በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

“የተመረጡ ዕቃዎች” የይሖዋን ቤት እየሞሉት ነው

“የተመረጡ ዕቃዎች” የይሖዋን ቤት እየሞሉት ነው

የተመረጡ ዕቃዎች” የይሖዋን ቤት እየሞሉት ነው

“[እኔ ይሖዋ ] አሕዛብን ሁሉ አናውጣለሁ፣ በአሕዛብ ሁሉ የተመረጠውም ዕቃ ይመጣል፤ ይህንም ቤት በክብር እሞላዋለሁ።”​ሐጌ 2:​7

1. በአደጋ ጊዜ ቶሎ ወደ አእምሮአችን የሚመጡት የቤተሰባችን አባላት የሆኑት ለምንድን ነው?

 በቤትህ ያሉት ምን ዓይነት የተመረጡ ዕቃዎች ናቸው? ቤትህ ውድ በሆኑ የቅንጦት ዕቃዎች የተሞላ ነውን? ዘመናዊ ኮምፒዩተርና አዲስ መኪና አለህ? እነዚህ ነገሮች ሁሉ ቢኖሩህም እንኳ ከሁሉ ይበልጥ ውድ የሆኑ በቤትህ ውስጥ ያሉ ነገሮች አብረውህ የሚኖሩ ሰዎች ማለትም የቤተሰብህ አባላት ናቸው ቢባል አትስማማም? አንድ ቀን ሌሊት ድንገት ከእንቅልፍህ ብንን ስትል ጭስ ጭስ ይሸትሃል። ቤትህ በእሳት ተያይዟል፤ ለማምለጥ ያለህ ጊዜ በደቂቃዎች ብቻ የሚቆጠር ነው! በመጀመሪያ ወደ አእምሮህ የሚመጣው ምንድን ነው? የቤትህ ዕቃ? ኮምፒዩተርህ? ወይስ መኪናህ? ከእነዚህ ሁሉ በመጀመሪያ ወደ አእምሮህ የሚመጡት የቤተሰብህ አባላት አይደሉምን? ሰዎች ከማንኛውም ነገር ይበልጥ ውድ ስለሆኑ እንደዚያ እንደሚሰማህ ምንም ጥርጥር የለውም።

2. የይሖዋ የፍጥረት ሥራ ምን ያህል ስፋት ያለው ነው? ኢየሱስ አብልጦ የወደደው የትኛውን የፍጥረት ሥራ ነው?

2 አሁን ደግሞ ስለ ይሖዋና ስለ ልጁ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ አስብ። “ሰማዩንና ምድሩን ባሕሩንም በእነርሱም የሚኖረውን ሁሉ” የፈጠረው ይሖዋ ነው። (ሥራ 4:​24) “ዋና ሠራተኛ” የነበረው ልጁ ደግሞ ይሖዋ ሌሎች ነገሮችን ሁሉ ለመፍጠር የተጠቀመበት ወኪሉ ነው። (ምሳሌ 8:​30, 31፤ ዮሐንስ 1:​3፤ ቆላስይስ 1:​15-17) ይሖዋም ሆነ ኢየሱስ ለሁሉም ፍጥረታት ከፍተኛ ግምት እንዳላቸው የታወቀ ነው። (ከዘፍጥረት 1:​31 ጋር አወዳድር።) ሆኖም ከፍጥረት ሥራዎቻቸው መካከል ከፍተኛ ግምት የሚሰጡት ለሰው ልጆች ነው ወይስ ለሌሎች ነገሮች? ለየትኛው ይመስልሃል? በጥበብ ተመስሎ የተገለጸው ኢየሱስ “ተድላዬም በሰው ልጆች ነበር” ሲል ተናግሯል። ወይም የዊልያም ኤፍ ቤክስ ትርጉም እንዳስቀመጠው ኢየሱስ “በሰው ልጆች ይደሰት” ነበር።

3. ይሖዋ በሐጌ አማካኝነት ምን ትንቢት ተናገረ?

