በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

‘ታናሹ ሺህ’ ሆኗል

‘ታናሹ ሺህ’ ሆኗል

‘ታናሹ ሺህ’ ሆኗል

“ታናሹ ለሺህ የሁሉም ታናሹ ለብርቱ ሕዝብ ይሆናል።”​ኢሳይያስ 60:​22

1, 2. (ሀ) ዛሬ ምድርን ጨለማ የሸፈናት ለምንድን ነው? (ለ) የይሖዋ ብርሃን ደረጃ በደረጃ ለሕዝቡ የበራላቸው እንዴት ነው?

 “ጨለማ ምድርን ድቅድቅ ጨለማም አሕዛብን ይሸፍናል፤ ነገር ግን በአንቺ ላይ እግዚአብሔር ይወጣል ክብሩም በአንቺ ላይ ይታያል።” (ኢሳይያስ 60:​2) እነዚህ ቃላት ከ1919 ጀምሮ በምድር ላይ ያለውን ሁኔታ በትክክል የሚገልጹ ናቸው። ሕዝበ ክርስትና “የዓለም ብርሃን” የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ በንጉሣዊ ሥልጣኑ መገኘቱን የሚያሳዩትን ምልክቶች ለመቀበል አሻፈረኝ ብላለች። (ዮሐንስ 8:​12፤ ማቴዎስ 24:​3) ‘ከዚህ የጨለማ ዓለም ገዥዎች’ መካከል ቀንደኛ በሆነው በሰይጣን ‘ታላቅ ቁጣ’ የተነሳ 20ኛው መቶ ዘመን በሰው ዘር ታሪክ ውስጥ ታይቶ የማያውቅ የከፋ ጭካኔና ውድመት የደረሰበት ጊዜ ሆኗል። (ራእይ 12:​12፤ ኤፌሶን 6:​12) ብዙዎቹ ሰዎች የሚኖሩት በመንፈሳዊ ጨለማ ውስጥ ነው።

2 ይሁንና ዛሬ ብርሃን የለም ማለት አይደለም። ይሖዋ የእርሱ “ሴት” መሰል ሰማያዊ ድርጅት ወኪሎች ለሆኑት ምድራዊ አገልጋዮቹ ማለትም ለቅቡዓን ቀሪዎቹ ‘ብርሃን እያበራላቸው’ ነው። (ኢሳይያስ 60:​1) በተለይ በ1919 ከባቢሎናዊ ምርኮ ነፃ ከወጡ በኋላ የአምላክን ክብር በማንጸባረቅ ‘ብርሃናቸውን በሰው ፊት አብርተዋል።’ (ማቴዎስ 5:​16) ከ1919 እስከ 1931 ድረስ ባለው ጊዜ የቀሩትን የባቢሎናዊ አስተሳሰብ ማነቆዎች ሁሉ በማስወገዳቸው የመንግሥቱ ብርሃን ድምቀት እየጨመረ ሄዷል። ይሖዋ “የእስራኤልን ቅሬታ ፈጽሞ አከማቻለሁ፤ እንደ ባሶራ በጎችና እንደ መንጋ በማሰማርያቸው ውስጥ በአንድነት አኖራቸዋለሁ፤ ከሰው ብዛት የተነሣ ድምፃቸውን ያሰማሉ” ሲል ቃል የገባውን ተስፋ በመፈጸሙ ቁጥራቸው ወደ አሥር ሺህዎች ከፍ አለ። (ሚክያስ 2:​12) በ1931 የይሖዋ ምሥክሮች የሚለውን ስም ሲቀበሉ በሕዝቦቹ ላይ የተንጸባረቀው የይሖዋ ክብር ይበልጥ ግልጽ ሆኗል።​—⁠ኢሳይያስ 43:​10, 12

3. የይሖዋ ብርሃን ከቅቡዓኑ በተጨማሪ በሌሎችም ላይ እንደሚፈነጥቅ ግልጽ የሆነው እንዴት ነው?

