በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

‘በልብና በአእምሮ ውስጥ የማወቅ ፍላጎት የሚቀሰቅስ’

‘በልብና በአእምሮ ውስጥ የማወቅ ፍላጎት የሚቀሰቅስ’

‘በልብና በአእምሮ ውስጥ የማወቅ ፍላጎት የሚቀሰቅስ’

ስለ አንተ የሚያስብ ፈጣሪ ይኖር ይሆን?  የተባለውን መጽሐፍ (እንግሊዝኛ) በማነብበት ጊዜ የተሰማኝን ደስታ በቃላት መግለጽ ያስቸግረኛል። መጽሐፉ ይበልጥ የማወቅ ጉጉትና ፍላጎት ያሳድራል። በልቤና በአእምሮዬ ውስጥ ከፍተኛ የሆነ የማወቅ ፍላጎት ስለቀሰቀሳችሁብኝ ላመሰግናችሁ እወዳለሁ።”

በኖርዝ ካረላይና ዩ ኤስ ኤ የምትኖር አንዲት የይሖዋ ምሥክር በ1998/99 በተደረጉ “የአምላክ የሕ ይወት መንገድ” የአውራጃ ስብሰባዎች ላይ በመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ታትሞ ስለወጣው መጽሐፍ የተሰማትን ስሜት የገለጸችው ከላይ እንዳለው በማለት ነበር። የመጽሐፉ ቅጂ ባይኖርህ እንኳ ሌሎች የሰጡትን ምላሽ ቀጥሎ ተመልከት።

በካሊፎርኒያ ሳን ዲዬጎ ዩ ኤስ ኤ ተደርጎ በነበረ አንድ የአውራጃ ስብሰባ ላይ የመጽሐፉን ቅጂ ያገኘ ሰው እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ይህ መጽሐፍ እምነትን በእጅጉ የሚያጠነክር ሆኖ አግኝቸዋለሁ። ልቤ ለይሖዋ የፍጥረት ሥራዎች ባለኝ አድናቆት እንዲሞላ አድርጓል። መጽሐፉን እያነበብኩ ገጽ 98 ላይ ደርሻለሁ፤ ሆኖም መጽሐፉ እንዳያልቅብኝ እየሳሳሁ ነው! መጽሐፉ እጅግ የሚያረካ ነው።”

በሩቅ ምሥራቅ የምትኖር አንዲት ሴት እንዲህ ስትል ጽፋለች:- “የአውራጃ ስብሰባው ተናጋሪ ‘ልዩ መጽሐፍ’ በማለት ተናግሮ ነበር፤ ለመጽሐፉ የሰጠው መግለጫም ከይዘቱ ጋር የሚስማማ ነው። አንዱ የመጽሐፉ የላቀ ገጽታ አንባቢው በአምላክ መኖር እንዲያምን የማያስገድድ መሆኑ ነው፤ ይሁንና ሐቁን በማያሻማ መንገድ ያስቀምጣል።”

ከእነዚህ እውነታዎች ውስጥ ጽንፈ ዓለማችንን፣ ሕይወትንና ራሳችንን የሚመለከቱ አስደናቂ የሆኑ ሳይንሳዊ ግኝቶች ተካትተዋል። ይህ የብዙዎቹን ስሜት ማርኳል። በካሊፎርኒያ የምትኖር አንዲት ሴት “ይህች ትንሽ መጽሐፍ ያሳደረችብኝን ተጽእኖ የምገልጽባቸው ቃላት የሉኝም” ስትል ጽፋለች። “በእያንዳንዱ ገጽ ላይ የሚገኙት ስለ ጽንፈ ዓለማችንና ስለ ሕይወት የሚገልጹ አዳዲስ ግኝቶች መጽሐፉን ማንበቤን እንድቀጥል አድርገውኛል። በእርግጥ ብዙ ነገር ተምሬአለሁ! ይህች ትንሽ መጽሐፍ ለእኔ ትልቅ ሀብት ነች፤ የቻልኩትን ያህል ብዙ ሰው እንዲያነብባትም አደርጋለሁ።”

