በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ፈጣሪህ ምን ዓይነት አምላክ እንደሆነ ተማር

ፈጣሪህ ምን ዓይነት አምላክ እንደሆነ ተማር

ፈጣሪህ ምን ዓይነት አምላክ እንደሆነ ተማር

“እኔ መልካምነቴን ሁሉ በፊትህ አሳልፋለሁ፤ የእግዚአብሔርንም ስም በፊትህ አውጃለሁ።”​—⁠ዘጸአት 33:​19

1. ፈጣሪ ሊከበር የሚገባው ለምንድን ነው?

መጨረሻውን የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍ የጻፈው ሐዋርያው ዮሐንስ ስለ ፈጣሪ የሚከተለውን ጥልቅ ቁም ነገር ያዘለ አዋጅ ዘግቧል:- “ጌታችንና አምላካችን ሆይ፣ አንተ ሁሉን ፈጥረሃልና ስለ ፈቃድህም ሆነዋልና ተፈጥረውማልና ክብር ውዳሴ ኃይልም ልትቀበል ይገባሃል።” (ራእይ 4:​11) ቀደም ሲል የነበረው ርዕስ እንዳብራራው የዘመናዊው ሳይንስ ግኝቶች አብዛኛውን ጊዜ በሁሉም ነገሮች ፈጣሪ ላይ እንድናምን የሚያደርጉ ተጨማሪ ምክንያቶች ያቀርባሉ።

2, 3. (ሀ) ሰዎች ስለ ፈጣሪ ምን መማር ያስፈልጋቸዋል? (ለ) ከፈጣሪ ጋር በአካል ለመተያየት ማሰብ ምክንያታዊ የማይሆነው ለምንድን ነው?

2 የፈጣሪን መኖር አምኖ መቀበሉ አስፈላጊ እንደሆነ ሁሉ ፈጣሪ ምን ዓይነት አምላክ እንደሆነ፣ ይኸውም ወደ እሱ እንድንሳብ የሚያደርጉን የራሱ ባሕርያትና መንገዶች ያሉት እውን አካል መሆኑን መማሩም የዚያኑ ያህል አስፈላጊ ነው። ቀደም ሲል ስለ እሱ የቱንም ያህል ብትማርም እሱን ይበልጥ ለማወቅ ጥረት ማድረጉ ጠቃሚ የሚሆን አይመስልህም? ይህን ማድረግ ከሰዎች ጋር እንደምናደርገው የግድ ከፈጣሪ ጋር በአካል መገናኘት አያስፈልገንም።

3 ከዋክብትን ሳይቀር ያስገኘው ይሖዋ ነው፤ ፀሐያችን ደግሞ መካከለኛ መጠን ያላት ኮከብ ናት። በአካል ወደ ፀሐይ ለመቅረብ አስበህ ታውቃለህ? በፍጹም! ብዙ ሰዎች ሌላው ቀርቶ በዓይናቸው ላለማየት ወይም ኃይለኛ ለሆነው ጨረሯ ቆዳቸውን ለረዥም ጊዜ ላለማጋለጥ ጥንቃቄ ያደርጋሉ። መካከሏ ላይ ያለው ሙቀት መጠን 15,000,000 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ (27,000,000 ዲግሪ ፈራናይት) ነው። ይህች ግለኑክሊየር (thermonuclear) ምድጃ በእያንዳንዱ ሴኮንድ ወደ አራት ሚልዮን ቶኖች የሚጠጋ መጠነቁስ ወደ ኃይል ትለውጣለች። ከዚህ ውስጥ ሙቀትና ብርሃን ሆኖ ወደ ምድር የሚደርሰው በጣም ጥቂቱ ኃይል ቢሆንም እዚህ ያለውን ሕይወት በሙሉ ጠብቆ ለማቆየት ይችላል። እነዚህ መሠረታዊ እውነታዎች ፈጣሪ ያለውን እጅግ ከፍተኛ ኃይል እንድናደንቅ ሊያደርጉን ይገባል። ኢሳይያስ ‘ፈጣሪ ስላለው ኃይል ብዛትና ስለ ችሎቱ ብርታት’ መጻፉ የተገባ ነበር።​—⁠ኢሳይያስ 40:​26

4. ሙሴ ምን ጠይቆ ነበር? ይሖዋስ ምን ምላሽ ሰጠው?

