በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በኢጣሊያ አጽናኝ መልእክት ማድረስ

በኢጣሊያ አጽናኝ መልእክት ማድረስ

ከሚያምኑት ወገን ነን

በኢጣሊያ አጽናኝ መልእክት ማድረስ

ይሖዋ “የመጽናናት ሁሉ አምላክ” ነው። አገልጋዮቹም የእርሱን ምሳሌ በመኮረጅ “በመከራ ሁሉ ያሉትን ማጽናናት” ይችላሉ። (2 ቆሮንቶስ 1:​3, 4፤ ኤፌሶን 5:​1) የይሖዋ ምሥክሮች እያከናወኑ ያሉት የስብከት ሥራ ዋነኛ ዓላማም ይኸው ነው።

ችግር ላይ የወደቀችን አንዲት ሴት መርዳት

በተለይ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ድህነት፣ ጦርነትና የተሻለ ኑሮ ፍለጋ ብዙዎች ወደ በለጸጉ አገሮች እንዲሰደዱ አድርጓቸዋል። ይሁን እንጂ አዳዲስ አካባቢዎችን መላመድ ቀላል አይደለም። ማንዮላ የአገሯ ተወላጅ ከሆኑ የአልባንያ ዝርያ ካላቸው ሰዎች ጋር በቦርጎማኔሮ ትኖር ነበር። በኢጣሊያ የምትኖረው ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ ስለነበር የይሖዋ ምሥክር ከሆነችው ከቫንዳ ጋር ለመነጋገር ፈራ ተባ ብላ ነበር። የሆነ ሆኖ በመጨረሻ ቫንዳ ከማንዮላ ጋር ቀጠሮ ያዘች። ምንም እንኳ ቋንቋ እንደ ጋሬጣ ሆኖ ችግር ቢፈጥርባቸውም ማንዮላ የአምላክን ቃል ለማጥናት ከፍተኛ ፍላጎት አደረባት። ይሁን እንጂ ለጥቂት ጊዜያት ካጠኑ በኋላ ቫንዳ በቤት ውስጥ ማንንም ሰው ሳታገኝ ትቀራለች። ምን አጋጥሟቸው ይሆን? እዚያ ከሚኖሩት ሰዎች መካከል አንዱ ማለትም የማንዮላ የወንድ ጓደኛ በግድያ ወንጀል ይፈለግ ስለነበር ሁሉም ከዚያ ቤት እንደጠፉ ቫንዳ ተገነዘበች!

ከአራት ወር በኋላ ቫንዳና ማንዮላ በድንገት ይገናኛሉ። “ክስት ያለውና የገረጣው ሰውነቷ አንድ ዓይነት ችግር ገጥሟት እንደነበር ይናገራል” በማለት ቫንዳ ታስታውሳለች። የቀድሞ የወንድ ጓደኛዋ በእስር ቤት እንደሚገኝና ይረዱኛል ብላ የተጠጋቻቸው ጓደኞቿም በጣም እንዳስቀየሟት ማንዮላ ተናገረች። በተስፋ መቁረጥ ስሜት ተውጣ አምላክ እንዲረዳት ጸለየች። ከዚያም ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ያነጋገረቻት ቫንዳ ትዝ አለቻት። እንደገና በመገናኘታቸው ማንዮላ ምንኛ ተደስታ ይሆን!

ተቋርጦ የነበረው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናታቸውን ቀጠሉ። ከዚያም ማንዮላ በክርስቲያን ስብሰባዎች ላይ መገኘት ጀመረች። ኢጣሊያ ለመኖር የሚያስችል ሕጋዊ የመኖሪያ ፈቃድ አገኘች። ከአንድ ዓመት በኋላ ማንዮላ የተጠመቀች የይሖዋ ምሥክር ሆነች። አምላክ በሰጣቸው ተስፋዎች በመጽናናት በትውልድ አገሯ ለሚኖሩ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ የያዘውን አጽናኝ መልእክት ለማካፈል ወደ አልባኒያ ተመልሳ ሄደች።

በስደተኞች ካምፕ መመሥከር

በኢጣሊያ የሚገኙ በርካታ ጉባኤዎች እንደ ማንዮላ ላሉ ስደተኞች ለመመሥከር ዝግጅት አድርገዋል። ለምሳሌ ያህል በፍሎረንስ የሚገኝ አንድ ጉባኤ አንድ የስደተኞች ካምፕ አዘውትሮ ለመጎብኘት ዝግጅት አደረገ። በካምፑ ውስጥ የሚኖሩ ብዙዎቹ ከምሥራቅ አውሮፓ፣ ከመቄዶንያ እና ከኮሶቮ የመጡ ስደተኞች የተለያዩ ችግሮችን አሳልፈዋል። አንዳንዶቹ ከአደገኛ ዕፆች ወይም ከአልኮል መጠጦች ጋር የተያያዙ ችግሮች አሉባቸው። ብዙዎቹም ይህን ፍላጎቶቻቸውን ለማርካት ጥቃቅን ነገሮችን ይሰርቃሉ።

