በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

“ነቅታችሁ ጠብቁ”

“ነቅታችሁ ጠብቁ”

“ነቅታችሁ ጠብቁ”

“ጌታችሁ በምን ሰዓት እንዲመጣ አታውቁምና እንግዲህ ንቁ።”​—⁠ማቴዎስ 24:​42

1. ለረጅም ዓመታት ይሖዋን ያገለገሉ ሰዎች በይሖዋ አገልግሎት ስላሳለፏቸው በርካታ ዓመታት እንዴት ይሰማቸዋል? አንድ ምሳሌ ጥቀስ።

 ይሖዋን ለረጅም ዓመታት ካገለገሉት ሰዎች መካከል ብዙዎቹ እውነትን ያወቁት ገና ወጣቶች ሳሉ ነበር። በጣም ውድ ዋጋ ያላት እንቁ በማግኘቱ ያለውን ሁሉ ሸጦ ያችን ዕንቁ እንደገዛው ነጋዴ እነዚህ ንቁ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎችም ራሳቸውን ክደው ሕይወታቸውን ለይሖዋ ወሰኑ። (ማቴዎስ 13:​45, 46፤ ማርቆስ 8:​34) አምላክ ለምድር ያለው ዓላማ እነሱ ይፈጸማል ብለው ከጠበቁት ጊዜ በላይ በመዘግየቱ እንዴት ይሰማቸዋል? ምንም የሚቆጩበት ነገር የለም! 60 ለሚያክሉ ዓመታት አምላክን ሲያገለግል ከቆየ በኋላ “በእምነቴ ለመቀጠል ከመቼውም ጊዜ የበለጠ ቆርጫለሁ። ሕይወት ትርጉም ያለው ሆኖልኛል። አሁንም እንኳን ቢሆን የወደፊቱን ጊዜ አላንዳች ፍርሐት እንድጠብቅ እየረዳኝ ነው” ሲል ከተናገረው ከወንድም ኤ ኤች ማክሚላን ጋር ይስማማሉ።

2.(ሀ) ኢየሱስ ለተከታዮቹ ምን ወቅታዊ ምክር ሰጥቶ ነበር? (ለ) በዚህ ርዕስ የትኞቹን ጥያቄዎች እንመረምራለን?

2 አንተስ ምን ይሰማሃል? በየትኛውም የዕድሜ ክልል የምትገኝ ብትሆን ኢየሱስ “ጌታችሁ በምን ሰዓት እንዲመጣ አታውቁምና እንግዲህ ንቁ” ሲል የተናገራቸውን ቃላት ልብ ልትላቸው ይገባል። (ማቴዎስ 24:​42) ይህ ቀላል አረፍተ ነገር ጥልቅ የሆነ እውነት ይዟል። ጌታ በዚህ ክፉ ሥርዓት ላይ የቅጣት ፍርድ ለማስፈጸም በየትኛው ቀን እንደሚመጣ አናውቅም። ደግሞም ማወቅ አያስፈልገንም። እኛ ማድረግ የሚኖርብን ጌታ በሚመጣበት ጊዜ የምንቆጭበት ነገር እንዳይኖር በሚያስችል መንገድ መመላለስ ነው። በዚህ ረገድ ነቅተን እንድንጠብቅ የሚረዱን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ምን ምሳሌዎች እናገኛለን? ኢየሱስ ይህን በምሳሌ ያብራራው እንዴት ነበር? በዚህ አምላካዊ ባልሆነ ዓለም የመጨረሻ ቀኖች ውስጥ እንደምንኖር የሚያሳዩ ምን ማስረጃዎች አሉ?

የማስጠንቀቂያ ምሳሌ

3. ዛሬ ያሉ ብዙዎቹ ሰዎች በኖኅ ዘመን ከነበሩት ሰዎች ጋር የሚመሳሰሉት እንዴት ነው?