ብዙዎችን ያስደሰተው የመጽሐፉ ገጽታ የፈጣሪን ባሕርያት ጎላ አድርጎ በመግለጽ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠው መግለጫ ነው። “በመጽሐፉ የመጨረሻ ገጾች ላይ የሚገኘው ስለ መጽሐፍ ቅዱስ የቀረበው ጠቅለል ያለ ማብራሪያ እስከ አሁን ካነበብኩት ውስጥ በጣም ያስደሰተኝ ክፍል ነው” በማለት አንድ ሰው ተናግሯል። በኒው ዮርክ ዩ ኤስ ኤ በተደረገ አንድ የአውራጃ ስብሰባ ላይ የተገኘች ሴት እንዲህ ስትል ጽፋለች:- “አዲስ ያወጣችሁት መጽሐፍ እስከ አሁን ካሳተማችኋቸው መጻሕፍት ሁሉ እጅግ ማራኪ ነው። የፈጣሪን መኖር ለማስረዳት በቀረቡት ሳይንሳዊ ማስረጃዎች እጅግ ተደንቄአለሁ። ስለ ራሱ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ የቀረበው እጥር ምጥን ያለ ማብራሪያ የተጠቀሱትን ነጥቦች ለማብራራትም ሆነ የማንበብን ፍላጎት ለመቀስቀስ በቂ ነው።”

ለመረዳት የማያስቸግር ሳይንስ

በመጀመሪያዎቹ ምዕራፎች ላይ የቀረበው ሳይንሳዊ መረጃ ለመረዳት የሚያስቸግር ይመስላል፤ ሆኖም አንዳንዶች የሰጧቸው ምላሾች እነሆ።

አንድ ካናዳዊ ሰው እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ደራሲዎቻቸው የተወሳሰቡ ቃላትን በመጠቀም ከሚጽፏቸው የሙያ መጻሕፍት ፍጹም የተለየ ነው። ስለ ፊዚክስ፣ ኬሚስትሪ፣ ዲ ኤን ኤ፣ ክሮሞሶሞችና ወዘተ የሚናገሩ የትምህርት ርዕሶችን ለመረዳት በማያስቸግር መንገድ ለማቅረብ መቻላችሁ የላቀ እውቀት እንዳላችሁ የሚያሳይ ነው። ከዓመታት በፊት ያጠናኋቸውን የዩኒቨርሲቲ መማሪያ መጻሕፍት እናንተ ብትጽፏቸው ኖሮ ምንኛ ደስ ባለኝ ነበር!”

አንድ የዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል:- “ቴክኒካዊ የሆነ ማብራሪያ ሳያበዛ ጉዳዩን ግልጽ በሆነ መንገድ ያቀርባል። መጽሐፉ አንባቢው እንዲያገናዝብ የሚያደርግ ሲሆን እውቅ የሆኑ በርካታ ሳይንቲስቶች የተናገሯቸውንም ይጠቅሳል። የጽንፈ ዓለምንና የሕይወትን መጀመሪያ ለማወቅ የሚፈልግ ሳይንቲስትም ይሁን ማንም ተራ ሰው ‘ሊያነብበው የሚገባ’ መጽሐፍ ነው።”

የነርስ ኮርስ የምትከታተል አንዲት ሴት እንዲህ ብላለች:- “በክፍል ውስጥ የምንጠቀምበትን ሐሳብ በምዕራፍ 4 ላይ ተጠቅሶ ሳገኘው ዓይኔን ማመን አቃተኝ! መጽሐፉን ለመምህራችን ሰጠሁትና ግሩም የሆነ መረጃ እንደሚያገኝበት ነገርሁት። በገጽ 54 ላይ ስለ አንጎል የሚናገረውን አሳየሁት። አነበበውና ‘ጥሩ መጽሐፍ ነው! አነብበዋለሁ’ አለ።”

በቤልጂየም የሚገኝ አንድ የፓርላማ አባል እንዲህ ሲል ጽፏል:- “እጅግ ያስደነቀኝና የማረከኝ ነገር መጽሐፍ ቅዱስ በአንድ አምላክ ስለ ማመን ከሚናገረው ነገር ጋር ዘመናዊ ሳይንስ የሚስማማ መሆኑን ለማሳየት የቀረበው ሳይንሳዊ ዝርዝር ነው። ይህ የተዋጣለት አቀራረብ ነው።”