3 ይሖዋ ለሰው ልጆች የላቀ ግምት እንደሚሰጥ ምንም ጥርጥር የለውም። በ520 ከዘአበ በነቢዩ ሐጌ አማካኝነት የተናገራቸው ትንቢታዊ ቃላት ለዚህ አንድ ማስረጃ ናቸው። ይሖዋ እንዲህ ሲል ተናገረ:- “አሕዛብን ሁሉ አናውጣለሁ፣ በአሕዛብ ሁሉ የተመረጠውም ዕቃ ይመጣል፤ ይህንም ቤት በክብር እሞላዋለሁ . . . ከፊተኛው ይልቅ የዚህ የሁለተኛው ቤት ክብር ይበልጣል።”​—⁠ሐጌ 2:​7, 9

4, 5. (ሀ) ‘የተመረጡ ዕቃዎች’ የሚለው አነጋገር ቃል በቃል ዕጹብ ድንቅ የሆኑ ቁሳዊ ነገሮችን የሚያመለክት ነው ብሎ መደምደም ምክንያታዊ የማይሆነው ለምንድን ነው? (ለ) ‘የተመረጡ ዕቃዎች’ የሚለው አነጋገር ምን ማለት ነው? ለምንስ?

4 የይሖዋን ቤት የሚሞሉት ‘የተመረጡ ዕቃዎች’ ምንድን ናቸው? የላቀ ክብር የሚያመጡትስ እንዴት ነው? የቅንጦት ዕቃዎችና ጌጣ ጌጦች ናቸው? ወርቅ፣ ብርና የከበሩ ድንጋዮች ናቸው? ይህ ፈጽሞ የማይመስል ነገር ነው። በብዙ ቢልዮን ዶላር በሚገመት ወጪ የተገነባውን ከአምስት መቶ ዓመታት ገደማ በፊት የተመረቀውን የቀድሞውን ቤተ መቅደስ አስብ! a ይሖዋ እነዚህ ወደ አገራቸው የተመለሱ አነስተኛ ቁጥር ያላቸው አይሁዶች ሰሎሞን ከሠራው ቤተ መቅደስ ይበልጥ የተዋበ ቤተ መቅደስ ይሠሩልኛል ብሎ እንደማይጠብቅ የታወቀ ነው!

5 ታዲያ የይሖዋን ቤት የሞሉት ‘የተመረጡ ዕቃዎች’ ምንድን ናቸው? መቼም ሰዎች መሆን እንዳለባቸው ግልጽ ነው። ደግሞም የይሖዋን ልብ ደስ ሊያሰኙ የሚችሉት በፍቅር ተነሳስተው የሚያገለግሉት ሰዎች እንጂ እንደ ብርና ወርቅ ያሉ ውድ ማዕድናት ሊሆኑ አይችሉም። (ምሳሌ 27:​11፤ 1 ቆሮንቶስ 10:​26) አዎን፣ ይሖዋ እሱ በሚፈልገው መንገድ የሚያመልኩትን ወንዶች፣ ሴቶችና ልጆች በሙሉ እንደ ውድ አድርጎ ይመለከታቸዋል። (ዮሐንስ 4:​23, 24) የሰሎሞንን ቤተ መቅደስ ካስዋቡት የከበሩ ነገሮች ይበልጥ ይሖዋ እንደ ውድ አድርጎ የሚመለከታቸው ‘የተመረጡ ዕቃዎች’ እነዚህ ሰዎች ናቸው።

6. የጥንቱ የአምላክ ቤተ መቅደስ ለምን ዓላማ አገልግሏል?

6 ኃይለኛ ተቃውሞ ቢኖርም ቤተ መቅደሱ በ515 ከዘአበ ተሠርቶ ሊጠናቀቅ ችሏል። በኢየሩሳሌም የሚገኘው ይህ ቤተ መቅደስ ከአይሁዳውያንና ወደ አይሁድ ከተለወጡት አሕዛብ ለተውጣጡት ብዙ ‘የተመረጡ ዕቃዎች’ ኢየሱስ መሥዋዕት እስከሆነበት ጊዜ ድረስ የንጹሕ አምልኮ ማዕከል ሆኖ አገልግሏል። ሆኖም ቀጥሎ እንደምንመለከተው ቤተ መቅደሱ ከዚህም የላቀ ትርጉም ነበረው።

የመጀመሪያው መቶ ዘመን ፍጻሜ

7. (ሀ) በኢየሩሳሌም የነበረው የጥንቱ የአምላክ ቤተ መቅደስ የምን ጥላ ነበር? (ለ) በስርየት ቀን ሊቀ ካህኑ የሚያከናውነውን ነገር ግለጽ።