3 ዛሬ ያሉ ሰዎች በብዙ ነገሮች በኖኅ ዘመን ከነበሩት ወንዶችና ሴቶች ጋር ይመሳሰላሉ። በዚያ ዘመን ምድር በዓመፅ ተሞልታ ነበር። የሰውም የልቡ ዝንባሌ “ሁልጊዜ ፈጽሞ ክፉ” ሆኖ ነበር። (ዘፍጥረት 6:​5) አብዛኞቹ ሰዎች በዕለት ተዕለት የኑሮ ጉዳዮች ሙሉ በሙሉ ተውጠው ነበር። ሆኖም ይሖዋ ታላቁን የጥፋት ውኃ ከማምጣቱ በፊት ሰዎች ንስሐ መግባት የሚችሉበትን አጋጣሚ ሰጥቷቸው ነበር። ለኖኅ የመስበክ ተልእኮ ሰጠው፤ ኖኅም ለ40 ወይም ለ50 ምናልባትም ከዚያ ለሚበልጡ ዓመታት “የጽድቅ ሰባኪ” በመሆን በታዛዥነት አገልግሏል። (2 ጴጥሮስ 2:​5) ይሁን እንጂ ሰዎቹ ለኖኅ የማስጠንቀቂያ መልእክት ጆሯቸውን አልሰጡም። ነቅተው በመጠበቅ ላይ አልነበሩም። ስለሆነም በመጨረሻ ከይሖዋ የቅጣት ፍርድ የተረፉት ኖኅና ቤተሰቡ ብቻ ነበሩ።​—⁠ማቴዎስ 24:​37-39

4. የኖኅ አገልግሎት የተሳካ ነበር ሊባል የሚችለው ለምንድን ነው? ስለ አንተም የስብከት አገልግሎት ተመሳሳይ ነገር ሊባል የሚችለው እንዴት ነው?

4 ታዲያ የኖኅ አገልግሎት የተሳካ ነበር ሊባል ይችላልን? አዎንታዊ ምላሽ የሰጡት ሰዎች ቁጥር ጥቂት መሆኑን አትመልከት። የሰዎቹ ምላሽ ምንም ይሁን ምን የኖኅ ስብከት የታቀደለትን ዓላማ አከናውኗል። ለምን እንደዚያ እንላለን? ምክንያቱም ሰዎች ይሖዋን ለማገልገል ወይም ላለማገልገል የራሳቸውን ምርጫ እንዲያደርጉ አጋጣሚ ሰጥቶአቸዋል። ስለ አንተ የአገልግሎት ክልልስ ምን ለማለት ይቻላል? የሚቀበሉህ ሰዎች እጅግ አናሳ ቢሆኑም አገልግሎትህ የተሳካ ነው። ለምን? ምክንያቱም በምትሰብክበት ጊዜ የአምላክን ማስጠንቀቂያ እያስተጋባህ ነው። በዚህም ኢየሱስ ለተከታዮቹ የሰጣቸውን ተልዕኮ ትፈጽማለህ።​—⁠ማቴዎስ 24:​14፤ 28:​19, 20

ለአምላክ ነቢያት ጆሮ አለመስጠት

5. (ሀ) በዕንባቆም ዘመን በይሁዳ ምን ዓይነት ሁኔታ ተስፋፍቶ ነበር? ሰዎቹስ ለትንቢታዊ መልእክቱ ምን ዓይነት ምላሽ ሰጡ? (ለ) የይሁዳ ሕዝብ ለይሖዋ ነቢያት ጥላቻ ያሳዩት እንዴት ነበር?

5 የጥፋት ውኃው ከደረሰ ከበርካታ መቶ ዓመታት በኋላ በይሁዳ ግዛት የነበረው ሁኔታ በጣም አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሶ ነበር። የጣዖት አምልኮ፣ የፍትሕ መጓደል፣ ጭቆናና ነፍስ ግድያ ሳይቀር የተለመዱ ነገሮች ሆነው ነበር። ንስሐ ካልገቡ በከለዳውያን ወይም በባቢሎናውያን እጅ ጥፋት እንደሚደርስባቸው ሕዝቡን ያስጠነቅቅ ዘንድ ይሖዋ ነቢዩ ዕንባቆምን አስነሳ። (ዕንባቆም 1:​5-7) ሆኖም ሕዝቡ ለመስማት ፈቃደኛ ሳይሆን ቀረ። ‘ከመቶ ከሚበልጡ ዓመታት በፊትም ነቢዩ ኢሳይያስ እንዲሁ ሲለፍፍ ነበር፤ ሆኖም ምንም አዲስ ነገር አልመጣም!’ ብለው አስበው ሊሆን ይችላል። (ኢሳይያስ 39:​6, 7) የይሁዳ ባለ ሥልጣናት ለተነገራቸው ማስጠንቀቂያ ደንታ ቢስ ከመሆናቸውም በላይ ለመልእክተኞቹም ጥላቻ አሳድረው ነበር። በአንድ ወቅት ነቢዩ ኤርምያስን ለመግደል ሞክረው የነበረ ሲሆን አኪቃም ባያድነው ኖሮ ገድለዉት ነበር። ንጉሥ ኢዮአቄም በሌላ ትንቢታዊ መልእክት ተቆጥቶ ነቢዩ ኦርዮን አስገድሏል።​—⁠ኤርምያስ 26:​21-24

6. ይሖዋ ዕንባቆምን ያጠነከረው እንዴት ነው?

