በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የአምላክ ትንቢታዊ ቃል ስለ ወደፊቱ ጊዜ ተስፋ ይሰጣል

የአምላክ ትንቢታዊ ቃል ስለ ወደፊቱ ጊዜ ተስፋ ይሰጣል

የአምላክ ትንቢታዊ ቃል ስለ ወደፊቱ ጊዜ ተስፋ ይሰጣል

እውነተኛ ክርስቲያኖች የአምላክ ቃል የሆነውን መጽሐፍ ቅዱስን በመማራቸው የወደፊቱን ጊዜ በተመለከተ እምነት፣ ተስፋና ብሩህ አመለካከት ሊኖራቸው ችሏል። ከይሖዋ ጋር የጠበቀ ዝምድና በመመሥረታቸው መጪውን ጊዜ በትምክህት ይጠባበቃሉ። “የአምላክ ትንቢታዊ ቃል” የአውራጃ ስብሰባ የመክፈቻ ንግግር እንዳብራራው የይሖዋ ምሥክሮች ከብዙ ዓመታት በፊት ጀምረው የመጽሐፍ ቅዱስን ትንቢት በትጋት ሲያጠኑ ኖረዋል። ታዲያ ይሖዋ በዚህ ስብሰባ ላይ ለተገኙት ሕዝቦቹ ምን አዘጋጅቶላቸው ነበር? በስብሰባው ላይ የተገኙ ሁሉ መጽሐፍ ቅዱሳቸውን በእጃቸው ይዘው ይሖዋ ምን እንዳዘጋጀላቸው ለማወቅ በጉጉት ይጠባበቁ ነበር። የእያንዳንዱ ቀን ስብሰባ ጭብጥ በንዑስ ርዕስ መልክ ቀርቧል።

የመጀመሪያው ቀን:- በአምላክ ቃል ብርሃን መመላለስ

“የአምላክ ቃል ይመራናል” የሚለው ንግግር የይሖዋን ሕዝቦች በሌሊት ጨለማ ጉዞ እንደ ጀመረ ሰው አድርጎ ገልጿቸው ነበር። ጎህ ሲቀድ በድንግዝግዝ መመልከት ይጀምራል፤ ሆኖም ፀሐይዋ ፍንትው ብላ ስትወጣ ግልጽ ሆኖ ይታየዋል። በ⁠ምሳሌ 4:​18 ላይ በተተነበየው መሠረት የይሖዋ ሕዝቦችም የአምላክ ትንቢታዊ ቃል በሚፈነጥቀው ደማቅ የእውነት ብርሃን አማካኝነት የሚሄዱበትን አቅጣጫ በግልጽ መመልከት ችለዋል። በመንፈሳዊ ጨለማ አይደናበሩም።

“የአምላክን ትንቢታዊ ቃል በትኩረት ተከታተሉ” የሚለው የጭብጡ ቁልፍ ንግግር ይሖዋን የሚከተሉ ሁሉ ሐሰተኛ መሲሆችንና ሐሰተኛ ነቢያትን የሚከተሉ ሰዎች የኋላ ኋላ ከሚያጋጥማቸው ብስጭትና ግራ መጋባት ነፃ እንደሚሆኑ አድማጮችን አስገንዝቦ ነበር። በአንጻሩ ግን ኢየሱስ ክርስቶስ እውነተኛ መሲህ መሆኑን የሚያረጋግጡ ማስረጃዎች በጣም ብዙ ናቸው! ለምሳሌ ያህል የኢየሱስ በተአምራዊ ሁኔታ መለወጥ የአምላክ መንግሥት ንጉሥ ሆኖ በዙፋን እንደሚቀመጥ ከወዲሁ የሚያመለክት ነበር። በተጨማሪም ኢየሱስ በ1914 ንጉሣዊ ሥልጣኑን ከያዘበት ጊዜ ጀምሮ በ⁠2 ጴጥሮስ 1:​19 ላይ የተጠቀሰው “የንጋት ኮከብ” ሆኗል። ተናጋሪው ኢየሱስ “መሲሐዊ የንጋት ኮከብ በመሆን ታዛዥ ለሆኑ የሰው ልጆች በሙሉ አዲስ ቀን፣ አዲስ ዘመን መጥባቱን ያበስራል” ሲል ገልጾ ነበር።

