በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ሥርዓት አልበኝነት መንስኤው ምንድን ነው?

ሥርዓት አልበኝነት መንስኤው ምንድን ነው?

ሥርዓት አልበኝነት መንስኤው ምንድን ነው?

“እኔ ምንም መናገር አልፈልግም።” እነዚህ ቃላት ውብ በሆነው የሳኦ ፓውሎ የመኖሪያ አካባቢ በሚገኝ አዲስ ቀለም በተቀባ ግድግዳ ላይ በትላልቅ ፊደላት የተጻፉ ነበሩ። ይህ የሥርዓት አልበኞች ድርጊት ነው ብለህ ልታስብ ትችላለህ። የተለያዩ ነገሮችን በግድግዳዎች ላይ መጻፍ (በእንግሊዝኛ ግራፊቲ) ደግሞ ከሥርዓት አልበኝነት ድርጊቶች ውስጥ አንዱ ነው።

ግዴለሽ የሆኑ ሥርዓት አልበኞች አዲስ መኪናህን ቢያበላሹብህ ምን እንደሚሰማህ እስቲ አስበው። ወይም ደግሞ ብዙዎችን የሚጠቅም የሕዝብ ንብረት በሥርዓት አልበኞች ሲበላሽ ወይም ሲጠፋ ተመልክተህ ይሆናል። ለምን? አዎን፣ ለምን? ሥርዓት አልበኝነት ለምን እንደተስፋፋ አስበህ ታውቃለህ? በብዙ ቦታዎች ሥርዓት አልበኞች የሕዝብ ስልኮችን በማበላሸት ወይም በማጥፋት የሚደሰቱ ይመስላሉ። እንደ ባቡሮችና አውቶቡሶች የመሳሰሉ የሕዝብ ማመላለሻዎች አብዛኛውን ጊዜ የጥቃቱ ዒላማዎች ናቸው። ሥርዓት አልበኛ የሆኑ ሰዎች ለምንም ነገር ግድ የሌላቸው ናቸው ለማለት ይቻላል። ሆኖም ለአብዛኛው የሥርዓት አልበኝነት ድርጊት መንስኤው ምንድን ነው?

በሪዮ ዲ ጀኔሮ የሚኖር ማርኮ * የሚባል ወጣት ይደግፈው የነበረው የእግር ኳስ ቡድን በመሸነፉ በጣም ስለተበሳጨ የአሸናፊው ቡድን ደጋፊዎች ተሳፍረው ይጓዙበት በነበረው አውቶቡስ ላይ ድንጋይ መወርወር ጀመረ። ወይም የክሎስን ሁኔታ ተመልከት። በትምህርቱ ጥሩ ውጤት ባለማምጣቱ ምክንያት በመናደድ ድንጋይ እየወረወረ መስኮቶችን ሰባበረ። ይሁን እንጂ አባቱ ልጃቸው ላደረሰው ጉዳት ካሳ እንዲከፍሉ በተጠየቁ ጊዜ ‘ለቀልድ’ ተብሎ የተደረገው ነገር ሌላ ጣጣ አመጣ። ኤርቪን የሚባል ሌላ ወጣት ትምህርት እየተማረ ይሠራ ነበር። እሱም ሆነ ጓደኞቹ ጥሩ ጠባይ እንዳላቸው ተደርገው ይታዩ ነበር። ሆኖም ጊዜያቸውን የሚያሳልፉት ጎረቤቶቻቸውን በመረበሽ ነበር። የኤርቪን ወላጆች ስለዚህ ጉዳይ ምንም አያውቁም ነበር። የሙት ልጅ የሆነው ቫልትር በሳኦ ፓውሎ ጎዳና ተዳዳሪ ከመሆን ሌላ ምንም አማራጭ አልነበረውም። የቅርብ ጓደኞቹ የሥርዓት አልበኞች ቡድን አባላት ነበሩ። አብሯቸው በመሆን የሚያደርጉትን ነገር ያደርግ የነበረ ሲሆን ካራቴም ተምሯል። እንደነዚህ ያሉ ምሳሌዎች ከሥርዓት አልበኝነት ድርጊቶች በስተጀርባ የተለያዩ ሰዎች መኖራቸውንና ለሥርዓት አልበኝነት መነሾ የሚሆኑት ወይም በሥርዓት አልበኝነት ውስጥ የሚገለጹት ስሜቶች የተለያዩ መሆናቸውን ያሳያሉ።