4 ይሁንና በ1513 ከዘአበ እስራኤላውያን ግብጽን ለቅቀው ከወጡ ከጥቂት ወራት በኋላ ሙሴ “እባክህ ክብርህን አሳየኝ” ብሎ ፈጣሪን እንደለመነ ታውቃለህ? (ዘጸአት 33:​18) አምላክ ፀሐይን ሳይቀር የፈጠረ በመሆኑ “ሰው አይቶኝ አይድንምና ፊቴን ማየት አይቻልህም” ብሎ ለሙሴ ለምን እንደነገረው ልንረዳ እንችላለን። ፈጣሪ ‘በሚያልፍበት’ ጊዜ ሙሴ በሲና ተራራ ላይ እንዲሸሸግ ፈቀደለት። ከዚያም ሙሴ በምሳሌያዊ አነጋገር የአምላክን ‘ጀርባ’ ማለትም የፈጣሪን ክብር ወይም መገኘቱን የሚያመለክት ብርሃን ተመልክቷል።​—⁠ዘጸአት 33:​20-23፤ ዮሐንስ 1:​18

5. ፈጣሪ የሙሴን ፍላጎት ያሟላው በምን መንገድ ነበር? ይህስ ምን ያረጋግጣል?

5 ሙሴ ፈጣሪን በይበልጥ ለማወቅ የነበረው ፍላጎት ተሳክቶለታል። ከሁኔታው ለመረዳት እንደሚቻለው አምላክ በአንድ መልአክ አማካኝነት እንደሚከተለው ብሎ በመናገር በሙሴ ፊት አልፏል:- “እግዚአብሔር፣ እግዚአብሔር መሐሪ፣ ሞገስ ያለው፣ ታጋሽም፣ ባለ ብዙ ቸርነትና እውነት፣ እስከ ሺህ ትውልድም ቸርነትን የሚጠብቅ፣ አበሳንና መተላለፍን ኃጢአትንም ይቅር የሚል፣ በደለኛውንም ከቶ የማያነጻ።” (ዘጸአት 34:​6, 7) ይህ እንደሚያሳየው ፈጣሪያችንን በይበልጥ ለማወቅ የሚያስፈልገን አንድ የሆነ አካል መመልከት ሳይሆን ስለ ማንነቱ ማለትም ስለ ባሕርያቱና ከሌሎች የተለየ ስለሚያደርገው ነገር ሙሉ ግንዛቤ ማግኘት ነው።

6. የሰውነታችን በሽታ መከላከያ ሠራዊት አስደናቂ የሆነው በምን መንገድ ነው?

6 ይህን ለማድረግ የሚያስችለን አንዱ መንገድ ደግሞ የአምላክን ባሕርያት በፈጠራቸው ነገሮች ውስጥ ሲንጸባረቁ መመልከት ነው። በሰውነትህ ውስጥ ያለውን የበሽታ መከላከያ ሠራዊት ተመልከት። ስለ ሰውነት መከላከያ ሠራዊት በተነሳ ጉዳይ ላይ ሳይንቲፊክ አሜሪካን እንዲህ ብሏል:- “ስንወለድ ጀምሮ እስክንሞት ድረስ በሽታ ለማስወገድ ወይም ለመከላከል የሚያስችል ዘወትር በተጠንቀቅ የሚጠባበቅ የበሽታ መከላከያ ሠራዊት አለን። ብዛትና ዓይነት ያላቸው ሞለኪውሎችና ሕዋሳት ከጥገኛ ተውሳኮችና በሽታ አምጪዎች . . . ይከላከሉልናል። እነዚህ መከላከያዎች ባይኖሩ ኖሮ የሰው ልጅ ሕልውና ባከተመ ነበር።” የዚህ ቅንባሮ ምንጩ ማን ነው? በዚህ መጽሔት ላይ የወጣ አንድ ርዕስ እንዲህ ይላል:- “ከሚክሮብና ከቫይረስ ወራሪዎች አካላችንን የሚከላከሉልን ብዛት ያላቸው ቀልጣፋ የሆኑ እርስ በርሳቸው ግንኙነት ያላቸው እነዚህ አስደናቂ ሕዋሳት ከተጸነሰ ከዘጠኝ ሳምንታት ገደማ በኋላ ቀዳሚ ሆነው ከሚወጡ ሕዋሳት የሚገኙ ናቸው።” አንዲት እርጉዝ ሴት በማደግ ላይ ላለው ሽል ጥቂት በሽታን የሚከላከሉ ሕዋሳት ታስተላልፍለታለች። ከጊዜ በኋላ በጡቷ ወተት አማካኝነት በሽታን የሚከላከሉ ሕዋሳትና ጠቃሚ የሆኑ ኬሚካሎች ለሕፃን ልጅዋ ታስተላልፋለች።

7. ስለ ሰውነታችን በሽታ መከላከያ ሠራዊት ምን ብለን ልናስብ እንችላለን? ወደ ምንስ መደምደሚያ ያደርሰናል?

