በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ፈጣሪ ሕይወትህን ትርጉም ያለው ሊያደርግልህ ይችላል

ፈጣሪ ሕይወትህን ትርጉም ያለው ሊያደርግልህ ይችላል

ፈጣሪ ሕይወትህን ትርጉም ያለው ሊያደርግልህ ይችላል

“እርሱ ብሎአልና፣ ሆኑም፤ እርሱም አዝዞአልና፣ ተፈጠሩም፤ የእግዚአብሔርን ስም ያመስግኑት።”​—⁠መዝሙር 148:​5

1, 2. (ሀ) የትኛውን ጥያቄ መመርመር አለብን? (ለ) በኢሳይያስ ጥያቄ ውስጥ ፍጥረት የተካተተው እንዴት ነው?

“አላወቅህምን?ይህ ጥያቄ ብዙዎች ‘ምኑን?’ ብለው እንዲመልሱ የሚያደርግ መሪ ጥያቄ ብቻ ሊመስል ይችላል። ሆኖም በቁም ነገር ሊታይ የሚገባው ጥያቄ ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘውን የኢሳይያስ መጽሐፍ 40ኛ ምዕራፍ በመመርመር ለዚህ ጥያቄ የተሰጠውን ምላሽ በተሻለ ሁኔታ መገንዘብ እንችላለን። ኢሳይያስ የሚባል አንድ የጥንት ዕብራዊ የጻፈው በመሆኑ ጥያቄው ብዙ ዘመናት ያስቆጠረ ነው። ሆኖም ዛሬም የሚነሣ ጥያቄ ሲሆን ለሕይወትህ ትርጉም ከሚሰጠው ጉዳይ ጋር በቀጥታ የሚዛመድ ነው።

2 በኢሳይያስ 40:​28 ላይ የተመዘገበው ይህ ጥያቄ በጣም አስፈላጊ በመሆኑ ትኩረታችን የሚያሻው ነው:- “አላወቅህምን? አልሰማህምን? እግዚአብሔር የዘላለም አምላክ፣ የምድርም ዳርቻ ፈጣሪ ነው።” (በሰያፍ የጻፍነው እኛ ነን።) ስለዚህ “አላወቅህምን?” ተብሎ የተጠየቀው ስለ ምድር ፈጣሪ ሲሆን በጥቅሱ ዙሪያ ያለው ሐሳብ ደግሞ ከምድርም ሌላ የሚጨምረው ነገር እንዳለ ያሳያል። ከሁለት ቁጥሮች በፊት ኢሳይያስ ስለ ከዋክብት ጽፎ ነበር:- “ዓይናችሁን ወደ ላይ አንሥታችሁ ተመልከቱ፤ እነዚህን የፈጠረ ማን ነው? ሠራዊታቸውን በቁጥር የሚያወጣ እርሱ ነው፣ . . . በኃይሉ ብዛትና በችሎቱ ብርታት አንድስ እንኳ አይታጣውም።”

3. ስለ ፈጣሪ ብዙ የምታውቅ ብትሆንም የበለጠ ለማወቅ መጣር ያለብህ ለምንድን ነው?

3 አዎን፣ “አላወቅህምን?” የሚለው ጥያቄ እኛ ያለንበትን ጽንፈ ዓለም የፈጠረውን አካል የሚመለከት ነው። አንተ በግልህ ይሖዋ አምላክ ‘የምድርን ዳርቻዎች እንደፈጠረ’ ታምን ይሆናል። በተጨማሪም ስለ ባሕርያቱና ስለ መንገዶቹ ብዙ ታውቅ ይሆናል። ይሁን እንጂ ፈጣሪ እስከ መኖሩም የሚጠራጠርና ምን ዓይነት እንደሆነ በትክክል የማያውቅ ሰው ቢያጋጥምህስ? ይህ አዲስ ነገር ሊሆንብህ አይገባም፤ ምክንያቱም ፈጣሪን የማያውቁ ወይም በፈጣሪ የማያምኑ በሚልዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች አሉ።​—⁠መዝሙር 14:​1፤ 53:​1

4. (ሀ) በዚህ ጊዜ ስለ ፈጣሪ መመርመር ተገቢ የሆነው ለምንድን ነው? (ለ) ሳይንስ ለየትኞቹ ጥያቄዎች መልስ የለውም?