3 ይሖዋ ብርሃኑን የሚልከው ‘ለታናሹ መንጋ’ ቀሪዎች ብቻ ነውን? (ሉቃስ 12:​32) በፍጹም። የመስከረም 1, 1931 መጠበቂያ ግንብ ስለ ሌላ ቡድን ተናግሮ ነበር። ሕዝቅኤል 9:​1-11ን በሚመለከት በተሰጠው ግሩም ማብራሪያ በእነዚህ ቁጥሮች ላይ የተጠቀሰው የጸሐፊ ቀለም ቀንድ የያዘው ሰው ቅቡዓን ቀሪዎችን እንደሚያመለክት ተገልጿል። ይህ “ሰው” በግንባራቸው ላይ ምልክት ያደረገባቸውስ እነማን ናቸው? ገነት በምትሆነው ምድር ላይ ለዘላለም የመኖር ተስፋ ያላቸው “ሌሎች በጎች” ናቸው። (ዮሐንስ 10:​16፤ መዝሙር 37:​29) በ1935 እነዚህ “ሌሎች በጎች” በዮሐንስ ራእይ ውስጥ የታዩት ‘ከሕዝብ የተውጣጡ እጅግ ብዙ ሰዎች’ መሆናቸውን ማስተዋል ተችሏል። (ራእይ 7:​9-14) ከ1935 አንስቶ እስከ ዛሬ ድረስ እጅግ ብዙ ሰዎችን ለመሰብሰቡ ሥራ ትልቅ ትኩረት ተሰጥቶት ቆይቷል።

4. በ⁠ኢሳይያስ 60:​3 ላይ የተገለጹት “ነገሥታት” እና “አሕዛብ” እነማን ናቸው?

4 ይህ የመሰብሰብ ሥራ በኢሳይያስ ትንቢት ውስጥ በተዘዋዋሪ መንገድ ተጠቅሷል:- “አሕዛብ ወደ ብርሃንሽ ነገሥታትም ወደ መውጫሽ ጸዳል ይመጣሉ።” (ኢሳይያስ 60:​3) እዚህ ላይ የተጠቀሱት “ነገሥታት” እነማን ናቸው? ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር የሰማያዊው መንግሥት ተባባሪ ገዥዎች የሚሆኑትና በምሥክርነቱ ሥራ በግንባር ቀደምትነት የተሰለፉት የ144, 000ዎቹ ቀሪዎች ናቸው። (ሮሜ 8:​17፤ ራእይ 12:​17፤ 14:​1) ዛሬ በሕይወት ያሉት በጥቂት ሺህዎች የሚቆጠሩ ቅቡዓን ቀሪዎች ‘በአሕዛብ’ ማለትም ምድራዊ ተስፋ ባላቸውና ከይሖዋ ለመማር መጥተው ሌሎቹም ተመሳሳይ እርምጃ እንዲወስዱ በሚያበረታቱት ሰዎች በቁጥር እጅግ ተበልጠዋል።​—⁠ኢሳይያስ 2:​3

ቀናተኛ የይሖዋ አገልጋዮች

5. (ሀ) የይሖዋ ሕዝቦች ቅንዓት እንዳልቀነሰ የሚያሳየው ምንድን ነው? (ለ) በ1999 የሚደነቅ ጭማሪ ያገኙት አገሮች የትኞቹ ናቸው? (ከገጽ 17-20 ድረስ ያለውን ሰንጠረዥ ተመልከት።)

5 በዘመናችን ያሉት የይሖዋ ምሥክሮች በዚህ በ20ኛው መቶ ዘመን ከፍተኛ ቅንዓት አሳይተዋል! ተጽዕኖው እየጨመረ ቢሄድም 2000 ዓመት እየቀረበ በመጣበት በአሁኑ ጊዜም ቅንዓታቸው አልቀነሰም። ዛሬም ቢሆን ‘ከአሕዛብ ሁሉ ደቀ መዛሙርት አድርጉ’ ሲል ኢየሱስ የሰጣቸውን ትእዛዝ በቁም ነገር በመፈጸም ላይ ናቸው። (ማቴዎስ 28:​19, 20) በ20ኛው መቶ ዘመን የመጨረሻ የአገልግሎት ዓመት በአገልግሎት የተሳተፉት የምሥራቹ አስፋፊዎች ቁጥር 5,912,492 ወደሚያክል አዲስ ከፍተኛ ቁጥር አድጓል። ለሌሎች ሰዎች ስለ አምላክና ስለ ዓላማው በመናገር 1, 144, 566, 849 ሰዓት አሳልፈዋል። ፍላጎት ላሳዩ ሰዎች 420, 047, 796 ተመላልሶ መጠየቅ ያደረጉ ሲሆን 4, 433, 884 ነፃ የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን መርተዋል። ቅንዓት የተሞላበት እንዴት ያለ ግሩም አገልግሎት ነው!