የከሰዓት በኋላው ፕሮግራም መክፈቻ የሆነው “ብርሃን አብሪዎች መሆን” የሚለው ንግግር ሐዋርያው ጳውሎስ “እንደ ብርሃን ልጆች ተመላለሱ” ሲል ምክር የሰጠበትን ኤፌሶን 5:​10ን በስፋት አብራርቷል። ክርስቲያኖች ብርሃን አብሪዎች የሆኑት የአምላክን ቃል ለሌሎች በማካፈል ብቻ ሳይሆን የኢየሱስን ምሳሌ በመኮረጅ መጽሐፍ ቅዱስን በሕይወታቸው ተግባራዊ በማድረግ ነው።

በዚህ መንገድ ብርሃን አብሪ ለመሆን ‘የአምላክን ቃል በማንበብ መደሰት አለብን።’ ይህ ርዕሰ ጉዳይ በሦስት ክፍል በቀረበ ሲምፖዚየም ተብራርቷል። የመጀመሪያው ተናጋሪ መጽሐፍ ቅዱስን “አምላክ ለሰው ልጆች ከሰጣቸው ስጦታዎች ሁሉ የላቀው ስጦታ” ሲሉ የገለጹትን አብርሃም ሊንከንን ከጠቀሰ በኋላ የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ ልማዳቸው ለይሖዋ ቃል ያላቸው አድናቆት ምን ያህል ስለመሆኑ ምን እንደሚጠቁም አድማጮቹን ጠይቆ ነበር። አድማጮች መጽሐፍ ቅዱስን በጥንቃቄ እንዲያነቡ፣ ጊዜ መድበው በቅዱሳን ጽሑፎች ላይ እንዲያሰላስሉና አዲስ ያገኟቸውን ነጥቦች ከዚህ ቀደም ከሚያውቁት ጋር ለማዛመድ እንዲጥሩ ማበረታቻ ተሰጥቷቸዋል።

“ጠንካራ ምግብ” መመገብ ከፈለግን እንዲሁ ማንበብ ብቻ ሳይሆን ማጥናት አስፈላጊ መሆኑን የሲምፖዚየሙ ቀጣይ ክፍል አጽንዖት ሰጥቶታል። (ዕብራውያን 5:​13, 14) በተለይም ደግሞ እስራኤላዊው ካህን ዕዝራ እንዳደረገው አስቀድመን ‘ልባችንን ካዘጋጀን’ ጥናቱ ገንቢ እንደሚሆን ተናጋሪው ገልጾ ነበር። (ዕዝራ 7:​10) ጥናት ይህን ያህል አስፈላጊ የሆነው ግን ለምንድን ነው? ምክንያቱም ከይሖዋ ጋር ያለንን ዝምድና በቀጥታ የሚነካ ስለሆነ ነው። ስለሆነም የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ምንም እንኳ አእምሮን መገሰጽንና ጥረትን የሚጠይቅ ቢሆንም የላቀ ግምት የሚሰጠው፣ አስደሳችና መንፈስ የሚያነቃቃ መሆን ይኖርበታል። ትርጉም ያለው ጥናት ለማድረግ ጊዜ ማግኘት የምንችለው እንዴት ነው? የሲምፖዚየሙ የመጨረሻ ተናጋሪ ብዙም አስፈላጊ ካልሆኑ ነገሮች ‘ጊዜ በመዋጀት መሆኑን’ ገልጾ ነበር። (ኤፌሶን 5:​16) አዎን ጊዜ ለማግኘት ቁልፉ ያለንን ጊዜ በአግባቡ መጠቀም ነው።

