በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

እምነት ሕይወትህን ሊለውጠው ይችላል

እምነት ሕይወትህን ሊለውጠው ይችላል

እምነት ሕይወትህን ሊለውጠው ይችላል

“በአምላክም ሳያምኑ ጥሩ ሥነ ምግባር ይዞ መመላለስ እንደሚቻል የተረጋገጠ ነው።” ይህንን ያሉት ስለ አምላክ ማወቅ አይቻልም የሚል አመለካከት ያላቸው አንድ ሴት ናቸው። በአምላክ የማያምኑ ቢሆንም ልጆቻቸውን በሙሉ በጥሩ ሥነ ምግባር ኮትኩተው እንዳሳደጉና ልጆቻቸውም በተራቸው የራሳቸውን ልጆች በተመሳሳይ መንገድ እንዳሳደጉ ተናግረዋል።

ታዲያ ይህ ማለት በአምላክ ማመን አያስፈልግም ማለት ነውን? እኚህ ሴት እንደዚያ ማለት የፈለጉ ይመስላል። በአምላክ የማያምኑ ሰዎች ሁሉ መጥፎ ይሆናሉ ማለት እንዳልሆነ ግልጽ ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ አምላክን ስለማያውቁ ነገር ግን ‘ከባሕርያቸው የሕግን ትእዛዝ ስለሚያደርጉ አሕዛብ’ ተናግሯል። (ሮሜ 2:​14) ስለ አምላክ ማወቅ አይቻልም የሚሉትን ጨምሮ ማንኛውም ሰው ሲወለድ ጀምሮ ሕሊና አለው። ብዙ ሰዎች ትክክል እና ስህተት የሆነውን ነገር የሚነግራቸውን የተፈጥሮ ዳኛ በለገሳቸው አምላክ ለማመን ባይፈቅዱም ሕሊናቸው በሚመራቸው መንገድ ለመሄድ ይሞክራሉ።

ይሁን እንጂ ያለ ተጨማሪ እገዛ ሕሊና በራሱ ከሚሰጠው መመሪያ ይልቅ በአምላክ ላይ መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረት ያለው ጠንካራ እምነት ማሳደር ለመልካም ሥራ በመገፋፋት ረገድ የበለጠ ኃይል አለው። የአምላክ ቃል በሆነው በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ እምነት ሕሊናን ይመራዋል፤ እንዲሁም መልካምና ክፉ የሆነውን በመለየት ረገድ ይበልጥ የሰላ እንዲሆን ያደርገዋል። (ዕብራውያን 5:​14) ከዚህም በላይ እምነት ሰዎች በከባድ ተጽእኖ ሥር ሆነውም ከፍተኛ የሥነ ምግባር ደረጃቸውን እንዲጠብቁ የሚያስችል ጥንካሬ እንዲኖራቸው ያደርጋል። ለምሳሌ ያህል በ20ኛው መቶ ዘመን በብዙ አገሮች ሥልጣን የተቆናጠጡት ብልሹ መንግሥታት ጥሩ ምግባር የነበራቸውን ብዙ ሰዎች አሰቃቂ የጭካኔ ድርጊት እንዲፈጽሙ አስገድደዋል። ይሁን እንጂ በአምላክ ላይ እውነተኛ እምነት ያላቸው ሰዎች ሕይወታቸውን አደጋ ላይ የሚጥል ቢሆንም እንኳ የሚመሩበትን መሠረታዊ ሥርዓት ለመተው ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል። ከዚህም በላይ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ እምነት ሰዎችን ሊለውጥ ይችላል። ያለቀለት የሚመስለውን ሕይወታቸውን ሊታደግላቸውና ከከባድ ስህተት ሊጠብቃቸው ይችላል። ጥቂት ምሳሌዎችን ተመልከት።