7 በሰውነትህ ውስጥ የሚገኘው የበሽታ ተከላካይ ሠራዊት የዘመኑ መድኃኒት ሊሰጥ ከሚችለው ከማንኛውም ነገር ይበልጣል ብለህ ለመደምደም የሚያስችልህ በቂ ምክንያት አለህ። ከዚህ የተነሣ ራስህን እንዲህ ብለህ ጠይቅ:- ‘ይህ ሁኔታ ይህን የመከላከያ ሠራዊት ስለ ፈጠረውና ስለሰጠን ፈጣሪ ምን ያመለክታል?’ ‘ፅንስ ከተጸነሰ ከዘጠኝ ሳምንታት ገደማ በኋላ ብቅ የሚለው’ እና አዲስ የሚወለደውን ልጅ ከበሽታ የሚከላከለው ይህ ቅንባሮ ጥበብንና አርቆ አሳቢነትን እንደሚያንጸባርቅ የተረጋገጠ ነው። ከዚህ ቅንባሮ ስለ ፈጣሪ ይበልጥ ልናስተውለው የምንችለው ነገር ይኖር ይሆን? ሕይወታቸውን የችግረኞችን ጤንነት በመንከባከብ ያሳለፉ እንደ አልበርት ሽዋይትዘር ስለመሳሰሉ ሰዎች ምን ይሰማናል? አብዛኛውን ጊዜ እነዚህን ርኅሩኅ በጎ አድራጊዎች በማወደስ እንናገራለን። ታዲያ ሀብታም ድሃ ብሎ ሳያበላልጥ ለሁሉም ሰዎች በእኩልነት የበሽታ መከላከያ ሠራዊት ስለሰጠው ፈጣሪ ምን ለማለት እንችላለን? አፍቃሪ፣ የማያዳላ፣ ርኅሩኅና ፍትሕ የማያዛባ አምላክ እንደሆነ ግልጽ ነው። ታዲያ ይህ ሙሴ ስለ ፈጣሪ ከሰማው መግለጫ ጋር የሚስማማ አይደለም?

ማንነቱን ያሳውቃል

8. ይሖዋ ራሱን የሚገልጥልን በየትኛው ልዩ መንገድ ነው?

8 ይሁንና ፈጣሪያችንን በይበልጥ እንድናውቅ የሚያስችለን ሌላም መንገድ አለ፤ ይህም በመጽሐፍ ቅዱስ አማካኝነት ነው። ይህ በተለይ አስፈላጊ የሚሆነው ሳይንስም ሆነ ጽንፈ ዓለም ሊገልጹልን የማይችሏቸው ነገሮች በመኖራቸውና መጽሐፍ ቅዱስ ይበልጥ ግልጽ የሚያደርጋቸው ነገሮች በመኖራቸው ነው። ለመጀመሪያው ምክንያት ምሳሌ የሚሆነን የፈጣሪ የግል ስም ነው። የፈጣሪን ስምና ስሙ የሚወክላቸውን ነገሮች የሚገልጽልን መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ ነው። በዕብራይስጥ ቋንቋ በተዘጋጁት የመጽሐፍ ቅዱስ የእጅ ግልባጭ ቅጂዎች ላይ በአብዛኛው በእንግሊዝኛ ጀሆቫ ተብለው በሚነበቡትና YHWH [የሐወሐ] ወይም JHVH [ጀሐቨሐ] ተብለው በሚተረጎሙት አራት ተናባቢ ፊደላት የተወከለው የአምላክ ስም 7,000 ጊዜ ያህል ተጠቅሶ ይገኛል።​—⁠ዘጸአት 3:​15፤ 6:​3

9. የፈጣሪ የግል ስም ትርጉም ምንድን ነው? ከዚህስ በመነሳት ምን ብለን ልንደመድም እንችላለን?

9 ፈጣሪን በተሻለ መንገድ ለማወቅ ከተፈለገ “በራሱ የተገኘ” ምስጢራዊ አካል ወይም “እኔ ነኝ” ብቻ ተብሎ የሚገለጽ ድብቅ አምላክ አለመሆኑን መረዳት ይኖርብናል። የግል ስሙ ይህን ያሳያል። “መሆን” ወይም “ይሆናል” የሚል ትርጉም ካለው የዕብራይስጥ ግሥ የተገኘ ነው። * (ከዘፍጥረት 27:​29፤ መክብብ 11:​3 ጋር አወዳድር።) የአምላክ ስም “እንዲሆን የሚያደርግ” የሚል ትርጉም ያለው ከመሆኑም በላይ ዓላማ አውጪና አስፈጻሚ መሆኑንም ጎላ አድርጎ ይገልጻል። ስሙን በማወቅና በመጠቀም የሰጠውን ተስፋ የሚፈጽምና ዓላማውንም ሙሉ በሙሉ እውን የሚያደርግ መሆኑን በተሻለ መንገድ ለመረዳት እንችላለን።

10. ከዘፍጥረት ዘገባ ምን አስፈላጊ ማስተዋል ማግኘት እንችላለን?