4 ትምህርት ቤቶች ጽንፈ ዓለምና ሕይወት ከየት እንደተገኙ ለሚነሱ ጥያቄዎች ሳይንስ መልስ ይሰጣል (ወይም ወደፊት መልስ ያገኛል) ብለው የሚያምኑ ተጠራጣሪዎች መፍለቂያ ሆነዋል። ዚ ኦሪጂን ኦቭ ላይፍ (በመጀመሪያ በታተመበት በፈረንሳይኛ ርዕሱ:- ኦ ኦሪዢን ደ ላ ቪ) በተባለው መጽሐፍ ላይ አዣን እና ለኔ የተባሉ ደራሲያን እንዲህ ብለዋል:- “በሃያ አንደኛው መቶ ዘመን መጀመሪያ ላይም ሕይወት ከየት ተገኘ የሚለው ክርክር አላበቃም። ለመፍታት አስቸጋሪ የሆነው ይህ ችግር በማንኛውም መስክ፣ ከግዙፉ ጠፈር አንስቶ እልቆቢስ እስከሆነው ቁስ አካል ድረስ ምርምር ማካሄድን የሚጠይቅ ነው።” ሆኖም ግን “ጥያቄው ሕያው እንደሆነ ይቀጥላል” የሚለው የመጨረሻው ምዕራፍ እንዲህ ይላል:- “ሕይወት በምድር ላይ እንዴት ተገኘ? ለሚለው ጥያቄ አንዳንድ ሳይንሳዊ መልሶችን አግኝተናል፤ ሆኖም ሕይወት ለምን ተገኘ? ሕይወት ዓላማ አለው? እነዚህን ጥያቄዎች ሳይንስ ሊመልስ አይችልም። ሳይንስ የሚያተኩረው ነገሮች ‘እንዴት’ ተገኙ በሚለው ላይ ብቻ ነው። ‘እንዴት’ እና ‘ለምን’ የሚሉት ደግሞ ፍጹም የተለያዩ ጥያቄዎች ናቸው። . . . ‘ለምን’ ለሚለው ጥያቄ ፍልስፍና፣ ሃይማኖትና ከሁሉም በላይ ደግሞ እያንዳንዳችን መልስ ማግኘት ይኖርብናል።”

መልሶችንና የሕይወትን ትርጉም ማግኘት

5. ስለ ፈጣሪ ይበልጥ በመማር ሊጠቀሙ የሚችሉት በተለይ ምን ዓይነት ሰዎች ናቸው?

5 አዎን፣ ሕይወት ለምን እንደተገኘ በተለይም ደግሞ እዚህ ያለነው ለምን እንደሆነ ለማወቅ እንፈልጋለን። ከዚህም በላይ ፈጣሪ አለ ወደሚል መደምደሚያ ስላልደረሱና ስለ መንገዶቹ እጅግም ስለማያውቁ ሰዎች ልናስብ ይገባል። ወይም ስለ አምላክ መጽሐፍ ቅዱስ ከሚያስተምረው ፈጽሞ የተለየ ጽንሰ ሐሳብ ስላላቸው ሰዎች አስቡ። በቢልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በሩቅ ምሥራቅ አገሮች ወይም አብዛኞቹ ሰዎች አምላክ ማራኪ የሆኑ የራሱ ባሕርያትና ሕልውና ያለው አካል እንደሆነ በማያውቁባቸው አገሮች ያደጉ ናቸው። እንደነዚህ ላሉት ሰዎች “አምላክ” የሚለው ቃል በውል የማይታወቅ አንድ ረቂቅ ኃይል ከማመልከት የበለጠ ትርጉም የለውም። ‘ፈጣሪን ወይም መንገዶቹን አላወቁም።’ እነዚህ ወይም ተመሳሳይ አመለካከት ያላቸው በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ፈጣሪ እንዳለ ቢያምኑ ዘላለማዊ የሆኑ ተስፋዎችን ጨምሮ እንዴት ያሉ ጥቅሞችን ሊያገኙ እንደሚችሉ አስቡ! በተጨማሪም ብዙዎች የሚመኙትን ብርቅ የሆነ ነገር ይኸውም በሕይወታቸው እውነተኛ ትርጉም፣ ዓላማና የአእምሮ ሰላም ሊያገኙ ይችላሉ።

6. በዛሬው ጊዜ የሚገኙ የብዙዎች ሕይወት ከፖል ጎገ እና ከቀለም ቅብ ሥዕሎቹ ውስጥ ከአንደኛው ጋር የሚመሳሰለው እንዴት ነው?

