በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የአመለካከት አድማስህን ማስፋት ይኖርብህ ይሆን?

የአመለካከት አድማስህን ማስፋት ይኖርብህ ይሆን?

የአመለካከት አድማስህን ማስፋት ይኖርብህ ይሆን?

በምዕራባዊ ጃፓን የምትገኘው የኮቤ ከተማ ከባድ የመሬት መንቀጥቀጥ በመታት ጊዜ የራስን ጥቅም መሥዋዕት የማድረግ መንፈስ ያላቸው ፈቃደኛ ሠራተኞች ጉዳት የደረሰባቸውን ነዋሪዎች ለመርዳት ወዲያው መጡ። ሆኖም እርዳታ ለመስጠት በዚያ የተገኘ አንድ የሐኪሞች ቡድን መድኃኒት ለማግኘት ያቀረበውን ጥያቄ በከተማው የጤና ቢሮ ውስጥ የሚሠራ አንድ ሰው ውድቅ አደረገው። በከተማው የሚገኝ የአንድ ትልቅ የማዘጋጃ ቤት ሆስፒታል ዲሬክተር ሆኖ የሚሠራው ይኸው ባለሥልጣን ሐኪሞቹ ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቁ መርፌዎችንና በደም ስር የሚወሰዱ ፈሳሾችን በመጠለያ ጣቢያዎቹ ከሚሰጡ ይልቅ ጉዳተኞቹ በኮቤ ወደሚገኙ ሆስፒታሎች ተወስደው እንዲታከሙ ፈለገ። በመጨረሻ ሐኪሞቹ ያቀረቡት ጥያቄ ተቀባይነት ቢያገኝም ባለሥልጣኑ መጀመሪያ ላይ ግትር አቋም መያዙና ርኅራሄ አለማሳየቱ ለብዙዎች ትችት ዳርጎታል።

ምናልባትም ባለሥልጣን የሆነ አንድ ሰው ባንተ ላይ ተመሳሳይ የሆነ ግትር አቋም የወሰደበት ጊዜ አጋጥሞህ ይሆናል። አልፎ ተርፎ አንተ ራስህ እንዲህ ዓይነት ስህተት የፈጸምክበት ጊዜ ይኖር ይሆናል። የአመለካከት አድማስህን ማስፋትህ ይጠቅምህ ይሆን?

የተሟላ ግንዛቤ ይኑርህ

አብዛኛውን ጊዜ ሰዎች አንድን ጉዳይ ከአንድ ጎን ወይም አቅጣጫ ብቻ በመመልከት ስለ ጉዳዩ ያላቸውን ግንዛቤና ማስተዋል ውስን ያደርጋሉ። በአብዛኛው ይህ የሚሆነው እንደ ትምህርት፣ የሕይወት ገጠመኝና አስተዳደግ በመሳሰሉ ነገሮች ምክንያት ነው። አንድ ሰው ስለ አንድ ጉዳይ የተሟላ ግንዛቤ ለማግኘት የሚጥር ከሆነ ጥበብ የተሞላበት ውሳኔ ማድረግ ይችላል። ለምሳሌ ያህል የትራፊክ መብራት የሌለበትን መኪና የሚበዛበት መስቀለኛ መንገድ እያቋረጥክ ከሆነ ከፊት ለፊትህ ያለውን ብቻ መመልከትህ ጥበብ ይሆናልን? በፍጹም! በተመሳሳይም ውሳኔ ማድረግና በኃላፊነት ስሜት እርምጃ መውሰድ እንድትችል የተሟላ ግንዛቤ ለመጨበጥ አስተሳሰብህን ሰፋ ማድረግህ በጣም ሊጠቅምህ ይችላል። አልፎ ተርፎም ሕይወት አድን ሊሆንልህ ይችላል።

በዚህ ረገድ ሁላችንም ማሻሻያ ማድረግ እንደምንችል የታወቀ ነው። ስለዚህ ‘የአስተሳሰብ አድማሴን በማስፋት ጥቅም ማግኘት የምችልባቸው አንዳንድ ዘርፎች ምንድን ናቸው?’ ብለህ ራስህን ጠይቅ።