10 መጽሐፍ ቅዱስ ስለ አምላክ ዓላማዎችና ባሕርያት እውቀት የምናገኝበት ምንጭ ነው። የዘፍጥረት ዘገባ የሰው ልጅ ከአምላክ ጋር ሰላማዊ ግንኙነት እንደነበረው እንዲሁም ረዥምና ትርጉም ያለው ሕይወት የማግኘት ተስፋ እንደነበረው ይገልጻል። (ዘፍጥረት 1:​28፤ 2:​7-9) ስሙ ከሚወክላቸው ነገሮች ጋር በሚስማማ መንገድ የሰው ዘር ከረዥም ጊዜ ጀምሮ የተጋፈጣቸውን ሥቃይና ኃዘን ይሖዋ እንደሚያስቆም እርግጠኞች ልንሆን እንችላለን። ዓላማዎቹን የሚያስፈጽም ስለመሆኑ የሚከተለውን እናነባለን:- “ግዑዙ ፍጥረት ለከንቱነት ተገዝቶአልና፣ ለከንቱነት የተገዛው በፈጣሪ ፈቃድ እንጂ በራሱ ፍላጎት አይደለም፤ ፈጣሪ ይህን ሲያደርግ ፍጥረት . . . ከእግዚአብሔር ልጆች ክብራማ ነፃነት ተቋዳሽ የመሆን ተስፋ ሰጥቶታል።”​—⁠ሮሜ 8:​20, 21 ዘ ኒው ቴስታመንት ሌተርስ በጄ ደብልዩ ሲ ዋንድ

11. የመጽሐፍ ቅዱስን ዘገባዎች መመርመር ያለብን ለምንድን ነው? ከእነዚህ ዘገባዎች ውስጥ አንደኛው የትኛው ነው?

11 በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ ከጥንቱ የእስራኤል ሕዝብ ጋር በነበረው ግንኙነት ስላደረገው ነገርም ሆነ ስላሳየው ስሜት የሚገልጽ በመሆኑ ስለ ፈጣሪያችን ይበልጥ እንድናውቅ ሊረዳን ይችላል። የኤልሳዕንና የእስራኤላውያን ጠላቶች የነበሩት የሶሪያውያን ሠራዊት አለቃ የንዕማንን ምሳሌ ተመልከት። በ2 ነገሥት ምዕራፍ 5 ላይ ተመዝግቦ በሚገኘው በዚህ ታሪክ ላይ በግዞት የተወሰደች አንዲት እስራኤላዊት ልጃገረድ ንዕማን ያለበት ሥጋ ደዌ እስራኤል በሚገኘው በኤልሳዕ እርዳታ ሊፈወስ እንደሚችል እንደተናገረች ታነብባለህ። ንዕማን፣ ኤልሳዕ እጁን በማወራጨት ምስጢራዊ የሆነ የፈውስ ሥርዓት ያከናውናል ብሎ ጠብቆ ነበር። ኤልሳዕ ግን ሶሪያዊው በዮርዳኖስ ወንዝ እንዲታጠብ ነገረው። ንዕማን በበታቾቹ ግፊት የተባለውን ባደረገ ጊዜ ተፈወሰ። ንዕማን ውድ የሆኑ ስጦታዎችን ሊሰጠው ቢፈልግም ኤልሳዕ ለመቀበል ፈቃደኛ አልሆነም። በኋላ ላይ ግን አንድ የሥራ ባልደረባው በድብቅ ወደ ንዕማን ሄዶ በውሸት አንዳንድ ውድ ነገሮችን ወሰደ። እምነት አጉዳይነቱ በሥጋ ደዌ ለመያዝ ዳርጎታል። ይህ ትምህርት የምናገኝበት አስደናቂ ታሪክ ነው።

12. ከኤልሳዕና ከንዕማን ታሪክ ፈጣሪያችንን በተመለከተ ምን መገንዘብ እንችላለን?