7 በኢየሩሳሌም የሚገኘው ቤተ መቅደስ አምልኮን በተመለከተ ለተደረገ አንድ የላቀ ዝግጅት ጥላ ነበር። በኢየሱስ ሊቀ ካህንነት አማካኝነት በ29 እዘአ ይሖዋ ያቋቋመውን መንፈሳዊ ቤተ መቅደስ የሚያመለክት ነበር። (ዕብራውያን 5:​4-10፤ 9:​11, 12) የእስራኤል ሊቀ ካህን በሚያከናውነውና ኢየሱስ በሚያከናውነው ነገር መካከል ያለውን ንጽጽር ተመልከት። በየዓመቱ በስርየት ቀን ሊቀ ካህኑ በቤተ መቅደሱ አደባባይ ወደሚገኘው መሠዊያ ቀርቦ የካህናትን ኃጢአት ለማስተሰረይ የወይፈን መሥዋዕት ያቀርባል። ከዚያም ደሙን ይዞ አደባባዩን ከቅድስቱ በሚለየው ደጃፍ በኩል ያልፍና ቅድስቱን ከቅድስተ ቅዱሳኑ በሚለየው መጋረጃ በኩል ይገባል። ሊቀ ካህኑ ወደ ቅድስተ ቅዱሳኑ ከገባ በኋላ ደሙን በቃል ኪዳኑ ታቦት ፊት ይረጨዋል። ከዚያም ካህናት ያልሆኑትን 12 የእስራኤል ነገዶች ኃጢአት ለማስተሰረይ ተመሳሳይ ቅደም ተከተል በመከተል የፍየል መሥዋዕት ያቀርባል። (ዘሌዋውያን 16:​5-15) ይህ ሥርዓት ከአምላክ መንፈሳዊ ቤተ መቅደስ አሠራር ጋር የሚመሳሰለው እንዴት ነው?

8. (ሀ) ኢየሱስ ከ29 እዘአ ጀምሮ መሥዋዕት ሆኖ የቀረበው በምን መንገድ ነው? (ለ) ኢየሱስ በምድራዊ አገልግሎቱ ወቅት ከይሖዋ ጋር ምን ልዩ ዝምድና ነበረው?

8 በተመሳሳይም ኢየሱስ በ29 እዘአ በተጠመቀበትና በአምላክ ቅዱስ መንፈስ በተቀባበት ጊዜ መሥዋዕት ሆኖ ቀርቧል። እንደ መሠዊያ የተመሰለው የአምላክ ፈቃድ ነው። (ሉቃስ 3:​21, 22) በእርግጥ ይህ ክንውን ኢየሱስ ለሚያሳልፈው የሦስት ዓመት ተኩል መሥዋዕታዊ ሕይወት መጀመሪያ ነበር። (ዕብራውያን 10:​5-10) በዚህ ወቅት ኢየሱስ በመንፈስ የተቀባ ልጅ በመሆን ከአምላክ ጋር ልዩ ዝምድና ነበረው። ኢየሱስ በሰማያዊ አባቱ ፊት አግኝቶት የነበረውን ይህን ልዩ ሞገስ ሌሎች ሰዎች ሙሉ በሙሉ ሊረዱት አይችሉም። በደጃፉ ላይ ያለው መጋረጃ ቅድስቱን በመገናኛው ድንኳን አደባባይ ከነበሩት ሰዎች እይታ እንደሚከልል ሁሉ የሰዎች የማስተዋል ዓይኖች የተጋረዱ ያክል ሆኖ ነበር።​—⁠ዘጸአት 40:​28

9. ኢየሱስ ሰው ሆኖ ወደ ሰማይ ሊገባ ያልቻለው ለምንድን ነበር? ይህስ ሁኔታ መፍትሄ ያገኘው እንዴት ነው?

9 ኢየሱስ በመንፈስ የተቀባ የአምላክ ልጅ ቢሆንም እንኳ ሰብዓዊ አካል ይዞ ሰማያዊ ሕይወት ማግኘት አይችልም ነበር። ለምን? ምክንያቱም ሥጋና ደም የአምላክን ሰማያዊ መንግሥት መውረስ አይችልም። (1 ቆሮንቶስ 15:​44, 50) ኢየሱስ ወደ ሰማይ እንዳይገባ ያገደው ሰብዓዊ ሥጋው በጥንቱ የአምላክ ቤተ መቅደስ ቅድስቱን ከቅድስተ ቅዱሳኑ በሚለየው መጋረጃ መመሰሉ የተገባ ነበር። (ዕብራውያን 10:​20) ሆኖም ኢየሱስ በሞተ በሦስተኛው ቀን አምላክ መንፈስ አድርጎ አስነሳው። (1 ጴጥሮስ 3:​18) አሁን ወደ አምላክ መንፈሳዊ ቤተ መቅደስ ቅድስተ ቅዱሳን ማለትም በቀጥታ ወደ ሰማይ መግባት ይችላል። የተፈጸመውም ነገር ይኸው ነበር። ጳውሎስ እንደሚከተለው ሲል ጽፏል:- “ክርስቶስ በእጅ ወደ ተሠራች፣ የእውነተኛይቱ ምሳሌ ወደምትሆን ቅድስት [ቅድስተ ቅዱሳንን ለማመልከት ሳይሆን አይቀርም] አልገባምና፣ ነገር ግን በእግዚአብሔር ፊት ስለ እኛ አሁን ይታይ ዘንድ ወደ እርስዋ ወደ ሰማይ ገባ።”​—⁠ዕብራውያን 9:​24

10. ኢየሱስ ወደ ሰማይ ሲመለስ ምን አደረገ?

