባቢውን አንድ በአንድ ተዘዋውሮ ተመልክቷል። ማየት የተሳነው አንድ ወንድም ለግንባታ የሚያገለግሉትን እንጨቶች በተፈላጊው መጠን ወደሚቆረጡበት ቦታ ሲያግዝ ውሏል። መስማት የተሳነው አንድ ወንድም ደግሞ የተቆረጡትን እንጨቶች ተፈላጊው ቦታ ያደርስ ነበር።

ብዙ ታዛቢዎች ወንድሞች ያሳዩት ትብብር እጅግ አስደንቋቸዋል። በአንድ ከተማ ውስጥ እየተጠገነ ባለ በአንዲት እህት ቤት አጠገብ አንድ የፖሊስ መኪና ቆሞ ነበር። ፖሊሶቹ ነገሩ ደንቋቸው ይመለከታሉ። አንደኛው ፖሊስ “በደስታ እየሠሩ ያሉ የሚመስሉት እነዚህ እነማን ናቸው? ለመሆኑ ስንት ቢከፈላቸው ነው?” ሲል አንድን ወንድም ጠየቀው። ወንድም ሁሉም ፈቃደኛ ሠራተኞች መሆናቸውን ነገረው። ከመኮንኖቹ አንዱ ለቤተ ክርስቲያኑ በየወሩ አሥራት የሚያወጣ ቢሆንም የመሬት መንቀጥቀጡ ከተከሰተ በኋላ ቄሱ እንዴት ሆንክ እንኳ ብለው ጠይቀውት እንደማያውቁ ተናገረ! በሚቀጥለው ቀን አንድ የፖሊስ ባለሥልጣን ለእህት ስልክ ደወለላት። እርሱም ወንድሞች ቤቷን ሲጠግኑላት ተመልክቶ ነበር። ሁሉም በጋለ መንፈስና ስሜት ሲሠሩ ሲመለከት አብሯቸው ለመሥራት ተገፋፍቶ እንደነበረ ገለጸላት!

በእርግጥም በቺሊ የተካሄደው የመልሶ ማቋቋም ሥራ ለፈቃደኛ ሠራተኞቹ አስደሳች ተሞክሮ ሲሆን ለታዛቢዎች ደግሞ ግሩም ምሥክርነት ነበር።