ከጉብዝናችን ወራት ጀምሮ ፈጣሪያችንን ማሰብ
የሕይወት ታሪክ
ከጉብዝናችን ወራት ጀምሮ ፈጣሪያችንን ማሰብ
ዴቪድ ዚ ሂብሽመን እንደተናገረው
“ይህ የሕይወቴ ማብቂያ ከሆነ በእርግጥ ይሖዋን በታማኝነት አገልግያለሁ የሚል ተስፋ አለኝ። ይሖዋን የምለምነው ነገር ውድ አካሌን ዴቪድን እንዲንከባከብልኝ ነው። ይሖዋ ሆይ፣ እርሱን ስለሰጠኸኝ እንዲሁም ስለትዳራችን ላመሰግንህ እወዳለሁ። እጅግ ግሩም፣ እጅግ አስደሳች ትዳር ነበር!”
መጋቢት 1992 ከባለቤቴ የቀብር ሥነ ሥርዓት ከተመለስኩ በኋላ የግል ማስታወሻዋ ላይ የጻፈችውን ይህን የመጨረሻ ቃሏን ሳነብ በውስጤ የተሰማኝን ስሜት ገምቱ። ልክ ከአምስት ወር በፊት ሔለን በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ያሳለፈችውን 60ኛ ዓመት አክብረን ነበር።
በ1931 በዩ ኤስ ኤ፣ ኦሃዮ፣ ኮሎምበስ በተካሄደው የአውራጃ ስብሰባ ላይ እኔና ሔለን ጎን ለጎን ተቀምጠን የነበረበት ቀን በደንብ ትዝ ይለኛል። ሔለን ገና 14 ዓመት የሞላት ባይሆንም እንኳ የስብሰባውን ከፍተኛ ትርጉም ከእኔ በተሻለ ሁኔታ ተገንዝባ ነበር። መበለት የነበረችው እናቷ እና እሷ ስብሰባው ከተካሄደ ከጥቂት ጊዜ በኋላ አቅኚ መሆናቸው (የሙሉ ጊዜ ወንጌላውያን የሆኑ የይሖዋ ምሥክሮች የሚታወቁበት ስም ነው) ሔለን ለአገልግሎቱ የነበራትን ቅንዓት የሚያሳይ ነበር። በደቡባዊ ዩናይትድ ስቴትስ ገጠራማ አካባቢዎች ለመስበክ ሲሉ ምቾት ያለው ቤታቸውን ለቅቀው ሄዱ።
ያገኘሁት ክርስቲያናዊ ውርስ
በ1910 ወላጆቼ ሁለት ሕፃናት ልጆቻቸውን ይዘው ከምሥራቃዊ ፔንሲልቫኒያ የክልሉ ምዕራባዊ ክፍል ወደሆነው ወደ ግሮቭ ሲቲ ተዛወሩ። እዚያ የቅድሚያ ክፍያ ሰጥተው አንድ አነስ ያለች ቤት ገዙ፤ ከዚያም የሪፎርምድ ቸርች ተከታዮች ሆኑ። ይህ ከሆነ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ዊልያም ኢቫንስ የሚባል አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪ (በወቅቱ የይሖዋ ምሥክሮች የሚጠሩት በዚህ ስም ነበር) መጥቶ አነጋገራቸው። በዚያን ወቅት ዕድሜው በ20ዎቹ አጋማሽ የሚገኘው አባቴና ከእርሱ በአምስት ዓመት የምታንሰው እናቴ ይህን ወዳጃዊ መንፈስ ያለው የዌልስ ሰው በጥሞና አዳመጡትና ቤታቸው ምሳ ጋበዙት። ብዙም ሳይቆይ የተማሩትን የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ተቀበሉ።
አባዬ ለጉባኤው ቀረብ እንድንል ሲል ቤተሰቡን ይዞ 40 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ወደምትገኘው የሻሮን ከተማ ተዛወረ።