እምነት የቤተሰብን ሕይወት ሊለውጥ ይችላል

“በእምነታችሁ ምክንያት የማይቻል የሚመስል ነገር ለማግኘት በቅታችኋል።” አንድ እንግሊዛዊ ዳኛ ይህን የተናገሩት የጆንንና የታኒያን ልጆች የማሳደግ ሕጋዊ መብት በተመለከተ ውሳኔ ባስተላለፉበት ጊዜ ነበር። ጆንና ታኒያ ጉዳያቸው ወደ ባለ ሥልጣኖች በቀረበበት ጊዜ በሕግ ተጋብተው የሚኖሩ ሰዎች አልነበሩም፤ የቤተሰብ ሕይወታቸውም ምስቅልቅል ያለ ነበር። ጆን የአደገኛ ዕፅና የቁማር ሱሰኛ ስለነበር እነዚህን መጥፎ ልማዶቹን ለማርካት የሚያስችል ገንዘብ ለማግኘት ሲል በወንጀል ተግባር ተሠማራ። ልጆቹንና እናታቸውን ዞር ብሎ ማየት ተወ። ታዲያ እንዲለወጥ ያደረገው ምን “ተዓምር” ተፈጠረ?

አንድ ቀን ጆን ትንሹ የወንድሙ ልጅ ስለ ገነት ሲናገር ሰምቶ በነገሩ ስለተማረከ የልጁን ወላጆች ይጠይቃቸዋል። የልጁም ወላጆች የይሖዋ ምሥክሮች ስለሆኑ ጆን ስለዚህ ጉዳይ ከመጽሐፍ ቅዱስ እንዲማር ረዱት። ቀስ በቀስ ጆንና ታኒያ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ እምነት በማዳበራቸው ሕይወታቸው ተለወጠ። በሕጋዊ መንገድ በጋብቻ ተሳስረው መኖር ጀመሩ። ሌሎች መጥፎ ልማዶቻቸውንም አሸነፉ። ስለ ቤተሰብ ሕይወታቸው ያጠኑ የነበሩት ባለ ሥልጣኖች ከጥቂት ጊዜ በፊት ጨርሶ የማይታሰብ የሚመስል ነገር እንደተከናወነ አስተዋሉ። ልጆቻቸውን በሥርዓት ለማሳደግ የሚያስችል ንጹሕ ቤት ያለው ደስተኛ ቤተሰብ ሆነዋል። ዳኛው ይህን “ተዓምር” ያስገኘው የጆንና የታኒያ አዲሱ እምነት ነው ማለታቸው ስህተት አልነበረም።

ከእንግሊዝ በሺህ የሚቆጠሩ ኪሎ ሜትሮች ርቆ በሚገኝ አካባቢ የምትኖር አንዲት ባለትዳር ወጣት ትዳሯን በማፍረስ በየዓመቱ ተመሳሳይ አሳዛኝ ውሳኔ ከሚያደርጉ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች አንዷ ልትሆን አስባ ነበር። አንድ ልጅ የነበራት ቢሆንም ባሏ በዕድሜ በጣም ይበልጣት ነበር። ከዚህ የተነሣ ዘመዶቿ ባሏን እንድትፈታው ይወተውቷት ስለነበር ፍቺ ለመፈጸም አንዳንድ ዝግጅት ማድረግ ጀምራለች። ይሁን እንጂ የይሖዋ ምሥክር ከሆነች ሴት ጋር መጽሐፍ ቅዱስ እያጠናች ነበር። ምሥክሯ ስለ ሁኔታው ባወቀች ጊዜ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ትዳር ምን እንደሚል፣ ለምሳሌ ያህል ጋብቻ ከአምላክ የተገኘ ስጦታ መሆኑንና አቃልላ ልትመለከተው የሚገባ ነገር እንዳልሆነ አስረዳቻት። (ማቴዎስ 19:​4-6, 9) ሴትየዋ ‘የገዛ ዘመዶቼ ቤተሰባችን እንዲፈርስ ሲፈልጉ ይቺ ባዕድ የሆነች ሴት ቤተሰባችን እንዳይፈርስ ይህን ያህል መጣሯ ያስገርማል’ በማለት ለራሷ አሰበች። አዲሱ እምነቷ ትዳሯ እንዳይፈርስ ረድቷታል።