6 ነገሩን በምሳሌ ለማስረዳት:- በ1891 ፖል ጎገ የተባለው ፈረንሳዊ ሠዓሊ የሚያረካ ኑሮ ለማግኘት ሲል የገነት አምሳያ ወደ ሆነችው ወደ ፈረንሳይ ፖሊኔዥያ ይሄዳል። ይሁንና ያሳለፈው መጥፎ አኗኗር በራሱና በሌሎች ላይ በሽታ አስከተለ። መሞቻው እንደደረሰ በተሰማው ጊዜ በትልቅ ሸራ ላይ አንድ ሥዕል ሣለ። ‘ሕይወት ትልቅ ምሥጢር እንደሆነ የሚተረጉም’ ይመስላል። ጎገ ለዚህ የቀለም ቅብ ሥዕል የሰጠው ስያሜ ምን እንደሆነ ታውቃለህ? “ከየት መጣን? ምንድን ነን? ወዴትስ እንሄዳለን?” የሚል ነበር። ሌሎች ሰዎች ተመሳሳይ ጥያቄዎች ሲጠይቁ ሰምተህ ይሆናል። በዛሬው ጊዜ እነዚህን ጥያቄዎች የሚጠይቁ ሰዎች በርካታ ናቸው። አጥጋቢ መልስ ሳያገኙ ሲቀሩ ግን ሕይወታቸው ትርጉም ስለሚያጣ መሄጃ ይጠፋቸዋል። ሕይወታቸው ከእንስሳ ሕይወት በምንም እንደማይለይ ሊሰማቸው ይችላል።​—⁠2 ጴጥሮስ 2:​12 *

7, 8. ሳይንሳዊ ምርምሮች በራሳቸው አጥጋቢ ያልሆኑት ለምንድን ነው?

7 በመሆኑም የፊዚክስ ፕሮፌሰር የሆኑት ፍሪማን ዳይሰን እንደሚከተለው በማለት የጻፉት ለምን እንደሆነ ለመረዳት ትችላለህ:- “ኢዮብ የጠየቃቸውን ጥያቄዎች ደግሜ ስጠይቅ እንዲሁ እንደኔ የሚጠይቁ ሌሎች በርካታ ሰዎች እንዳሉ አውቃለሁ። መከራና ሥቃይ የሚደርስብን ለምንድን ነው? ዓለም ይህን ያህል ኢፍትሐዊ የሆነችው ለምንድን ነው? ሥቃይና ሐዘን የሚደርሰው ለምን ዓላማ ነው?” (ኢዮብ 3:​20, 21፤ 10:​2, 18፤ 21:​7) ቀደም ሲል እንደተጠቀሰው ብዙ ሰዎች መልስ ለማግኘት የሚጥሩት ከአምላክ ሳይሆን ከሳይንስ ነው። የስነ ሕይወት ምሁራን፣ የውቅያኖስ ተመራማሪዎችና ሌሎች ሊቃውንት ስለ ዓለማችንና በዓለማችን ላይ ስለሚኖረው ሕይወት አዳዲስ እውቀት እያገኙ ነው። የጠፈርና የፊዚክስ ተመራማሪዎች ደግም ምርምራቸውን ወደ ሌላ አቅጣጫ በማነጣጠር ስለ ሥርዓተ ፀሐይ፣ ስለ ከዋክብት፣ ሩቅ ስላሉት ጋላክሲዎች ሳይቀር ብዙ ነገር እየተገነዘቡ ነው። (ከዘፍጥረት 11:​6 ጋር አወዳድር።) እነዚህ እውነታዎች ወደየትኞቹ ምክንያታዊ መደምደሚያዎች ያደርሳሉ?

8 የአምላክ “አእምሮ” ወይም በጽንፈ ዓለም ውስጥ የሚታየው የአምላክ “የእጅ ጽሑፍ” እያሉ የሚናገሩ አንዳንድ ሳይንቲስቶች አሉ። ሆኖም ይህ አባባል ቁልፍ ነጥቡን ስቶ ይሆን? ሳይንስ የተባለው መጽሔት የሚከተለውን ብሏል:- “ተመራማሪዎች የጠፈር ጥናት የአምላክን ‘አእምሮ’ ወይም ‘የእጅ ጽሑፍ’ ይገልጻል ሲሉ የጽንፈ ዓለሙ አነስተኛ ክፍል የሆነው ግዑዝ መዋቅር የተገኘው ከመለኮታዊ ምንጭ ነው ማለታቸው ነው።” እንዲያውም የፊዚክስ ሊቅና የኖቤል ተሸላሚ የሆኑት ስቲቨን ዋይንበርግ “የጽንፈ ዓለም ምንነት ይበልጥ የገባን በመሰለን መጠን ይበልጥ የማይጨበጥ ሆኖብናል” ሲሉ ጽፈዋል።

9. እኛንም ሆነ ሌሎችን ስለ ፈጣሪ ለመማር የሚረዳን የትኛው ማስረጃ ነው?