6. ለአቅኚዎች ምን አዲስ ዝግጅት ተደርጓል? ምን ምላሽስ ተገኝቷል?

6 በጥር 1999 የአስተዳደር አካል በአቅኚዎች የሰዓት ግብ ላይ ማስተካከያ መደረጉን አስታውቆ ነበር። ብዙዎች ይህንን አጋጣሚ በመጠቀም በዘወትር ወይም በረዳት አቅኚነት ተሠማርተዋል። ለምሳሌ ያህል በ1999 የመጀመሪያዎቹ አራት ወራት ውስጥ የኔዘርላንድ ቅርንጫፍ ቢሮ ከአንድ ዓመት በፊት በተመሳሳይ ወቅት ከተቀበላቸው የአቅኚነት ማመልከቻዎች በአራት እጥፍ የሚበልጡ ማመልከቻዎች ደርሰውታል። ጋና “በአቅኚዎች የሰዓት ግብ ላይ ማስተካከያ ከተደረገ ወዲህ የዘወትር አቅኚዎቻችን ቁጥር ዕድገት ማድረጉን ቀጥሏል” ስትል ሪፖርት አድርጋለች። በ1999 የአገልግሎት ዓመት በዓለም ዙሪያ የአቅኚዎች ቁጥር 738, 343 ደርሷል። ይህም ‘ለመልካም ሥራ ያለንን ቅንዓት’ የሚያረጋግጥ ድንቅ ማስረጃ ነው።​—⁠ቲቶ 2:​14

7. ይሖዋ የአገልጋዮቹን ቅንዓት የተሞላበት እንቅስቃሴ የባረከው እንዴት ነው?

7 ይሖዋ ይህን ቅንዓት የተሞላበት እንቅስቃሴ ባርኮታልን? እንዴታ። በኢሳይያስ በኩል እንዲህ ብሏል:- “ዓይኖችሽን አንሥተሽ ተመልከቺ፤ እነዚህ ሁሉ ተሰብስበው ወደ አንቺ ይመጣሉ፤ ወንዶች ልጆችሽ ከሩቅ ይመጣሉ፣ ሴቶች ልጆችሽንም በጫንቃ ይሸከሙአቸዋል።” (ኢሳይያስ 60:​4) የተሰበሰቡት ቅቡዓን “ወንዶች” እና “ሴቶች” ልጆች እስከዛሬም ድረስ አምላክን በቅንዓት በማገልገል ላይ ናቸው። አሁን ደግሞ የኢየሱስ ሌሎች በጎች በ234 አገሮችና የባሕር ደሴቶች ውስጥ ከይሖዋ “ወንዶች” እና “ሴቶች” ልጆች ጎን እየተሰበሰቡ ነው።

“በጎ ሥራ ሁሉ”

8. የይሖዋ ምሥክሮች የሚያከናውኗቸው ‘በጎ ሥራዎች’ ምንድን ናቸው?

8 ክርስቲያኖች የመንግሥቱን ምሥራች የመስበክና ፍላጎት ያሳዩ ሰዎች ደቀ መዛሙርት እንዲሆኑ የመርዳት ኃላፊነት አለባቸው። ይሁን እንጂ ‘ለበጎ ሥራ ሁሉ የተዘጋጁ’ ናቸው። (2 ጢሞቴዎስ 3:16) በመሆኑም ቤተሰባቸውን በፍቅር ይንከባከባሉ፣ የእንግዳ ተቀባይነት መንፈስ አላቸው እንዲሁም የታመሙትን ይጠይቃሉ። (1 ጢሞቴዎስ 5:​8፤ ዕብራውያን 13:​16) በተጨማሪም ፈቃደኛ ሠራተኞች የመንግሥት አዳራሽ ግንባታን በመሳሰሉትም ምሥክርነት ለመስጠት በሚያስችሉ ፕሮጄክቶች ይካፈላሉ። በቶጎ አንድ አዳራሽ ተሠርቶ ካለቀ በኋላ በአካባቢው ያለ በተዓምራዊ ፈውስ የሚያምን የአንድ ቤተ ክርስቲያን ኃላፊዎች የይሖዋ ምሥክሮች የራሳቸውን አዳራሽ ራሳቸው መገንባት ሲችሉ እነርሱ ግን ሌሎች ሰዎችን ቀጥረው የሚያሠሩበት ምክንያት ምን እንደሆነ ለማወቅ ተነሥተዋል! ከቶጎ የተላከው ሪፖርት እንደገለጸው በጥሩ ሁኔታ የሚገነቡ የመንግሥት አዳራሾች ሌሎች ሰዎች አዳራሽ በሚገነባባቸው አካባቢዎች ቤት ለመሥራት ወይም ለመከራየት እስኪጥሩ በአካባቢው ሰዎች ዘንድ በጎ ተጽእኖ ያሳድራሉ።

9. የይሖዋ ምሥክሮች የተፈጥሮ አደጋዎች ሲደርሱ ምን ምላሽ ሰጥተዋል?

