“የፖላንድ ወንድማማቾች” ስደት የደረሰባቸው ለምን ነበር?
“የፖላንድ ወንድማማቾች” ስደት የደረሰባቸው ለምን ነበር?
የፖላንድ ፓርላማ በ1638 የፖላንድ ወንድማማቾች በሚል ስያሜ የሚታወቀውን አነስተኛ ሃይማኖታዊ ቡድን የሚያሽመደምድ አንድ ከባድ እርምጃ ወሰደ። ቤተ ክርስቲያናቸውና የማተሚያ መሣሪያቸው እንዲወድም ተደረገ። በራኮው የሚገኘው ዩኒቨርሲቲ ተዘጋ። በዚያ ያስተምሩ የነበሩት ፕሮፌሰሮችም ከአገር ተባረሩ።
ከሃያ ዓመት በኋላ ፓርላማው ተጨማሪ እርምጃዎችን ወሰደ። 10, 000 እና ከዚያም በላይ የሚሆኑት መላው የቡድኑ አባላት አገሪቷን ለቀው እንዲወጡ ትእዛዝ ተላለፈ። በወቅቱ በአውሮፓ ካሉት አገሮች ሁሉ የተለያዩ አመለካከቶችን በማስተናገድ ትታወቅ በነበረችው አገር ሁኔታው ይህን ያህል የከፋው ለምን ነበር? የፖላንድ ወንድማማቾች ጥፋታቸው ምን ነበር?
ነገሩ የጀመረው በፖላንድ የካልቪኒስት ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሰፊ ልዩነት በተፈጠረ ጊዜ ነበር። ትልቁ አወዛጋቢ ጉዳይ የሥላሴ መሠረተ ትምህርት ነበር። በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚካሄደው የማሻሻያ እንቅስቃሴ መሪዎች ይህ መሠረተ ትምህርት ቅዱስ ጽሑፋዊ አይደለም የሚል ተቃውሞ አስነሱ። ይህም የቤተ ክርስቲያኒቱን መሪዎች ስላስቆጣቸው የማሻሻያ እንቅስቃሴው ቡድን ተገንጥሎ ወጣ።
ካልቪኒስቶች ተቃዋሚዎቹን አርዮሳውያን a ብለው ቢጠሯቸውም የአዲሱ ቡድን ደጋፊዎች ግን ክርስቲያኖች ወይም የፖላንድ ወንድማማቾች በሚለው መጠሪያ መጠራትን መርጠዋል። ወደ ፖላንድ ተጉዞ የዚህ ንቅናቄ ቡድን ዋነኛ አቀንቃኝ በነበረው የፎስተስ ሶኪነስ ዘመድና የሰርቬተስን መርሆ በተከተለው በኢጣሊያዊው በላይሊየስ ሶኪነስ ስምም ሶሲኒያውያን ተብለው ይጠሩ ነበር።
በዚህ ወቅት ከመኳንንት አንዱ የነበረው ያን ሼንየንስኪ አዲሱ ቤተ ክርስቲያን ማደግ የሚችልበት “የተመቻቸ ቦታ” እንዲያገኝ ለማድረግ ስላሰበ የፖላንድ ንጉሥ የሰጠውን ልዩ መብት በመጠቀም ሼንየንስኪ የራኮውን ከተማ ቆረቆረ። ከጊዜ በኋላ ይህች ከተማ በፖላንድ የሶሲኒያውያን ዋና ማዕከል ሆነች። ሼንየንስኪ አምልኮን በነፃነት ማካሄድን ጨምሮ ሌሎችንም በርካታ መብቶች ለራኮው ዜጎች አጎናጽፏቸው ነበር።
የእጅ ሞያተኞች፣ ሐኪሞች፣ መድኃኒት ቀማሚዎች፣ የከተማ ሰዎች፣ የተለያዩ ሃይማኖታዊ ወገኖች መኳንንት ወደዚች አዲስ ከተማ ተስበው ነበር። ከዚህም በተጨማሪ ከፖላንድ፣ ከሊትዋኒያ፣ ከትራንሲልቫኒያ፣ ከፈረንሳይ እና ከእንግሊዝ ሳይቀር አገልጋዮች ወደ ከተማዋ ጎርፈው ነበር። ይሁን እንጂ ወደዚህ ከመጡት አዲስ ሰዎች መሃል የሶሲኒያውያኑን እምነት የተጋሩት ሁሉም አልነበሩም። በመሆኑም በቀጣዮቹ ሦስት ዓመታት ማለትም ከ1569 እስከ 1572 ባሉት ዓመታት ራኮው ስፍር ቁጥር የሌላቸው ሃይማኖታዊ ውይይቶች የሚካሄዱባት መድረክ ሆና ነበር። ውጤቱስ ምን ሆነ?
