በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ስለ ወደፊቱ ጊዜ ልታውቅ ትችላለህ!

ስለ ወደፊቱ ጊዜ ልታውቅ ትችላለህ!

ስለ ወደፊቱ ጊዜ ልታውቅ ትችላለህ!

አብዛኞቹ ሰዎች ስለ ወደፊቱ ጊዜ በቁም ነገር ያስባሉ። ዕቅድ ማውጣት፣ መዋዕለ ንዋያቸውን በደህና ነገር ላይ ማፍሰስ እንዲሁም ከስጋት ነፃ መሆን ይፈልጋሉ። ሆኖም ነገ ምን ይዞ እንደሚመጣ እርግጠኛ መሆን የሚቻልበት መንገድ አለን?

ሰዎች የወደፊቱ ጊዜ ምን ይዞ እንደሚመጣ ለማወቅ ያላደረጉት ሙከራ የለም። ፊውቸረሎጂስትስ እየተባሉ የሚጠሩ የማኅበራዊ ሕይወት ሳይንቲስቶች ወቅታዊ አዝማሚያዎችን ካጤኑ በኋላ በዚያ ላይ በመመሥረት የራሳቸውን ትንበያ ይሰነዝራሉ። የኢኮኖሚ ጠበብቶችም በሙያቸው መስክ የራሳቸውን ትንበያ ይሰነዝራሉ። ኮከብ ቆጣሪዎችና ጠንቋዮች ደግሞ ስለ ወደፊቱ ጊዜ ለመተንበይ አውደ ነገሥት ያያሉ፤ ደግሞም ብዙ ሰዎች ተከትለዋቸዋል። ለምሳሌ ያህል ፈረንሳዊው ኮከብ ቆጣሪ ኖስትረዳመስ ከሞተ ብዙ መቶ ዘመናት ያለፉ ቢሆንም እስከ አሁን ዝነኛ እንደሆነ ቀጥሏል።

እነዚህ ሁሉ ነቢይ ተብዬዎች ጨርሶ እምነት የሚጣልባቸው ሆነው አልተገኙም። ለምን? ምክንያቱም ለይሖዋ አምላክና ለቃሉ ለመጽሐፍ ቅዱስ ምንም ትኩረት ስለማይሰጡ ነው። ከዚህም የተነሳ እንደሚከተሉት ላሉ መሠረታዊ ጥያቄዎች መልስ የላቸውም:- ‘በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አስቀድመው የተነገሩት ነገሮች እንደሚፈጸሙ እርግጠኛ መሆን የሚያስችለኝ ምክንያት ምንድን ነው? አምላክ ለሰዎች ካለው ዓላማ ጋር እንዴት ይስማማሉ? እኔም ሆንኩ ቤተሰቤ ከእነዚህ ትንቢቶች ልንጠቀም የምንችለው እንዴት ነው?’ መጽሐፍ ቅዱስ ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ይሰጣል።

የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ልቆ የሚታይባቸው ሌሎች በርካታ መንገዶችም አሉ። ከኮከብ ቆጠራ ትንበያ በተለየ መልኩ የግል ምርጫ የማድረግ ነፃነት ይሰጣል። ስለሆነም ሕይወቱ ለዕድል ተገዢ የሚሆን የለም። (ዘዳግም 30:​19) ኖስትረዳመስ የሠራቸው ዓይነት የጽሑፍ ሥራዎች ምንም የሚጨበጥ ነገር የሌላቸው ባዶ ትንቢቶች ሲሆኑ ይህን ክፍተት ለመድፈን ምስጢራዊና ልብ የሚያንጠለጥል ነገር ይጨምሩባቸዋል። ሆኖም የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት የሚጨበጥ ነው። አምላክ አንድን ነገር ለማድረግ ያሰበው ለምን እንደሆነ ይገልጻል። (2 ዜና መዋዕል 36:​15) ደግሞም ‘አምላክ ሊዋሽ ስለማይችል’ ይሖዋ የተናገራቸው ትንቢቶች ፍጻሜያቸውን ሳያገኙ አይቀሩም። (ቲቶ 1:​2) ስለሆነም በአምላክ ቃል የሚመሩ ግለሰቦች ውድ የሆነ ጊዜያቸውንና ጉልበታቸውን ፍሬ ቢስ የሆኑ ነገሮችን በማሳደድ ከማባከን ዓላማና ትርጉም ያለው ደስተኛ ሕይወት ይመራሉ።​—⁠መዝሙር 25:​12, 13

እነዚህና ሌሎች በርካታ ነጥቦች “የአምላክ ትንቢታዊ ቃል” በሚል ጭብጥ በዓለም ዙሪያ በተደረጉት የ1999/​2000 የይሖዋ ምሥክሮች የአውራጃ ስብሰባዎች ላይ ተብራርተዋል። ንግግሮቹ፣ ቃለ ምልልሶቹ፣ ሠርቶ ማሳያዎቹና የቀረበው የመጽሐፍ ቅዱስ ድራማ የአምላክን ትንቢታዊ ቃል የሚያጠኑና በሕይወታቸው ተግባራዊ የሚያደርጉት ሰዎች የሚያገኙትን መንፈሳዊ ውርሻ የሚያጎሉ ነበሩ። የሚቀጥለው ርዕስ የአውራጃ ስብሰባውን አንዳንድ ጎላ ያሉ ነጥቦች ይከልሳል።