9 ሌላ ዓይነት በጎ ሥራ ያስፈለገባቸውም ጊዜያት ነበሩ። ባለፈው የአገልግሎት ዓመት ብዙ አገሮች በተፈጥሮ አደጋ ተመትተው ነበር። ከአንዴም ብዙ ጊዜ እርዳታ ለመስጠት በቦታው የደረሱት የመጀመሪያ ሰዎች የይሖዋ ምሥክሮች ሆነው ተገኝተዋል። ለምሳሌ ያህል አብዛኛው የሆንዱራስ ክፍል ሚች በተባለው ኃይለኛ አውሎ ነፋስ ከፍተኛ ውድመት ደርሶበት ነበር። ቅርንጫፍ ቢሮው ወዲያውኑ የእርዳታ ጥረቶችን የሚያቀናጅ የአስቸኳይ እርዳታ ኮሚቴ አቋቋመ። በሆንዱራስና በሌሎች ብዙ አገሮች የሚገኙ ምሥክሮች ልብስ፣ ምግብ፣ መድኃኒትና ሌሎች መሠረታዊ ቁሳ ቁሶችን በእርዳታ ሰጡ። የአካባቢ ሕንጻ ሥራ ኮሚቴዎችም ያላቸውን ችሎታ በመጠቀም ቤቶችን መልሰው መገንባቱን ተያያዙት። ብዙም ሳይቆይ የችግሩ ተጠቂ የሆኑት ወንድሞቻችን ወደ መደበኛው እንቅስቃሴያቸው መመለስ ችለዋል። በኢኳዶር የደረሰው ከባድ የጎርፍ መጥለቅለቅ አንዳንድ ቤቶችን ባፈረሰበት ወቅት የይሖዋ ምሥክሮች ለወንድሞቻቸው ደርሰውላቸዋል። አንድ የመንግሥት ባለ ሥልጣን የይሖዋ ምሥክሮች ችግሩን ውጤታማ በሆነ መንገድ ለማሸነፍ ያደረጉትን እንቅስቃሴ ከተመለከቱ በኋላ “እኔ ይህን ቡድን ብይዝ ተዓምር እሠራ ነበር! እንደ እናንተ ያሉ ሰዎች በየአገሩ ሊኖሩ ይገባል” ብለዋል። እንዲህ ያለው በጎ ሥራ ለይሖዋ አምላክ ክብር የሚያመጣ ከመሆኑም ሌላ ‘ለሁሉም ነገር የሚጠቅመውን ለአምላክ የማደር ባሕርይ’ እንደለበስን የሚያሳይ ማረጋገጫ ነው።​—⁠1 ጢሞቴዎስ 4:​8

‘እንደ ደመና እየበረሩ መጡ’

10. የቅቡዓኑ ቁጥር እያሽቆለቆለ ቢሄድም የይሖዋ ስም ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ በስፋት ሊታወጅ የቻለው እንዴት ነው?

10 አሁን ደግሞ ይሖዋ እንዲህ በማለት ይጠይቃል:- “እርግቦች ወደ ቤታቸው እንደሚበርሩ፣ እነዚህ እንደ ደመና የሚበርሩ እነማን ናቸው? . . . ልጆችሽን ከሩቅ . . . ያመጡ ዘንድ ደሴቶች የተርሴስ መርከቦችም አስቀድመው ይጠባበቁኛል። መጻተኞች ቅጥርሽን ይሠራሉ፣ ነገሥታቶቻቸውም ያገለግሉሻል።” (ኢሳይያስ 60:​8-10) ከይሖዋ ለመጣው ‘ብርሃን’ መጀመሪያ ምላሽ የሰጡት ‘ወንዶች ልጆቹ’ ማለትም ቅቡዓን ክርስቲያኖች ናቸው። ከዚያ በኋላ የመጡት “መጻተኞች” የተባሉት ማለትም ቅቡዓን ወንድሞቻቸው በምሥራቹ ስብከት በግንባር ቀደምትነት የሚሰጡትን አመራር በመከተል በታማኝነት የሚያገለግሏቸው እጅግ ብዙ ሰዎች ናቸው። በመሆኑም የቅቡዓኑ ቁጥር እያሽቆለቆለ ቢሄድም የይሖዋ ስም ከዚህ በፊት ሆኖ በማያውቅ መጠን በምድር ዙሪያ እየታወጀ ነው።