የተከፋፈለ ቤት
የሶሲኒያውያኑ እንቅስቃሴ ራሱ ጽንፈኛ አመለካከት ባላቸው ወገኖችና ለዘብተኛ በሆኑት ወገኖች ለሁለት ተከፍሎ ነበር። በመካከላቸው ልዩነት ቢኖርም በጋራ የሚያምኑባቸው ነገሮች ከሌሎች የተለዩ ነበሩ። የሥላሴን ትምህርት አይቀበሉም፣ ሕፃናትን አያጠምቁም እንዲሁም በአብዛኛው መሣሪያ አይታጠቁም፣ በማንኛውም የሕዝብ ሥልጣን ለማገልገል ፈቃደኛ አይሆኑም ነበር። b ሲኦል የማሰቃያ ቦታ ነው የሚልም እምነት አልነበራቸውም። ከዚህም በተጨማሪ በሰፊው ተቀባይነት ለነበራቸው ሃይማኖታዊ ወጎች ቦታ አልሰጧቸውም።
የካልቪኒስቶችም ሆኑ የካቶሊክ ቀሳውስት በዚህ ቡድን ላይ ጠንካራ የተቃውሞ እንቅስቃሴ ቢያካሂዱም ሶሲኒያውያን አገልጋዮች እንደ ሲጊስማንድ ዳግማዊ አውጉስቶስና ስቴፈን ባቶሪ ያሉት የፖላንድ ነገሥታት ሃይማኖትን በተመለከተ ያራምዱት የነበረውን ሁሉንም የማስተናገድ ፖሊሲ በመጠቀም ትምህርታቸውን አስፋፍተዋል።
ባድኒ ያከናወነው ጉልህ ስፍራ የሚሰጠው ተግባር
በወቅቱ በሰፊው ይሠራበት የነበረው የካልቪኒስት የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም የብዙዎቹን አንባቢዎች ፍላጎት የሚያረካ አልነበረም። መጽሐፉ የተተረጎመው ከመጀመሪያዎቹ ቋንቋዎች ሳይሆን ከላቲኑ ቩልጌት እንዲሁም በወቅቱ ከነበረው የፈረንሳይኛ ትርጉም ነበር። አንድ ምንጭ እንደገለጸው ከሆነ “ለትርጉሙ ውበት ሲባል ሐሳቡን በታማኝነትና በትክክል የማስቀመጡ ጉዳይ ወደ ጎን ገሸሽ ተደርጓል።” ብዙ ስህተቶች ነበሩበት። በመሆኑም ሻይመን ባድኒ የተባለ አንድ ስመ ጥር ምሁር ትርጉሙን የማረም ኃላፊነት ተሰጠው። ይሁንና ባድኒ የበፊቱን ትርጉም ከማረም ይልቅ ሙሉ በሙሉ አዲስ ትርጉም ማዘጋጀት እንደሚቀልል አሰበ። ከዚያም በ1567 ሥራውን ተያያዘው።
ባድኒ ትርጉሙን የሠራው እያንዳንዱን ቃልና የቃሉን ተመሳሳይ አማራጮች በጥልቀት በመመርመር ነበር። ከዚያ ቀደም በፖላንድ እንዲህ ያደረገ አንድም ሰው አልነበረም። የዕብራይስጡ አገላለጽ አስቸጋሪ ሆኖ ሲያገኘው ቃል በቃል ትርጉሙ ምን ማለት እንደሆነ በኅዳጉ ላይ ማስታወሻ ያስቀምጥ ነበር። አስፈላጊ በሚሆንበት ጊዜ አዳዲስ ቃላት የፈጠረ ሲሆን በዘመኑ የዕለት ተዕለት መግባቢያ በሆነው ቀላል የፖሊሽ ቋንቋ ተጠቅሟል። ግቡ የመጀመሪያውን መልእክት በታማኝነት የተከተለና ትክክለኛ የሆነ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ለአንባቢዎች ማቅረብ ነበር።