9 ይሁንና የሕይወትን እውነተኛ ትርጉም ማወቅ የሚቻለው ፈጣሪን በማወቅ እንደሆነ ባደረጉት ጥልቅ ጥናት ከተገነዘቡት በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች መካከል ትሆን ይሆናል። ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ሲል የጻፈውን አስታውስ:- “ሰዎች ስለ አምላክ ምንም አናውቅም ብለው ሊናገሩ አይችሉም። ከዓለም መጀመሪያ ጀምሮ ሰዎች የአምላክን ማንነት በፈጠራቸው ሥራዎች አማካኝነት መረዳት ይችላሉ። ይህ ዘላለማዊ ኃይሉንና አምላክነቱን ያሳያል።” (ሮሜ 1:​20 ሆሊ ባይብል፣ ኒው ላይፍ ቨርሺን) አዎን፣ ሰዎች ፈጣሪን እንዲቀበሉና ከእርሱ ጋር በተያያዘ የሕይወትን ትርጉም እንዲያገኙ ለመርዳት የሚያስችሉ ዓለማችንን የሚመለከቱ ሐቆች አሉ። ይህን ጉዳይ ከሦስት ዘርፎች አንፃር እንመለከታለን፤ እነርሱም በዙሪያችን ያለው ጽንፈ ዓለም፣ የሕይወት አመጣጥና የአንጎላችን ችሎታ ናቸው።

አሳማኝ ምክንያቶች

10. ‘መጀመሪያ’ የሚለው አገላለጽ ምን ያመለክታል? (ዘፍጥረት 1:​1፤ መዝሙር 111:​10)

10 ጽንፈ ዓለማችን እንዴት ተገኘ? ስለ ጠፈር ምርምርና የጠፈር አካላትን አቅርበው ስለሚያሳዩ መሣሪያዎች ከሚቀርቡ ሪፖርቶች አብዛኞቹ ሳይንቲስቶች ጽንፈ ዓለማችን ያልነበረበት ጊዜ እንዳለ ማስተዋላቸውን ሳትሰማ አትቀርም። ጽንፈ ዓለም መጀመሪያ የነበረው ሲሆን በሁሉም አቅጣጫ እየሰፋ በመሄድ ላይ ይገኛል። ይህ ምን ያመለክታል? የጠፈር ተመራማሪ የሆኑት ሰር በርናርድ ሎቨል የሚሉትን አዳምጥ:- “ጽንፈ ዓለም ለግምት የሚያዳግት ከፍተኛ ይዘት ያለው ሆኖ መጠኑ ግን አንድ ነጥብ የሚያክል ደቃቅ አካል የነበረበት ጊዜ ካለ ከዚህ አካል በፊት ምን ነበረ ብለን ለመጠየቅ እንገደዳለን። . . . መጀመሪያ መኖር አለበት የሚለውን ሐሳብ መቀበል ይኖርብናል።”

11. (ሀ) ጽንፈ ዓለም ምን ያህል ሰፊ ነው? (ለ) በጽንፈ ዓለም ውስጥ ያለው የተስተካከለና ዝንፍ የማይል አደረጃጀት ምን ያመለክታል?

11 ምድራችንን ጨምሮ የጽንፈ ዓለሙ አደረጃጀት በጣም በረቀቀ ሁኔታ የተስተካከለ ነው። ለምሳሌ ያህል ፀሐይና ሌሎች ከዋክብት በጣም አስደናቂ የሆኑ ሁለት ባሕርያት አሏቸው። ለረዥም ዘመናት ኃይላቸው አይቀንስም፣ ሳይናወጡም ይኖራሉ። በሚታየው ጽንፈ ዓለም ውስጥ ከ50 ቢልዮን (50,000,000,000) እስከ 125 ቢልዮን ብዛት ያላቸው ጋላክሲዎች መኖራቸውን በቅርብ ጊዜ የተሰጡ ግምታዊ አኃዞች ያሳያሉ። እኛ የምንገኝበት የሚልኪ ዌይ ጋላክሲ ደግሞ በቢልዮኖች የሚቆጠሩ ከዋክብትን ያቀፈ ነው። የአንድ መኪና ሞተር ነዳጅና አየር በትክክል ተመጣጥኖ ሊቀርብለት እንደሚገባ እናውቃለን። መኪና ካለህ መኪናህ ያለምንም ችግር በብቃት እንዲንቀሳቀስ ለማድረግ ሞተሩን እንዲያስተካክልልህ አንድ የሰለጠነ መካኒክ ትቀጥር ይሆናል። አንድ ተራ ሞተር እንዲህ ያለው ዝንፍ የማይል አሠራር የሚያስፈልገው ከሆነ ለምሳሌ ያህል በአስተማማኝ ሁኔታ “ስትቃጠል” የምትኖረው ፀሐያችንስ? ቁልፍ የሆኑት ኃይሎች በምድር ላይ ሕይወት ሊያኖር በሚያስችል መንገድ ተስተካክለው እንደተሠሩ በግልጽ ለመመልከት ይቻላል። እንዲህ ያለው ዝንፍ የማይል አሠራር በድንገት የተገኘ ነው? በጥንት ዘመን ይኖር የነበረው ኢዮብ “ሰማያት የሚገዙበትን ሕግ ያወጅከው ወይም በምድር ላይ ያሉትን የተፈጥሮ ሕጎች ያወጣኸው አንተ ነህን?” የሚል ጥያቄ ቀርቦለት ነበር። (ኢዮብ 38:​33 ዘ ኒው ኢንግሊሽ ባይብል) እነዚህን ሕጎች ማንም ሰው አላወጣቸውም። ታዲያ እንዲህ ያለው ዝንፍ የማይል አሠራር ከየት መጣ?​—⁠መዝሙር 19:​1

12. ከፍጥረት በስተጀርባ የማሰብ ችሎታ ያለው አንድ ኃይል አለ ብሎ ማሰብ ምክንያታዊ የሚሆነው ለምንድን ነው?