11. (ሀ) አሁንም ምን ነገር መከናወኑን ቀጥሏል? በ1999ስ ምን ውጤት ተገኝቷል? (ለ) በ1999 ከፍተኛ የተጠማቂዎች ቁጥር የነበራቸው አገሮች የትኞቹ ናቸው? (ከገጽ 17-20 ያለውን ሰንጠረዥ ተመልከት።)

11 ከዚህም የተነሣ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ‘ወደ ቤታቸው እንደሚበርሩ እርግቦች’ በመጉረፍ የክርስቲያን ጉባኤን መሸሸጊያ በማድረግ ላይ ናቸው። በየዓመቱ በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች ይጨመራሉ። በሩ አሁንም ክፍት ነው። ኢሳይያስ እንዲህ ብሏል:- “በሮችሽም ሁል ጊዜ ይከፈታሉ፤ ሰዎች የአሕዛብን ብልጥግና የተማረኩትንም ነገሥታቶቻቸውን ወደ አንቺ ያመጡ ዘንድ ሌሊትና ቀን አይዘጉም።” (ኢሳይያስ 60:​11) ባለፈው ዓመት 323, 439 ሰዎች ራሳቸውን ለይሖዋ መወሰናቸውን በውኃ ጥምቀት ያሳዩ ሲሆን ይሖዋ አሁንም በሩን አልዘጋውም። ‘በአሕዛብ ሁሉ የተመረጠ ዕቃ’ የተባሉት የእጅግ ብዙ ሰዎች አባላት ዛሬም በተከፈተው በር እየጎረፉ ነው። (ሐጌ 2:​7) ጨለማውን ጥለው ለመውጣት የሚፈልጉ ሰዎች ፊት ተነስተው አያውቁም። (ዮሐንስ 12:​46) ከእነዚህ ሰዎች መካከል ማናቸውም ለዚህ ብርሃን ያላቸውን አድናቆት እንዳያጡ ምኞታችን ነው!

ተቃውሞ ቢገጥማቸውም የማይበገሩ ሆነዋል

12. ጨለማን የሚያፈቅሩ ሰዎች ብርሃኑን ለማጥፋት የሞከሩት እንዴት ነው?

12 ጨለማን የሚያፈቅሩ ሰዎች የይሖዋን ብርሃን አይወድዱትም። (ዮሐንስ 3:​19) እንዲያውም አንዳንዶች ይህንን ብርሃን ለማጥፋት ይሞክራሉ። ይህ እንግዳ ነገር አይደለም። “ለሰው ሁሉ የሚያበራው እውነተኛው ብርሃን” ኢየሱስ ሳይቀር የፌዝና የተቃውሞ ዒላማ ከመሆንም አልፎ በአገሩ ሰዎች እጅ ተገድሏል። (ዮሐንስ 1:​9) በ20ኛው መቶ ዘመንም የይሖዋ ምሥክሮች ማፌዣ ሆነዋል፣ ታስረዋል፣ እገዳ ተጥሎባቸዋል አልፎ ተርፎም የይሖዋን ብርሃን የታመኑ ሆነው በማንጸባረቃቸው ተገድለዋል። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ተቃዋሚዎች የአምላክን ብርሃን ስለሚያንጸባርቁት ሰዎች በመገናኛ ብዙሐን ውሸት ማሠራጨቱን ሥራዬ ብለው ተያይዘውታል። አንዳንዶችም ሰዎች የይሖዋ ምሥክሮች አደገኛ ናቸውና ሥራቸው በከፊልም ሆነ ሙሉ በሙሉ እገዳ ሊጣልበት ይገባል ብለው እንዲያምኑ ለማድረግ ይፈልጋሉ። እንዲህ ያሉት ተቃዋሚዎች ተሳክቶላቸዋልን?

13. ሥራችንን በተመለከተ ለመገናኛ ብዙሀን በጥበብ እውነታውን መግለጻችን ምን ውጤት አስገኝቷል?