ለሌሎች ያለህ አመለካከት

ሰዎችን ስትመለከት ወደ አእምሮህ የሚመጣው ነገር ምንድን ነው? ሌላ አማራጭ ወይም አስታራቂ ሐሳብ የሌለ ይመስል የሚናገሩትን ወይም የሚያደርጉትን ነገር በደፈናው ስህተት ወይም ትክክል አድርገህ የመፈረጅ አዝማሚያ አለህ? አንድ ሰው የሚሰነዝረው አስተያየት ወይ ምስጋና አሊያም ነቀፋ ነው፤ ከዚህ ውጭ ሊሆን አይችልም ብለህ ማሰብ አለብህን? አንድን ሰው ሙሉ በሙሉ ትክክል ወይም ደግሞ ሙሉ በሙሉ ስህተት አድርገህ መመልከት ይኖርብሃልን? እንዲህ ዓይነት አመለካከት መያዝ በተለያዩ ቀለማት ባሸበረቀ የፀደይ መስክ ላይ ጥቁርና ነጭ ቀለም ብቻ ለማንሳት እንደሚሞክር ፎቶግራፍ አንሺ ከመሆን ተለይቶ አይታይም። ወይም ዓይን በሚማርከው የመልክአ ምድር አቀማመጥ ከመደሰት ይልቅ አንድ ደንታ ቢስ የሆነ ጎብኚ ጥሎት በሄደው ጥቃቅን ቆሻሻ ደስታው እንዲወሰድበት እንደሚፈቅድ መንገደኛ አንተም በአንድ ሰው ደካማ ጎኖች ላይ ትኩረት ማድረግ ይቀናሃል?​—⁠ከመክብብ 7:​16 ጋር አወዳድር

ይሖዋ የሰው ልጆች ለሚሠሩት ስህተት ያለውን አመለካከት በማጤን ብዙ ትምህርት ማግኘት ይቻላል። ምንም እንኳ የሰዎችን ድክመቶችና ጉድለቶች ቢያውቅም በእነዚህ ላይ አያተኩርም። አመስጋኝ የሆነው መዝሙራዊ “ኃጢአትንስ ብትጠባበቅ፣ አቤቱ፣ ማን ይቆማል?” ሲል ተናግሯል። (መዝሙር 130:​3) ይሖዋ ንስሐ የሚገቡ ኃጢአተኞች የፈጸሟቸውን ስህተቶች ከእነሱ ለማራቅ ፈቃደኛ ነው። አዎን፣ የፈጸምናቸው ስህተቶች ከእርሱ ጋር ያለንን ዝምድና እንዳያጎድፉብን ደብዛቸው እስኪጠፋ ድረስ ጠርጎ ያስወግዳቸዋል። (መዝሙር 51:​1፤ 103:​12) ንጉሥ ዳዊት አንድ ወቅት ከቤርሳቤህ ጋር ከባድ ኃጢአት ቢፈጽምም ይሖዋ እርሱን በተመለከተ ሲናገር ‘በፍጹም ልቡ ተከትሎኛል፣ በፊቴም ቅን ነገር ብቻ አድርጓል’ ለማለት ችሏል። (1 ነገሥት 14:​8) አምላክ ዳዊትን በተመለከተ እንዲህ ብሎ ሊናገር የቻለው ለምንድን ነው? ምክንያቱም ንስሐ በገባው በዳዊት ጥሩ ባሕርያት ላይ ትኩረት ስላደረገ ነው። ይሖዋ ከጉዳዩ ጋር ዝምድና ያላቸውን ነገሮች በሙሉ ካጤነ በኋላ ለአገልጋዩ ምሕረት መዘርጋቱን ለመቀጠል መረጠ።