ከተወሰኑ ወራት በኋላ በ1911 ወይም በ1912 አባዬና እማዬ ተጠመቁ። የጥምቀት ንግግሩን የሰጠው የመጀመሪያው የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ፕሬዚዳንት የነበረው ቻርለስ ቴዝ ራስል ነበር። ታኅሣሥ 4, 1916 ስወለድ ለወላጆቼ አምስተኛ ልጅ ነበርኩ። በተወለድኩበት ጊዜ “ሌላ ተወዳጅ ወንድም” ተወለደ ሲሉ ተናገሩ። ይህም የሆነው “ተወዳጅ” የሚል ትርጉም ያለው ዴቪድ የሚል ስም ስለወጣልኝ ነበር።የአራት ሳምንት ልጅ ሳለሁ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደተገኘሁበት የአውራጃ ስብሰባ ይዘውኝ ሄዱ። በእነዚያ የቀድሞዎቹ ዓመታት የጉባኤ ስብሰባዎች ላይ ለመገኘት አባቴና ወንድሞቼ ብዙ ኪሎ ሜትሮች በእግር ይጓዙ የነበረ ሲሆን እማዬ ደግሞ እኔንና እህቴን በከተማ ውስጥ ባቡር ትወስደን ነበር። ስብሰባዎቹ የጠዋትና የከሰዓት በኋላ ክፍለ ጊዜ ነበራቸው። ቤት ውስጥ የምናደርገው ውይይት አብዛኛውን ጊዜ መጠበቂያ ግንብ እና ወርቃማው ዘመን (ቀደም ሲል ንቁ! የሚታወቅበት ስም ነው) በተባሉት መጽሔቶች ላይ በሚወጡ ርዕሶች ያተኮረ ነበር።
ጥሩ ምሳሌ ከሚሆኑ ሰዎች መጠቀም
በዚያን ጊዜ ፒልግሪም በመባል የሚታወቁ ብዙ ተጓዥ ተናጋሪዎች ጉባኤያችንን ይጎበኙ ነበር። በአብዛኛው አንድ ወይም ሁለት ቀን እኛ ጋር ያሳልፉ ነበር። እስካሁን ድረስ ከአእምሮዬ የማይጠፋው አንዱ ተናጋሪ ‘ከጉብዝናው ወራት’ ጀምሮ ታላቁን ፈጣሪውን ያሰበው ዎልተር ጄ ቶርን ነው። (መክብብ 12:1) ልጅ በነበርኩበት ጊዜ አባቴ የሰው ልጆችን ታሪክ በምስልና በድምፅ የሚያቀርበውን ባለ አራት ክፍል “የፍጥረት ፎቶ ድራማ” ለማሳየት ሲሄድ አብሬው እሄድ ነበር።
ምንም እንኳ ወንድም ኢቫንስና ባለቤቱ ሚርያም ልጆች ባይኖሯቸውም ለቤተሰባችን መንፈሳዊ ወላጆችና አያቶች ሆነውልን ነበር። ዊልያም ሁልጊዜ አባቴን “ልጄ” ብሎ ይጠራው የነበረ ሲሆን እርሱና ሚርያም ቤተሰባችን ውስጥ የወንጌላዊነት መንፈስ እንዲሰርጽ አድርገዋል። በ20ኛው ምዕተ ዓመት መጀመሪያ ላይ ወንድም ኢቫንስ፣ ስዋንሲ አካባቢ በሚገኙ ቦታዎች የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ለማዳረስ ሲል ወደ ዌልስ በተደጋጋሚ ተጉዟል። እዚያም ከአሜሪካ የመጣው ሰባኪ በመባል ይታወቅ ነበር።
በ1928 ወንድም ኢቫንስ ሥራውን አቁሞ በዌስት ቨርጂኒያ ተራራማ ቦታዎች መስበክ ጀመረ። ሁለት ታላላቅ ወንድሞቼ ማለትም የ21 ዓመቱ ክላረንስ እና የ19 ዓመቱ ካርል አብረውት ማገልገል ጀመሩ። አራት ወንዶች ነበርን፤ አራታችን በሙሉ ጊዜ አገልግሎት በርካታ ዓመታት አሳልፈናል። እንዲያውም በወጣትነት ዕድሜያችን ሁላችንም የይሖዋ ምሥክሮች ተጓዥ የበላይ ተመልካቾች ሆነን አገልግለናል። አሁን በ90ዎቹ ዕድሜ ላይ የምትገኘው የእናቴ የመጨረሻዋ ታናሽ እህት ሜሪ በቅርብ ጊዜ እንዲህ ስትል ጽፋልኛለች:- “ወንድም ኢቫንስ ለአገልግሎቱ ከነበረው ቅንዓት የተነሳ ለስብከት ወደ ግሮቭ ሲቲ በመምጣቱ ምንኛ አመስጋኞች ነን!” አክስቴ ሜሪ ከጉብዝናቸው ወራት ጀምሮ ፈጣሪያቸውን ካሰቡት መካከል አንዷ ነች።
በአውራጃ ስብሰባዎች ላይ መገኘት