12 በዛሬው ጊዜ በሚገኙ በብዙ ባህሎች ዘንድ የተለመደ ነገር ከሆነው በተቃራኒ የጽንፈ ዓለሙ ታላቅ ፈጣሪ ለአንዲት ትንሽ ልጃገረድ ሞገስ ለማሳየት ታላቅነቱ እንደማያግደው ዘገባው ማራኪ በሆነ መንገድ ያሳያል። በተጨማሪም ፈጣሪ ለአንድ ዘር ወይም ብሔር እንደማያዳላ ያረጋግጣል። (ሥራ 10:​34, 35) ደስ የሚለው ነገር ጥንትም ሆነ ዛሬ ያሉ አንዳንድ “ፈዋሾች” እንደሚያደርጉት የማጭበርበሪያ ዘዴ ተጠቅሞ እንዲፈወስ ባለማድረጉ ፈጣሪ አስደናቂ ጥበቡን አሳይቷል። ሥጋ ደዌን እንዴት መፈወስ እንደሚቻል ያውቃል። በተጨማሪም የማጭበርበር ድርጊት እንዲስፋፋ ባለመፍቀድ አስተዋይነቱንና ፍትሑን አሳይቷል። በዚህም ጊዜ ቢሆን ይህ ሙሴ ስለ ይሖዋ ባሕርያት ከሰማው ነገር ጋር የሚስማማ አይደለም? ይህ አጭር የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ ስለ ፈጣሪያችን ብዙ ነገር አሳውቆናል!​—⁠መዝሙር 33:​5፤ 37:​28

13. ከመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎች ጠቃሚ የሆኑ ትምህርቶች እንዴት ልናገኝ እንደምንችል በምሳሌ አስረዳ።

13 የእስራኤላውያንን ምስጋና ቢስነት ስለሚያሳዩ ድርጊቶችና አምላክ ስለ ወሰደው እርምጃ የሚናገሩ ሌሎች ዘገባዎች ይሖዋ ለፍጡሮቹ የሚያስብ መሆኑን ያረጋግጣሉ። እስራኤላውያን አምላክን በተደጋጋሚ እንደፈተኑትና እንዳሳዘኑት መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። (መዝሙር 78:​40, 41) በመሆኑም ፈጣሪ ስሜት አልባ ወይም ሰዎች ለሚያደርጓቸው ነገሮች ደንታ ቢስ አይደለም። በተጨማሪም ታዋቂ ስለነበሩ ግለሰቦች ከሚናገሩ ትረካዎች ብዙ የምንማራቸው ነገሮች አሉ። ዳዊት የእስራኤል ንጉሥ እንዲሆን በተመረጠበት ጊዜ አምላክ ለሳሙኤል “ሰው ውጫዊ መልክን ያያል፣ እኔ ግን ውስጣዊ ልብን አያለሁ” ብሎት ነበር። (1 ሳሙኤል 16:​71980 ትርጉም) አዎን፣ ፈጣሪ የሚያየው የውስጥ ማንነታችንን እንጂ ውጪያዊ ቁመናችንን አይደለም። ይህ ምንኛ የሚያረካ ነው!

14. የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎችን ስናነብ ምን ጠቃሚ ነገር ልናደርግ እንችላለን?

14 ሠላሳ ዘጠኙ የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፎች ከኢየሱስ ዘመን በፊት የተጻፉ ቢሆንም ልናነባቸው ይገባል። እንዲህ የምናደርገው እንዲያው የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎችን ወይም ታሪኮችን ለማወቅ ስንል ብቻ አይደለም። የፈጣሪያችንን ማንነት በእርግጥ ለማወቅ የምንፈልግ ከሆነ በእነዚህ ዘገባዎች ላይ ልናሰላስል ይገባል፤ ምናልባትም ‘ይህ ታሪክ ስለ ባሕርያቱ ምን የሚገልጸው ነገር አለ? እዚህ ላይ ግልጽ ሆነው የሚታዩት ባሕርያት የትኞቹ ናቸው?’ እያልን ልናሰላስል እንችላለን። * እንዲህ ማድረጉ ሌላው ቀርቶ የአምላክን መኖር የሚጠራጠሩ ሰዎች ጭምር መጽሐፍ ቅዱስ መለኮታዊ ምንጭ ያለው መሆኑን እንዲገነዘቡ ሊረዳቸውና አፍቃሪ የሆነውን የመጽሐፉን ደራሲ በይበልጥ ለማወቅ የሚችሉበት መሠረት ሊጥል ይችላል።

ታላቁ አስተማሪ ፈጣሪን እንድናውቅ ይረዳናል

15. የኢየሱስ ድርጊቶችና ትምህርቶች ስለ ፈጣሪ ለማወቅ ሊረዱ የሚገባው ለምንድን ነው?