10 ኢየሱስ የደመ ሕይወቱን ቤዛዊ ዋጋ ለይሖዋ በማቅረብ መሥዋዕት በመሆን ያፈሰሰውን ደም በሰማይ ረጭቷል። ይሁን እንጂ ኢየሱስ ከዚህም የበለጠ ነገር አድርጓል። ከመሞቱ ጥቂት ቀደም ብሎ ለተከታዮቹ “ስፍራ አዘጋጅላችሁ ዘንድ እሄዳለሁና፤ ሄጄም ስፍራ ባዘጋጅላችሁ፣ እኔ ባለሁበት እናንተ ደግሞ እንድትሆኑ ሁለተኛ እመጣለሁ ወደ እኔም እወስዳችኋለሁ” ብሏቸው ነበር። (ዮሐንስ 14:​2, 3) ስለዚህ ኢየሱስ ወደ ቅድስተ ቅዱሳኑ ወይም ወደ ሰማይ የመግባት መብት በማግኘት ሌሎችም ወደዚያ መግባት የሚችሉበት በር ከፍቷል። (ዕብራውያን 6:​19, 20) ቁጥራቸው 144, 000 የሆኑት እነዚህ ግለሰቦች በአምላክ መንፈሳዊ ቤተ መቅደስ ዝግጅት ውስጥ የበታች ካህናት ሆነው ያገለግላሉ። (ራእይ 7:​4፤ 14:​1፤ 20:​6) የእስራኤል ሊቀ ካህን በቅድሚያ የካህናቱን ኃጢአት ለማስተሰረይ የወይፈኑን ደም ይዞ ወደ ቅድስተ ቅዱሳኑ ይገባ እንደነበረ ሁሉ የፈሰሰው የኢየሱስ ደም ዋጋ በቅድሚያ ጥቅም ላይ የዋለው ለእነዚህ 144, 000 የበታች ካህናት ነበር። b

በዘመናችን ያሉ ‘የተመረጡ ዕቃዎች’

11. የእስራኤል ሊቀ ካህን የፍየል መሥዋዕት የሚያቀርበው ስለ እነማን ነበር? ይህስ ለምን ነገር ጥላ ነበር?

11 አጠቃላዩ ቅቡዓኑን የመሰብሰቡ ሥራ በ1935 የተጠናቀቀ ይመስላል። c ሆኖም ይሖዋ ቤቱን በክብር መሙላቱን አላቆመም። ‘የተመረጡ ዕቃዎች’ ገና አሁንም ወደ ቤቱ ይመጣሉ። የእስራኤል ሊቀ ካህን ሁለት እንስሳትን መሥዋዕት ያቀርብ እንደነበር አስታውስ። ለካህናት ኃጢአት የወይፈን መሥዋዕት፣ የካህናት ነገድ ላልሆኑት ሰዎች ኃጢአት ደግሞ የፍየል መሥዋዕት ያቀርብ ነበር። ካህናቱ በሰማያዊ መንግሥት ከኢየሱስ ጋር የሚሆኑትን ቅቡዓን ያመለክታሉ። የካህናት ነገድ ያልሆኑት ሰዎችስ ማንን ያመለክታሉ? መልሱ በዮሐንስ 10:​16 ላይ ተመዝግበው በሚገኙት በሚከተሉት በኢየሱስ ቃላት ውስጥ ይገኛል:- “ከዚህም በረት ያልሆኑ ሌሎች በጎች አሉኝ፤ እነርሱን ደግሞ ላመጣ ይገባኛል ድምፄንም ይሰማሉ፣ አንድም መንጋ ይሆናሉ እረኛውም አንድ።” ስለዚህ የፈሰሰው የኢየሱስ ደም ለሁለት የሰዎች ቡድን ጥቅም አስገኝቷል። የመጀመሪያው በሰማይ ከኢየሱስ ጋር የመግዛት ተስፋ ያላቸው ክርስቲያኖች ቡድን ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ ገነት በምትሆነው ምድር ላይ የዘላለም ሕይወት ለማግኘት የሚጠባበቁ ሰዎች ቡድን ነው። በሐጌ ትንቢት ላይ ‘የተመረጡ ዕቃዎች’ በሚል የተጠቀሰው ይህ ሁለተኛው ቡድን እንደሆነ ከሁኔታዎች መረዳት ይቻላል።​—⁠ሚክያስ 4:​1, 2፤ 1 ዮሐንስ 2:​1, 2

12. ብዙ ‘የተመረጡ ዕቃዎች’ ወደ አምላክ ቤት በመምጣት ላይ ያሉት እንዴት ነው?