6 ይሁዳ ለ70 ዓመት ባድማ እንደምትሆን በመለኮታዊ መንፈስ አነሳሽነት አስቀድሞ እንደተናገረው እንደ ኤርምያስ ሁሉ የዕንባቆም መልእክትም ኃይለኛና ብዙዎችን የሚያስቆጣ ነበር። (ኤርምያስ 25:​8-11) ስለሆነም ዕንባቆም “አቤቱ፣ እኔ ስጮኽ የማትሰማው እስከ መቼ ነው? ስለ ግፍ ወደ አንተ እጮሃለሁ፣ አንተም አታድንም” ሲል ጭንቀቱን የገለጸው ለምን እንደሆነ ሊገባን ይችላል። (ዕንባቆም 1:​2) ይሖዋ በሚከተሉት እምነት የሚያጠነክሩ ቃላት መለሰለት:- “ራእዩ ገና እስከ ተወሰነው ጊዜ ነው፣ ወደ ፍጻሜውም ይቸኩላል፣ እርሱም አይዋሽም፤ ቢዘገይም በእርግጥ ይመጣልና ታገሠው፤ እርሱ አይዘገይም።” (ዕንባቆም 2:​3) ይሖዋ ጭቆናንና የፍትሕ መጓደልን የሚያስወግድበት ‘የተወሰነ ጊዜ’ አለው። የትንቢቱ አፈጻጸም የዘገየ መስሎ ቢታይ እንኳን ዕንባቆም ተስፋ መቁረጥ ወይም ከሥራው ወደ ኋላ ማለት አልነበረበትም። ከዚህ ይልቅ በእያንዳንዷ ቀን የጥድፊያ ስሜቱን ሳያጠፋ ‘መጠበቅ’ ነበረበት። የይሖዋ ቀን አይዘገይም!

7. ኢየሩሳሌም በመጀመሪያው መቶ ዘመን እዘአ ዳግመኛ ጥፋት የተቆረጠባት ለምን ነበር?

7 ይሖዋ ዕንባቆምን ካነጋገረው 20 ከሚያክሉ ዓመታት በኋላ የይሁዳ ዋና ከተማ ኢየሩሳሌም ጠፍታለች። ኢየሩሳሌም ከዓመታት በኋላ ዳግመኛ የተገነባች ሲሆን ዕንባቆምንም አስጨንቀውት ከነበሩት መጥፎ ሁኔታዎች ብዙዎቹ ተስተካክለዋል። ይሁን እንጂ በመጀመሪያው መቶ ዘመን እዘአ ደግሞ ይህችው ከተማ ነዋሪዎቿ ከዳተኞች በመሆናቸው ምክንያት ጥፋት ተቆረጠባት። ሆኖም ይሖዋ በመራራት ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች ከጥፋቱ የሚድኑበትን ዝግጅት አደረገ። በዚህ ጊዜ ግን መልእክቱን እንዲያደርስ የተጠቀመበት ከሁሉ የላቀውን ነቢይ ኢየሱስ ክርስቶስን ነው። በ33 እዘአ ኢየሱስ ለተከታዮቹ “ኢየሩሳሌም ግን በጭፍራ ተከባ ስታዩ በዚያን ጊዜ ጥፋትዋ እንደ ቀረበ እወቁ። የዚያን ጊዜ በይሁዳ ያሉ ወደ ተራራዎች ይሽሹ፣ በመካከልዋም ያሉ ከእርስዋ ፈቀቅ ይበሉ፣ በገጠር ያሉም ወደ እርስዋ አይግቡ” ሲል ነግሯቸው ነበር።​—⁠ሉቃስ 21:​20, 21

8. (ሀ) ኢየሱስ ከሞተ በኋላ ጊዜ እያለፈ ሲሄድ አንዳንዶቹ ክርስቲያኖች ምን አጋጥሟቸው ሊሆን ይችላል? (ለ) ኢየሱስ ኢየሩሳሌምን አስመልክቶ የተናገራቸው ትንቢታዊ ቃላት ፍጻሜያቸውን ያገኙት እንዴት ነበር?