“ሥርዓት አልበኝነት የበቀል ወይም የፖለቲካዊ አመለካከት መግለጫ ሊሆን ይችላል። አንዳንድ ጊዜ ወጣቶችም ሆኑ አዋቂዎች ‘ለቀልድ’ ሲሉ ብቻ ይህን ወንጀል ይፈጽማሉ” ሲል ዘ ዎርልድ ቡክ ኢንሳይክለፒዲያ ተናግሯል። ይሁን እንጂ ሥርዓት አልበኝነት ወጣቶች ለጨዋታ ብለው የሚያደርጉት ነገር ነው ተብሎ ብቻ የሚታለፍ አይደለም፤ ከፍተኛ የንብረት ውድመት አልፎ ተርፎም የሕይወት ጥፋት ሊያስከትል የሚችል ነገር ነው። አንድ ነገር በማድረግ ‘ለመዝናናት’ የፈለጉ የተወሰኑ ወጣቶች አንድ ሰው መንገድ ላይ ተኝቶ ሲያገኙ ቤንዚን አርከፍክፈው እሳት ለኮሱበት። ጉዳት የደረሰበት ይህ ሕንዳዊ ሆስፒታል ከገባ በኋላ ሞተ። “ወጣቶቹ ከዚህ ቀደም በርካታ ለማኞች ጎዳና ላይ በእሳት ስለተቃጠሉና ምንም እርምጃ ስላልተወሰደ ግድ የሚሰጠው ሰው ይኖራል ብለው እንዳላሰቡ” አንድ ዘገባ ገልጿል። ሥርዓት አልበኝነት በሕይወት ላይ ጉዳት ያስከትልም አያስከትል የሚያመጣው የገንዘብ ኪሳራና የስሜት ቀውስ ይህ ነው አይባልም። ስለዚህ ሥርዓት አልበኝነትን ሊቆጣጠር ወይም ሊያስቀር የሚችለው ምንድን ነው?

ሥርዓት አልበኝነትን ሊያስቆም የሚችለው ማን ነው?

የፖሊስ ኃይልና ትምህርት ቤቶች ሥርዓት አልበኝነትን ሊያስቀሩ ይችላሉን? አንዱ ችግር ባለ ሥልጣናቱ “በሕይወት ላይ ጉዳት” ከማያስከትሉ ጥፋቶች ይልቅ የአደገኛ ዕፆች ዝውውርን ወይም የነፍስ ግድያዎችን በመሳሰሉ ይበልጥ ከባድ በሆኑ ወንጀሎች ጊዜያቸው መያዙ ነው። አንድ ፖሊስ እንዳለው አንድ ወጣት ችግር ውስጥ ሲወድቅ አብዛኛውን ጊዜ ወላጆች “ተወቃሽ የሚያደርጉት አብሯቸው የሚውላቸውን ልጆች ወይም ትምህርት ቤቱን ወይም ወጣቱን የያዙትን ፖሊሶች ነው።” ትምህርትና ሕጋዊ እርምጃ ሥርዓት አልበኝነትን ይቀንስ ይሆናል፤ ሆኖም የወላጆች አመለካከት ካልተቀየረስ? አንድ የወጣቶች ጠባይ ማረሚያ ኃላፊ እንዲህ ብለዋል:- “የችግሩ መንስዔ መሰልቸትና የአጋጣሚ ጉዳይ ነው። [ልጆቹ] አምሽተው ይመጣሉ፤ የሚሠሩት ነገር ደግሞ የላቸውም። ምናልባት ምንም ቁጥጥር አይደረግባቸው ይሆናል፤ ቁጥጥር ቢደረግባቸው ኖሮ ከቤት አይወጡም ነበር።”

በብዙ ቦታዎች ሥርዓት አልበኝነት አሳሳቢ ችግር ቢሆንም ሁኔታዎች እንዴት መልካቸውን ሊቀይሩ እንደሚችሉ ተመልከት። በመግቢያው ላይ የተጠቀሱት ሥርዓት አልበኛ የነበሩ ወጣቶች ተለውጠዋል፤ አሁን ለማኅበረሰቡ ጠንቅ የሆነ ጠባይ የላቸውም። እነዚህ ወጣት ጥፋተኞች ቀደም ሲል የነበራቸውን አኗኗር እንዲቀይሩ ያደረጋቸው ምንድን ነው? በተጨማሪም ሥርዓት አልበኝነት መቀነስ ብቻ ሳይሆን እንደሚወገድ ስትሰማ ትገረም ይሆን? የሚቀጥለውን ርዕስ እንድታነብብ እንጋብዝሃለን።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.4 ስሞቹ ተቀይረዋል።