የባድኒ ሙሉ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም በ1572 ታትሞ ወጣ። ይሁን እንጂ አሳታሚዎቹ የግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች ትርጉሙን በርዘውበት ነበር። ባድኒ ተስፋ ባለመቁረጥ ሌላ የተስተካከለ ትርጉም ለማዘጋጀት ታጥቆ የተነሣ ሲሆን ይህንን ሥራውን ከሁለት ዓመታት በኋላ ለማጠናቀቅ በቅቷል። የባድኒ ድንቅ የግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች ትርጉም ከዚያ ቀደም በፖላንድ ቋንቋ ከተተረጎሙት ሁሉ እጅግ የላቀ ነበር። ከዚህም በላይ በብዙ ቦታዎች ላይ ይሖዋ የሚለውን መለኮታዊ ስም መልሶ አስገብቷል።
በ16ኛው መቶ ዘመን መጨረሻ ላይ እንዲሁም በ17ኛው መቶ ዘመን የመጀመሪያ ሦስት አሥርተ ዓመታት ወቅት የንቅናቄው መናኸሪያ የሆነችው ራኮው የሃይማኖትና የትምህርት ማዕከል ሆና ነበር። የፖላንድ ወንድማማቾች መሪዎችና ጸሐፊዎች ትራክቶቻቸውንና ጽሑፎቻቸውን የሚያሳትሙት እዚሁ ነበር።
ትምህርትን አበረታትተዋል
የፖላንድ ወንድማማቾች የሕትመት ሥራ ከፍተኛ ዕድገት ማሳየት የጀመረው በ1600 በራኮው ማተሚያ መሣሪያ በተተከለ ጊዜ ነበር። የማተሚያው መሣሪያ ትናንሽ ጽሑፎችንም ሆነ ትላልቅ መጻሕፍትን በበርካታ ቋንቋዎች ማተም የሚችል ነበር። ራኮው የሕትመት ሥራ ማዕከል እንደመሆኗ መጠን በአውሮፓ ካሉት የተሻሉ ከተሞች ተርታ ተሰልፋ ነበር። ከዚያ በኋላ በነበሩት 40 ዓመታት ውስጥ እስከ 200 የሚደርሱ ጽሑፎች በዚሁ ማተሚያ እንደታተሙ ይታመናል። የፖላንድ ወንድማማቾች ንብረት የሆነውና በዚያው አቅራቢያ የሚገኘው የወረቀት ፋብሪካ ከፍተኛ ጥራት ያለው ወረቀት ለዚሁ የጽሑፍ ሥራ ያቀርብ ነበር።
ብዙም ሳይቆይ የፖላንድ ወንድማማቾች የእምነት አጋሮቻቸውንም ሆነ ሌሎች ሰዎችን ማስተማር አስፈላጊ እንደሆነ ተገነዘቡ። ይህንንም ለማድረግ ሲባል በ1602 የራኮው ዩኒቨርሲቲ ተቋቋመ። ወዲያውም የፖላንድ ወንድማማቾች ልጆች እንዲሁም ካቶሊክና ፕሮቴስታንት ልጆች ወደ ዩኒቨርሲቲው ተላኩ። ዩኒቨርሲቲው የሃይማኖታዊ ትምህርት መስጫ ማዕከል ቢሆንም የሚያስተምረው ሃይማኖትን ብቻ አልነበረም። የባዕድ አገር ቋንቋዎች፣ የግብረገብ፣ የምጣኔ ሀብት፣ የታሪክ፣ የሕግ፣ የሎጂክ፣ የተፈጥሮ ሳይንስ፣ የሒሳብ፣ የሕክምና እንዲሁም የአካል ማጎልበቻ ትምህርት የሥርዓተ ትምህርቱ ክፍል ነበሩ። ዩኒቨርሲቲው በአካባቢው ላለው ማተሚያ ምሥጋና ይግባውና በየጊዜው እያደገ የሚሄድ ትልቅ ቤተ መጻሕፍት ነበረው።