8 ዓመታት እያለፉ ሲሄዱ በኢየሩሳሌም የነበሩ አንዳንድ ክርስቲያኖች ታዲያ የኢየሱስ ትንቢት የሚፈጸመው መቼ ነው ብለው ሳያስቡ አይቀሩም። ደግሞም ከእነሱ መካከል አንዳንዶቹ ምን መሥዋዕትነቶች ከፍለው ሊሆን እንደሚችል አስቡ። ምናልባትም ነቅተው ለመጠበቅ ካላቸው ቁርጠኝነት የተነሳ ብዙ ትርፍ የሚያስገኙ የንግድ አጋጣሚዎችን ትተው ይሆናል። ጊዜው እየተራዘመ ሲሄድ ተዳክመው ይሆን? የኢየሱስ ትንቢት የሚፈጸመው በእነርሱ ትውልድ ሳይሆን ወደፊት በሚመጣ ሌላ ትውልድ ላይ እንደሆነ በማሰብ ጊዜያቸውን በከንቱ እንዳባከኑ ተሰምቷቸው ነበርን? በ66 እዘአ የሮማ ሠራዊት ኢየሩሳሌምን በከበበበት ወቅት የኢየሱስ ትንቢት ፍጻሜውን ማግኘት ጀመረ። ነቅተው ይጠብቁ የነበሩት ክርስቲያኖች ምልክቱን አስተውለው ስለነበር ከከተማይቱ ሸሽተው በመውጣታቸው በኢየሩሳሌም ላይ ከደረሰው ጥፋት ድነዋል።

ነቅቶ የመጠበቅን አስፈላጊነት በምሳሌ ማስረዳት

9, 10. (ሀ) ኢየሱስ ከሠርግ የሚመለስ ጌታቸውን የሚጠብቁ ባሮችን አስመልክቶ የተናገረውን ምሳሌ ጠቅለል ባለ ሁኔታ እንዴት ትገልጸዋለህ? (ለ) ባሮቹ ጌታቸውን መጠበቁ አስቸጋሪ ሆኖባቸው ሊሆን የሚችለው ለምንድን ነው? (ሐ) ባሮቹ በትዕግሥት መጠበቃቸው ጠቃሚ የሆነው ለምንድን ነው?

9 ኢየሱስ ነቅቶ የመጠበቅን አስፈላጊነት ለማጉላት ደቀ መዛሙርቱን ከሠርግ የሚመለስ ጌታቸውን ከሚጠባበቁ ባሮች ጋር አመሳስሏቸዋል። ጌታቸው አንድ ሌሊት መምጣቱ እንደማይቀር ያውቁ ነበር፤ ይሁን እንጂ የሚመጣው በየትኛው ሰዓት ላይ ነው? ከሌሊቱ በየትኛው ክፍል? በመጀመሪያው ወይስ በሁለተኛው ወይስ በሦስተኛው? ምንም የሚያውቁት ነገር የለም። ኢየሱስ እንዲህ አለ:- “[ጌታቸው] ከሌሊቱም በሁለተኛው ወይም በሦስተኛው ክፍል መጥቶ እንዲሁ [ነቅተው ሲጠብቁ] ቢያገኛቸው፣ እነዚያ ባሪያዎች ብፁዓን ናቸው።” (ሉቃስ 12:​35-38) እነዚህ ባሮች ምን ያህል በጉጉት ይጠብቁ እንደነበር ልትገምቱ ትችላላችሁ። ትንሽ ኮሽታ በሰሙና ጥላ ውልብ ባለ ቁጥር ‘ጌታችን ይሆን?’ ይላሉ።

10 ጌታው ከሌሊቱ በሁለተኛው ክፍል ማለትም ከሦስት ሰዓት እስከ እኩለ ሌሊት ባለው ጊዜ ቢመጣስ? ሁሉም ባሮቹ፣ ከማለዳ ጀምረው በሥራ ሲደክሙ የነበሩት ጭምር በንቃት ይቀበሉት ይሆን? ወይስ ከመካከላቸው አንዳንዶቹ እንቅልፍ ይጥላቸው ይሆን? ጌታው ከሌሊቱ ስድስት ሰዓት እስከ ሌሊቱ ዘጠኝ ሰዓት ባለው ጊዜ ማለትም ከሌሊቱ በሦስተኛው ክፍል ቢመጣስ? ጌታቸው በጣም እንደ ዘገየ ተሰምቷቸው ተስፋ የሚቆርጡ አልፎ ተርፎም የሚያኮርፉ አንዳንድ ባሮች ይኖሩ ይሆን? a ደስተኛ ናችሁ የሚባሉት ጌታው በመጣበት ጊዜ ነቅተው ሲጠብቁ የተገኙት ባሮች ብቻ ናቸው። በምሳሌ 13:​12 ላይ የሚገኙት “የምትዘገይ ተስፋ ልብን ታሳዝናለች፤ የተገኘች ፈቃድ ግን የሕይወት ዛፍ ናት” የሚሉት ቃላት በእነሱ ላይ ይሠራሉ።

11. ጸሎት ነቅተን እንድንጠብቅ ሊረዳን የሚችለው እንዴት ነው?