13 በፍጹም። አስፈላጊ ሆኖ በሚገኝበት ጊዜ ሁሉ የይሖዋ ምሥክሮች እውነታውን ለማስረዳት ወደ ዜና ማሰራጫዎች ሄደዋል። ከዚህም የተነሣ የይሖዋ ስም በጋዜጦችና በመጽሔቶች ላይ እንዲሁም በቴሌቪዥንና በራዲዮ በሰፊው ተነሥቷል። ይህም በምሥክርነቱ ሥራ ጥሩ ውጤት አስገኝቷል። ለምሳሌ ያህል በዴንማርክ “የዴንማርኮች እምነት እያሽቆለቆለ ያለው ለምንድን ነው?” በሚል ርዕስ በብሔራዊው ቴሌቪዥን አንድ ፕሮግራም ተላልፎ ነበር። ከሌሎች እምነቶች ጋር የይሖዋ ምሥክሮችም ለቃለ ምልልሱ ተጋብዘው ቀረቡ። ከዚያ በኋላ ፕሮግራሙን የተከታተለች አንዲት ሴት “የአምላክ መንፈስ ያላቸው እነማን እንደሆኑ በግልጽ ታይቷል” ስትል አስተያየቷን ሰጥታለች። ሴትየዋ አሁን መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት ጀምራለች።

14. ተቃዋሚዎች በቅርቡ ምን ነገር በመገንዘብ የኃፍረት ማቅ ይከናነባሉ?

14 የይሖዋ ምሥክሮች በዚህ ዓለም ያሉ ብዙ ሰዎች እንደሚቃወሟቸው ያውቃሉ። (ዮሐንስ 17:​14) ይሁንና የኢሳይያስ ትንቢት ያበረታታቸዋል:- “የአስጨናቂዎችሽም ልጆች አንገታቸውን ደፍተው ወደ አንቺ ይመጣሉ፣ የናቁሽም ሁሉ ወደ እግርሽ ጫማ ይሰግዳሉ፤ የእግዚአብሔርም ከተማ፣ የእስራኤል ቅዱስ የሆንሽ ጽዮን ይሉሻል።” (ኢሳይያስ 60:​14) ተቃዋሚዎች እስካሁን ድረስ ሲቃወሙ የነበሩት አምላክን መሆኑን የሚገነዘቡበትና የኃፍረት ማቅ የሚከናነቡበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም። እንዲህ ዓይነቱን ውጊያ በድል አድራጊነት የሚወጣው ማን ነው?

15. የይሖዋ ምሥክሮች “የአሕዛብን ወተት” የጠጡት እንዴት ነው? ይህስ በማስተማርና በወንጌላዊነት ሥራቸው ላይ የተንጸባረቀው እንዴት ነው?

15 ይሖዋ እንዲህ በማለት ተጨማሪ ቃል ገብቷል:- “የዘላለም ትምክህት . . . አደርግሻለሁ። የአሕዛብንም ወተት ትጠጪያለሽ የነገሥታትንም ጡት ትጠቢያለሽ፤ እኔ እግዚአብሔር . . . መድኃኒትሽ [“አዳኝሽ፣” NW ] . . . እንደሆንሁ ታውቂያለሽ።” (ኢሳይያስ 60:​15, 16) አዎን፣ ይሖዋ የሕዝቡ አዳኝ ነው። በእርሱ ከታመኑ “ለዘላለም” ይዘልቃሉ። እውነተኛውን አምልኮ ለማስፋፋት ዘመኑ ያፈራቸውን አንዳንድ ነገሮች በመጠቀማቸው “የአሕዛብን ወተት” ጠጥተዋል። ለምሳሌ ያህል ኮምፒዩተሮችንና የመገናኛ ቴክኖሎጂዎችን በጥበብ መጠቀማቸው የመጠበቂያ ግንብ በ121 ቋንቋዎች ንቁ! ደግሞ በ62 ቋንቋዎች በተመሳሳይ ጊዜ ታትሞ እንዲወጣ አስችሏል። የአዲሲቱ ዓለም ትርጉምን ወደ አዳዲስ ቋንቋዎች ለመተርጎም የሚያስችል ለዚሁ ዓላማ ብቻ የሚያገለግል የኮምፒዩተር ፕሮግራም የተዘጋጀ ሲሆን እንዲህ ያለው የትርጉም ሥራ ለደስታ ምክንያት ሆኗል። በ1999 የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች ትርጉም በክሮኤሽያ ቋንቋ ሲወጣ ብዙዎች እንባቸውን መቆጣጠር አልቻሉም። አንድ አረጋዊ ወንድም “ይህን መጽሐፍ ቅዱስ ለረጅም ጊዜ ስጠብቅ ቆይቻለሁ። ከእንግዲህ ብሞትም አይቆጨኝም!” ብለዋል። የአዲሲቱ ዓለም ትርጉም ሙሉ በሙሉም ሆነ በከፊል ሥርጭቱ በ34 ቋንቋዎች ከ100 ሚልዮን ቅጂ በልጧል።