“አምላክ ለደከሙት ኃይል ይሰጣል” የተሰኘው ንግግር በዛሬው ጊዜ ብዙ የደከማቸው ሰዎች እንዳሉ ገልጾ ነበር። ክርስቲያናዊ አገልግሎታችንን ለማከናወን ‘ከወትሮው የበለጠ ኃይል’ እንድናገኝ ከፈለግን ‘ለደከሙት ኃይል በሚሰጠው’ በይሖዋ ላይ መመካት አለብን። (2 ቆሮንቶስ 4:​7፤ ኢሳይያስ 40:​29) ብርታት እንድናገኝ ከሚረዱን ነገሮች መካከል የአምላክ ቃል፣ ጸሎት፣ ክርስቲያን ጉባኤ፣ አዘውትሮ በአገልግሎት መሳተፍ፣ የክርስቲያን የበላይ ተመልካቾችና የሌሎች የታማኝነት ምሳሌ ይገኙበታል። “ከጊዜው የተነሳ አስተማሪዎች መሆን” በሚል ጭብጥ የቀረበው ንግግር ክርስቲያኖች አስተማሪዎች እንዲሁም ሰባኪዎች መሆንና “የማስተማር ዘዴያቸውን” ለማሻሻል ከፍተኛ ጥረት ማድረግ እንደሚያስፈልጋቸው አጉልቶ ነበር።​—⁠2 ጢሞቴዎስ 4:​2

“ከአምላክ ጋር የሚዋጉ አያሸንፉም” የሚለው የዕለቱ የመደምደሚያ ንግግር በቅርቡ በአንዳንድ አገሮች የይሖዋ ምሥክሮችን ከአደገኛ ኑፋቄዎች ለመፈረጅ የተደረጉ የተሳሳቱ ሙከራዎችን ጠቅሶ ነበር። ሆኖም ኢሳይያስ 54:​17 እንደሚከተለው ስለሚል የምንፈራበት ምክንያት የለም:- “በአንቺ ላይ የተሠራ መሣሪያ ሁሉ አይከናወንም፤ በፍርድም በሚነሣብሽ ምላስ ሁሉ ትፈርጂበታለሽ። የእግዚአብሔር ባሪያዎች ርስት ይህ ነው፣ ጽድቃቸውም ከእኔ ዘንድ ነው፣ ይላል እግዚአብሔር።”

ሁለተኛው ቀን:- በነቢያት መጻሕፍት በኩል የተገለጡት ነገሮች

በዕለት ጥቅሱ ላይ ውይይት ከተደረገ በኋላ “ብርሃናችንን በማብራት ይሖዋን ማስከበር” የሚል ርዕስ ያለው የአውራጃ ስብሰባው ሁለተኛ ሲምፖዚየም ቀረበ። የመጀመሪያው ንግግር የአንድ ክርስቲያን ግብ በማንኛውም ቦታ በመስበክ ይሖዋን ማስከበር መሆኑን የሚያስገነዝብ ነበር። ቀጥሎ የቀረበው ክፍል አዎንታዊ ምላሽ የሚሰጡትን ሰዎች ወደ አምላክ ድርጅት የመምራትን አስፈላጊነት ገልጾ ነበር። እንዴት? የአምላክ ድርጅት እንዴት እንደሚንቀሳቀስ እንዲያውቁ ለመርዳት ከእያንዳንዱ የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት በፊት ወይም በኋላ አምስት ወይም አሥር ደቂቃ ለዚህ ዓላማ በመመደብ ነው። የዚህ ሲምፖዚየም ሦስተኛ ንግግር በመልካም ሥራዎች አምላክ እንዲከበር የማድረግን አስፈላጊነት አበክሮ ገልጿል።

“የይሖዋን ማሳሰቢያዎች ከልብ ውደዱ” በሚል ርዕስ የቀረበው ንግግር ከ⁠መዝሙር 119 የተመረጡ ጥቅሶችን አብራርቷል። የመርሳት ዝንባሌ ስላለን በየጊዜው ማሳሰቢያ እንደሚያስፈልገን ጥያቄ የለውም። ስለሆነም ልክ እንደ መዝሙራዊው ለይሖዋ ማሳሰቢያዎች ፍቅር ማዳበራችን ምንኛ አስፈላጊ ነው!