12 እነዚህ ‘የተመረጡ ዕቃዎች’ አሁንም የይሖዋን ቤት በመሙላት ላይ ናቸው። በቅርብ ዓመታት በምሥራቅ አውሮፓ፣ በአንዳንድ የአፍሪካ ክፍሎችና በሌሎች አገሮችም ተጥለው የነበሩ እገዳዎች መነሳታቸው ስለተቋቋመው የአምላክ መንግሥት የሚገልጸው ምሥራች ቀደም ሲል ባልደረሰባቸው ክልሎች በስፋት እንዲሰራጭ በር ከፍቷል። የተመረጡት ወደ አምላክ የቤተ መቅደስ ዝግጅት በሚመጡበት ጊዜ ኢየሱስ በሰጠው ትእዛዝ መሠረት እነሱም በተራቸው ሌሎችን ደቀ መዛሙርት ለማድረግ ይጥራሉ። (ማቴዎስ 28:​19, 20) ይህን በሚያደርጉበት ጊዜ ወጣት አረጋዊ ሳይል ‘የተመረጡ ዕቃዎች’ በመሆን የይሖዋን ቤት ሊያስጌጡ የሚችሉ ብዙ ግለሰቦችን ያገኛሉ። ይህ እንዴት ባለ ሁኔታ በመከናወን ላይ እንዳለ ጥቂት ምሳሌዎችን ተመልከት።

13. በቦሊቪያ የምትገኝ አንዲት ትንሽ ልጅ የመንግሥቱን መልእክት በማሰራጨት ረገድ ያላትን ቅንዓት ያሳየችው እንዴት ነው?

13 በቦሊቪያ የምትገኝ የይሖዋ ምሥክር ወላጆች ያሳደጓት አንዲት የአምስት ዓመት ልጅ የወረዳ የበላይ ተመልካች በሚጎበኝበት ሳምንት የትምህርት ቤት ፈቃድ እንድትሰጣት አስተማሪዋን ጠየቀች። ፈቃድ የጠየቀችው ለምን ነበር? ልዩ እንቅስቃሴ በሚደረግበት በዚህ ሳምንት በአገልግሎት ለመሳተፍ ስለፈለገች ነበር። ድርጊቷ ወላጆቿን ቢያስገርማቸውም እንዲህ ዓይነት ግሩም ዝንባሌ በማሳየቷ ተደስተዋል። በአሁኑ ጊዜ ይህች ትንሽ ልጅ አምስት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን የምትመራ ሲሆን ከእነዚህ ጥናቶቿ መካከል አንዳንዶቹ በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ ይገኛሉ። አስተማሪዋን እንኳ ሳይቀር ወደ መንግሥት አዳራሽ ይዛት መጥታለች። ከመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቿ መካከል አን​ዳንዶቹ የይሖዋን ቤት የሚያስከብሩ ‘የተመረጡ ዕቃዎች’ ሊሆኑ ይችላሉ።

14. በኮሪያ አንዲት እህት ያነጋገረችው ግለሰብ ፍላጎት የሌለው ቢመስልም ባሳየችው ጽናት የተካሰችው እንዴት ነው?

14 በኮሪያ አንዲት ክርስቲያን ሴት ባቡር እየጠበቀች ሳለች በጆሮ ማዳመጫ ሙዚቃ እየሰማ ያለ አንድ ተማሪ ቀርባ ታነጋግራለች። “ሃይማኖት አለህ?” ስትል ጠየቀችው። “እኔ ምንም ሃይማኖት አልፈልግም” ሲል መለሰላት። እህት በዚህ አላቆመችም። “ከጊዜ በኋላ አንድ ሰው አንድ ሃይማኖት መርጦ መያዝ ሊፈልግ ይችላል። ሆኖም ስለ ሃይማኖት ምንም የማያውቅ ከሆነ ትክክለኛ ያልሆነውን ሃይማኖት ሊመርጥ ይችላል” ስትል ነገረችው። የተማሪው አመለካከት ተለወጠና እህታችንን በጉጉት ያዳምጣት ጀመር። ስለ አንተ የሚያስብ ፈጣሪ ይኖር ይሆን? (እንግሊዝኛ) የተባለውን መጽሐፍ ካበረከተችለት በኋላ አንድ ሃይማኖት መርጦ መያዝ የሚፈልግበት ጊዜ ሲመጣ ይህ መጽሐፍ በጣም እንደሚረዳው ነገረችው። መጽሐፉን ምንም ሳያንገራግር ተቀበለ። በቀጣዩ ሳምንት ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት የጀመረ ሲሆን አሁን በሁሉም የጉባኤ ስብሰባዎች ላይ ይገኛል።

