በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የአንባብያን ጥያቄዎች

በዛሬው ጊዜ በቀዶ ሕክምና እንዲመክን የተደረገን ወንድ (ሴት) ካስፈለገ መውለድ እንዲችሉ ይደረጋል ስለሚባል አንድ ክርስቲያን ይህን ዘዴ የወሊድ መቆጣጠሪያ አማራጭ አድርጎ ሊመለከተው ይችላል?

በዛሬው ጊዜ በቀዶ ሕክምና እንዲመክን የተደረገን ወንድ (ሴት) ካስፈለገ መውለድ እንዲችሉ ይደረጋል ስለሚባል አንድ ክርስቲያን ይህን ዘዴ የወሊድ መቆጣጠሪያ አማራጭ አድርጎ ሊመለከተው ይችላል?

በቀዶ ሕክምና መምከን በሰፊው የሚሠራበት የቤተሰብ ምጣኔ ዘዴ እየሆነ መጥቷል። ይህ ዘዴ በብዙዎች ዘንድ ተቀባይነት የማግኘቱ ጉዳይ በማኅበራዊና በትምህርት ደረጃ እንዲሁም በሃይማኖታዊ አመለካከት ላይ የተመካ ይመስላል። “አቤቱ፣ መንገድህን አስተምረኝ፣ . . . በቀና መንገድ ምራኝ” የሚለውን የመዝሙራዊውን ምኞት በሚጋሩት በይሖዋ ምሥክሮች ዘንድ ሃይማኖታዊ እምነት ወሳኝ ጉዳይ ነው። (መዝሙር 27:​11) በቀዶ ሕክምና መምከን ምን ነገሮችን ያካትታል?

ወንዶችን ለማምከን የሚደረግ ቀዶ ሕክምና ቅንጣሲቦይ (vasectomy) ይባላል። በማኅደረ ቆለጥ (scrotum) ውስጥ የሚገኙ ሁለት ትንንሽ የወንድ ዘር ቱቦዎች ተቆርጠው ይታሰራሉ። ይህ በተለያዩ የሕክምና ዘዴዎች ሊከናወን የሚችል ቢሆንም ዓላማው የወንድ ዘር ከቆለጥ እንዳይወጣ ማገድ ነው። ሴቶችን ለማምከን የሚደረገው ቀዶ ሕክምና ደግሞ በእንግሊዝኛ ቲውባል ሊጌሽን ይባላል። ይህ በአብዛኛው የሚከናወነው እንቁላሎቹን ከእንቁልጢዎች ወደ ማህፀን የሚወስዱትን የማህፀን ቱቦዎች ቆርጦና ቋጥሮ (ወይም ተኩሶ) በመድፈን ነው።

እነዚህ ዘዴዎች ዘላቂ እንደሆኑ ማለትም አንድን ሰው ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ መካን እንደሚያደርጉት ለረጅም ጊዜ ይታሰብ ነበር። ሆኖም አንዳንድ ሰዎች በወሰዱት እርምጃ በመቆጨት ወይም አዳዲስ ሁኔታዎች በመፈጠራቸው ምክንያት የተደረገላቸውን ቅንጣሲቦይ ወይም ቲውባል ሊጌሽን ለማስወገድ የሕክምና እርዳታ ፈልገዋል። የተራቀቁ የሕክምና መሣሪያዎች በመፈልሰፋቸውና ደቂቅ ቀዶ ሕክምና (microsurgery) በመጀመሩ ምክንያት በቀዶ ሕክምና የተከናወነውን መምከን ለማስወገድ የሚደረጉ ጥረቶች ይበልጥ ስኬታማ ሆነዋል። የተቆረጡትን ጥቃቅን የቱቦ ጫፎች እንደገና በማገናኘት ወንዶችን ለማምከን የተደረገውን ቀዶ ሕክምና በማስወገድ ረገድ ተመርጠው በተወሰዱ ዕጩዎች ላይ ከ50 እስከ 70 በመቶ ስኬት ማግኘት እንደሚቻል ማንበባችን እንግዳ ነገር አይደለም። ሴቶችን ለማምከን የተደረገውን ቀዶ ሕክምና በመሻር ረገድ ደግሞ ከ60 እስከ 80 በመቶ ስኬት እንደሚገኝ ይነገራል። አንዳንዶች ይህን ሲሰሙ በቀዶ ሕክምና መምከን ለዘለቄታው የሚቀጥል ሆኖ መታየት እንደሌለበት ተሰምቷቸዋል። ቅንጣሲቦይ እና ቲውባል ሊጌሽን መውለድ ሲያስፈልግ ማቋረጥ እንደሚቻሉት ሌሎች የወሊድ መቆጣጠሪያ ዘዴዎች ማለትም እንደሚዋጡ እንክብሎች፣ ኮንዶሞችና የማህፀን ቆቦች (diaphragms) ሊታዩ እንደሚችሉ ይሰማቸው ይሆናል። ይሁን እንጂ ልብ ልንላቸው የሚገቡ አንዳንድ አሳሳቢ ነገሮች አሉ።