12 በሰብዓዊ ዓይን ሊታይ ከማይችል አንድ ነገር ወይም አንድ አካል የመጣ ይሆን? ይህን ጥያቄ ዘመናዊ ሳይንስ ከሚለው አንፃር ተመልከተው። በአሁኑ ጊዜ አብዛኞቹ የጠፈር ሊቃውንት ብላክ ሆል የሚባሉ ከፍተኛ ኃይል ያላቸው የጠፈር አካላት መኖራቸውን ይቀበላሉ። ብዙ ጠበብት እንደሚሉት እነዚህ አካላት ሊታዩ የማይችሉ ቢሆኑም በእርግጥ አሉ። መጽሐፍ ቅዱስም በተመሳሳይ በጽንፈ ዓለም ውስጥ ሊታዩ የማይችሉ ኃያላን መንፈሳዊ ፍጥረታት እንዳሉ ይናገራል። እንዲህ ያሉ ሊታዩ የማይችሉ ኃያላን መንፈሳዊ ፍጥረታት የሚገኙ ከሆነ በጽንፈ ዓለም ውስጥ የሚታየው የተስተካከለ አሠራር በጣም ኃያልና ጥበበኛ ከሆነ ፈጣሪ ተገኘ ቢባል ለማመን ይከብዳል?​—⁠ነህምያ 9:​6

13, 14. (ሀ) ሳይንስ የሕይወትን አመጣጥ በተመለከተ ምን ነገር አረጋግጧል? (ለ) ሕይወት በምድር ላይ መኖሩ ምን ያመለክታል?

13 ሰዎች አምላክ መኖሩን እንዲቀበሉ ለመርዳት ከምናቀርባቸው የማስረጃ ዘርፎች ሁለተኛው የሕይወትን አመጣጥ የሚመለከት ይሆናል። ሉዊ ፓስተር ካገኘው የቤተ ሙከራ ውጤት ወዲህ ሕይወት ያለው ነገር ሕይወት ከሌለው ነገር በቅጽበታዊ ለውጥ ሊገኝ አይችልም የሚለው አስተሳሰብ ተቀባይነት አግኝቷል። ታዲያ ምድራዊ ሕይወት እንዴት ተገኘ? በ1950ዎቹ ዓመታት ሳይንቲስቶች በምድር ላይ ያለው ሕይወት አንድ የተለየ ዓይነት ጥንታዊ ከባቢ አየር በመብረቅ በመመታቱ ምክንያት ከተፈጠረ በኋላ ቀስ በቀስ በውቅያኖስ ውስጥ እየተሻሻለ ከመጣ ሕይወት የተገኘ መሆኑን የሚያረጋግጥ ማስረጃ ለማግኘት ይሞክሩ ነበር። ይሁን እንጂ በቅርቡ የተገኙ ማስረጃዎች እንደሚያረጋግጡት እንዲህ ዓይነቱ ከባቢ አየር ኖሮ ስለማያውቅ ሕይወት በዚህ ዓይነት ሊጀምር የሚችል መሆኑ የማይመስል ነገር ሆኗል። በመሆኑም ሌሎች ሳይንቲስቶች የተሻለ ማብራሪያ ለመስጠት እየጣሩ ናቸው። ይሁን እንጂ እነሱም ቁም ነገሩን ሳያስተውሉ ቀርተው ይሆን?

14 ጽንፈ ዓለሙንና በውስጡ ያለውን ሕይወት በማጥናት በርካታ ዐሥርተ ዓመታት ያሳለፉት ሰር ፍሬድ ሆይል የተባሉ እንግሊዛዊ ሳይንቲስት እንዲህ ብለዋል:- “እውነት የመሆን አጋጣሚው እጅግ በጣም ጠባብ የሆነውን ሕይወት ጭፍን ከሆኑ የተፈጥሮ ኃይሎች ተገኘ የሚለውን ንድፈ ሐሳብ ከመቀበል ይልቅ ሕይወት የመጣው በዓላማና አእምሮ ከሚጠይቅ አድራጎት ነው ብሎ ማሰብ የተሻለ ይሆናል።” አዎን፣ ስለ ሕይወት አስደናቂነት ይበልጥ ባወቅን መጠን ሕይወት አእምሮ ካለው አካል የተገኘ መሆኑ ይበልጥ ምክንያታዊ ይሆንልናል።​—⁠ኢዮብ 33:​4፤ መዝሙር 8:​3, 4፤ 36:​9፤ ሥራ 17:​28

15. አፈጣጠርህ ልዩ ነው ለማለት የሚቻለው ለምንድን ነው?