11 ጊዜው የዘገየ ቢመስልም የኢየሱስ ተከታዮች ነቅተው እንዲጠብቁ የሚረዳቸው ነገር ምንድን ነው? ኢየሱስ ከመያዙ ጥቂት ቀደም ብሎ በጌቴሴማኒ የአትክልት ሥፍራ አብረውት ለነበሩ ሦስት ሐዋርያቱ “ወደ ፈተና እንዳትገቡ ነቅታችሁ ጠብቁ፤ በትጋት ጸልዩ” ሲል ነግሯቸው ነበር። (ማቴዎስ 26:​41 NW ) በዚህ ወቅት አብሮ የነበረው ጴጥሮስ ዓመታት ካለፉ በኋላ ለክርስቲያን ባልደረቦቹ ተመሳሳይ ምክር ሰጥቷል። እንዲህ ሲል ጻፈ:- “ዳሩ ግን የነገር ሁሉ መጨረሻ ቀርቦአል። እንግዲህ እንደ ባለ አእምሮ አስቡ፣ ትጸልዩም ዘንድ በመጠን ኑሩ [“ትጉ፣” NW ]።” (1 ጴጥሮስ 4:​7) ልባዊ ጸሎት የክርስቲያናዊ ሕይወታችን ክፍል መሆን እንዳለበት ምንም ጥርጥር የለውም። አዎን፣ ነቅተን እንድንጠብቅ ይረዳን ዘንድ ይሖዋን መለመን ያስፈልገናል።​—⁠ሮሜ 12:​12፤ 1 ተሰሎንቄ 5:​17

12. የግምት አስተያየት በመሰንዘርና ነቅቶ በመጠባበቅ መካከል ያለው ልዩነት ምንድን ነው?

12 በተጨማሪም ጴጥሮስ “የነገር ሁሉ መጨረሻ ቀርቧል” እንዳለ ልብ በል። ምን ያህል ቀርቧል? ሰዎች ትክክለኛውን ቀንና ሰዓት መገመት አይችሉም። (ማቴዎስ 24:​36) ይሁን እንጂ የግምት አስተያየት በመሰንዘርና መጨረሻውን በጉጉት በመጠባበቅ መካከል ልዩነት አለ። መጽሐፍ ቅዱስ የግምት አስተያየት መስጠትን አያበረታታም። በጉጉት መጠባበቅን ግን ያበረታታል። (ከ2 ጢሞቴዎስ 4:​3, 4፤ ከቲቶ 3:​9 ጋር አወዳድር።) መጨረሻውን በጉጉት እየተጠባበቅን ለመኖር ከምንችልባቸው መንገዶች አንዱ ምንድን ነው? መጨረሻው ቅርብ መሆኑን የሚጠቁሙትን ምልክቶች በትኩረት መከታተል ነው። እንግዲያው ይህን ለማድረግ እንችል ዘንድ የምንኖረው በመጨረሻው ቀን ስለመሆኑ እርግጠኛ የምንሆንባቸውን ስድስት ማስረጃዎች ብንከልስ ጥሩ ይሆናል።

ስድስት አሳማኝ ማስረጃዎች

13. ጳውሎስ በ⁠2 ጢሞቴዎስ ምዕራፍ 3 ላይ የመዘገበው ትንቢት ‘በመጨረሻው ቀን’ እንደምንኖር የሚያሳምንህ እንዴት ነው?

13 አንደኛው ማስረጃ፣ ጳውሎስ ስለ ‘መጨረሻው ቀን ’ የተናገራቸው ቃላት ፍጻሜያቸውን እንዳገኙ በግልጽ እንመለከታለን። ጳውሎስ እንደሚከተለው ሲል ጽፏል:- “ነገር ግን በመጨረሻው ቀን የሚያስጨንቅ ዘመን እንዲመጣ ይህን እወቅ። ሰዎች ራሳቸውን የሚወዱ ይሆናሉና፣ ገንዘብን የሚወዱ፣ ትምክህተኞች፣ ትዕቢተኞች፣ ተሳዳቢዎች፣ ለወላጆቻቸው የማይታዘዙ፣ የማያመሰግኑ፣ ቅድስና የሌላቸው፣ ፍቅር የሌላቸው፣ ዕርቅን የማይሰሙ፣ ሐሜተኞች፣ ራሳቸውን የማይገዙ፣ ጨካኞች፣ መልካም የሆነውን የማይወዱ፣ ከዳተኞች፣ ችኩሎች፣ በትዕቢት የተነፉ፣ ከእግዚአብሔር ይልቅ ተድላን የሚወዱ ይሆናሉ፤ የአምልኮት መልክ አላቸው ኃይሉን ግን ክደዋል፤ ከእነዚህ ደግሞ ራቅ። ነገር ግን ክፉዎች ሰዎችና አታላዮች፣ እያሳቱና እየሳቱ፣ በክፋት እየባሱ ይሄዳሉ።” (2 ጢሞቴዎስ 3:​1-5, 13) ይህ ትንቢት በጊዜያችን ፍጻሜውን እያገኘ እንዳለ እየተመለከትን አይደለም? ይህን ሊክዱ የሚችሉት ሐቁን ላለማየት ዓይናቸውን የጨፈኑ ብቻ ናቸው! b

