በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ድርጅት ያስፈልገናል

የይሖዋ ድርጅት ያስፈልገናል

የይሖዋ ድርጅት ያስፈልገናል

“በአምላክ አምናለሁ በድርጅት መልክ በተዋቀረ ሃይማኖት ግን አላምንም” የሚል ሰው አጋጥሞህ ያውቃል? በአንድ ወቅት ቀናተኛ የቤተ ክርስቲያን ተሳላሚ የነበሩ ሆኖም ሃይማኖታቸው መንፈሳዊ ፍላጎታቸውን ሳያሟላላቸው በመቅረቱ ግራ የተጋቡ ሰዎች አብዛኛውን ጊዜ ተመሳሳይ ነገር ሲናገሩ ይሰማል። በጥቅሉ ከሃይማኖታዊ ድርጅቶች የሚጠብቁትን ነገር ባለማግኘታቸው ቢበሳጩም እንኳ ብዙዎቹ አሁንም አምላክን የማምለክ ፍላጎት እንዳላቸው ይናገራሉ። ሆኖም የአንድ ቤተ ክርስቲያን ወይም የሌላ ድርጅት አባል ሆነው አምላክን ከማምለክ ይልቅ በራሳቸው መንገድ ማምለኩ የተሻለ እንደሆነ ያምናሉ።

ስለዚህ ጉዳይ መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? አምላክ ክርስቲያኖች በድርጅት መልክ እንዲሰባሰቡ ይፈልጋል?

የጥንቶቹ ክርስቲያኖች በመደራጀታቸው ተጠቅመዋል

ይሖዋ በ33 እዘአ በዋለው የጰንጠቆስጤ ዕለት መንፈስ ቅዱሱን ያፈሰሰው ብቻቸውን ተነጥለው ለሚገኙ ጥቂት አማኞች ሳይሆን በኢየሩሳሌም ከተማ በሚገኝ ሰገነት ላይ ‘አብረው በተሰበሰቡ’ የወንዶችና የሴቶች ቡድን ላይ ነበር። (ሥራ 2:​1) በዚህ ጊዜ ዓለም አቀፋዊ ድርጅት ለመሆን የበቃው የክርስቲያን ጉባኤ ተቋቋመ። የጉባኤው መቋቋም ለቀድሞዎቹ ደቀ መዛሙርት በረከት ሆኖላቸው ነበር። ለምን? አንደኛ ነገር የአምላክን መንግሥት ምስራች ደረጃ በደረጃ “በዓለም ሁሉ” የመስበክ ወሳኝ ሥራ ተሰጥቷቸው ነበር። (ማቴዎስ 24:​14) በጉባኤው ያሉ አዳዲስ አማኞች የስብከቱን ሥራ ማከናወን የሚችሉበትን መንገድ በተመለከተ ተሞክሮ ካላቸው መሰል አማኞች መማር ይችሉ ነበር።

ብዙም ሳይቆይ የመንግሥቱ መልእክት በኢየሩሳሌም ቅጥር ብቻ ሳይወሰን ርቀው ወደሚገኙ ከተማዎች ተዳረሰ። በ62 እና በ64 እዘአ መካከል ሐዋርያው ጴጥሮስ የመጀመሪያ ደብዳቤውን “በጳንጦስና በገላትያ በቀጰዶቅያም በእስያም በቢታንያም ለተበተኑ” ክርስቲያኖች ጽፎላቸዋል። እነዚህ ቦታዎች በሙሉ በዛሬዋ ቱርክ ውስጥ ይገኛሉ። (1 ጴጥሮስ 1:​1) በተጨማሪም በፍልስጤም፣ በሊባኖስ፣ በሶርያ፣ በቆጵሮስ፣ በግሪክ፣ በቀርጤስና በኢጣሊያ የሚኖሩ አማኞች ነበሩ። ጳውሎስ ከ60-61 እዘአ ለቆላስይስ ክርስቲያኖች በጻፈው ደብዳቤ መሠረት ምሥራቹ ‘ከሰማይ በታች ባለው ፍጥረት ሁሉ ዘንድ ተሰብኮ ነበር።’​—⁠ቆላስይስ 1:​23