15 የፈጣሪን መኖር የሚጠራጠሩ ወይም ስለ አምላክ ድንግዝግዝ ያለ አመለካከት ያላቸው ሰዎች ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ብዙም እንደማያውቁ ግልጽ ነው። ሙሴ የኖረው ከማቴዎስ በፊት ይሁን በኋላ የማያውቁ፣ ኢየሱስ ስላደረጋቸውም ሆነ ስላስተማራቸው ነገሮች ምንም የማያውቁ ሰዎች አጋጥመውህ ይሆናል። ይህ ጉዳይ በጣም አሳዛኝ ነው፤ ምክንያቱም አንድ ሰው ከታላቁ አስተማሪ ከኢየሱስ ስለ ፈጣሪ ብዙ ለመማር ይችላል። ከአምላክ ጋር የቅርብ ግንኙነት ስለነበረው ፈጣሪያችን ምን ዓይነት እንደሆነ ሊገልጽልን ይችላል። (ዮሐንስ 1:​18፤ 2 ቆሮንቶስ 4:​6፤ ዕብራውያን 1:​3) እሱም ይህንን አድርጓል። እንዲያውም በአንድ ወቅት “እኔን ያየ አብን አይቶአል” ብሎ ተናግሯል።​—⁠ዮሐንስ 14:​9

16. ኢየሱስ ከአንዲት ሳምራዊት ሴት ጋር ያደረገው ውይይት ምን ያሳያል?

16 ይህን ምሳሌ ተመልከት። ኢየሱስ ረዥም መንገድ በመጓዙ ደክሞት የነበረ ቢሆንም በሲካር አቅራቢያ ያገኛትን አንዲት ሳምራዊት ሴት አነጋግሮ ነበር። ‘አብን በመንፈስና በእውነት ማምለክ’ ያለውን አስፈላጊነት መሠረት ያደረገ ጥልቅ የእውነት እውቀት አካፍሏታል። በዘመኑ የነበሩ አይሁዶች የሰማርያ ሰዎችን ያገልሏቸው ነበር። ከዚህ በተቃራኒ ግን ኢየሱስ፣ ይሖዋ በሁሉም ብሔራት ውስጥ የሚገኙ ቅን ልብ ያላቸውን ወንዶችና ሴቶች ለመቀበል ያለውን ፈቃድ ያንጸባረቀ ሲሆን ይህን ደግሞ ቀደም ሲል በኤልሳዕና በንዕማን ሁኔታ ላይ ለመመልከት ችለናል። በዛሬው ዓለም ላይ ተስፋፍቶ የሚገኘውን ጠባብ አስተሳሰብ የሚንጸባረቅበት ሃይማኖታዊ ጥላቻን ይሖዋ እንደማይደግፍ ማረጋገጫ ሊሆነን ይገባል። በተጨማሪም ኢየሱስ በወቅቱ ባሏ ካልሆነ ሰው ጋር ትኖር የነበረችን ሴት ለማስተማር ፈቃደኛ እንደነበረ ለመመልከት እንችላለን። ኢየሱስ በሴትየዋ ላይ ከመፍረድ ይልቅ ሊጠቅማት በሚችል መንገድ በክብር አነጋግሯታል። ከዚያ በኋላ ሌሎች የሰማርያ ሰዎችም ኢየሱስን ካዳመጡ በኋላ እንዲህ ሲሉ ደመደሙ:- “እርሱም በእውነት ክርስቶስ የዓለም መድኃኒት እንደ ሆነ እናውቃለን።”​—⁠ዮሐንስ 4:​2-30, 39-42፤ 1 ነገሥት 8:​41-43፤ ማቴዎስ 9:​10-13

17. ስለ አልዓዛር ትንሣኤ የሚናገረው ታሪክ ምን ያስገነዝባል?