14. በ⁠ራእይ 12:​9 ላይ የሚገኙት ስለ ዲያብሎስ የሚናገሩት ቃላት በዛሬው ጊዜ ፍጻሜያቸውን እያገኙ ያሉት እንዴት ነው? በቅርቡስ ምን ይደርስበታል?

14 ሁለተኛው ማስረጃ፣ በራእይ 12:​9 ፍጻሜ መሠረት የሰይጣንና የአጋንንቱ ከሰማይ መባረር ያስከተለውን ውጤት እየተመለከትን ነው። በዚህ ጥቅስ ላይ እንደሚከተለው እናነባለን:- “ዓለሙንም ሁሉ የሚያስተው፣ ዲያብሎስና ሰይጣን የሚባለው ታላቁ ዘንዶ እርሱም የቀደመው እባብ ተጣለ፤ ወደ ምድር ተጣለ መላእክቱም ከእርሱ ጋር ተጣሉ።” ይህም በምድር ላይ ትልቅ ወዮታ አስከትሏል። በእርግጥም፣ በተለይ ከ1914 ወዲህ የሰው ልጅ በታላቅ ወዮታ ውስጥ ይገኛል። ሆኖም ዲያብሎስ ወደ ምድር ሲጣል ‘የቀረው ጊዜ ጥቂት መሆኑን’ እንደሚያውቅ በራእይ ላይ የሚገኘው ትንቢት አክሎ ይገልጻል። (ራእይ 12:​12) በዚህ ጊዜ ሰይጣን በቅቡዓን የክርስቶስ ተከታዮች ላይ ጦርነት ያውጃል። (ራእይ 12:​17) በዘመናችን የሰይጣን ጥቃት ያስከተለውን ውጤት በሚገባ ተመልክተናል። c ሆኖም በቅርቡ ሰይጣን “ከእንግዲህ አሕዛብን እንዳያስት” ወደ ጥልቁ ይጣላል።​—⁠ራእይ 20:​1-3

15. ራእይ 17:​9-11 በመጨረሻው ቀን እንደምንኖር ተጨማሪ ማስረጃ የሚሰጠን እንዴት ነው?

15 ሦስተኛው ማስረጃ፣ በራእይ 17:​9-11 ላይ ተመዝግቦ በሚገኘው ትንቢት ውስጥ የተገለጸው ስምንተኛውና የመጨረሻው ‘ንጉሥ ’ ሕልውና ባገኘበት ዘመን ውስጥ የምንኖር መሆናችን ነው። እዚህ ላይ ሐዋርያው ዮሐንስ ሰባት የዓለም ኃያላን መንግሥታትን ማለትም ግብፅን፣ አሦርን፣ ባቢሎንን፣ ሜዶ ፋርስን፣ ግሪክን፣ ሮምንና አንግሎ አሜሪካን የሚወክሉ ሰባት ነገሥታት ተመልክቷል። በተጨማሪም ዮሐንስ ‘ከሰባቱ የወጣ’ ሌላ ‘ስምንተኛ ንጉሥ’ አይቷል። ዮሐንስ የተመለከተው ስምንተኛውና የመጨረሻው ንጉሥ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን ያመለክታል። ዮሐንስ ይህ ስምንተኛ ንጉሥ ‘ወደ ጥፋት እንደሚሄድ’ የገለጸ ሲሆን ከስምንተኛው በኋላ የሚነሳ ሌላ ምድራዊ ንጉሥ አልተጠቀሰም። d

16. ናቡከደነፆር በሕልም ያየውን ምስል በሚመለከት የተፈጸሙ ሁኔታዎች በመጨረሻዎቹ ቀኖች ውስጥ እንደምንኖር የሚያመለክቱት እንዴት ነው?