አንደኛው ነገር እንደገና መውለድ የመቻል አጋጣሚ ቀጥሎ በተዘረዘሩት ነገሮች ክፉኛ ሊስተጓጎል መቻሉ ነው:- የማምከን ቀዶ ሕክምናው ሲካሄድ በቱቦዎቹ ላይ የደረሰው ጉዳት መጠን፣ ተቆርጦ የተጣለው ቱቦ ወይም የተወው ጠባሳ መጠን፣ ቀዶ ሕክምናው ከተካሄደበት ጊዜ አንስቶ ያለፉት ዓመታት እና በቅንጣሲቦይ ረገድ ደግሞ የወንዱን ዘር የሚፃረሩ ፀረ እንግዳ አካላት መፈጠራቸው። በተጨማሪም በአብዛኞቹ አገሮች ደቂቅ ቀዶ ሕክምና ለማካሄድ የሚያገለግሉ መሣሪያዎች አለመኖር ወይም ክፍያው ከአቅም በላይ የመሆኑ ጉዳይ ችላ ሊባል አይገባውም። በመሆኑም ብዙዎች መውለድ ፈልገው ማምከኑ እንዲወገድላቸው ቢመኙም ይህ ሳይሳካላቸው ይቀራል። ለእነርሱ ሁኔታው ዘላቂ ነው። * ስለዚህ ከላይ የተጠቀሱት በሕክምና የተከናወነን መምከን እንደገና ወደ ቀድሞው መመለስ እንደሚቻል ለማሳየት የቀረቡት አኃዛዊ መረጃዎች እንዲያው ቲዎሪ ብቻ ናቸው እንጂ አስተማማኝ አይደሉም።

ከእውነታው ጋር ዝምድና ያላቸው አንዳንድ ጭብጦች አሉ። በወንዶች ላይ በቀዶ ሕክምና የሚከናወነውን መካንነት ወደ ቀድሞው ሁኔታ መመለስን በተመለከተ ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ የታተመ አንድ ጽሑፍ 12,000 የአሜሪካ ዶላር የሚፈጅ ቀዶ ሕክምና ከተደረገ በኋላ “ማስረገዝ የሚችሉት 63 በመቶ የሚያክሉ ታካሚዎች ብቻ” መሆናቸውን ጠቅሷል። በተጨማሪም “በቀዶ ሕክምና መካን ከሆኑት ወንዶች መካከል ውሎ አድሮ እንደገና መውለድ መቻል የፈለጉት ስድስት ከመቶ የሚሆኑ” ብቻ ናቸው። መካከለኛ አውሮፓን በሚመለከት በጀርመን የተካሄደ አንድ ጥናት በቀዶ ሕክምና ለመምከን መርጠው ከጊዜ በኋላ መውለድ የፈለጉ ወደ 3 ከመቶ የሚጠጉ ወንዶች ናቸው። ከተደረጉት ሙከራዎች ውስጥ ግማሹ ቢሳካ እንኳ 98.5 በመቶ ለሚሆኑት በቅንጣሲቦይ የተደረገን መካንነት እንደገና ወደ ቀድሞው መመለስ የማይቻል ይሆንባቸዋል ማለት ነው። በተጨማሪም ደቂቅ ቀዶ ሕክምና የሚያካሂዱ ዶክተሮች ጥቂት በሆኑባቸው ወይም ጨርሶ በሌሉባቸው አገሮች አኃዙ ከፍተኛ ይሆናል።