በዚህ ማኅበረሰብ ውስጥ መስበክ ፈታኝ ነበር። ይሁን እንጂ ፓኦላ የተባለ አንድ የሙሉ ጊዜ ወንጌላዊ በመጨረሻ ዣክሊና የምትባል አንዲት የመቄዶንያ ሴት አገኘ። ጥቂት ውይይት ካደረጉ በኋላ ዣክሊና ጓደኛዋ ሱዛናም መጽሐፍ ቅዱስን እንድትመረምር አበረታታቻት። ሱዛናም በበኩሏ ለሌሎች ዘመዶቿ ነገረቻቸው። ወዲያው አምስት የቤተሰቡ አባላት መጽሐፍ ቅዱስን አዘውትረው ማጥናት፣ በክርስቲያን ስብሰባዎች ላይ መገኘትና የተማሯቸውን ነገሮች በሥራ ላይ ማዋል ጀመሩ። ከፊታቸው የተደቀኑባቸው በርካታ ችግሮች ቢኖሩባቸውም ከይሖዋና ከቃሉ ማጽናኛ አግኝተዋል።

አንዲት መነኩሲት ከይሖዋ ማጽናኛ አገኘች

ፎርሚያ በሚባል ከተማ የምትኖር አሱንታ የተባለች አንዲት የሙሉ ጊዜ ወንጌላዊ ቀስ ብላ በትግል የምትራመድ አንዲት ሴት አነጋገረች። ሴትዬዋ በሽተኞችንና አቅመ ደካሞችን በሐኪም ቤትና በግል ቤቶች እርዳታ እንዲያገኙ የሚያደርግ የአንድ ሃይማኖታዊ ማኅበር መነኩሴ ነበረች።

አሱንታ መነኩሲቷን “በጣም ያምሻል፣ አይደል? የሚያሳዝነው ሁላችንም የተለያዩ ችግሮች ያሉብን መሆኑ ነው” አለቻት። በዚህ ጊዜ መነኩሲቷ እያለቀሰች ሥር የሰደደ የጤና እክል እንዳለባት ነገረቻት። አሱንታ የመጽሐፍ ቅዱስ አምላክ ሊያጽናናት እንደሚችል በመንገር አበረታታቻት። መነኩሴዋም አሱንታ የሰጠቻትን በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ መጽሔት በደስታ ተቀበለች።

በቀጣዩ ጊዜ ተገናኝተው እየተወያዩ ሳለ ፓልሚራ የተባለችው ይህችው መነኩሲት ብዙ መከራ እንዳሳለፈች ሳትሸሽግ ተናግራለች። መነኩሴዎች በሚያስተዳድሩት አንድ ተቋም ውስጥ ለረዥም ጊዜ ኖራለች። በሕመም ምክንያት ለተወሰነ ጊዜ ወጥታ ስትመለስ እንዳትገባ ከለከሏት። ይሁን እንጂ ፓልሚራ በመነኩሴነት ለአምላክ የገባችውን መሃላ መጠበቅ እንዳለባት ተሰማት። “ከሕመሟ ለመዳን” ወደ ፈዋሾች ዘንድ ብትሄድም ጭራሹኑ የአእምሮ መቃወስ ደረሰባት። ፓልሚራ መጽሐፍ ቅዱስ ለማጥናት ተስማማች እንዲሁም ለአንድ ዓመት በክርስቲያን ስብሰባዎች ላይ ተገኘች። ከዚያም መኖሪያዋን ቀይራ ወደ ሌላ አካባቢ በመሄዷ ምሥክሮቹ ሊያገኟት ሳይችሉ ቀሩ። አሱንታ ያገኘቻት ከሁለት ዓመት በኋላ ነበር። ፓልሚራ ከቤተሰቧና ከቀሳውስት ከፍተኛ ተቃውሞ እንደደረሰባት ተናገረች። የሆነ ሆኖ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቷን ቀጠለች፣ መንፈሳዊ እድገት አድርጋ ከተጠመቀች በኋላ የይሖዋ ምሥክር ሆነች።

አዎን፣ ብዙዎች ‘አጽናኝ የሆነው አምላክ’ በሚሰጠው መልእክት ማበረታቻ አግኝተዋል። (ሮሜ 15:​4, 5) በኢጣሊያ የሚኖሩ የይሖዋ ምሥክሮችም ድንቅ የሆነውን የአምላክ የማጽናኛ መልእክት ለሌሎች በማድረስ አምላክን መምሰላቸውን ለመቀጠል በቁርጠኝነት ተነስተዋል።