በ1922 በሴዳር ፖይንት ኦሃዮ በተካሄደው አዲስ ምዕራፍ ከፋች በሆነው የአውራጃ ስብሰባ ላይ መገኘት የቻሉት አባዬና ክላረንስ ብቻ ነበሩ። ሆኖም በ1924 መኪና ስለነበረን ቤተሰባችን ባጠቃላይ በኮለምበስ ኦሃዮ በተደረገው የአውራጃ ስብሰባ ላይ ተገኝቶ ነበር። ልጆች የሆንነው ለስምንት ቀን በሚቆየው ስብሰባ ላይ ራሳችን ባጠራቀምነው ገንዘብ ምግብ እንድንገዛ ይጠበቅብን ነበር። ወላጆቼ የቤተሰቡ አባላት ሁሉ ራሳቸውን መደገፍ መቻል አለባቸው የሚል አመለካከት ነበራቸው። በመሆኑም ዶሮና ጥንቸል እናረባ ነበር፤ እንዲሁም የንብ ቀፎዎች ነበሩን። በተጨማሪም ወንዶች የሆነው ሁሉ ጋዜጣ የምናድላቸው ደንበኞች ነበሩን።
በ1927 በቶሮንቶ ካናዳ የተካሄደው የአውራጃ ስብሰባ የሚደረግበት ጊዜ ሲቃረብ ፓል የሚባል የስድስት ወር ሕፃን ወንድም ነበረን። ወላጆቼ ከቀሩት ልጆች ጋር ወደ ቶሮንቶ ሲሄዱ እኔ ግን ባለ ትዳር የሆነችው አክስቴ እየረዳችኝ ፖልን ለመንከባከብ ቤት እንድቀር ተደረገ። ለዚህ
ማካካሻ አሥር ዶላር ተሰጠኝና አንድ አዲስ ሙሉ ልብስ ገዛሁ። ለስብሰባዎች በአግባቡ እንድንለብስና ልብሳችንን በንጽሕና እንድንይዝ ሁልጊዜ ሥልጠና ይሰጠን ነበር።በ1931 በኮለምበስ ኦሃዮ የተደረገው ፈጽሞ የማይረሳው የአውራጃ ስብሰባ ሲካሄድ ክላረንስ እና ካርል ትዳር መሥርተው ከሚስቶቻቸው ጋር በአቅኚነት ያገለገሉ ነበር። ሁለቱም የሚኖሩት ራሳቸው በሠሩት ተንቀሳቃሽ ቤት ውስጥ ነበር። ካርል የዌስት ቨርጂኒያ፣ ዊሊንግ ተወላጅ የሆነችውን ክሌይር ሆስተንን አግብቶ ስለነበር በኮለምበስ በተካሄደው የአውራጃ ስብሰባ ላይ ከክሌይር ታናሽ እህት ከሔለን ጎን የተቀመጥኩት በዚህ ምክንያት ነበር።
የሙሉ ጊዜ አገልግሎት
የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን ያጠናቀኩት በ1932 የ15 ዓመት ልጅ ሳለሁ ስለነበር በሚቀጥለው ዓመት በደቡብ ካሮላይና በአቅኚነት ያገለግል ለነበረው ለወንድሜ ለክላረንስ አንዲት የሠራች መኪና ይዤለት ሄድኩ። ለአቅኚነት አገልግሎት አመልክቼ ከክላረንስና ከሚስቱ ጋር ማገልገል ጀመርኩ። በዚህ ጊዜ ሔለን በኬንታኪ ሆፕኪንስቪል በአቅኚነት እያገለገለች የነበረ ሲሆን ለመጀመሪያ ጊዜ ደብዳቤ ጻፍኩላት። የመልስ ደብዳቤዋ ላይ “አቅኚ ሆነሃል ወይ?” ስትል ጠየቀችኝ።
“አቅኚ ነኝ፤ በአቅኚነት ለመቀጠልም ተስፋ አደርጋለሁ” ስል መለስኩላት። ይህን ደብዳቤ ሔለን እስከሞተችበት ጊዜ ድረስ ወደ 60 ለሚጠጉ ዓመታት አስቀምጣዋለች። በዚያ ደብዳቤ ላይ ዘ ኪንግደም፣ ዘ ሆፕ ኦቭ ዘ ዎርልድ (እንግሊዝኛ) የተባለውን ቡክሌት በምሰብክበት የአገልግሎት ክልል ውስጥ ለሚገኙ ቄሶችና የሕግ ባለሥልጣኖች ማበርከቴን ነግሬያት ነበር።
በ1933 አባዬ በጎማ የሚሽከረከር የድንኳን ቤት ሠራልኝ። ድንኳኑ ርዝመቱ 2.4 ሜትር ስፋቱ ደግሞ 2 ሜትር የሆነ ከፊትና ከኋላ መስኮት ያለው ሲሆን ዙሪያውን በቋሚ ብረቶች የተወጠረ ሸራ የለበሰ ተጎታች ቤት ነበር። በአቅኚነት ባሳለፍኳቸው በቀጣዮቹ አራት ዓመታት ትንሿ መኖሪያዬ ይህች ቤት ነበረች።