ከዚያም የስብሰባው ጉልህ ክፍል የሆነው “ትንቢታዊውን ቃል መታዘዝ ወደ ጥምቀት ይመራል” የሚል ርዕስ ያለው የጥምቀት ንግግር ቀረበ። የጥምቀት ዕጩዎቹ ክርስቶስን የሚኮርጁት በመጠመቅ ብቻ ሳይሆን ፈለጉን በቅርብ በመከተል ጭምር መሆኑን ማሳሰቢያ አግኝተው ነበር። (1 ጴጥሮስ 2:​21) እነዚህ አዲሶች ኢየሱስ በመንፈስ ከተቀቡ ደቀ መዛሙርቱ ጎን ተሰልፈው የሚያገለግሉ “ሌሎች በጎች” እንደሚሰበስብ በ⁠ዮሐንስ 10:​16 ላይ በተናገረው ትንቢት ፍጻሜ መካፈል መቻላቸው እንዴት ያለ ትልቅ መብት ነው!

“መንፈስ የሚለውን መስማት” የሚለው የከሰዓት በኋላው ፕሮግራም መክፈቻ የሆነው ንግግር የይሖዋ መንፈስ በመጽሐፍ ቅዱስ፣ “በታማኝና ልባም ባሪያ” እንዲሁም በመጽሐፍ ቅዱስ በሰለጠነ ሕሊናችን አማካኝነት እንደሚነግረን አብራርቷል። (ማቴዎስ 24:​45) ስለሆነም ክርስቲያኖች አምላክን እንዴት ማስደሰት እንደሚችሉ ለማወቅ ቃል በቃል ከሰማይ ድምፅ መስማት አያስፈልጋቸውም። “ለአምላክ ያደሩ ከመሆን ጋር የሚስማሙ ትምህርቶችን አጥብቆ መያዝ” በሚል ርዕስ ቀጥሎ የቀረበው ንግግር ክርስቲያኖች ይህ ዓለም ከሚነዛቸው የሥነ ምግባር አቋምን ከሚያዳክሙ ፕሮፓጋንዳዎች እንዲርቁ የሚያሳስብ ምክር ለግሷል። በእርግጥም ገደብ ያልተበጀለት የማወቅ ጉጉት ከሐዲዎች እንዲሁም ሌሎች የሰይጣን ወኪሎች ለሚያሰራጩት ጎጂ ሐሳብ ሊያጋልጥ ይችላል። ከዚህ ይልቅ መጽሐፍ ቅዱስንና በመጠበቂያ ግንብ እና በንቁ! መጽሔቶች ላይ የሚወጡትን ሁሉንም ርዕሶች አዘውትሮ ማንበቡ ምንኛ የተገባ ነው።

“የጤናማውን ቃል ሥርዓት እንደያዙ መቀጠል” በሚል ርዕስ ቀጥሎ የቀረበው ንግግር ቅዱስ ጽሑፋዊ ከሆነው የእውነት “ሥርዓት” ወይም ደንብ ጋር በሚገባ መተዋወቅ ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ጠበቅ አድርጎ ገልጾ ነበር። (2 ጢሞቴዎስ 1:​13) ይህን ሥርዓት በጥልቀት መረዳት ለአምላክ ያደሩ ለመሆን ብቻ ሳይሆን ከእውነት ጋር የማይስማሙ ነገሮችንም ለመለየት ቁልፍ ነው።