በድርጅት መልክ መሰባሰብ የሚያስገኘው ሁለተኛ ጥቅም ክርስቲያኖች አንዳቸው ለሌላው ማበረታቻ መስጠት መቻላቸው ነበር። ክርስቲያኖች ከጉባኤው ጋር በመተባበር ቀስቃሽ ንግግሮችን ማዳመጥ፣ ቅዱሳን ጽሑፎችን አብረው ማጥናት፣ እምነት የሚያጠናክሩ ተሞክሮዎችን መለዋወጥና ከመሰል አማኞች ጋር አብረው መጸለይ ይችሉ ነበር። (1 ቆሮንቶስ ምዕራፍ 14) እንዲሁም የጎለመሱ ወንዶች ‘የእግዚአብሔርን መንጋ ይጠብቁ’ ነበር።​—⁠1 ጴጥሮስ 5:​2

ክርስቲያኖች የጉባኤው አባል እንደመሆናቸው መጠን እርስ በርስ ለመተዋወቅና አንዳቸው ለሌላው ፍቅር ለማሳየት የሚያስችል አጋጣሚ ነበራቸው። የጥንቶቹ ክርስቲያኖች ከጉባኤው ጋር መተባበራቸው ጫና እንዳስከተለባቸው ከማሰብ ይልቅ በጉባኤው ታንጸዋል እንዲሁም ተበረታትተዋል።​—⁠ሥራ 2:​42፤ 14:​27፤ 1 ቆሮንቶስ 14:​26፤ ቆላስይስ 4:​15, 16

ዓለም አቀፋዊ ኅብረት ያለው ጉባኤ ወይም ድርጅት ያስፈለገበት ሌላው ምክንያት አንድነትን ለማጎልበት ነበር። ክርስቲያኖች ‘በአንድ ንግግር የተባበሩ’ መሆንን ተምረዋል። (1 ቆሮንቶስ 1:​10) ይህ በጣም አስፈላጊ ነበር። የጉባኤው አባላት የተለያየ ዓይነት የትምህርት ደረጃና አስተዳደግ የነበራቸው ሰዎች ናቸው። ቋንቋቸው ይለያይ ነበር፤ እንዲሁም ግልጽ የሆኑ የባሕርይ ልዩነቶችም ነበሯቸው። (ሥራ 2:​1-11) አልፎ አልፎ ጎላ ያሉ አለመግባባቶች ተከስተዋል። ሆኖም ክርስቲያኖች እንዲህ ዓይነት አለመግባባቶችን ለመፍታት ከጉባኤው እገዛ አግኝተዋል።​—⁠ሥራ 15:​1, 2፤ ፊልጵስዩስ 4:​2, 3

የጉባኤው ሽማግሌዎች ሊፈቷቸው ያልቻሉ ከበድ ያሉ ጥያቄዎች ሲነሱ እንደ ጳውሎስ ለመሰሉ የጎለመሱ ተጓዥ የበላይ ተመልካቾች ይላኩ ነበር። አንገብጋቢ የሆኑ መሠረተ ትምህርት ነክ ጉዳዮች በኢየሩሳሌም ወደሚገኘው ማዕከላዊ የአስተዳደር አካል ተልከዋል። በመጀመሪያ የአስተዳደር አካሉ በኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያት አባልነት የተመሠረተ ሲሆን ከጊዜ በኋላ ግን በኢየሩሳሌም በሚገኘው ጉባኤ የነበሩትን ሽማግሌዎችም አካትቷል። እያንዳንዱ ጉባኤ የአስተዳደር አካሉና እርሱ የሾማቸው ተወካዮች አገልግሎቱን ለማደራጀት፣ ወንዶችን ለአገልግሎት መብቶች ለመሾምና መሠረተ ትምህርት ነክ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ውሳኔ ለማስተላለፍ ያላቸውን ከአምላክ የተሰጣቸውን ሥልጣን ተቀብሎ ነበር። የአስተዳደር አካሉ ለአንድ አከራካሪ ጉዳይ መፍትሔ ሲሰጥ ጉባኤዎች ውሳኔውን ተቀብለው ‘ከምክሩ የተነሳ ደስ ይላቸው ነበር።’​—⁠ሥራ 15:​1, 2, 28, 30, 31

አዎን፣ ይሖዋ በአንደኛው መቶ ዘመን በድርጅት ተጠቅሟል። ይሁን እንጂ ዛሬስ?