በአሥራ ሰባተኛው መቶ ዘመን የፖላንድ ወንድማማቾች እየጎለበቱ እንደሚሄዱ በግልጽ ማየት ይቻል ነበር። ይሁንና እውነታው ከዚያ የተለየ ሆኗል።
የቤተ ክርስቲያንና የመንግሥት ግጭት
የፖላንድ የሳይንስ አካዳሚ አባል የሆኑት ዘቢግኒየቭ ኦጎኖፈስኪ “በ17ኛው መቶ ዘመን ሦስተኛ አሥርተ ዓመት መጨረሻ ላይ በፖላንድ የነበሩት አርዮሳውያን ሁኔታ በፍጥነት ማሽቆልቆል ጀምሮ ነበር” በማለት ያስረዳሉ። ይህም የካቶሊክ ቀሳውስት ግምባራቸውን ሳያጥፉ ያደረጉት ትግል ውጤት ነው። ቀሳውስቱ የፖላንድ ወንድማማቾችን ለማጣጣል ስም ማጥፋትንና ውግዘትን ጨምሮ ያልተጠቀሙበት
ዘዴ አልነበረም። በፖላንድ የተደረገው የፖለቲካ ለውጥም ለዚህ ጥቃት ሁኔታውን አመቻችቶ ነበር። አዲሱ የፖላንድ ንጉሥ ሲግመንት ሦስተኛ ቫሳ የፖላንድ ወንድማማቾች ጠላት ነበር። በእርሱ እግር የተተኩትም ቢሆኑ በተለይ ደግሞ ጆን ዳግማዊ ካዝሚር ቫሳ በተመሳሳይ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የፖላንድ ወንድማማቾችን ለመጣል የምታደርገውን ጥረት ደግፈዋል።ውዝግቡ ወደከፋ ደረጃ የደረሰው ጥቂት የራኮው ተማሪዎች ሆነ ብለው መስቀልን አርክሰዋል የሚል ክስ በቀረበ ጊዜ ነበር። ይህ አጋጣሚ የፖላንድ ወንድማማቾችን ማዕከል ለማጥፋት እንደ ሽፋን ሆኖ አገልግሏል። የራኮው ዩኒቨርሲቲ ባለቤት የራኮውን ዩኒቨርሲቲና ማተሚያ በመደገፍ ‘ክፋትን አስፋፍተዋል’ በሚል ወንጀል ተከስሰው በፓርላማው ፍርድ ቤት ፊት ቀረቡ። የፖላንድ ወንድማማቾች፣ ሰላም የሚያደፈርስ እንቅስቃሴ በማድረግ፣ በፈንጠዝያ እንዲሁም ሥነ ምግባር በጎደለው አኗኗር ተከሰሱ። ፓርላማው የራኮው ዩኒቨርሲቲ እንዲዘጋና የፖላንድ ወንድማማቾች ንብረት የሆኑት ማተሚያም ሆነ ቤተ ክርስቲያን እንዲቃጠሉ አዘዘ። አማኞችም ከተማዋን ለቀው እንዲወጡ ትእዛዝ ተላለፈ። የዩኒቨርሲቲው ፕሮፌሰሮችም አገሪቷን ለቅቀው ካልወጡ እንደሚገደሉ የሚገልጽ ውሳኔ ተላለፈ። አንዳንድ የፖላንድ ወንድማማቾች አባላት እንደ ሲሌሲያ እና ስሎቫኪያ ወዳሉት አስተማማኝ ቦታዎች ተሰደዱ።