15 ስለዚህ የመጀመሪያው የማስረጃ ዘርፍ ጽንፈ ዓለምን ሁለተኛው ደግሞ በምድር ላይ ያለውን ሕይወት አመጣጥ የሚመለከት ነው። አሁን ደግሞ ሦስተኛውን ነጥብ እርሱም የእኛ የሰው ልጆችን ልዩ የሆነ አፈጣጠር ተመልከት። የሰው ልጆች በሙሉ በብዙ መንገዶች አፈጣጠራቸው ልዩ ነው። ስለዚህ አንተም ልዩ ነህ ማለት ነው። ግን እንዴት? አንጎል በጣም ኃይለኛ ከሆነ ኮምፒዩተር ጋር ይመሳሰላል ተብሎ ሲነገር ሳትሰማ አትቀርም። የቅርብ ጊዜ ሳይንሳዊ ግኝቶች እንደሚያመለክቱት ግን ይህ ዓይነቱ ንጽጽር ጨርሶ ትክክል አይደለም። በማሳቹሴትስ የቴክኖሎጂ ተቋም የሚሠሩ አንድ ሳይንቲስት እንዲህ ብለዋል:- “የዛሬዎቹ ኮምፒዩተሮች በማየት፣ በመናገር፣ በመንቀሳቀስ ወይም በማመዛዘን ችሎታቸው ከአራት ዓመት ሕፃን ጋር እንኳን አይመጣጠኑም። . . . እጅግ በጣም ኃይለኛ ነው የሚባለው ኮምፒዩተር ያለው መረጃ የማጠናቀር አቅም አንዲት ቀንድ አውጣ ካላት ሥርዓተ ነርቭ ጋር እኩል እንደሆነ ተገምቷል። ይህ ደግሞ [በጭንቅላታችሁ] ውስጥ ያለው ባለ ከፍተኛ ኃይል ኮምፒዩተር ካለው አቅም እጅግ በጣም ያንሳል።”

16. የቋንቋ ችሎታህ ምን ያመለክታል?

16 በአንጎልህ ምክንያት ካለህ ችሎታዎች አንዱ ቋንቋ ነው። ሁለት፣ ሦስት ወይም ከዚያ የሚበልጥ ቋንቋ የሚናገሩ ሰዎች ቢኖሩም አንድ ቋንቋ ብቻ ለመናገር መቻላችን ራሱ ከሌሎች ምድራዊ ፍጥረታት ልዩ ያደርገናል። (ኢሳይያስ 36:​11፤ ሥራ 21:​37-40) ፕሮፌሰር አር ኤስ እና ዲ ኤች ፋውትስ “ሐሳቡንና ስሜቱን በቋንቋ የማስተላለፍ ችሎታ ያለው ሰው ብቻ ነውን?” ብለው ከጠየቁ በኋላ እንዲህ ብለዋል:- “በከፍተኛ ደረጃ ላይ የሚገኙት እንስሳት በሙሉ . . . በሰውነት እንቅስቃሴ፣ በማሽተት፣ በመጣራት፣ በመጮህና በመዘመር፣ እንዲሁም እንደ ንቦች በጭፈራ አማካኝነት ሐሳብ እንደሚለዋወጡ የታወቀ ነው። ይሁን እንጂ ከሰው በቀር ሌሎቹ እንስሳት የዳበረ ሰዋስው ያለው ቋንቋ ያላቸው አይመስልም። በተጨማሪም እንስሳት አንድን ነገር የሚወክል ሥዕል የመሳል ችሎታ የላቸውም። ይህ ራሱ ትልቅ ግምት ሊሰጠው የሚችል ልዩነት ነው። ከመሞጫጨር ያለፈ ነገር አያደርጉም።” በእርግጥ በአእምሮአቸው ተጠቅመው በቋንቋ ለመናገርና ትርጉም ያለው ሥዕል ለመሳል የሚችሉት የሰው ልጆች ብቻ ናቸው።​—⁠ከኢሳይያስ 8:​1፤ 30:​8፤ ሉቃስ 1:​3 ጋር አወዳድር።

17. አንድ እንስሳ መልኩን በመስተዋት ውስጥ በመመልከቱና አንድ ሰው እንደዚያ በማድረጉ መካከል ያለው አንዱ መሠረታዊ ልዩነት ምንድን ነው?