15. በጃፓን አንዲት ልጅ ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንዲጀምሩ የምታደርገው እንዴት ነው? ጥረቷስ ምን በረከት አስገኝቶላታል?

15 በጃፓን የምትገኝ ሜጉሚ የተባለች አንዲት የ12 ዓመት ልጅ የምትማርበትን ትምህርት ቤት በጣም አመቺ የመስበኪያና የማስተማሪያ መስክ አድርጋ ትመለከታለች። ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን ማስጀመር ችላለች። ሜጉሚ ይህ ሊሳካላት የቻለው እንዴት ነው? በምሳ ዕረፍት ወቅት መጽሐፍ ቅዱስ ስለምታነብ ወይም ለስብሰባዎች ስለምትዘጋጅ የክፍል ጓደኞቿ ምን እያደረገች እንዳለች ይጠይቋታል። አንዳንዶቹም ሜጉሚ በአንዳንድ የትምህርት ቤት እንቅስቃሴዎች ለምን እንደማትካፈል ይጠይቋታል። ሜጉሚ ለጥያቄያቸው መልስ ከሰጠች በኋላ አምላክ ስም እንዳለው ትነግራቸዋለች። ይህም የአድማጮቿን ፍላጎት ይቀሰቅሰዋል። ከዚያም መጽሐፍ ቅዱስ እንዲያጠኑ ግብዣ ታቀርብላቸዋለች። በአሁኑ ጊዜ ሜጉሚ 20 ጥናቶች የምትመራ ሲሆን ከእነዚህ መካከል አሥራ ስምንቱ የክፍል ጓደኞቿ ናቸው።

16. በካሜሩን አንድ ወንድም ሊያፌዙበት ጠርተውት ከነበሩት ሰዎች መካከል አንዳንዶቹን ጥናት ማስጀመር የቻለው እንዴት ነው?

16 በካሜሩን ስምንት ሆነው በቡድን የሚሠሩ ሰዎች በመንገድ ላይ ለሚያልፉ ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስ ጽሑፎችን ያበረክት የነበረን አንድ ወንድም ተመልክተው ጠሩት። ወንድምን በእምነቱ ሊያፌዙበት ፈልገው በሥላሴ፣ በእሳታማ ሲኦል ወይም በነፍስ አለመሞት ለምን እንደማያምን ጠየቁት። ወንድማችን ግን መጽሐፍ ቅዱስ በመጠቀም ላቀረቧቸው ጥያቄዎች መልስ ሰጣቸው። በዚህ ምክንያት ሦስቱ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለመጀመር ተስማሙ። ከሦስቱ አንዱ፣ ዳንኤል በስብሰባዎች ላይ መገኘት የጀመረ ሲሆን ከመናፍስትነት ጋር ግንኙነት ያላቸውን ዕቃዎቹን በሙሉ አስወግዷል። (ራእይ 21:​8) አንድ ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ተጠመቀ።

17. በኤልሳልቫዶር የሚገኙ ወንድሞች መጀመሪያ ላይ የመንግሥቱን መልእክት ለመስማት ፈቃደኛ ላልነበረ ሰው ለመመስከር ብልሃት የተጠቀሙት እንዴት ነበር?