ዛሬ ድርጅት ያስፈልገናል

በመጀመሪያው መቶ ዘመን እንደነበሩት መሰሎቻቸው ሁሉ ዛሬም የይሖዋ ምሥክሮች የመንግሥቱን ምሥራች እንዲሰብኩ የተሰጣቸውን ተልእኮ በቁም ነገር ይመለከቱታል። ይህን ሥራ የሚያከናውኑበት አንደኛው መንገድ መጽሐፍ ቅዱስንና መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት የሚረዱ ጽሑፎችን በማሰራጨት ሲሆን ይህ ደግሞ ድርጅት እንዲኖር የሚጠይቅ ነው።

ክርስቲያናዊ ጽሑፎች በጥንቃቄ ተዘጋጅተው፣ ትክክለኝነታቸው ከተረጋገጠ በኋላ መታተምና ከዚያም ወደየጉባኤዎች መላክ አለባቸው። ቀጥሎም ጽሑፎቹን ማንበብ ለሚፈልጉ ሰዎች ለማድረስ ፈቃደኛ የሆኑ ግለሰብ ክርስቲያኖች ያስፈልጋሉ። በዚህ መንገድ የመንግሥቱ መልእክት በሚልዮን ለሚቆጠሩ ሰዎች ተዳርሷል። አንዳንድ የአገልግሎት ክልሎች በተደጋጋሚ ተሸፍነው ሌሎች ደግሞ ችላ እንዳይባሉ የምሥራቹ አስፋፊዎች የስብከት እንቅስቃሴያቸውን ሥርዓታማ በሆነ መንገድ ለማከናወን ጥረት ያደርጋሉ። ይህ ሁሉ መደራጀትን የሚጠይቅ ነው።

‘አምላክ ለሰው ፊት ስለማያዳላ’ መጽሐፍ ቅዱሶችና መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎች መተርጎም አለባቸው። (ሥራ 10:​34) በአሁኑ ጊዜ ይህ መጽሔት በ132 ቋንቋዎች የሚገኝ ሲሆን የእርሱ ተጓዳኝ የሆነው ንቁ! ደግሞ በ83 ቋንቋዎች ይታተማል። ይህ በዓለም ዙሪያ በአግባቡ የተደራጁ የትርጉም ቡድኖች እንዲኖሩ የሚጠይቅ ነው።

የጉባኤው አባላት በጉባኤና በትልልቅ ስብሰባዎች ላይ ሲገኙ ማበረታቻ ያገኛሉ። በስብሰባው ላይ ቀስቃሽ የሆኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ንግግሮችን ያዳምጣሉ፣ አብረው ቅዱሳን ጽሑፎችን ያጠናሉ፣ የሚያንጹ ተሞክሮዎችን ይለዋወጣሉ እንዲሁም ከመሰል አማኞች ጋር በኅብረት ይጸልያሉ። በተጨማሪም በመጀመሪያው መቶ ዘመን እንደነበሩት ወንድሞቻቸው ሁሉ አፍቃሪ የሆኑ ተጓዥ የበላይ ተመልካቾች ከሚያደርጉላቸው እምነት የሚያጠናክር ጉብኝት ጥቅም ያገኛሉ። በመሆኑም ዛሬ ክርስቲያኖች ‘አንድ እረኛ ያለው አንድ መንጋ ሆነዋል።’​—⁠ዮሐንስ 10:​16

እርግጥ፣ እንደ ቀድሞዎቹ መሰሎቻቸው ሁሉ የይሖዋ ምሥክሮችም ፍጹማን አይደሉም። ዛሬም አንድ ላይ በስምምነት ይሠራሉ። ይህም በመሆኑ የመንግሥቱ ስብከት ሥራ በምድር ዙሪያ በመካሄድ ላይ ይገኛል።​—⁠ሥራ 15:​36-40፤ ኤፌሶን 4:​13

[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ዛሬ ክርስቲያኖች ‘አንድ እረኛ ያለው አንድ መንጋ ሆነዋል’