ከፍተኛ የሥነ ምግባር ደረጃ

16, 17. (ሀ) የይሖዋን ከፍተኛ የአቋም ደረጃዎች መጠበቅ ቀላል ባይሆንም እንደዚያ ማድረጋችን በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? (ለ) ወጣቶች በዓለም ከመበከል ሊርቁ እንደሚችሉ የሚያሳይ የትኛው ምሳሌ ነው?

16 ኢየሱስ “ክፉ የሚያደርግ ሁሉ ብርሃንን ይጠላል” ብሏል። (ዮሐንስ 3:​20) በሌላ በኩል ግን በብርሃን መመላለሳቸውን የሚቀጥሉ ሰዎች የይሖዋን ከፍተኛ የአቋም ደረጃ ያፈቅራሉ ማለት ነው። ይሖዋ በኢሳይያስ በኩል “ሕዝብሽም ሁሉ ጻድቃን ይሆናሉ” ብሏል። (ኢሳይያስ 60:​21ሀ) የፆታ ብልግና፣ ውሸት፣ ስግብግብነት እና ኩራት በእጅጉ ተስፋፍቶ በሚገኝበት ዓለም ውስጥ የጽድቅ የአቋም ደረጃዎችን መጠበቅ በጣም ተፈታታኝ ሊሆን ይችላል። ለምሳሌ ያህል በአንዳንድ አገሮች ውስጥ ኑሮ እየተወደደ በመሆኑ በአንድ ልብ ሀብትን ወደ ማሳደድ ዘወር ማለት ቀላል ሆኗል። ይሁን እንጂ ጳውሎስ እንዲህ ሲል አስጠንቅቋል:- “ባለ ጠጎች ሊሆኑ የሚፈልጉ በጥፋትና በመፍረስ ሰዎችን በሚያሰጥምና በሚያሰንፍ በሚጎዳም በብዙ ምኞትና በፈተና በወጥመድም ይወድቃሉ።” (1 ጢሞቴዎስ 6:​9) አንድ ሰው ወደ ንግዱ ዓለም ጭልጥ ብሎ በመግባቱ እንደ ክርስቲያናዊ ስብሰባ፣ ቅዱስ አገልግሎት፣ የሥነ ምግባር መሠረታዊ ሥርዓትና የቤተሰብ ኃላፊነት ያሉትን አስፈላጊ ነገሮች ችላ ሲል ማየት እንዴት የሚያሳዝን ነው!

17 በተለይ ብዙዎቹ እኩዮቻቸው በአደገኛ ዕፆችና በሥነ ምግባር ብልግና ተጠላልፈው ለሚያዩት ወጣቶች የጽድቅ የአቋም ደረጃዎችን መጠበቅ አስቸጋሪ ሊሆንባቸው ይችላል። በሱሪናም አንዱ ጥሩ ቁመና ያለው ወጣት ወደ አንዲት የ14 ዓመት ልጃገረድ ቀርቦ ከእርሱ ጋር የፆታ ግንኙነት እንድትፈጽም ይጋብዛታል። መጽሐፍ ቅዱስ ከጋብቻ ውጭ እንዲህ ያለ ግንኙነት መፈጸምን እንደሚከለክል በማስረዳት እምቢተኛነቷን ትገልጻለች። ሌሎች የትምህርት ቤቱ ልጃገረዶች ግን ከዚህ ልጅ ጋር መተኛት የማይመኝ እንደሌለ በመንገር ሐሳቧን እንድትለውጥ ግፊት ለማሳደር በመሞከር አላገጡባት። ሆኖም ይህች ልጅ ከአቋሟ ፍንክች አላለችም። ከጥቂት ሳምንታት በኋላ ልጁ ታምሞ ሲመረመር የኤች አይ ቪ ቫይረስ እንዳለበት ተረጋገጠ። ልጅቷ ‘ከዝሙት ራቁ’ የሚለውን የይሖዋን ትእዛዝ በመከተሏ ደስተኛ ሆናለች። (ሥራ 15:​28, 29) የይሖዋ ምሥክሮች ትክክለኛ ለሆነው ነገር የጸና አቋም ባላቸው በመካከላቸው ባሉት ወጣቶች ይኮራሉ። የእነርሱም ሆነ የወላጆቻቸው እምነት የይሖዋ አምላክን ስም ‘ያስውባል’ ወይም በሌላ አባባል ለስሙ ክብር ያመጣል።​—⁠ኢሳይያስ 60:​21ለ