ክርስቶስ ኢየሱስ የሌሎችን ስህተት በተመለከተ ይህ ዓይነቱን ሰፋ ያለ አመለካከት በትክክል አንጸባርቋል። (ዮሐንስ 5:​19) ኢየሱስ የሐዋርያቱን ድክመቶች ሲመለከት ምሕረት ያደርግላቸውና ችግራቸውን ይረዳላቸው ነበር። ፍጹማን ያልሆኑ ሰዎች ‘መንፈሳቸው ዝግጁ ቢሆንም እንኳ ሥጋቸው ግን ደካማ’ መሆኑን ተገንዝቧል። (ማቴዎስ 26:​41) ኢየሱስ ይህን በአእምሮው በመያዝ የደቀ መዛሙርቱን ድክመትና ጉድለት በትዕግሥትና በማስተዋል ሊይዝ ችሏል። የእርሱ ትኩረት ያረፈው በሚሠሯቸው ስህተቶች ላይ ሳይሆን በመልካም ባሕርያቶቻቸው ላይ ነበር።

አንድ ወቅት ላይ ሐዋርያቱ ከመካከላቸው ማን ታላቅ እንደሆነ በመከራከራቸው ምክንያት ኢየሱስ እርምት ከሰጣቸው በኋላ እንዲህ ሲል አክሎ ተናግሯል:- “ነገር ግን እናንተ በፈተናዎቼ ከእኔ ጋር ጸንታችሁ የኖራችሁ ናችሁ፤ አባቴ እኔን እንደ ሾመኝ እኔ ደግሞ በመንግሥቴ ከማዕዴ ትበሉና ትጠጡ ዘንድ፣ በአሥራ ሁለቱም በእስራኤል ነገድ ስትፈርዱ በዙፋኖች ትቀመጡ ዘንድ ለመንግሥት እሾማችኋለሁ።” (ሉቃስ 22:​24-30) አዎን፣ ኢየሱስ ሐዋርያቱ ብዙ ድክመቶች ቢኖሩባቸውም ለእርሱ ያሳዩትን ታማኝነትና ፍቅር አልዘነጋም። (ምሳሌ 17:​17) ኢየሱስ እነርሱ ማድረግ በሚችሉትና ወደፊት በሚያደርጉት ነገር ላይ ትምክህት ስለነበረው ከእነርሱ ጋር የመንግሥት ቃል ኪዳን አድርጓል። አዎን፣ ‘ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን እስከ መጨረሻ ወድዷቸዋል።’​—⁠ዮሐንስ 13:​1

ስለዚህ አንድ ሰው ያሉት ለየት ያሉ ባሕርያትና ድክመቶች የሚያበሳጩህ ከሆነ እንደ ይሖዋና እንደ ኢየሱስ ሁን። የአስተሳሰብ አድማስህን ሰፋ ለማድረግና ከጉዳዩ ጋር ዝምድና ያላቸውን ነገሮች በሙሉ ግምት ውስጥ ለማስገባት ሞክር። ለነገሮች ተገቢ የሆነ አመለካከት በመያዝ ወንድሞችህን መውደድና ማድነቅ ቀላል እንዲሆንልህ ያደርጋል።

ቁሳዊ ነገሮች በመስጠት

ክርስቲያኖች ደስታ ከሚያገኙባቸው ነገሮች መካከል አንዱ መስጠት ነው። ሆኖም የመስጠት መብታችንን በአንድ ነገር ላይ ብቻ ለምሳሌ ያህል በመስክ አገልግሎት በመሳተፍ ብቻ መወሰን ይኖርበታልን? (ማቴዎስ 24:​14፤ 28:​19, 20) ወይስ የሌሎችን ሥጋዊ ፍላጎትና ደኅንነት ለማካተት የአመለካከት አድማስህን ሰፋ ማድረግ ትችላለህ? እርግጥ ነው፣ በመንፈሳዊ መስጠት የላቀ ቦታ እንደሚሰጠው ሁሉም ክርስቲያኖች ይገነዘባሉ። (ዮሐንስ 6:​26, 27፤ ሥራ 1:​8) ይሁን እንጂ በመንፈሳዊ ረገድ ሰጪ መሆን አስፈላጊ የሆነውን ያህል በቁሳዊ ረገድ ሰጪ መሆንም ፈጽሞ ቸል ሊባል አይገባም።​—⁠ያዕቆብ 2:​15, 16