በመጋቢት 1934 ክላረንስና ካርል፣ ሚስቶቻቸው፣ ሔለንና እናቷ፣ የክላረንስ አማችና እኔ ስምንት ሆነን በካሊፎርኒያ ሎስ አንጅለስ በሚካሄደው የአውራጃ ስብሰባ ላይ ለመገኘት ወደ ምዕራብ አመራን። አንዳንዶቹ የተጓዙትና የተኙት በእኔ ተጎታች ቤት ውስጥ ነበር። እኔ መኪናው ውስጥ ስተኛ የቀሩት ደግሞ ማደሪያ ተከራዩ። መኪና ተበላሽቶብን ስለነበር ሎስ አንጅለስ የደረስነው ለስድስት ቀን በሚቆየው የአውራጃ ስብሰባ ሁለተኛ ቀን ላይ ነበር። መጋቢት 26 ስብሰባው ላይ እኔና ሔለን በውኃ ጥምቀት አማካኝነት ራሳችንን ለይሖዋ መወሰናችንን አሳየን።
የአውራጃ ስብሰባው ላይ በወቅቱ የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ፕሬዚዳንት የነበረው ጆሴፍ ኤፍ ራዘርፎርድ ከሁሉም አቅኚዎች ጋር በግል ተገናኝቶ ነበር። ለመጽሐፍ ቅዱስ እውነት የቆምን ደፋር ተዋጊዎች መሆናችንን በመግለጽ አበረታታን። በዚህ ወቅት አቅኚዎች በአገልግሎታቸው መቀጠል እንዲችሉ የገንዘብ ድጎማ ለመስጠት ዝግጅት ተደርጎ ነበር።
በሕይወታችን ዘመን ሁሉ የጠቀመን ትምህርት
በሎስ አንጅለስ ከተካሄደው የአውራጃ ስብሰባ ስንመለስ ሁላችንም በደቡብ ካሮላይና፣ ቨርጂኒያ፣ ምዕራብ ቨርጂኒያ እና በኬንታኪ ክልሎች ለሚኖሩ ሰዎች የመንግሥቱን መልእክት ሰበክን። ከዓመታት በኋላ ሔለን ያን ጊዜ በተመለከተ እንዲህ ስትል ጽፋለች:- “ወደማናውቀው አገር በእንግድነት የመጣን ሰዎች ስለነበርን ድጋፍ የሚሰጠን ጉባኤም ሆነ የሚረዱን ወዳጆች አልነበሩንም። ሆኖም ትምህርት እያገኘሁ እንደነበር አሁን ተገንዝቤአለሁ። ተሞክሮ እያካበትሁ ነበር።”
እንዲህ ስትል ጠይቃለች:- “አንዲት ወጣት ከጓደኞቿና ከምትኖርበት አካባቢ ርቃ ሳለች ጊዜዋን እንዴት ትጠቀምበታለች? ያን ያህል ከባድ አልነበረም። አንድም የተሰላቸሁበት ቀን ትዝ አይለኝም። ብዙ አነብብ ነበር። የሚወጡትን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎች ከማንበብና ከማጥናት ወደኋላ ብለን አናውቅም። ከእናቴ ሳልርቅ የነበረንን ገንዘብ በአግባቡ መጠቀም፣ ዕቃ መገዛዛት፣ የመኪና ጎማ መቀየር፣ ምግብ ማብሰል፣ ልብስ መስፋትና መስበክ እማር ነበር። ምንም የሚቆጨኝ ነገር የለም፤ እንዲያውም ይህንኑ መድገም ብችል በደስታ አደርገው ነበር።”
ምንም እንኳ የሔለን እናት አንድ ቆንጆ ቤት የነበራት ቢሆንም በእነዚያ ዓመታት እርሷና ሔለን በአንዲት ትንሽ ተጎታች ቤት ውስጥ ባላቸው ነገር ረክተው በደስታ ይኖሩ ነበር። በ1937 በኮለምበስ ኦሃዮ ከተደረገው የአውራጃ ስብሰባ በኋላ የሔለን እናት ጤና እያጣች በመሄዷ ሆስፒታል ለመግባት ተገደደች። በምዕራብ ቨርጂኒያ፣ ፊሊፒ በተመደበችበት የአገልግሎት ቦታ እያለች ኅዳር 1937 ሞተች።
ጋብቻና ከዚያ በኋላ ያለው የአገልግሎት እንቅስቃሴ