ጭማሪው የተገኘው ከይሖዋ ነው

18. (ሀ) ይሖዋ ለሕዝቦቹ ምን ታላላቅ ነገሮችን አድርጎላቸዋል? (ለ) ጭማሪው ገና እንደሚቀጥል የሚያሳየው ምንድን ነው? በብርሃን መመላለሳቸውን የሚቀጥሉ ሰዎች ምን ክብራማ ተስፋ ይጠብቃቸዋል?

18 አዎን፣ ይሖዋ በሕዝቦቹ ላይ ብርሃኑን እየፈነጠቀ፣ እየባረካቸው፣ እየመራቸውና እያጠነከራቸው ነው። በዚህ በ20ኛው መቶ ዘመን የሚከተሉት የኢሳይያስ ቃላት ፍጻሜያቸውን ሲያገኙ ተመልክተዋል:- “ታናሹ ለሺህ የሁሉም ታናሹ ለብርቱ ሕዝብ ይሆናል፤ እኔ እግዚአብሔር በዘመኑ ይህን አፋጥነዋለሁ።” (ኢሳይያስ 60:​22) በ1919 ከነበረው እፍኝ የማይሞላ ቁጥር ተነሥቶ ዛሬ ‘ታናሹ ሺህ’ ሆኗል። አሁንም እድገቱ ገና አላበቃም! ባለፈው ዓመት 14, 088, 751 ሰዎች በኢየሱስ ሞት መታሰቢያ በዓል ላይ ተገኝተዋል። ከእነዚህ መካከል ብዙዎቹ የይሖዋ ምሥክሮች አይደሉም። በዚህ ትልቅ ትርጉም ያለው በዓል ላይ መገኘታቸው ያስደስተናል። ወደ ብርሃን የሚያደርጉትንም ጉዞ እንዲገፉበት እናበረታታቸዋለን። ይሖዋ አሁንም ደማቅ ብርሃኑን በሕዝቡ ላይ እያበራ ነው። ወደ ድርጅቱ ለመምጣት አሁንም በሩ ክፍት ነው። እንግዲያውስ ሁላችንም በይሖዋ ብርሃን መመላለሳችንን ለመቀጠል ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ። ይህን ማድረጋችን ዛሬ የሚያስገኝልን በረከት እንዴት ታላቅ ነው! ወደፊት ደግሞ መላው ፍጥረት ይሖዋን በሚያወድስበትና በክብሩ ታላቅነት በሚደሰትበት ጊዜ እንዴት ያለ የደስታ ምንጭ ይሆንልናል!​—⁠ራእይ 5:​13, 14

ልታብራራ ትችላለህን?

በእነዚህ የመጨረሻ ቀናት የይሖዋን ክብር የሚያንጸባርቁት እነማን ናቸው?

የይሖዋ ሕዝቦች ቅንዓት እንዳልቀነሰ የሚያረጋግጠው ምንድን ነው?

የይሖዋ ምሥክሮች ራሳቸውን ያስጠመዱባቸው አንዳንድ በጎ ሥራዎች ምንድን ናቸው?

ጠንካራ ተቃውሞ ቢኖርም ስለ ምን ነገር እርግጠኞች ነን?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[ከገጽ 17-20 የሚገኝ ሰንጠረዥ]

የ1999 የአገልግሎት ዓመት የይሖዋ ምሥክሮች ዓለም አቀፍ ሪፖርት

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሰዎች አሁንም ወደ ይሖዋ ድርጅት እየጎረፉ ነው

[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ይሖዋ ብርሃንን ለሚያፈቅሩ ሰዎች በሩ ክፍት እንደሆነ እንዲቆይ በማድረጉ ደስተኞች ነን