17 ከዚህም በላይ ራስህን የመገንዘብ ችሎታ አለህ። አንተነትህን ታውቃለህ። (ምሳሌ 14:​10) አንዲት ወፍ፣ ውሻ ወይም ድመት መልካቸውን በመስተዋት ውስጥ አይተው ሲጮሁ ወይም ለመጣላት ሲፍጨረጨሩ አይተህ ታውቃለህ? የራሳቸውን መልክ ስለማያውቁ ሌላ እንስሳ ያዩ ይመስላቸዋል። አንተ ግን መልክህን በመስተዋት ስታይ ራስህን እንዳየህ ታውቃለህ። (ያዕቆብ 1:​23, 24) መልክህ ምን እንደሚመስል ለማረጋገጥ ወይም ከጥቂት ዓመታት በኋላ ምን እንደምትመስል ለማሰብ ትችላለህ። እንዲህ የሚያደርግ እንስሳ የለም። አዎን፣ አንጎልህ ከሌሎች እንስሳት የተለየህ ያደርግሃል። ታዲያ ለዚህ ሁሉ ሊመሰገን የሚገባው ማን ነው? ይህ ዓይነቱ አንጎል ከአምላክ ካልሆነ በቀር ከየት ሊገኝ ይችላል?

18. ከእንስሳት የሚለዩህ የትኞቹ አእምሯዊ ችሎታዎች ናቸው?

18 በተጨማሪም አንጎልህ ሥነ ጥበብና ሙዚቃ ለማጣጣም እንዲሁም የሥነ ምግባር ስሜት እንዲኖርህ ያስችላል። (ዘጸአት 15:​20፤ መሳፍንት 11:​34፤ 1 ነገሥት 6:​1, 29-35፤ ማቴዎስ 11:​16, 17) አንተ ይህን ማድረግ ስትችል እንስሳት ግን የማይችሉት ለምንድን ነው? እንስሳት በአንጎላቸው የሚጠቀሙት ምግብ እንደ መፈለግ፣ ተጓዳኝ እንደማግኘትና ጎጆ እንደ መሥራት ያሉትን የዕለት ተዕለት ፍላጎቶቻቸውን ለማሟላት ብቻ ነው። ስለ ወደፊቱ ጊዜ የሚያስቡት የሰው ልጆች ብቻ ናቸው። እንዲያውም አንዳንዶች አልፈው ተርፈው አንዳንድ ድርጊቶቻቸው በአካባቢያችን ላይ ወይም ከበርካታ ዓመታት በኋላ በሚመጡት ዘሮቻቸው ላይ ስለሚያስከትሉት ውጤት ያስባሉ። ለምን? መክብብ 3:​11 ስለ ሰው ልጆች ሲናገር “ዘላለማዊነትን በሰው ልቦና አሳድሮአል” ይላል። አዎን፣ ዘላለማዊነት ምን ትርጉም እንዳለው ለማወቅ ወይም ዘላለማዊ ሕይወት ምን እንደሆነ ለመገመት መቻልህ ልዩ ያደርግሃል።

ፈጣሪ ሕይወትህን ትርጉም ያለው እንዲያደርግልህ ፍቀድለት

19. ሌሎች ስለ ፈጣሪ እንዲያስቡ ለመርዳት የትኞቹን ሦስት የማስረጃ ዘርፎች ልትጠቀም ትችላለህ?

19 የዳሰስነው ሦስት የማስረጃ ዘርፎችን ብቻ ነው። በጣም ግዙፍ የሆነው ጽንፈ ዓለም በማይዛባ ሥርዓት የሚመራ መሆኑን፣ በምድር ላይ ያለውን ሕይወት አመጣጥና የተለያዩ ነገሮችን ማከናወን የሚችለውን ልዩ የሆነውን የሰው አንጎል ተመልክተናል። እነዚህ ሦስት ነጥቦች ምን ይጠቁማሉ? ሌሎች አንድ መደምደሚያ ላይ እንዲደርሱ ለመርዳት በሚከተለው ዓይነት አቀራረብ መጠቀም ትችላለህ። ጽንፈ ዓለም መጀመሪያ ነበረው? ብለህ በመጠየቅ መጀመር ትችላለህ። አብዛኞቹ ሰዎች የአዎንታ መልስ ይሰጣሉ። ከዚያም ታዲያ ይህ ጅምር አንድ አስጀማሪ ነበረው ወይስ አልነበረውም? ብለህ ጠይቅ። አብዛኞቹ ሰዎች ጽንፈ ዓለም አንድ አስጀማሪ እንደነበረው ይቀበላሉ። ይህ ደግሞ ወደ መጨረሻው ጥያቄ ይመራል። አስጀማሪው ዘላለማዊ የሆነ ነገር ነው ወይስ ሕያው የሆነ አካል? ፍሬ ነገሩ እንዲህ ባለ ምክንያታዊና ግልጽ በሆነ መንገድ ሲቀርብ ብዙ ሰዎች አንድ ፈጣሪ መኖር አለበት! ወደሚል መደምደሚያ ይደርሳሉ። ይህ ከሆነ ታዲያ ሕይወት ትርጉም ያለው መሆን የለበትም?