ሰኔ 10, 1938 ምዕራብ ቨርጂኒያ፣ ዊሊንግ አቅራቢያ በኤልም ግሮቭ በሚገኘው ሔለን በተወለደችበት ቤት ውስጥ ቀለል ያለ ዝግጅት አድርገን እኔና ሔለን ተጋባን። የጋብቻ ንግግሩን የሰጠው እኔ ከመወለዴ ከጥቂት ዓመታት በፊት ለቤተሰቦቼ እውነትን የነገራቸው ተወዳጁ ወንድም ኢቫንስ ነበር። ከሠርጋችን በኋላ እኔና ሔለን ወደ ምሥራቃዊ ኬንታኪ ተመልሰን በአቅኚነት ለመቀጠል አቀድን። ይሁን እንጂ በዞን አገልጋይነት እንድንሠራ ጥሪ ሲቀርብልን ፈጽሞ ያልጠበቅነው ነገር ነበር። ይህ ሥራ በምዕራባዊ ኬንታኪና በአንዳንድ የቴኔሲ ክፍሎች የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች ቡድኖችን በአገልግሎታቸው ለመርዳት መጎብኘትን ያጠቃልል ነበር። በዚያን ጊዜ በጎበኘንባቸው ቦታዎች በሙሉ የነበሩት የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች 75 ያህል ብቻ ነበሩ።
በወቅቱ ብሔራዊ ስሜት የብዙዎችን አስተሳሰብ አዛብቶ ስለነበር በክርስቲያናዊ ገለልተኝነቴ የተነሳ ብዙም ሳልቆይ እታሠራለሁ የሚል ግምት አደረብኝ። (ኢሳይያስ 2:4) ይሁን እንጂ በነበረኝ የስብከት እንቅስቃሴ ታሪክ የተነሳ የምዝገባ ቦርዱ በሙሉ ጊዜ አገልግሎት እንድቀጥል የሚያስችል ፈቃድ ሰጠኝ።
በተጓዥነት የምናከናውነውን አገልግሎት ስንጀምር ሁሉም ሰው ማለት ይቻላል ገና ወጣቶች መሆናችንን ሳይጠቅስ አያልፍም ነበር። በኬንታኪ ሆፕኪንስቪል አንዲት እህት ሔለንን እቅፍ አድርጋ ከሳመቻት በኋላ “ታስታውሽኛለሽ?” ስትል ጠየቀቻት። በ1933 ሔለን ይህችን ሴት የባለቤቷ ንብረት በሆነው የከተማው የገበያ አዳራሽ ውስጥ አግኝታ መስክራላት ነበር። የሰንበት ትምህርት ቤት አስተማሪ የነበረች ቢሆንም ሔለን የሰጠቻትን መጽሐፍ ካነበበች በኋላ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ያልሆኑ ትምህርቶችን ስላስተማረቻቸው ተማሪዎቿን ይቅርታ ጠየቀች። ቤተ ክርስቲያኑን ለቅቃ ከወጣች በኋላ በምትኖርበት አካባቢ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት መስበክ ጀመረች። እኔና ሔለን በምዕራባዊ ኬንታኪ ለሦስት ዓመታት ስንጎበኝ ይቺ እህትና ባለቤቷ ቤታቸውን እንደቤታችን እንድንጠቀምበት ፈቅደውልን ነበር።
በእነዚያ ዓመታት በአካባቢው አነስተኛ ቁጥር ያላቸው ሰዎች የተገኙባቸው ትላልቅ ስብሰባዎች እናደርግ የነበረ ሲሆን ኤ ኤች ማክሚላን ከእነዚህ ስብሰባዎች በአንዱ ላይ አገልግሏል። ሔለን ልጅ በነበረችበት ጊዜ ወላጆቿ ቤት ያርፍ ስለነበር በስብሰባው ወቅት 5 ሜትር ርዝመት ያለው ተንቀሳቃሽ ቤታችን ውስጥ በነበረን አንድ ትርፍ አልጋ ላይ እያደረ እኛ ጋር ማረፍ መረጠ። እርሱም ቢሆን በ1900 የ23 ዓመት ልጅ በነበረበት ወቅት ሕይወቱን ለይሖዋ ወስኖ በጉብዝናው ዘመን ታላቁ ፈጣሪውን አስቧል።