በራሳችን ጉባኤም ሆነ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ መንፈሳዊ ወንድሞቻችን ስለሚያስፈልጓቸው ነገሮች ስናስብ እነርሱን ለመርዳት ምን ማድረግ እንደምንችል ይበልጥ በተሟላ ሁኔታ መገንዘብ እንችላለን። ይህን ለማድረግ አቅማቸው የሚፈቅድላቸው ወንድሞች ለሌሎች በልግስና ሲያካፍሉ አንዱ የሌላውን ጉድለት እንዲሞላ ያስችላል። በዚህ መንገድ ወንድሞቻችን ሁሉ የሚያስፈልጓቸው ነገሮች ይሟላሉ። አንድ ክርስቲያን ሽማግሌ ጉዳዩን እንዲህ ሲል ገልጾታል:- “በአንደኛው የዓለም ክፍል ችግር ሲከሰት በሌላው የዓለም ክፍል የሚገኙ ወንድሞች በችግራቸው ይደርሱላቸዋል። እነርሱ የመርዳት አቅም ከሌላቸው ደግሞ በሌላ ቦታ የሚገኙ ወንድሞች እርዳታ ይሰጣሉ። በዚህ መንገድ በዓለም ዙሪያ ያሉ ወንድሞቻችን የሚያስፈልጓቸው ነገሮች ይሟሉላቸዋል። በእርግጥም ዓለም አቀፋዊው ወንድማማችነት አስደናቂ ነው።”​—⁠2 ቆሮንቶስ 8:​13-15፤ 1 ጴጥሮስ 2:​17

በምሥራቅ አውሮፓ ከተደረጉት ብሔራት አቀፍ ስብሰባዎች በአንዱ ላይ ለመገኘት ልባዊ ምኞት የነበራት አንዲት ክርስቲያን እህት በዚያ ለመገኘት ሁኔታዋ ሳይፈቅድላት ቀረ። ሆኖም በዚያ የሚኖሩ ወንድሞች ከፍተኛ የመጽሐፍ ቅዱስ እጥረት እንደሚገጥማቸው ስትሰማ በስብሰባው ላይ በተገኘ አንድ ሰው በኩል ለመጽሐፍ ቅዱስ መግዣ የሚሆን አስተዋጽዖ ላከች። በዚህ መንገድ በውጭ አገር ለሚገኙ ወንድሞቿ ያላትን በማካፈል ከመስጠት የሚገኘውን ደስታ አገኘች።​—⁠ሥራ 20:​35

ምናልባትም የአስተሳሰብ አድማስህን በማስፋት እያደገ ለሚሄደው ለዓለም አቀፋዊው መጽሐፍ ቅዱስ የማስተማር ሥራ ከበፊቱ የበለጠ አስተዋጽኦ ማበርከት ትችል ይሆናል። እንዲህ ማድረግህ ላንተም ሆነ ለሌሎች ደስታ ያስገኛል።​—⁠ዘዳግም 15:​7፤ ምሳሌ 11:​24፤ ፊልጵስዩስ 4:​14-19

ምክር በምትሰጥበት ጊዜ

ምክር ወይም ተግሣጽ እንድንሰጥ የሚያደርግ ሁኔታ በሚፈጠርበት ጊዜ አሳቢነትና ሚዛናዊ የሆነ አመለካከት መያዝ የመንፈሳዊ ወንድሞቻችንን አክብሮት እንድናገኝና በእርግጥ ውጤታማ የሆነ እርዳታ እንድንሰጥ ያግዘናል። የተወሰኑ እውነታዎችን ይዘን በችኮላ የተዛባ መደምደሚያ ላይ ለመድረስ መጣደፍ በጣም ቀላል ነው። እንዲህ ማድረጋችን ስፍር ቁጥር በሌለው ደንቦቻቸው በሌሎች ላይ ሸክም መጫን እንደሚቀናቸው በኢየሱስ ዘመን እንደነበሩት ሃይማኖታዊ መሪዎች ጠባብ አመለካከት እንዳለን አልፎ ተርፎም አስተሳሰባችን ድፍን እንደሆነ ሊያሳይ ይችላል። (ማቴዎስ 23:​2-4) በአንጻሩ ደግሞ የይሖዋን ሚዛናዊና ምሕረት የተላበሰ የጽድቅ አስተሳሰብ በማንጸባረቅ ወደ አንድ ጽንፍ ከማጋደል ከተቆጠብንና ሙሉ በሙሉ በቅዱስ ጽሑፋዊ መሠረታዊ ሥርዓቶች ላይ የተመሠረተ ጥሩ ምክር ከሰጠን ሌሎች ምክሩን ለመቀበልና የሰጠናቸውን ሐሳብ በሥራ ለማዋል በጣም ይቀላቸዋል።