16 አራተኛው ማስረጃ፣ ናቡከደነፆር በሕልም ባየው ምስል እግሮች በተመሰለው ዘመነ መንግሥት የምንኖር መሆኑ ነው። ነቢዩ ዳንኤል በሰው መልክ የተሠራው የዚህ አስገራሚ ግዙፍ ምስል ትርጉም ምን እንደሆነ ተናግሯል። (ዳንኤል 2:​36-43) ምስሉ የተሠራባቸው አራት ዓይነት የብረት ማዕድናት ከምስሉ ራስ (ከባቢሎን ግዛት) ጀምሮ እስከ እግሩና ጣቶቹ (ዛሬ በመግዛት ላይ እስከሚገኙት መንግሥታት) ያሉትን የተለያዩ የዓለም ኃያላን መንግሥታትን ያመለክታሉ። በምስሉ የተወከሉት የዓለም ኃያል መንግሥታት በሙሉ አልፈዋል። አሁን የምንኖረው በሕልም በታየው ምስል በእግሮቹ በተመሰለው ዘመነ መንግሥት ነው። ሌሎች ኃይሎች እንደሚነሱ የተጠቀሰ ነገር የለም። e

17. የመንግሥቱ ስብከት እንቅስቃሴያችን በመጨረሻው ቀን እንደምንኖር ተጨማሪ ማስረጃ የሚሰጠን እንዴት ነው?

17 አምስተኛው ማስረጃ፣ ኢየሱስ ይህ የነገሮች ሥርዓት ከማለቁ በፊት ይከናወናል ብሎ የተናገረው ዓለም አቀፍ የስብከት ሥራ በመከናወን ላይ መሆኑን እያየን ነው። ኢየሱስ “ለአሕዛብም ሁሉ ምስክር እንዲሆን ይህ የመንግሥት ወንጌል በዓለም ሁሉ ይሰበካል፣ በዚያን ጊዜም መጨረሻው ይመጣል” ሲል ተናግሯል። (ማቴዎስ 24:​14) በዛሬው ጊዜ ይህ ትንቢት ከዚህ ቀደም ሆኖ በማያውቅ መጠን በመፈጸም ላይ ነው። አሁንም ገና ያልተነኩ የአገልግሎት ክልሎች መኖራቸው እሙን ነው፤ ይሖዋ የፈቀደው ጊዜ ሲደርስ ከዚህ የበለጠ ሰፊ የአገልግሎት በር ይከፈት ይሆናል። (1 ቆሮንቶስ 16:​9) የሆነ ሆኖ መጽሐፍ ቅዱስ በምድር ላይ የሚኖር እያንዳንዱ ግለሰብ ምሥክርነቱ እስኪደርሰው ድረስ ይሖዋ ታላቁን መከራ እንደሚያቆየው የሚናገርበት አንድም ቦታ የለም። ከዚህ ይልቅ ምሥራቹ ይሖዋ በሚፈልገው መጠን ከተሰበከ በኋላ መጨረሻው ይመጣል።​—⁠ከማቴዎስ 10:​23 ጋር አወዳድር።

18. ታላቁ መከራ በሚጀምርበት ጊዜ ስለ አንዳንዶቹ ቅቡዓን ምን ለማለት ይቻላል? እንዲህ ለማለት የሚቻለውስ እንዴት ነው?

18 ስድስተኛው ማስረጃ፣ ምንም እንኳ ታላቁ መከራ በሚጀምርበት ጊዜ አንዳንዶቹ ገና እዚሁ ምድር ላይ እንደሚሆኑ ከሁኔታዎች መረዳት ቢቻልም ታማኝ ቅቡዓን የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት ቁጥር እየቀነሰ በመሄድ ላይ ነው። በአሁኑ ጊዜ አብዛኞቹ ቅቡዓን በዕድሜ ከመግፋታቸውም በላይ ባለፉት ዓመታት ደግሞ የእውነተኞቹ ቅቡዓን ቁጥር እየተመናመነ መጥቷል። ኢየሱስ ታላቁን መከራ አስመልክቶ ሲናገር “እነዚያ ቀኖችስ ባያጥሩ ሥጋ የለበሰ ሁሉ ባልዳነም ነበር፤ ነገር ግን እነዚያ ቀኖች ስለ ተመረጡት ሰዎች ያጥራሉ” ብሏል። (ማቴዎስ 24:​21, 22) ስለዚህ ታላቁ መከራ በሚፈነዳበት ጊዜ አንዳ​ንድ ‘የተመረጡ ቅቡዓን’ በምድር ላይ ይኖራሉ ማለት ነው። f

ከፊታችን ምን ይጠብቀናል?