በኅዳር 1941 ተጓዥ የበላይ ተመልካቾች የሚያከናውኑት ሥራ ለአጭር ጊዜ ተቋርጦ ስለነበር በኬንታኪ ሃዛርድ በአቅኚነት እንዳገለግል ተመደብኩ። እንደገና ከካርልና ከባለቤቱ ከክሌይር ጋር አብሮ የማገልገል አጋጣሚ አገኘን። እዚያ እያለን የሔለን የወንድሟ ልጅ ጆሴፍ ሆስተን ከእኛ ጋር በአቅኚነት ማገልገል ጀመረ። በብሩክሊን ኒው ዮርክ በሚገኘው በዓለም አቀፉ የይሖዋ ምሥክሮች ዋና መሥሪያ ቤት በታማኝነት እያገለገለ ሳለ ሃርት አታክ በተባለ የልብ በሽታ ድንገት እስከሞተበት እስከ 1992 ድረስ ወደ 50 ለሚጠጉ ዓመታት በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ተካፍሏል።
በ1943 በኮኔክቲከት ሮክቪል እንድናገለግል ተመደብን። እኔና ሔለን ማገልገል የለመድነው በደቡባዊ ዩናይትድ ስቴትስ ስለነበር ይህ ምድብ ወደ ሌላ ዓለም የሄድን ያህል ነበር። በሮክቪል ሔለን በቋሚነት በአንድ ሳምንት ከ20 የሚበልጡ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች ትመራ ነበር። መጨረሻ ላይ ለመንግሥት አዳራሽ የሚሆን አንድ አነስ ያለ ክፍል ተከራየንና የአንድ ትንሽ ጉባኤ ማዕከል ተደራጀ።
በሮክቪል እያገለገልን ሳለ በደቡብ ላንሲንግ ኒው ዮርክ በሚገኘው በጊልያድ የመጠበቂያ ግንብ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት በአምስተኛው ክፍል እንድንሳተፍ ጥሪ ቀረበልን። በኬንታኪ በአቅኚነት ስናገለግል ጓደኞቻችን የነበሩት ኦብሬ እና ብረዝ ቢቭንስ አብረውን እንደሚማሩ ስንሰማ በጣም ተደሰትን።
ትምህርት ቤትና አዲሱ ምድባችን
ምንም እንኳ ገና ወጣቶች የነበርን ቢሆንም አብዛኞቹ የክፍል ጓደኞቻችን ከእኛም ያንሱ ነበር። አዎን፣ ታላቁ ፈጣሪያቸውን በጉብዝናቸው ወራት አስታውሰዋል። የእኛ የምረቃ ሥነ ሥርዓት የተከናወነው ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ሊያበቃ በተቃረበበት በሐምሌ 1945 ነበር። በሚስዮናዊነት የምናገለግልበት አገር እስኪነገረን ድረስ በብሩክሊን ኒው ዮርክ በሚገኘው የፍላትቡሽ ጉባኤ እያገለገልን
ቆየን። በመጨረሻ በጥቅምት 21, 1946 ወንድምና እህት ቢቭንስን ጨምሮ ከስድስት የክፍል ጓደኞቻችን ጋር በጓቲማላ፣ ጓቲማላ ሲቲ ወደሚገኘው አዲሱ ቤታችን ተጓዝን። በዚያን ጊዜ በማዕከላዊ አሜሪካ በምትገኘው በዚህች አገር የነበሩት የይሖዋ ምሥክሮች 50 አይሞሉም ነበር።በሚያዝያ 1949 ጥቂት የምንሆን ሚስዮናውያን በስፋቱም ሆነ በእንቅስቃሴው የአገሪቱ ሁለተኛ ከተማ ወደሆነው ወደ ኩዊትዛልቴናንጎ ተዛወርን። ይህች ከተማ ከባሕር ወለል በላይ 2, 300 ሜትር ከፍታ ላይ የምትገኝ ሲሆን ተራራው ላይ ያለው አየር መንፈስ የሚያድስና ጥርት ያለ ነው። ሔለን በዚያ የነበረንን እንቅስቃሴ ጠቅለል አድርጋ ስትገልጽ እንዲህ በማለት ጽፋለች:- “በበርካታ ከተማዎችና መንደሮች ውስጥ የመስበክ መብት አግኝተን ነበር። ሌሊት በአሥር ሰዓት ገደማ ተነስተን በአውቶቡስ (በአብዛኛው በመስኮት ፋንታ ወደታች የሚዘረጋ ሸራ ያላቸው ናቸው) ሩቅ ወደሆነ ከተማ እንሄድ ነበር። ማምሻው ላይ ወደ ቤት እስክንመለስ ድረስ እዚያ ለስምንት ሰዓት ያህል እንሰብክ ነበር።” ዛሬ በኩዊትዛልቴናንጎ የሚገኙትን ስድስት ጉባኤዎች ጨምሮ በርካታ በሚሆኑት በእነዚህ ቦታዎች ጉባኤዎች አሉ።