ውርጃ በቤተሰብ ሕይወት ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድር አሳዛኝ ድርጊት ነው። በየዓመቱ 45 ሚልዮን ሕፃናት ሆን ተብሎ በሚፈጸም ውርጃ ምክንያት ሕይወታቸውን እንደሚያጡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሪፖርት ገምቷል። ስለሚፈጸመው ስለ እያንዳንዱ ውርጃ ራሱ ካሰብን የሚያሳዝን ነው። የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት በፊሊፒንስ የምትገኝ አንዲት ሴት እንዲህ ያለውን አሳዛኝ ድርጊት እንዳትፈጽም ጠብቋታል።

ሴትየዋ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ተገናኘችና አምላክ ከእኛ የሚፈልገው ምንድን ነው?  a የተባለ መጽሐፍ ቅዱስ ማጥኛ ብሮሹር ትወስድና ጥናት ትጀምራለች። መጽሐፍ ቅዱስ ለማጥናት የተስማማችበት ምክንያት ምን እንደሆነ ከወራት በኋላ ተናግራለች። ምሥክሮቹ መጀመሪያ ሄደው ሲያነጋግሯት ነፍሰ ጡር የነበረች ቢሆንም እርሷና ባሏ ፅንሱን ለማስወረድ ተስማምተው ነበር። ነገር ግን በ24ኛው ገጽ ላይ ያለው በእናቱ ማሕፀን ያለን ልጅ የሚያሳየው ሥዕል የሴትየዋን ልብ ነካው። ከዚያ ጋር ተያይዞ የቀረበው ‘የሕይወት ምንጭ አምላክ’ ስለሆነ ሕይወት ቅዱስ ነው የሚለው መጽሐፍ ቅዱሳዊ ማብራሪያ ሐሳቧን ቀይራ ልጁን ለማሳደግ እንድትወስን አደረጋት። (መዝሙር 36:​9) አሁን የአንድ ደስ የሚል ጤናማ ልጅ እናት ሆናለች።

እምነት የተናቁትን ሰዎች ይረዳቸዋል

በኢትዮጵያ ጉስቁልቁል ያለ ልብስ የለበሱ ሁለት ሰዎች የይሖዋ ምሥክሮች ወደሚያደርጉት የአምልኮ ስብሰባ ሄዱ። በስብሰባው መጨረሻ ላይ አንድ ምሥክር በወዳጃዊ መንፈስ ቀርቦ ተዋወቃቸው። ሰዎቹ ገንዘብ እንዲሰጣቸው ለመኑት። ምሥክሩ ግን የሰጣቸው ገንዘብ ሳይሆን ከዚያ የተሻለ ነገር ነበር። በአምላክ ላይ እምነት እንዲኖራቸው አበረታታቸው። ይህም ‘ከወርቅ የበለጠ ዋጋ’ ያለው ነገር ነው። (1 ጴጥሮስ 1:​7) ከሁለቱ አንዱ ጥሩ ምላሽ በማሳየት መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት ጀመረ። ይህም ሕይወቱን ለወጠው። በእምነት እያደገ ሲሄድ ትንባሆ ማጨሱን፣ ስካሩን፣ የሥነ ምግባር ብልግናውን እንዲሁም ጫት መቃሙን አቆመ። ከመለመን ይልቅ ራሱን እንዴት ማስተዳደር እንደሚችል ተምሮ አሁን ንጹህና አርኪ ሕይወት መምራት ጀምሯል።

በኢጣሊያ የ47 ዓመት ዕድሜ ያለው አንድ ሰው አሥር ዓመት ተፈርዶበት በእስር ቤቱ ለሚገኙ እስረኞች የሥነ አእምሮ ሕክምና በሚሰጥበት ሆስፒታል ውስጥ ይገባል። መንፈሳዊ እገዛ ለመስጠት ወደ እስር ቤቱ እንዲገባ የተፈቀደለት አንድ የይሖዋ ምሥክር መጽሐፍ ቅዱስ ያስጠናው ጀመር። ሰውዬው ፈጣን እድገት አደረገ። እምነት ሕይወቱን በከፍተኛ ደረጃ ስለለወጠለት ሌሎች እስረኞች ችግራቸውን ለማሸነፍ የሚረዳ ምክር ለማግኘት ወደ እርሱ ይመጡ ጀመር። በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተው እምነቱ በሌሎች ዘንድ አክብሮትና ጥሩ ግምት እንዲሁም በእስር ቤቱ ባለ ሥልጣናት ዘንድ አመኔታ እንዲያተርፍ ረድቶታል።