ስለ ፈጣሪ የተሻለ እውቀት ማግኘት

መጽሐፉ በብዙ አገሮች የሚኖሩ ሰዎች ስለ አምላክ የተሻለ እውቀት እንዲያገኙና ይበልጥ ወደ እርሱ እንዲቀርቡ ረድቷቸዋል። በጃፓን ፉኩኦካ ከተማ የሚኖር አንድ አንባቢ እንደሚከተለው ብሏል:- “ለመጀመሪያ ጊዜ ሌንሶቹ ሙሉ በሙሉ በይሖዋ ላይ ያነጣጠሩ ያህል ነበር። መጽሐፉ የሚያሳምንበት መንገድ እጅግ የሚያስደንቅ ነው። እስከ አሁን ድረስ አስቤው በማላውቀው መንገድ ስለ ይሖዋ ግንዛቤ ለማግኘት ችያለሁ።” አንድ ሳልቫዶሪያዊ ሰው እንዲህ ብሏል:- “አምላክ መሐሪ፣ ሞገስ ያለው፣ ታጋሽና ፍቅራዊ ደግነቱ የበዛ መሆኑን በግልጽ አብራርታችኋል። በእርግጥም ወደ እሱና ወደ ልጁ ይበልጥ ለመቅረብ የሚያስፈልገን ዋናው ነገር ይህ ነው። የይሖዋን ስሜትና የልጁን የኢየሱስን ሰብዓዊ ስሜቶች የሚያብራራ የመጀመሪያው መጽሐፍ ነው።” በዛምቢያ የሚገኝ አንድ አንባቢ ደግሞ “ስለ ይሖዋ ያለኝ አመለካከት ቀደም ሲል አስቤው በማላውቀው መንገድ አዲስ አቅጣጫን ይዟል” ብሏል።

የይሖዋ ምሥክሮች ስለ አንተ የሚያስብ ፈጣሪ ይኖር ይሆን? የተባለውን መጽሐፍ ለሌሎች ለማበርከት እንደሚጓጉ እሙን ነው። አንዲት ሴት እንዲህ ብላለች:- “ምዕራፍ 10ን [“ፈጣሪ የሚያስብልን ከሆነ ይህን ያክል መከራና ሥቃይ ለምን ኖረ?”] አንብቤ ስጨርስ ‘ለጃፓን የሚያስፈልገው መጽሐፍ በትክክል ይህ ነው!’ ከማለት ሌላ ምንም ለመናገር አልቻልኩም። በዚህ ምዕራፍ ውስጥ የሚገኘውን እውቀት የራሴ ለማድረግና በመስክ አገልግሎት ላይ ልጠቀምበት እፈልጋለሁ።” አባቷ ካህን ሆኖ በሚያገለግልበት ቤተ መቅደስ ውስጥ ያደገችን አንዲት ልጃገረድ መጽሐፍ ቅዱስ ታስጠና የነበረች አንዲት ሌላ ሴት እንዲህ ብላለች። “ስለ ፈጣሪ የሚናገረውን ሐሳብ ለመቀበል ተቸግራ ነበር። የመጽሐፉ ማብራሪያ ድርቅ ያለ አይደለም፤ ሆኖም እውነታዎቹ ቁልጭ ብለው ቀርበዋል፤ ስለዚህ ቡዲስቶች ሳይቀሩ ያለ ምንም ማመንታት ሊያነቡት ይችላሉ ብዬ አስባለሁ። በተጨማሪም የይሖዋን ፍቅር ይበልጥ እንድንገነዘብ ያደርገናል።”

ከእንግሊዝ የሚከተለው ግምገማ መጥቶ ነበር:- “ፈጣሪ የተባለውን መጽሐፍ አንብቤ ብጨርስም እንደገና ማንበብ ልጀምር ነው። እንዴት ያለ ግሩም መጽሐፍ ነው! አንድ ሰው መጽሐፉን ማንበቡ ይሖዋን እንዲወድደው ያደርገዋል። መጽሐፉን ያበረከትሁላት ጎረቤቴ ሁለት ምዕራፍ ካነበበች በኋላ ‘ማንበቤን ለማቆም አልቻልኩም፤ በጣም አስደሳች ነው’ ብላለች። ሰዎች ታላቁ ፈጣሪያችንን እንዲያውቁና እንዲወድዱ መጽሐፉ እንደሚረዳቸው እርግጠኛ ነኝ።”

በሜሪላንድ ዩ ኤስ ኤ የሚኖር አንድ ሰው እንዲህ ብሏል:- “መንፈሳዊነቴን በእጅጉ የሚያጠነክርልኝ ሆኖ አግኝቸዋለሁ! በሥራ ጉዳይ ለማገኛቸው በሙሉ አንድ ቅጂ ለመስጠት አቅጄአለሁ። አንዳንድ ጊዜ ሥራ ለሚበዛባቸው የተማሩ ሰዎች መመስከር ያስቸግረኛል። አሁን ግን በዚህ መጽሐፍ አማካኝነት ማራኪና ውጤታማ የሆነ አቀራረብ ሊኖረኝ ይችላል።”

ስለ አንተ የሚያስብ ፈጣሪ ይኖር ይሆን? የተባለው መጽሐፍ በምድር ዙሪያ በሚገኙ ሰዎች ላይ በጎ ተጽእኖ እንደሚያሳድር እሙን ነው።

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

ከላይ ያለው መጽሐፍ የሽፋን ሥዕል፣ Eagle Nebula: J. Hester and P. Scowen (AZ State Univ.), NASA