ብዙም ሳይቆይ በካረቢያን የባሕር ዳርቻ በምትገኘው በስፋቷ ሦስተኛ በሆነችው ፖርቶ ባሪዮስ በምትባለው የጓቲማላ ከተማ የሚያገለግሉ ሚስዮናውያን አስፈልገው ነበር። ጓቲማላ ውስጥ ለአምስት ዓመት አብረናቸው ያገለገልነው ውድ ጓደኞቻችን ወንድምና እህት ቢቭንስ ወደዚህ አዲስ ምድብ ከተዛወሩት መካከል ነበሩ። ከእነርሱ በመለያየታችን በጣም ከማዘናችን የተነሣ በሕይወታችን ውስጥ ክፍተት እንደተፈጠረ ሆኖ ተሰምቶናል። በሚስዮናውያን ቤት ውስጥ የቀረነው እኔና ሔለን ብቻ ስለነበርን አነስ ወዳለ አፓርትመንት ተዛወርን። በ1955 እኔና ሔለን ይበልጥ ሞቃታማ በሆነው የማዛቴናንጎ ከተማ አዲስ የአገልግሎት ምድብ ተቀበልን። በ1953 ከጊልያድ የተመረቁት የመጨረሻው ወንድሜ ፖል እና ባለቤቱ ዶሎረስ እኛ ወደዚያ ከመሄዳችን ትንሽ ቀደም ብሎ በማዛቴናንጎ አገልግለው ነበር።
በ1958 ጓቲማላ ውስጥ ከ700 የሚበልጡ ምሥክሮች፣ 20 ጉባኤዎችና ሦስት ወረዳዎች ነበሩ። እኔና ሔለን በትንንሽ ቡድን የታቀፉ የይሖዋ ምሥክሮችንና በኩዊትዛልቴናንጎ የሚገኘውን ጉባኤ ጨምሮ በርካታ ጉባኤዎችን በመጎብኘት እንደገና በተጓዥነት አገልግሎት ተካፈልን። ከዚያም በነሐሴ 1959 ወደ ጓቲማላ ሲቲ እንድንመለስ ጥሪ ቀረበልንና በቅርንጫፍ ቢሮው መኖር ጀመርን። እኔ በቅርንጫፍ ቢሮው እንድሠራ ተመድቤ እያለሁ ሔለን ለተጨማሪ 16 ዓመታት በሚስዮናዊነት አገልግሎት ቀጥላለች። ከዚያም እርሷም በቅርንጫፍ ቢሮው ውስጥ መሥራት ጀመረች።
ተጨማሪ በረከቶች
ከዓመታት በፊት ይሖዋን ከሚያገለግሉት መካከል ምንጊዜም የመጨረሻ ትንሹ እኔ ነበርኩ። አሁን ግን በ1996 በፓተርሰን ኒው ዮርክ ለቅርንጫፍ ቢሮ አባላት በተዘጋጀው ትምህርት ቤት ስካፈል እንደነበረው ሁሉ አብዛኛውን ጊዜ በዕድሜ ከሁሉም በልጬ የምታየው እኔ ነኝ። በወጣትነቴ ዘመን በዕድሜ ከሚበልጡኝ ከፍተኛ እርዳታ እንዳገኘሁ ሁሉ ከቅርብ አሥርተ ዓመታት ወዲህ በጉብዝናቸው ወራት ፈጣሪያቸውን ማሰብ የሚፈልጉ ብዙ ወጣቶችን የመርዳት መብት አግኝቻለሁ።
ይሖዋ በዚህ በጓቲማላ ለሕዝቦቹ በረከቱን ማዝነቡን ቀጥሏል። በ1999 ጓቲማላ ሲቲ ውስጥ ከ60 የሚበልጡ ጉባኤዎች ነበሩ። እንዲሁም በስተ ሰሜን፣ ደቡብ፣ ምሥራቅና ምዕራብ ሌሎች ብዙ ጉባኤዎችና በሺዎች የሚቆጠሩ የአምላክ መንግሥት ምሥራች አዋጅ ነጋሪዎች አሉ። ከ53 ዓመት ገደማ በፊት ወደ ጓቲማላ ስንመጣ የነበሩት 50 እንኳ የማይሞሉ የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ቁጥራቸው አድጎ ከ19, 000 በላይ ሆኗል!