በ1658 ፓርላማው የፖላንድ ወንድማማቾች ንብረታቸውን ሸጠው በሦስት ዓመት ጊዜ ውስጥ አገሪቱን መልቀቅ እንዳለባቸው የሚገልጽ አዋጅ አወጣ። ከዚያም ቀነ ገደቡ ወደ ሁለት ዓመት ተቀነሰ። ከዚያ በኋላ ይህ እምነት አለኝ የሚል ሰው ቢገኝ ይገደል ነበር።
አንዳንድ ሶሲኒያውያን በኔዘርላንድስ ተቀምጠው የሕትመት ሥራቸውን ቀጠሉ። በትራንሲልቫንያ የሚገኝ አንድ ጉባኤ እስከ 18ኛው መቶ ዘመን መጀመሪያ ድረስ ሲንቀሳቀስ ቆይቷል። በሳምንት እስከ ሦስት ጊዜ ድረስ በሚከናወኑት ስብሰባዎቻቸው ላይ መዝሙራትን ይዘምሩ፣ የሚሰጡትን ስብከቶች ያዳምጡና ትምህርቶቻቸውን ለማብራራት ታስቦ በጥያቄና መልስ ከተዘጋጀው ሃይማኖታዊ መጽሐፋቸው አንዳንድ ነገር ይነበብላቸው ነበር። የጉባኤውን ንጽሕናም ለመጠበቅ ሲባል የእምነቱ አባላት ምክር ይሰጣቸው፣ ይገሰጹ እንዲሁም ካስፈለገ ከጉባኤው ይወገዱ ነበር።
የፖላንድ ወንድማማቾች የአምላክ ቃል ተማሪዎች ነበሩ። አንዳንድ ውድ የሆኑ እውነቶችን ተረድተው የነበረ ሲሆን ያለማመንታትም ለሌሎች ያካፍሉ ነበር። ይሁን እንጂ የኋላ ኋላ በመላዋ አውሮፓ ስለተበታተኑ አንድነታቸውን ጠብቀው ለማቆየት ተሳናቸው። በኋላም የፖላንድ ወንድማማቾች ማኅበር ከናካቴው ጠፋ።
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a አርዮስ (250-336 እዘአ) የእስክንድርያ ቄስ ሲሆን ኢየሱስ ከአብ ያንሳል ብሎ የተከራከረ ሰው ነው። በ325 እዘአ የኒቂያ ጉባኤ የእርሱን አመለካከት ሳይቀበለው ቀርቷል።—የሰኔ 22, 1989 ንቁ! (እንግሊዝኛ) ገጽ 27ን ተመልከት።
b የኅዳር 22, 1988 ንቁ! (እንግሊዝኛ) ገጽ 19 ላይ የሚገኘውን “ሶሲኒያውያን—የሥላሴን ትምህርት ያልተቀበሉት ለምንድን ነው?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የአንድ ሶሲኒያዊ አገልጋይ ንብረት የነበረ ቤት
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ከላይ:- የዛሬዋ ራኮው። በስተቀኝ:- በ1650 “የአርዮሳውያንን እምነት” ርዝራዥ ሁሉ ለማስወገድ የተመሠረተው ገዳም። ከታች:- የካቶሊክ ቀሳውስት ከፖላንድ ወንድማማቾች ጋር ግጭት ለማስነሳት እዚህ ቦታ ላይ መስቀል ተክለው ነበር
[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]
Title card of Biblia nieświeska by Szymon Budny, 1572