ጋዜጦች ባለፉት ጥቂት ዓመታት በአፍሪካ ውስጥ ስለተደረጉ የእርስ በርስ ጦርነቶች ዘግበዋል። በተለይ ደግሞ ገና በሕፃንነታቸው ለጦርነት ስለሚመለመሉ ልጆች የሚገልጸው ዘገባ በጣም የሚዘገንን ነው። እነዚህ ልጆች ለተሰለፉለት አንጃ ያላቸውን ታማኝነት እንዲያረጋግጡ ሲባል አደገኛ ዕፅ እንዲወስዱ፣ ጨካኞች እንዲሆኑ እንዲሁም በገዛ ዘመዶቻቸው ላይ ሰብዓዊ ርኅራኄ የጎደለው ድርጊት እንዲፈጽሙ ግፊት ይደረግባቸዋል። በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተው እምነት እንዲህ ዓይነት ሕይወት ያላቸውን ሰዎች ለመለወጥ የሚያስችል ጥንካሬ አለውን? ቢያንስ በሁለት አጋጣሚዎች እንዲህ ዓይነት ጥንካሬ እንዳለው ታይቷል።

በላይቤሪያ የሚገኘው አሌክስ በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያገለግል ነበር። ይሁንና በ13 ዓመቱ ከአንዱ ተዋጊ አንጃ ጋር ተቀላቀለና በብዙዎች ዘንድ በመጥፎ የሚታወቅ አደገኛ ወታደር ሆነ። ጀግና ተዋጊ እንዲሆን ሲልም ጠንቋይ ዘንድ ሄደ። አሌክስ ብዙዎቹ ጓደኞቹ ሲገደሉ አይቷል። በ1997 ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ሲገናኝ ምሥክሮቹ ዝቅ አድርገው እንዳልተመለከቱት አስተዋለ። ከዚህ ይልቅ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ዓመፅ ምን እንደሚል አስተማሩት። አሌክስ ከሠራዊቱ ወጣ። እምነቱ እያደገ ሲሄድም “ከክፉ ፈቀቅ ይበል፣ መልካምንም ያድርግ፣ ሰላምን ይሻ ይከተለውም” የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር ሥራ ላይ ማዋል ጀመረ።​—⁠1 ጴጥሮስ 3:​11

ይህ በእንዲህ እንዳለ ገና በሕፃንነቱ ወደ ውትድርና ዓለም የገባ ሳምሶን የሚባል ልጅ አሁን አሌክስ ወደሚኖርበት መንደር ይመጣል። ሳምሶን የቤተ ክርስቲያን መዘምራን አባል የነበረ ቢሆንም በ1993 ወደ ውትድርናው ዓለም ገብቶ በአደገኛ ዕፅ ሱሰኛነት፣ በመናፍስት ሥራ እና በሥነ ምግባር ብልግና ተጠመደ። ከዚያም በ1997 ትጥቅ እንዲፈታ ተደረገ። ሳምሶን ከአንድ ጓደኛው ጋር ተገናኝቶ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን እንዲያጠና ማበረታቻ ያገኘው ልዩ የፀጥታ ኃይል አባል ለመሆን ወደ ሞኖሮቪያ እያቀና ሳለ ነበር። ከዚህ የተነሣ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ እምነት አዳብሯል። ይህም የጦረኝነት ጎዳናውን ለመተው የሚያስችል ድፍረት እንዲያገኝ ረድቶታል። ዛሬ አሌክስና ሳምሶን ሰላማዊና ሥነ ምግባራዊ ሕይወት ይመራሉ። በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተው እምነታቸው ባይሆን ኖሮ ያን የመሰለውን በጭካኔ ድርጊት የተሞላ ሕይወታቸውን ሊለውጥ የሚችል ነገር ይኖር ነበርን?