17 ራሳችንን ከኢየሱስ ድርጊቶችና ትምህርቶች ጋር በደንብ በማስተዋወቅ ስለ ፈጣሪ ብዙ ለመማር እንደምንችል የሚያሳይ ሌላ ምሳሌ እንመልከት። የኢየሱስ ወዳጅ የነበረው አልዓዛር በሞተበት ጊዜ ስለነበረው ሁኔታ አስብ። ቀደም ሲል ኢየሱስ ሙታንን ወደ ሕይወት የመመለስ ኃይል እንዳለው አሳይቶ ነበር። (ሉቃስ 7:​11-17፤ 8:​40-56) ይሁንና የአልዓዛር እህት ማርያም ስታለቅስ ሲመለከታት ምን ተሰማው? ኢየሱስ “በመንፈሱ አዘነ በራሱም ታወከ።” ግድየለሽ ወይም ቸልተኛ አልነበረም፤ ‘እንባውን አፍስሷል።’ (ዮሐንስ 11:​33-35) ይህ ደግሞ እንዲያው ለታይታ ያደረገው ነገር አልነበረም። ኢየሱስ በጎ ለማድረግ በመገፋፋት አልዓዛርን ከሞት አስነስቶታል። ይህ አጋጣሚ ሐዋርያቱ የፈጣሪን ስሜቶችና ድርጊቶች እንዲያደንቁ እንዴት እንደረዳቸው ለመገመት ትችላለህ። ይህ የፈጣሪን ባሕርያትና መንገዶች እንድናስተውል ሊረዳን ይገባል።

18. ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን ስለ ማጥናት እንዴት ሊሰማቸው ይገባል?

18 መጽሐፍ ቅዱስን በማጥናታችንና ስለ ፈጣሪ ይበልጥ ለማወቅ በመማራችን የምናፍርበት ምንም ምክንያት የለም። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲያው ጊዜ ያለፈበት መጽሐፍ አይደለም። ዮሐንስ መጽሐፍ ቅዱስን በደንብ በማጥናት የኢየሱስ የቅርብ ወዳጅ ለመሆን የበቃ ሰው ነበር። ከጊዜ በኋላ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “የእግዚአብሔርም ልጅ እንደ መጣ፣ እውነተኛም የሆነውን እናውቅ ዘንድ ልቡናን [“ማስተዋልን፣” NW] እንደ ሰጠን እናውቃለን፤ እውነተኛም በሆነው በእርሱ አለን፣ እርሱም ልጁ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። እርሱ እውነተኛ አምላክና የዘላለም ሕይወት ነው።” (1 ዮሐንስ 5:​20) “እውነተኛ” የሆነውን ፈጣሪ ለማወቅ ‘ማስተዋላችንን’ መጠቀማችን ወደ ‘ዘላለም ሕይወት’ ሊመራን እንደሚችል ተመልከት።

ሌሎች ስለ እሱ እንዲማሩ እንዴት ልትረዳቸው ትችላለህ?

19. ስለ አምላክ ሕልውና የሚጠራጠሩ ሰዎችን ለመርዳት ምን ተደርጓል?

19 የሚያስብልን ርኅሩኅ ፈጣሪ መኖሩን ለአንዳንድ ሰዎች ለማሳመንና ምን ዓይነት አምላክ መሆኑን እንዲገነዘቡ ለመርዳት ብዙ መድከም ያስፈልጋል። ቀደም ብሎ እንደተጠቀሰው ስለ ፈጣሪ መኖር የሚጠራጠሩ ወይም ስለ ፈጣሪ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከሚገኘው አመለካከት ጋር የሚቃረን አመለካከት ያላቸው በብዙ ሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች አሉ። ታዲያ እንዴት ልትረዳቸው ትችላለህ? በ1998/99 በተደረጉት የይሖዋ ምሥክሮች የአውራጃና ብሔራት አቀፍ ስብሰባዎች ላይ ስለ አንተ የሚያስብ ፈጣሪ ይኖር ይሆን? የተባለ ውጤታማ የሆነ አዲስ መጽሐፍ በብዙ ቋንቋዎች መዘጋጀቱ ተገልጾ ነበር።

20, 21. (ሀ) ፈጣሪ የተባለውን መጽሐፍ ውጤታማ በሆነ መንገድ እንዴት ልንጠቀምበት እንችላለን? (ለ) ይህ መጽሐፍ ውጤታማ መሆኑን የሚያረጋግጡ ተሞክሮዎችን ተናገር።