17 በኤል ሳልቫዶር አንድ ሰው የይሖዋ ምሥክሮች ወደ ቤቱ በመምጣት ላይ መሆናቸውን ሲመለከት ኃይለኛ የሆነ ውሻውን ያወጣና በሩ ላይ ያስረዋል። ከዚያም ምሥክሮቹ አልፈው እስኪሄዱ ድረስ ከጠበቀ በኋላ ውሻውን መልሶ ያስገባዋል። ወንድሞች ይህን ሰው ለማነጋገር ፈጽሞ አልቻሉም። ስለዚህ አንድ ቀን ለየት ያለ አቀራረብ ለመሞከር ወሰኑ። ሰውዬው ሊሰማቸው እንደሚችል ያውቁ ስለነበረ ለውሻው ለመመስከር ወሰኑ። ወደ ቤቱ መጥተው ለውሻው ሰላምታ ከሰጡና ከእርሱ ጋር ለመነጋገር የሚያስችል አጋጣሚ በማግኘታቸው የተሰማቸውን ደስታ ከገለጹ በኋላ መላው ምድር ገነት ስለምትሆንበት፣ የሚቆጣ ማንም ሰው ስለማይኖርበት፣ እንስሳት እንኳ ሳይቀር ሰላማውያን ስለሚሆኑበት ጊዜ መናገር ጀመሩ። ከዚያም ውሻውን በአክብሮት ደህና ዋል ብለው ከተሰናበቱ በኋላ መንገዳቸውን ቀጠሉ። የቤቱ ባለቤት ከቤቱ ወጥቶ እስከዚያ ቀን ድረስ እንዲያነጋግሩት አጋጣሚ ባለመስጠቱ ይቅርታ ሲጠይቃቸው በጣም ተደነቁ። መጽሔቶች ከወሰደ በኋላ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ተጀመረለት። ዛሬ ይህ ሰው ወንድማችን ማለትም ‘ከተመረጡት ዕቃዎች’ መካከል አንዱ ሊሆን ችሏል!

“አትፍሩ”

18. ብዙዎቹ ክርስቲያኖች ምን ተፈታታኝ ሁኔታዎች ይገጥሟቸዋል? ሆኖም ይሖዋ አምላኪዎቹን እንዴት ይመለከታቸዋል?

18 ወሳኝ በሆነው የመንግሥቱን ምሥራች በመስበኩና ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ እየተካፈልክ ነውን? ከሆነ በእርግጥ ትልቅ መብት አግኝተሃል። ይሖዋ ‘የተመረጡ ዕቃዎችን’ ወደ ቤቱ የሚያስገባው በዚህ ሥራ አማካኝነት ነው። (ዮሐንስ 6:​44) እርግጥ ነው፣ አንዳንድ ጊዜ እንደ መዳከም ወይም ተስፋ እንደመቁረጥ ልትል ትችላለህ። አንዳንድ ጊዜ ታማኝ የይሖዋ አገልጋዮች እንኳ ሳይቀሩ ከከንቱነት ስሜት ጋር ይታገላሉ። ግን አይዞህ! ይሖዋ እሱን የሚያመልኩት ሁሉ በፊቱ ውድ ናቸው። ስለ አንተ መዳን በጣም ያስባል።​—⁠2 ጴጥሮስ 3:​ 9

19. ይሖዋ በሐጌ አማካኝነት ምን ማበረታቻ ሰጥቷል? እነዚህ ቃላት የብርታት ምንጭ ሊሆኑልን የሚችሉት እንዴት ነው?

19 በተቃውሞም ይሁን በደረሰብን ሌላ አሳዛኝ ሁኔታ ምክንያት ተስፋ የመቁረጥ ስሜት ከተሰማን ይሖዋ ወደ አገራቸው ለተመለሱት አይሁዳውያን የተናገራቸው ቃላት ማበረታቻ ሊሰጡን ይችላሉ። በሐጌ 2:​4-6 ላይ እንደሚከተለው እናነባለን:- “አሁን ግን፣ ዘሩባቤል ሆይ፣ በርታ፣ ይላል እግዚአብሔር፤ ታላቁም ካህን የኢዮሴዴቅ ልጅ ኢያሱ ሆይ፣ በርታ፣ እናንተም የአገሩ ሕዝብ ሆይ፣ በርቱና ሥሩ፣ ይላል እግዚአብሔር፤ እኔ ከእናንተ ጋር ነኝና፣ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር። መንፈሴም በመካከላችሁ ይኖራልና አትፍሩ። የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና:- ገና አንድ ጊዜ በቅርብ ዘመን እኔ ሰማያትንና ምድርን ባሕርንና የብስንም አናውጣለሁ።” ይሖዋ አይዟችሁ ማለት ብቻ ሳይሆን ብርታት የምናገኝበትንም ዝግጅት እንዳደረገልን ልብ በል። እንዴት? “እኔ ከእናንተ ጋር ነኝ” የሚል ዋስትና ሰጥቶናል። የሚያጋጥሙን መሰናክሎች ምንም ዓይነት ይሁኑ ይሖዋ ከእኛ ጋር እንዳለ ማወቃችን ምንኛ እምነት የሚያጠነክር ነው!​—⁠ሮሜ 8:​31

20. የይሖዋ ቤት ከዚህ በፊት ሆኖ በማያውቅ ሁኔታ በክብር እየተሞላ ያለው በምን መንገድ ነው?