በመሆኑም የወንዶች ወይም የሴቶች በቀዶ ሕክምና መምከን ጊዜያዊ የወሊድ መቆጣጠሪያ እንደሆነ በማሰብ ጉዳዩን አቅልሎ መመልከቱ ትክክል አይደለም። በተጨማሪም አንድ እውነተኛ ክርስቲያን ግምት ውስጥ የሚያስገባቸው ሌሎች ነገሮች አሉ።

አንድ መሠረታዊ የሆነ ነጥብ የመዋለድ ችሎታ ከፈጣሪ የተገኘ ስጦታ መሆኑ ነው። የእርሱ የመጀመሪያ ዓላማ ከሚያካትታቸው ነገሮች መካከል ፍጹማን የሆኑ ሰዎች ተዋልደው ‘ምድርን መሙላትና መግዛት’ ይገኝበታል። (ዘፍጥረት 1:​28) የጥፋት ውኃ የምድር ነዋሪዎች ብዛት ወደ ስምንት ዝቅ እንዲል ካደረገ በኋላ አምላክ እነዚህን መሠረታዊ መመሪያዎች በድጋሚ ሰጥቷል። (ዘፍጥረት 9:​1) አምላክ ይህን መመሪያ በድጋሚ ለእስራኤል ብሔር ባይሰጥም እንኳ እስራኤላውያን ልጅ መውለድን በጣም አስፈላጊ ነገር አድርገው ይመለከቱ ነበር።​—⁠1 ሳሙኤል 1:​1-11፤ መዝሙር 128:​3

አምላክ ለእስራኤላውያን የሰጠው ሕግ ሰዎች ያላቸውን የመዋለድ ችሎታ በተመለከተ ስላለው አመለካከት ፍንጭ የሚሰጡ ነገሮች ይዟል። ለምሳሌ ያህል ትዳር ያለው አንድ ሰው የዘር ሐረግ መስመሩን የሚቀጥልለት ወንድ ልጅ ከመውለዱ በፊት ቢሞት የእርሱ ወንድም ሚስትየውን በማግባት ለወንድሙ ወንድ ልጅ መውለድ ነበረበት። (ዘዳግም 25:​5) ይህን ይበልጥ የሚያጠናክረው ባልዋ ከሰው ጋር ሲጣላ እርሱን ለማገዝ የምትሞክርን ሚስት በሚመለከት የተሰጠው ሕግ ነበር። ከባልዋ ጋር የተጣላውን ሰው ብልት ከያዘች እጅዋ መቆረጥ ነበረበት። አምላክ ዓይን በዓይን በሚለው ሕግ መሠረት በእርሷም ሆነ በባልዋ የመራቢያ አካላት ላይ ተመሳሳይ ቅጣት እንዲፈጸም አለመጠየቁ ከፍተኛ ትርጉም ያዘለ ነበር። (ዘዳግም 25:​11, 12) ይህ ሕግ የመራቢያ አካላት በአክብሮት እንዲያዙ እንደሚያደርግ ግልጽ ነው። እነዚህ አካላት በከንቱ መጥፋት አልነበረባቸውም። *