ይሖዋ ምርጥ እንደሆንክ አድርጎ እንደሚመለከትህ አስብ። እንዴት ትልቅ ክብር ነው! “ ‘የተመረጡ ዕቃዎች’ የይሖዋን ቤት እየሞሉት ነው” የሚለው በሐጌ ትንቢት ላይ የተመሠረተው ንግግር አድማጮች ‘የእጅግ ብዙ ሰዎች’ አባል የሆነ እያንዳንዱ ሰው በይሖዋ ፊት በእርግጥ ተፈላጊ መሆኑን እንዲገነዘቡ ያደረገ በጣም አበረታች ንግግር ነበር። (ራእይ 7:​9) በመሆኑም ይሖዋ ለመጨረሻ ጊዜ አሕዛብን በሚያናውጥበት ‘በታላቁ መከራ’ ወቅት እነዚህን ሰዎች ያድናቸዋል። (ሐጌ 2:​7, 21, 22፤ ማቴዎስ 24:​21) ሆኖም “የትንቢት መጻሕፍት ነቅተን እንድንከታተል ይረዱናል” በሚለው ንግግር እንደተብራራው የይሖዋ ሕዝቦች ይህ እስከሚሆንበት ጊዜ ድረስ በመንፈሳዊ ነቅተው መጠባበቅ አለባቸው። ተናጋሪው “ጌታችሁ በምን ሰዓት እንዲመጣ አታውቁምና እንግዲህ ንቁ” ሲል ኢየሱስ የተናገራቸውን ቃላት ጠቅሶ ነበር። (ማቴዎስ 24:​42) በመንፈሳዊ ንቁ ሆነን መቀጠል የምንችለው እንዴት ነው? በይሖዋ አገልግሎት ራሳችንን በማስጠመድ፣ ዘወትር በመጸለይና የይሖዋን ታላቅ ቀን መጠባበቃችንን በመቀጠል ነው።

የዕለቱ የመደምደሚያ ንግግር “ትንቢታዊው ቃል በፍጻሜው ዘመን” የሚል ነበር። ይህ ንግግር ለመጪዎቹ ዓመታት ሁሉ ሲታወስ የሚቆይ ነው። ለምን? ምክንያቱም ተናጋሪው የዳንኤልን ትንቢት በትኩረት ተከታተል! የሚል ርዕስ ያለው አዲስ መጽሐፍ መውጣቱን አስታውቆ ነበር። “ይህ በተዋቡ ሥዕላዊ መግለጫዎች ያሸበረቀው ባለ 320 ገጽ ጽሑፍ እያንዳንዱን የዳንኤል መጽሐፍ ክፍል ይሸፍናል” ሲል ተናግሯል። ይሖዋ በትንቢታዊ ቃሉ ላይ የእውቀት ብርሃን እየፈነጠቀ እንዳለ የሚያሳይ እንዴት ያለ እምነት የሚያጠነክር ማስረጃ ነው!

ሦስተኛው ቀን:- የአምላክ ትንቢታዊ ቃል በምንም ዓይነት ሳይፈጸም አይቀርም

የአውራጃ ስብሰባው የመጨረሻ ቀን የጀመረው “በተቀጠረው ጊዜ ፍጻሜያቸውን የሚያገኙ ትንቢታዊ ቃላት” በሚል ሲምፖዚየም ነበር። ሦስቱ ክፍሎች ነቢዩ ዕንባቆም የተናገራቸውን የይሖዋን ሦስት የቅጣት ፍርዶች የሚያብራሩ ነበሩ። የመጀመሪያው በዓመፀኛዋ ይሁዳ ላይ የተነገረ ሲሆን ሁለተኛው በጨቋኟ ባቢሎን ላይ የተነገረ ነው። ሦስተኛውና ገና ወደፊት የሚፈጸመው ደግሞ በክፉ ሰዎች ሁሉ ላይ የሚመጣውን ጥፋት የሚያመለክት ነው። የሲምፖዚየሙ የመጨረሻ ተናጋሪ “በእርግጥም ይሖዋ ታላቅ ኃይሉን ሙሉ በሙሉ በሚሰነዝርበት ጊዜ በጣም የሚያስፈራ ይሆናል” በማለት በአድማጮቹ ውስጥ መጠነኛ አምላካዊ ፍርሃት እንዲያድር አድርጓል።

የአውራጃ ስብሰባው ቀስቃሽ የመጽሐፍ ቅዱስ ድራማ ርዕስ “መንፈሳዊ ውርሻችንን ማድነቅ” የሚል ነበር። ይህ ማንነታችንን እንድንመረምር የሚያደርግ ድራማ ያዕቆብና ዔሳው ለመንፈሳዊ ነገሮች የነበራቸውን ዝንባሌ የሚያነጻጽር ነበር። ዔሳው መንፈሳዊ ውርሻውን ስላቃለለ ይህ ውርሻ እንደ ውድ ሀብት አድርጎ ለሚመለከተው ለያዕቆብ ተሰጥቷል። በስብሰባው ላይ የተገኙት “ይሖዋ ምን [መንፈሳዊ ውርሻ] ሰጥቶናል?” የሚል ጥያቄ ቀርቦላቸው ነበር። ተናጋሪው “የቃሉን የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት፣ የዘላለም ሕይወትን ተስፋና የምሥራቹ አዋጅ ነጋሪዎች በመሆን እሱን የመወከል መብት ሰጥቶናል” ሲል መለሰ።