አመስጋኝ የምሆንባቸው በርካታ ነገሮች
የትኛውም ሰው ቢሆን በሕይወቱ ችግር ሳያጋጥመው የሚያልፍ የለም። ሆኖም ምንጊዜም ‘ትካዜያችንን በይሖዋ ላይ’ መጣል እንችላለን። (መዝሙር 55:22) አብዛኛውን ጊዜ አፍቃሪ የሆኑ ጓደኞቻችን በሚሰጡን ድጋፍ አማካኝነት ያጽናናናል። ለምሳሌ ያህል ሔለን ከመሞቷ ጥቂት ዓመታት በፊት በዕብራውያን 6:10 ላይ የሚገኘው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ የተቀረጸበት አንድ ትንሽ ፍሬም በስጦታ ሰጠችኝ:- “እግዚአብሔር፣ ቅዱሳንን ስላገለገላችሁ እስከ አሁንም ስለምታገለግሉአቸው፣ ያደረጋችሁትን ሥራ ለስሙም ያሳያችሁትን ፍቅር ይረሳ ዘንድ ዓመፀኛ አይደለምና።”
አያይዛ የሰጠችኝ ማስታወሻ በከፊል እንዲህ ይላል:- “ውዴ ሆይ፣ ለአንተ ያለኝን ፍቅር ከመስጠት በቀር ሌላ ላደርግልህ የምችለው ነገር የለም . . . ይህ ጥቅስ ከአንተ ሁኔታ ጋር ይስማማል፤ በመሆኑም ዴስክህ ላይ እንድታስቀምጠው እጠይቅሃለሁ። ይህን ስል ግን እኔ ስለሰጠሁህ ሳይሆን ለረጅም ዓመታት ካከናወንከው አገልግሎት አንፃር ለአንተ የሚስማማ ስለሆነ ነው።” እስካሁን ድረስ ይህ ጽሑፍ በጓቲማላ ቅርንጫፍ በሚገኘው የቢሮዬ ዴስክ ላይ አስቀምጬዋለሁ።
ከወጣትነቴ አንስቶ ይሖዋን ያገለገልኩ ሲሆን አሁን ዕድሜዬ በገፋባቸው ዓመታት ሥራዬን ለማከናወን የሚያስችለኝ ጥሩ ጤንነት ስለሰጠኝ ይሖዋን አመሰግነዋለሁ። ዘወትር የመጽሐፍ ቅዱስ ንባቤን ሳደርግ ውዷ ሔለን በራሷ መጽሐፍ ቅዱስ ላይ አስምራባቸው ሊሆን ይችላል ብዬ የማስባቸው ጥቅሶች ብዙ ጊዜ ያጋጥሙኛል። መዝሙር 48:14ን ደግሜ ሳነበው እንደዚያ ተሰምቶኛል። “ለዓለምና ለዘላለም ይህ አምላካችን ነው፣ እርሱም ለዘላለም ይመራናል።”
በአዲሱ ዓለም ውስጥ የቀድሞዎቹ ብሔራት ሕዝቦች ወዳጆቻቸውን ከሞት የሚቀበሉበትን ቀን በተመለከተ ያለውን ተስፋ ለሌሎች ማካፈል ያስደስተኛል። ምንኛ ግሩም ተስፋ ይጠብቀናል! ይሖዋ በእርግጥ “ኀዘንተኞችን የሚያጽናና አምላክ” መሆኑን ስናስታውስ ያን ጊዜ የደስታ እንባ እናነባለን!—2 ቆሮንቶስ 7:6
[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ከላይ አንስቶ ከግራ ወደ ቀኝ:- እማዬ፣ አባዬ፣ አክስቴ ኢቫ እና ወንድሞቼ ካርል እና ክላረንስ፣ 1910
[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ከሄለን ጋር በ1947 እና 1992