ክርስቲያኖች ለእስራኤላውያን በተሰጠው ደንብ ስር አለመሆናቸውን እናውቃለን፤ በመሆኑም በዘዳግም 25:​11, 12 ላይ የሚገኘው ሕግ በእነርሱ ላይ ተፈጻሚነት የለውም። ብዙ ባልና ሚስቶች አንድ ዓይነት የወሊድ መቆጣጠሪያ ዘዴ ለመጠቀም ሲወስኑ ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ ማግባትና የቻሉትን ያህል ብዙ ልጆች መውለድ እንዳለባቸው መመሪያም ሆነ ያን ዓይነት ሐሳብ አለማስተላለፉን ግምት ውስጥ ያስገባሉ። (ማቴዎስ 19:​10-12) ሐዋርያው ጳውሎስ ኃይለኛ የጾታ ስሜት የሚሰማቸው ‘ባል የሞተባቸው ቆነጃጅት እንዲያገቡና ልጆችን እንዲወልዱ’ አበረታቷል። (1 ጢሞቴዎስ 5:​11-14) ጳውሎስ ለክርስቲያኖች ልጆች መውለድ የሚያስችላቸውን የመራቢያ ኃይላቸውን በፈቃደኝነት መሥዋዕት በማድረግ ለዘለቄታው ስለሚቀጥል መካንነት አልጠቀሰላቸውም።

ክርስቲያኖች አምላክ የመራባት ችሎታቸውን ከፍ አድርጎ እንደሚመለከት የሚያሳዩትን እነዚህን ነጥቦች ቢያመዛዝኑ ጥሩ ነው። ባልና ሚስት ተገቢ በሆኑት የቤተሰብ ምጣኔ ዘዴዎች መጠቀም ቢያስፈልጋቸው እንኳ የሚጠቀሙበትን ጊዜ መወሰን አለባቸው። ወደፊት እርግዝና ከተከሰተ እናትየው ወይም ልጁ ከባድ የጤንነት ችግር አልፎ ተርፎም የሞት አደጋ እንደሚደቀንባቸው የሚያሳዩ ተጨባጭ የሕክምና መረጃዎች ከተገኙ በዚህ ጊዜ የሚያደርጉት ውሳኔ ከበድ እንደሚል የተረጋገጠ ነው። በዚህ ሁኔታ ስር የሚገኙ አንዳንዶች ማንኛውም እርግዝና የእናትየውን (አስቀድሞም ሌሎች ልጆች ይኖሯት ይሆናል) ወይም ከጊዜ በኋላ የጤና እክል ይዞ በመወለድ የልጁን ሕይወት አደጋ ላይ እንዳይጥል ለማድረግ ቀደም ሲል በተገለጸው መሠረት በቀዶ ሕክምና መካን ለመሆን ተገደዋል።

ሆኖም እንዲህ ዓይነት ያልተለመደና ለየት ያለ አደጋ ያልተደቀነባቸው ክርስቲያኖች ‘ጤናማ አስተሳሰብ’ ለመያዝና አስተሳሰባቸውንና ድርጊታቸውን አምላክ ለመራቢያ ኃይል ባለው አመለካከት መቅረጽ እንደሚፈልጉ የተረጋገጠ ነው። (1 ጢሞቴዎስ 3:​2 NW፣ ቲቶ 1:​8፤ 2:​2, 5-8) ይህ ቅዱሳን ጽሑፎች ለሚጠቁሙት ነገር ብስለት የተሞላበት የጠንቃቃነት ባሕርይ ማሳየትን ያንጸባርቃል። ይሁን እንጂ አንድ ክርስቲያን የአምላክን መመዘኛዎች በግዴለሽነት ቸል እንደሚል በይፋ የታወቀ ቢሆንስ? ሌሎች ሰዎች እርሱ (ወይም እርሷ) ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር የሚስማማ ውሳኔ ማድረግን በተመለከተ ባተረፉት ስም ረገድ ጥሩ ምሳሌ መሆናቸውን አይጠራጠሩም? እርግጥ አንድ አገልጋይ ስሙ በዚህ መልኩ ከጎደፈ ልዩ ለሆኑ የአገልግሎት መብቶች ያለውን ብቃት ሊነካበት ይችላል። ሆኖም አንድ ሰው ይህን ቀዶ ሕክምና ያከናወነው ባለማወቅ ከሆነ ሁኔታው ከዚህ የተለየ መልክ ይኖረዋል።​—⁠1 ጢሞቴዎስ 3:​7