ትክክለኛው ዓይነት እምነት

በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ እውነተኛ እምነት ያለውን ኃይል ከሚያሳዩት በጣም ብዙ ምሳሌዎች መካከል እነዚህ ጥቂቶቹ ብቻ ናቸው። እርግጥ ነው፣ በአምላክ እናምናለን ብለው የሚናገሩ ሰዎች ሁሉ ከመጽሐፍ ቅዱስ የአቋም ደረጃዎች ጋር ተስማምተው ይኖራሉ ማለት አይደለም። እንዲያውም በአምላክ እናምናለን ከሚሉት ከአንዳንዶቹ ሰዎች ይልቅ በአምላክ አናምንም የሚሉ አንዳንዶች የተሻለ ሕይወት ይመሩ ይሆናል። ይህ የሆነበት ምክንያት በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ እምነት በአምላክ አምናለሁ ከማለት የበለጠ ነገር ስለሚጨምር ነው።

ሐዋርያው ጳውሎስ እምነት “ተስፋ ስለ ምናደርገው ነገር የሚያስረግጥ፣ የማናየውንም ነገር የሚያስረዳ ነው” ብሏል። (ዕብራውያን 11:​1) በመሆኑም እምነት በማይታበሉ ማስረጃዎች ላይ ተመሥርቶ ስለማይታዩት ነገሮች በጽኑ ማመንንም ይጠይቃል። በተለይ አምላክ እንዳለ፣ ስለ እኛ እንደሚያስብና ፈቃዱን የሚያደርጉ ሰዎችን የሚባርካቸው መሆኑን በሚመለከት ፍጹም እርግጠኛ መሆንን ይጨምራል። ሐዋርያው ጳውሎስ “ወደ እግዚአብሔር የሚደርስ እግዚአብሔር እንዳለ ለሚፈልጉትም ዋጋ እንዲሰጥ ያምን ዘንድ ያስፈልገዋልና” ብሏል።​—⁠ዕብራውያን 11:​6

የጆንንና የታኒያን እንዲሁም በዚህ ርዕስ ውስጥ የተጠቀሱትን የሌሎችንም ሕይወት የለወጠው እንዲህ ያለ እምነት ነው። የአምላክ ቃል የሆነው መጽሐፍ ቅዱስ ውሳኔ ለማድረግ የሚያስችል መመሪያ ይሰጠናል የሚል ሙሉ ትምክህት እንዲኖራቸው ረድቷቸዋል። ለእነርሱ አመቺ መሆኑን ብቻ በማየት ስህተት የሆነ ነገር ከማድረግ ጊዜያዊ መሥዋዕትነት እንዲከፍሉ ረድቷቸዋል። ሁሉም ተሞክሮዎች አንዳቸው ከሌላው የሚለያዩ ቢሆንም አጀማመራቸው ተመሳሳይ ነው። ከይሖዋ ምሥክሮች አንዱ ከእነርሱ ጋር መጽሐፍ ቅዱስ በማጥናቱ ሰዎቹ መጽሐፍ ቅዱስ “የእግዚአብሔር ቃል ሕያው ነውና፣ የሚሠራም” ነው የሚለው ነገር እውነት መሆኑን ማስተዋል ችለዋል። (ዕብራውያን 4:​12) የአምላክ ቃል ያለው ኃይል እያንዳንዳቸው ሕይወታቸውን በተሻለ መንገድ ለመምራት የሚያስችል ለውጥ እንዲያደርጉ ረድቷቸዋል።

ዛሬ የይሖዋ ምሥክሮች ከ230 በሚበልጡ አገሮችና የባሕር ደሴቶች ላይ በመንቀሳቀስ ላይ ናቸው። አንተም ከእነርሱ ጋር መጽሐፍ ቅዱስ እንድታጠና ይጋብዙሃል። ለምን? በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ እምነት በአንተም ሕይወት ውስጥ ቢሆን ትልቅ ለውጥ ሊያመጣ እንደሚችል ስለሚያምኑ ነው።

[የግርጌ ማስታወሻ]

a ኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር የተዘጋጀ።

[በገጽ 3 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ እምነት ሰዎች በሕይወታቸው ጥሩ ለውጥ እንዲያደርጉ ይረዳቸዋል

[በገጽ 2 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

Title card of Biblia nieświeska by Szymon Budny, 1572