20 ይሖዋ በእርግጥ ከሕዝቦቹ ጋር እንደሆነ አረጋግጧል። ልክ በነቢዩ ሐጌ አማካኝነት እንደተናገረው ነው። “ከፊተኛው ይልቅ የዚህ የሁለተኛው ቤት ክብር ይበልጣል፣ . . . በዚህም ስፍራ ሰላምን እሰጣለሁ።” (ሐጌ 2:​9) በእርግጥም በዛሬው ጊዜ በይሖዋ መንፈሳዊ ቤተ መቅደስ ውስጥ መገኘት ትልቅ ክብር ነው። በየዓመቱ በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ወደ እውነተኛው አምልኮ በመጉረፍ ላይ ናቸው። እነዚህም በመንፈሳዊ በሚገባ እየተመገቡ ሲሆን በአምላክ አዲስ ዓለም ውስጥ ካልሆነ በስተቀር በዚህ ሁከት በነገሠበት ዓለም ውስጥ ተወዳዳሪ ያልተገኘለት ሰላም አግኝተው ይኖራሉ።​—⁠ኢሳይያስ 9:​6, 7፤ ሉቃስ 12:​42

21. ቁርጥ ውሳኔያችን ምን መሆን አለበት?

21 ይሖዋ ብሔራትን በአርማጌዶን የሚያናውጥበት ጊዜ ሩቅ አይደለም። (ራእይ 16:​14, 16) ስለዚህ የቀረውን ጊዜ የበለጠ ሕይወት ለማዳን እንጠቀምበት። በይሖዋ ላይ ጠንካራና የማይናወጥ ትምክህት ይኑረን። ይሖዋ ሥራው ተጠናቅቋል ብሎ እስከሚነግረን ድረስ ቤቱ ‘በተመረጡ ዕቃዎች’ እንዲሞላ በማድረግ በታላቁ መንፈሳዊ ቤተ መቅደስ ውስጥ እሱን እያመለክን ለመቀጠል ቁርጥ ውሳኔያችን ይሁን።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

a ሰሎሞን ለሠራው ቤተ መቅደስ የተደረገው መዋጮ አሁን ባለው የዋጋ ተመን ቢሰላ ወደ 40 ቢልዮን የአሜሪካ ዶላር ይጠጋል። ከግንባታ የተረፈው ሁሉ በቤተ መቅደሱ ግምጃ ቤት ውስጥ እንዲቀመጥ ተደርጓል።​—⁠1 ነገሥት 7:​51

b ኢየሱስ እንደ እስራኤል ሊቀ ካህን ማስተሰረያ የሚያስፈልገው የራሱ ኃጢአት የለውም። ሆኖም አብረውት ካህናት የሚሆኑት ሰዎች ኃጢአተኛ ከሆነው የሰው ዘር የተዋጁ ስለሆኑ ኃጢአት አለባቸው።​—⁠ራእይ 5:​9, 10

c የየካቲት 15, 1998 መጠበቂያ ግንብ ከገጽ 17-22 ተመልከት።

ታስታውሳለህን?

ይሖዋ ከቁሳዊ ነገሮች ይልቅ እንደ ውድ አድርጎ የሚመለከታቸው ነገሮች ምንድን ናቸው?

የፈሰሰው የኢየሱስ ደም ጥቅም ያስገኘለት ሁለት የሰዎች ቡድን የትኛው ነው?

የይሖዋን ቤት በክብር የሚሞሉት ‘የተመረጡ ዕቃዎች’ ምንድን ናቸው?

የሐጌ ትንቢት በዛሬው ጊዜ ፍጻሜውን እያገኘ እንዳለ የሚያሳይ ምን ማስረጃ አለን?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

የጥንቱ የይሖዋ ቤተ መቅደስ ለምን ነገር ትንቢታዊ ጥላ እንደሆነ ታውቃለህ?

መጋረጃ

ቅድስት

መሠዊያ

ቅድስተ ቅዱሳን

ደጀ ሰላም

አደባባይ

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሊቀ ካህኑ ለካህናት ኃጢአት የወይፈን መሥዋዕት፣ የካህናት ነገድ ላልሆኑት እስራኤላውያን ደግሞ የፍየል መሥዋዕት ያቀርብ ነበር

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ዓለም አቀፉ የመንግሥቱ ስብከት ሥራ ብዙዎች ወደ ይሖዋ ቤት እንዲጎርፉ እያደረገ ነው