ከተወሰኑ ዓመታት በፊት ከተለያዩ ጉባኤዎች የተውጣጡ ወጣት ወንድሞች አብረው በስፖርት እንቅስቃሴዎች ይሳተፉ ነበር። የሚያሳዝነው ግን በመካከላቸው የፉክክር መንፈስ አደገና ሻካራ ቃላት የመለዋወጥ ሁኔታ ተከሰተ። በአካባቢው ያሉ ሽማግሌዎች ችግሩን የፈቱት በምን መንገድ ነው? ወጣቶች መዝናናት እንደሚያስፈልጋቸው በመገንዘብ ሙሉ በሙሉ እንቅስቃሴውን ማቆም እንዳለባቸው አልነገሯቸውም። (ኤፌሶን 5:​17፤ 1 ጢሞቴዎስ 4:​8) ከዚህ ይልቅ የፉክክር መንፈስ ወዴት ሊመራ እንደሚችል በመንገር ጠንካራ ሆኖም ምክንያታዊ የሆነ ማሳሰቢያ ሰጧቸው። በተጨማሪም ኃላፊነት የሚሰማቸው በዕድሜ የበሰሉ ወንድሞች በመካከላቸው እንዲገኙ ቢያደርጉ ጥሩ እንደሚሆን ሐሳቦች ሰጧቸው። ወጣቶቹ ምክሩ የያዘውን ጥበብና ሚዛናዊነት በማድነቅ አዎንታዊ ምላሽ ሰጡ። ከዚህም በላይ ለሽማግሌዎቹ ያላቸው አክብሮትና ፍቅር ጨመረላቸው።

የአመለካከት አድማስህን ለማስፋት ጥረት አድርግ

ስለ አንድ ነገር ሆን ብለህ መሠረተ ቢስ ጥላቻ እንዲያድርብህ ላታደርግ ብትችልም አመለካከትህን ለማስፋት ግን ከልብ ጥረት ማድረግ ይጠይቃል። የአምላክን ቃል በምታጠናበት ጊዜ ይሖዋ ያለው ዓይነት አመለካከት እንዲኖርህ ባጠናኸው ነገር ላይ አሰላስል። (መዝሙር 139:​17) በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የሰፈሩት ሐሳቦችና በውስጣቸው የተካተቱት መሠረታዊ ሥርዓቶች የተሰጡበትን ምክንያት ለመረዳት ሞክር፤ እንዲሁም ይሖዋ ነገሮችን በሚያመዛዝንበት መንገድ ለማየት ሞክር። እንዲህ ማድረጋችን ዳዊት ካቀረበው ጸሎት ጋር ይስማማል:- “አቤቱ፣ መንገድህን አመልክተኝ፣ ፍለጋህንም አስተምረኝ። . . . በእውነትህ ምራኝ፣ አስተምረኝም።”​—⁠መዝሙር 25:​4, 5

ሰፋ ያለ የአመለካከት አድማስ በያዝክ መጠን ትባረካለህ። አመለካከትን ማስፋት ከሚያስገኛቸው በረከቶች አንዱ ሚዛናዊና አስተዋይ በመሆንህ የምታተርፈው መልካም ስም ነው። በተለያዩ ሁኔታዎች ስር እርዳታ በምታበረክትበት ጊዜ ይበልጥ ምክንያታዊና ማስተዋል በተሞላ መንገድ ምላሽ መስጠት ትችላለህ። ይህ በአጸፌታው አስደናቂ የሆነው ክርስቲያናዊ ወንድማማችነት ላለው አንድነትና ስምምነት አስተዋጽኦ ያበረክታል።

[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በልግስና መስጠት ሌሎችን ይጠቅማል፣ ለሰጪው ደስታ ያስገኛል እንዲሁም ሰማያዊ አባታችንን ያስደስታል