ቀጥሎ የቀረበው ክፍል “ውድ የሆነው መንፈሳዊ ውርሻችን ለእናንተ ምን ትርጉም አለው?” የሚል ነበር። የይሖዋን አገልግሎትና መንፈሳዊ መብቶችን ከግልና ከቁሳዊ ፍላጎቶች በማስቀደም ለመንፈሳዊ ውርሻችን ያለንን ትክክለኛ ዝንባሌ እናሳያለን። በዚህ መንገድ ከአዳም፣ ከዔሳውና ታማኝ ካልሆኑት እስራኤላውያን ፈጽሞ በተለየ መልኩ ሕይወታችንን ከይሖዋ ጋር ባለን ዝምድና ዙሪያ እንገነባለን።

“በትንቢት እንደተነገረው​—⁠ሁሉን አዲስ ማድረግ” የተባለው የሕዝብ ንግግር ስለ “አዲስ ሰማይ” እና ስለ “አዲስ ምድር” የሚናገሩ አራት ቁልፍ ትንቢቶችን አጣምሮ ያቀረበ ነበር። (ኢሳይያስ 65:​17-25፤ 66:​22-24፤ 2 ጴጥሮስ 3:​13፤ ራእይ 21:​1, 3-5) ይሖዋ እነዚህ ትንቢቶች በ537 ከዘአበ ወደ አገራቸው በተመለሱት ሕዝቦቹ ላይ ካገኙት ተፈጻሚነት የላቀ ተፈጻሚነት እንደሚኖራቸው አስቦ እንደነበር ግልጽ ነው። አዎን፣ ይሖዋ ንጉሣዊ መንግሥቱን (“አዲስ ሰማይ”) እና ክብራማ በሆነ ዓለም አቀፋዊ ገነት ላይ ነዋሪ የሚሆኑትን የዚህን መንግሥት ምድራዊ ተገዢዎች (“አዲስ ምድር”) በአእምሮው ይዞ ነበር።

“በአምላክ ቃል እየተመራን በጉጉት የምንጠብቃቸው ነገሮች” የሚለው ንግግር የአውራጃ ስብሰባው አስደሳችና ቀስቃሽ መደምደሚያ ነበር። ሁሉም፣ የመንግሥቱ ስብከት ሥራ ሊጠናቀቅ ‘የቀረው ዘመን አጭር መሆኑን’ እንዲገነዘቡ አድርጎ ነበር። (1 ቆሮንቶስ 7:​29) አዎን፣ ይሖዋ በሰይጣንና በእሱ ቁጥጥር ሥር ባለው ክፉ ሥርዓት ላይ ያስተላለፈው ፍርድ ሊፈጸም በተቃረበበት ጊዜ ላይ እንገኛለን። “ነፍሳችን እግዚአብሔርን ተስፋ ታደርገዋለች፣ ረዳታችንና መጠጊያችን እርሱ ነውና” ሲል የዘመረው መዝሙራዊ ዓይነት ስሜት ይኑረን። (መዝሙር 33:​20) ትምክህታቸውን በአምላክ ትንቢታዊ ቃል ላይ የጣሉ ሁሉ እንዴት ያለ ክብራማ ተስፋ ከፊታቸው ተዘርግቶላቸዋል!

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ቀስቃሽ የሆነው ድራማ የይሖዋ አገልጋዮች ለመንፈሳዊ ውርሻ ያላቸው አድናቆት ከፍ እንዲል አድርጓል

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ትንቢታዊውን ቃል የታዘዙ ብዙዎች ተጠምቀዋል