19, 20. ነቅቶ መኖርና ነቅቶ መጠበቅ ከምንጊዜውም ይበልጥ ዛሬ አጣዳፊ የሆነው ለምንድን ነው?

19 የወደፊቱ ጊዜ ምን ይዞልናል? በጣም አስደሳች የሆነ ጊዜ ይጠብቀናል። ጳውሎስ “የጌታ ቀን፣ ሌባ በሌሊት እንደሚመጣ፣ እንዲሁ ይመጣል” ሲል አስጠንቅቋል። ከዚያም በዓለማዊ ጥበብ ተራቅቀናል የሚሉ ሰዎችን በሚመለከት “ሰላምና ደኅንነት ነው ሲሉ፣ . . . ጥፋት በድንገት ይመጣባቸዋል” ብሏል። ስለዚህ ጳውሎስ አንባቢዎቹን “እንግዲያስ እንንቃ በመጠንም እንኑር እንጂ እንደ ሌሎች አናንቀላፋ” ሲል አጥብቆ አሳስቧቸዋል። (1 ተሰሎንቄ 5:​2, 3, 6) አዎን፣ ሰብዓዊ ድርጅቶች ሰላምና ደህንነት ያስገኛሉ ብለው ተስፋ የሚያደርጉ ሁሉ ሐቁን ችላ ብለዋል። እንዲህ ያሉት ግለሰቦች ጭልጥ ያለ እንቅልፍ ላይ ናቸው!

20 የዚህ ሥርዓት ጥፋት በአስደንጋጭ ሁኔታ ድንገት ይመጣል። ስለዚህ የይሖዋን ቀን ነቅታችሁ መጠባበቃችሁን ቀጥሉ። አምላክ ራሱ ለዕንባቆም ቀኑ “አይዘገይም” ሲል ነግሮታል! በእርግጥም ነቅቶ የመጠበቅ ጉዳይ የአሁኑን ያክል አጣዳፊ የሆነበት ጊዜ የለም።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

a ጌታው ለባሮቹ የሰጠው ቀጠሮ የለም። ስለ አመጣጡም ሆነ ስለ አካሄዱ የመናገርም ሆነ፣ የዘገየ ስለመሰላቸው ምክንያቱን የማስረዳት ግዴታ የለበትም።

b ይህን ትንቢት በተመለከተ ዝርዝር ማብራሪያ ለማግኘት ኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር የታተመውን ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራ እውቀት የተባለውን መጽሐፍ ምዕራፍ 11 ተመልከት።

c ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት ኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር የታተመውን ራእይ —⁠ታላቁ መደምደሚያው ደርሷል! የተባለውን መጽሐፍ ገጽ 180-6 ተመልከት።

e ኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር የታተመውን የዳንኤልን ትንቢት በትኩረት ተከታተል! የተባለውን መጽሐፍ ምዕራፍ 4 ተመልከት።

f ስለ በጎችና ፍየሎች በሚናገረው ምሳሌ ውስጥ የሰው ልጅ በታላቁ መከራ ወቅት በክብር መጥቶ ለፍርድ ይቀመጣል። ለክርስቶስ ቅቡዓን ወንድሞች በሰጡት ድጋፍ መሠረት ሰዎችን ይዳኛል። ፍርዱ የሚከናወነው የክርስቶስ ቅቡዓን ወንድሞች በሙሉ ከምድር ላይ ከሄዱ ከረጅም ጊዜ በኋላ ቢሆን ኖሮ በዚህ መሠረት የዘላለም ሕይወት ወይም የዘላለም ጥፋት ፍርድ መስጠት ትርጉም የለሽ ይሆናል።​—⁠ማቴዎስ 25:​31-46

ታስታውሳለህን?

• ነቅተን እንድንጠብቅ ሊረዱን የሚችሉ ቅዱስ ጽሑፋዊ ምሳሌዎች የትኞቹ ናቸው?

• ኢየሱስ ነቅቶ የመጠበቅን አስፈላጊነት በምሳሌ ያስረዳው እንዴት ነው?

• በመጨረሻዎቹ ቀናት ውስጥ እንደምንኖር የሚያሳዩ ስድስት ማስረጃዎች የትኞቹ ናቸው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኤ ኤች ማክሚላን ለስድስት አሥርተ ዓመታት ያህል ይሖዋን በታማኝነት አገልግሏል

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን ጌታቸውን ነቅተው ከሚጠባበቁ ባሪያዎች ጋር አመሳስሏቸዋል