^ አን.6 “ተቆርጦ የነበረውን የወንድ ዘር ከቆለጥ የሚወጣበትን ቱቦ እንደገና ለማገናኘት የሚደረግ የቀዶ ሕክምና ሙከራ ቢያንስ 40 ከመቶ ስኬት ያለው ሲሆን የተሻለ ደቂቅ የቀዶ ሕክምና ዘዴ ከተገኘ ደግሞ የስኬቱ መጠን ሊጨምር እንደሚችል አንዳንድ ማስረጃዎች ያሳያሉ። ሆኖም በቅንጣሲቦይ አማካኝነት የሚደረግ መካንነት ዘላቂ ተደርጎ መታየት አለበት።” (ኢንሳይክለፒዲያ ብሪታኒካ) “በቀዶ ሕክምና የሚከናወን መምከን ለዘለቄታው እንደሚቀጥል ተደርጎ መታየት አለበት። ታካሚው ቀዶ ጥገናውን ስለማስወገድ የሰማው ነገር ቢኖርም በቀዶ ሕክምና አማካኝነት የተነጣጠሉትን ቱቦዎች እንደገና ማያያዝ ከፍተኛ ወጪ ከመጠየቁም በላይ ስኬታማነቱ አስተማማኝ ሊሆን አይችልም። የቲውባል መካንነትን ለማስወገድ ቀዶ ሕክምና የሚያደርጉ ሴቶች ከማህፀን ውጪ ጽንስ የመያዛቸው አጋጣሚ ከፍተኛ ነው።”​—⁠ከንቴምፐራሪ ኦብስተትሪሺያንስ/ጋይነኮለጂስትስ፣ ሰኔ 1998

^ አን.10 ከዚህ ጋር ተዛማጅነት ያለው የሚመስል አንድ ሌላ ሕግ ደግሞ ብልቱ ከፍተኛ ጉዳት የደረሰበት ወንድ ፈጽሞ ወደ አምላክ ጉባኤ መግባት እንደሌለበት ይናገራል። (ዘዳግም 23:​1) ሆኖም ቅዱሳን ጽሑፎችን ጠለቅ ብሎ ማስተዋል ይህ ሁኔታ “እንደ ግብረ ሰዶም ለመሳሰሉ ርኩስ ዓላማዎች ሆን ተብሎ ከማኮላሸት ጋር ግንኙነት ያለው መሆኑ” ግልጽ እንደሆነ ጠቅሷል። ከዚህ የተነሳ ይህ ሕግ ማኮላሸትን ወይም ከማኮላሸት የማይተናነስ ድርጊትን የወሊድ መቆጣጠሪያ አድርጎ አላካተተም። በተጨማሪም ማስተዋል እንዲህ ይላል:- “ይሖዋ ጃንደረባዎች የእርሱ አገልጋዮች እንደሆኑ በመቁጠር በእርሱ ዘንድ ተቀባይነት የሚያገኙበት ጊዜ እንደሚመጣና ታዛዥ ከሆኑ ደግሞ ከወንዶችና ከሴቶች ልጆች የሚበልጥ ስም እንደሚያገኙ በሚያጽናና መንገድ በትንቢት ተናግሯል። በኢየሱስ ክርስቶስ አማካኝነት ሕጉ ሲወገድ እምነት ያላቸው ሰዎች በሙሉ ቀድሞ የነበራቸው አቋም ወይም ሁኔታ ምንም ይሁን ምን የአምላክ መንፈሳዊ ልጆች መሆን ችለዋል። ሥጋዊ ልዩነቶች ተወግደው ነበር።​—⁠ኢሳ 56:​4, 5፤ ዮሐ 1:​12