20, 21. ሕይወታችን ትርጉም ያለው እንዲሆን ስለ ፈጣሪ ማወቃችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

20 የሥነ ምግባር ስሜታችንና ራሱን ሥነ ምግባርን ጨምሮ መላው ሕልውናችን ከፈጣሪ ጋር የተያያዘ መሆን አለበት። ዶክተር ሮሎ ሜይ በአንድ ወቅት እንዲህ ሲሉ ጽፈው ነበር:- “ብቸኛው ብቃት ያለው የሥነ ምግባር አቋም በመሠረታዊ የሕይወት ትርጉም ላይ የተመሠረተ ነው።” ይህ የሚገኘው የት ነው? ቀጥለው እንዲህ ብለዋል:- “የመጨረሻው አቋም የአምላክ ባህርይ ነው። ከፍጥረት መጀመሪያ አንስቶ እስከ መጨረሻው ድረስ የሕይወት መሠረት የሚሆኑት የአምላክ የአቋም መስፈርቶች ናቸው።”

21 በመሆኑም መዝሙራዊው እንደሚከተለው ብሎ ሲለምን ትሕትናና ጥበብ ለምን እንዳሳየ ለመረዳት እንችላለን:- “አቤቱ፣ መንገድህን አመልክተኝ፣ ፍለጋህንም አስተምረኝ። አንተ የመድኃኒቴ አምላክ ነህና በእውነትህ ምራኝ፣ አስተምረኝም።” (መዝሙር 25:​4, 5) ፈጣሪን በተሻለ መንገድ እያወቀው ሲሄድ የመዝሙራዊው ሕይወት ይበልጥ ትርጉም፣ ዓላማና አቅጣጫ ያለው እንደሆነለት የተረጋገጠ ነው። ሁላችንም ተመሳሳይ የሆነ ነገር ልናገኝ እንችላለን።​—⁠ዘጸአት 33:​13

22. የፈጣሪን መንገዶች ማወቅ ምንን ይጨምራል?

22 የፈጣሪን ‘መንገዶች’ ማወቅ፣ ፈጣሪ ምን ዓይነት እንደሆነ፣ ማለትም ባሕርያቱንና መንገዶቹን በይበልጥ ማወቅን ይጨምራል። ሆኖም ፈጣሪ የማይታይና እጅግ ከፍተኛ ኃይል ያለው በመሆኑ እሱን በተሻለ መንገድ ማወቅ የምንችለው እንዴት ነው? የሚቀጥለው ርዕስ ይህን ያብራራል።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.6 ዶክተር ቪክቶር ኢ ፍራክል በናዚ የማጎሪያ ካምፖች ካገኟቸው ተሞክሮዎች በመነሳት እንዲህ ብለዋል:- “ሰው የሕይወትን ትርጉም ለማግኘት የሚያደርገው ፍለጋ በሕይወቱ ውስጥ አንደኛውን ቦታ የሚይዝ ኃይል እንጂ” እንደ እንስሳት “በደመ ነፍስ የሚመጣ ‘ሁለተኛ ደረጃ የሚይዝ ነገር አይደለም።’” አክለውም ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ካበቃ ከአሥርተ ዓመታት በኋላ በፈረንሳይ ውስጥ የተደረገ አንድ ጥናት “ጥያቄ ከቀረበላቸው ሰዎች ውስጥ 89 በመቶ የሚሆኑት ሰው ሕይወቱ ትርጉም ያለው እንዲሆን ‘አንድ ነገር’ እንደሚፈልግ ማመናቸውን አሳይቷል” ብለዋል።

ምን ብለህ ትመልሳለህ?

◻ ሳይንስ ስለ ጽንፈ ዓለም በሚሰጠው ማብራሪያ ብቻ መርካት የሌለብን ለምንድን ነው?

◻ ሌሎች ስለ ፈጣሪ እንዲያስቡ ለመርዳት ምን ልትጠቀም ትችላለህ?

◻ እውነተኛ ትርጉም ያለው ሕይወት ለመኖር ፈጣሪን ማወቅ ቁልፍ የሆነው ለምንድን ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕላዊ መግለጫ]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

መልስህ ምንድን ነው?

ጽንፈ ዓለማችን

↓ ↓

መጀመሪያ መጀመሪያ

የለውም አለው

↓ ↓

ሠሪ የለውም ሠሪ አለው

↓ ↓

ዘላለማዊ ዘላለማዊ

በሆነ ነገር በሆነ አካል

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በጽንፈ ዓለም ላይ የሚታየው ግዙፍነትና ዝንፍ የማይል አሠራር ብዙዎች ስለ ፈጣሪ እንዲያስቡ አድርጓቸዋል

[ምንጭ]

ገጽ 15 እና 18:- Jeff Hester (Arizona State University) and NASA