20 በፈጣሪያችን ላይ ያለህን እምነት እንዲሁም ለባሕርያቱና ለመንገዶቹ ያለህን አድናቆት የሚያዳብርልህ መጽሐፍ ነው። እርግጠኛ ሆነን የምንናገረው ለምንድን ነው? ስለ አንተ የሚያስብ ፈጣሪ ይኖር ይሆን? (እንግሊዝኛ) የተባለው መጽሐፍ የተዘጋጀው በተለይ እነዚህን ግቦች እንዲያሟላ ታስቦ ስለሆነ ነው። “ሕይወትህ ትርጉም ያለው ሊሆን የሚችለው እንዴት ነው?” የሚለው ጭብጥ በመጽሐፉ ውስጥ ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ የሚተኮርበት ነው። ሌላው ቀርቶ ላቅ ያለ ትምህርት ያላቸውን ሰዎች አእምሮ ሊነካ የሚችል ይዘት ያለው ነው። ቢሆንም በሁላችንም ውስጥ ያለውን ምኞትና ጉጉት የሚነካ አቀራረብ ያለው ነው። የፈጣሪን መኖር የሚጠራጠሩ አንባቢዎችን የሚያስደንቅና የሚያሳምን ሐሳብ ይገኝበታል። መጽሐፉ አንባቢዎቹ በፈጣሪ ያምናሉ ከሚል ተነስቶ ሐሳብ የሚሰጥ አይደለም። የአምላክን መኖር የሚጠራጠሩ ሰዎች በመጽሐፉ ውስጥ በተጠቀሱ የቅርብ ጊዜ ሳይንሳዊ ግኝቶችና ጽንሰ ሐሳቦች ይመሰጣሉ። እነዚህ ማስረጃዎች በአምላክ የሚያምኑ ሰዎችንም እምነት ይበልጥ የሚያጠናክሩ ናቸው።

21 የመጽሐፉ የተወሰነ ክፍል የአምላክን ባሕርያት የተለያዩ ገጽታዎች በሚያጎላ መንገድ የመጽሐፍ ቅዱስን ታሪክ አጠር አድርጎ የሚያቀርብና አንባቢዎች በተሻለ መንገድ አምላክን ለማወቅ እንዲችሉ የሚረዳ መሆኑን ይህን አዲስ መጽሐፍ በማጥናት ለመመልከት ይቻላል። መጽሐፉን ያነበቡ በርካታ ሰዎች ይህን እውነት ሆኖ እንዳገኙት ተናግረዋል። (በገጽ 25-6 ላይ የሚገኘውን የሚቀጥለውን ርዕስ ተመልከት።) ራስህን ከመጽሐፉ ጋር በደንብ በማስተዋወቅና ሌሎች ስለ ፈጣሪ የተሻለ እንዲያውቁ ለመርዳት በመጽሐፉ በመጠቀም አንተም ይህን እውነት ሆኖ እንድታገኘው ምኞታችን ነው።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.9 ኢየሱሳዊው ምሁር ኤም ጄ ግርንትሃነር ዘ ካተሊክ ቢብሊካል ኳርተርሊ ዋና አዘጋጅ በነበሩበት ወቅት ከዚህ ጋር ተመሳሳይ ለሆነው ግሥ የሰጡትን ማብራሪያ በመጠቀም ይህ ግሥ “በፍጹም ድብቅ ሕልውናን የሚያመለክት ሐሳብ የለውም፤ ከዚህ ይልቅ ተጨባጭ በሆነ መንገድ ራሱን የሚገልጽ መሆኑን የሚያሳይ ነው” ብለው ነበር።

^ አን.14 ወላጆች ለልጆቻቸው የመጽሐፍ ቅዱስን ታሪኮች በሚነግሯቸው ጊዜ እነዚህን የመሳሰሉ ጥያቄዎች በመጠቀም ልጆቻቸውን ሊረዷቸው ይችላሉ። በዚህ መንገድ ልጆች ከአምላክ ጋር በሚገባ ሊተዋወቁና በቃሉም ላይ ማሰላሰልን ሊማሩ ይችላሉ።

አስተውለሃል?

◻ ሙሴ በሲና ተራራ ላይ ይሖዋን በደንብ ለማወቅ የቻለው እንዴት ነበር?

◻ መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት አምላክ ምን እንደሚመስል ለማወቅ የሚረዳ ቁልፍ የሆነው ለምንድን ነው?

◻ ወደ ፈጣሪያችን የበለጠ ለመቅረብ መጽሐፍ ቅዱስን በምናነብበት ጊዜ ምን ልናደርግ እንችላለን?

ፈጣሪ የተባለውን መጽሐፍ በምን መልኩ ልትጠቀምበት አቅደሃል?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የሰውነታችን በሽታ መከላከያ ሠራዊት ስለ ፈጣሪያችን ምን ያስገነዝባል?

[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ቴትራግራማተን (በዕብራይስጥ የተጻፈ የአምላክ ስም) ጎላ ብሎ የሚታይበት የሙት ባሕር ጥቅሎች አንድ ክፍል

[ምንጭ]

Courtesy of the Shrine of the Book, Israel Museum, Jerusalem

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኢየሱስ በማርያም ሐዘን የተነሳ ከተሰማው ስሜትና ካደረገው ነገር ምን ልንማር እንችላለን?