በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የዳንኤል መጽሐፍ ተብራራ!

የዳንኤል መጽሐፍ ተብራራ!

የዳንኤል መጽሐፍ ተብራራ!

የስብሰባው ተካፋዮች የዳንኤልን ትንቢት በትኩረት ተከታተል! የተባለውን አዲስ ባለ 320 ገጽ መጽሐፍ የራሳቸው ቅጂ ለማግኘት ጓጉተው ነበር። ስለ መጽሐፉ ምን ተሰማቸው? እስቲ አንዳንዶች የሰጡትን አስተያየት እንመልከት።

“እንደ አብዛኞቹ ወጣቶች ሁሉ እኔም የጥንት ታሪክ ማጥናት አልወድም። ስለሆነም የዳንኤልን ትንቢት በትኩረት ተከታተል! የተባለውን አዲስ መጽሐፍ የግል ቅጂ ሳገኝ ለማንበብ ብዙም አልጓጓሁም ነበር፤ ሆኖም እንዲሁ እንደዋዛ ጀመርኩት። የነበረኝ ዝንባሌ ምንኛ የተሳሳተ ነበር! እስከ ዛሬ ካየኋቸው ምርጥ መጽሐፎች አንዱ ሆኖ አግኝቸዋለሁ። አንዴ ከጀመሩት ልቀቁኝ ልቀቁኝ አይልም! ከብዙ ሺህ ዓመታት በፊት የተፈጸመ የጥንት ታሪክ እያነበብኩ እንዳለሁ አይሰማኝም። ለመጀመሪያ ጊዜ ራሴን በዳንኤል ቦታ ማስቀመጥ እንደምችል ተሰማኝ። ከቤተሰብ ተነጥሎ ወደ ባዕድ አገር መሄድና በዚያም የአቋም ጽናትን የሚፈታተኑ ተደጋጋሚ ፈተናዎችን መቋቋም በእርግጥ ምን ያህል ከባድ እንደሆነ በዓይነ ሕሊናዬ መመልከት እችላለሁ። ይህን መጽሐፍ ስላዘጋጃችሁ በጣም አመሰግናችኋለሁ።”​—⁠አንያ

“ይሖዋ ሕዝቦቹን የሚመለከቱትን ጉዳዮች ሙሉ በሙሉ የሚቆጣጠር መሆኑን የሚገልጸው የማያሻማ መልእክት እጅግ ጠቃሚ ሆኖ አግኝቸዋለሁ። አምላካችን ነገሮች በፍጹም ከእሱ ዓላማ ዝንፍ እንዲሉ እንደማይፈቅድ ዳንኤል ካያቸው ራእዮችና ሕልሞች እንዲሁም ሌሎች ሰዎች ካዩአቸውና ዳንኤል ከተረጎማቸው ሕልሞች በግልጽ መረዳት ይቻላል። ይህም አምላክ ስለሚያመጣው አዲስ ዓለም በሚናገሩት የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢታዊ መግለጫዎች ላይ ያለንን ተስፋ የሚያጠናክር ነው።”​—⁠ቼስተር

“ዳንኤልን ሕያው አድርጋችሁ ያቀረባችሁበት መንገድ እጅግ ማርኮኛል። ዳንኤልን የሚያሳስቡትንና የሚያስጨንቁትን ነገሮች ጎላ አድርጋችሁ በመግለጻችሁ ዳንኤልን በተሻለ ሁኔታ እንደተዋወቅሁት ነው የተሰማኝ። ይሖዋ ዳንኤልን በጣም ተወዳጅ ሆኖ ያገኘው ለምን እንደሆነ ይበልጥ ግልጽ ሆኖልኛል። ያ ሁሉ ስደትና ፈተና ሲደርስበት ይጨነቅ የነበረው ስለ ራሱ አይደለም። ከምንም በላይ ያሳስበው የነበረው ይሖዋና ውብ የሆነው የይሖዋ ስም ነበር። እነዚህ ነጥቦች ግልጽ ሆነው እንዲቀመጡ ስላደረጋችሁ አመሰግናችኋለሁ።”​—⁠ጆይ

“በጉጉት ስንጠብቀው የነበረ ነገር ነው! ከዚህ ቀደም የዳንኤል መጽሐፍ እንዲህ ለእያንዳንዳችን እንደሚሠራ ሆኖ ተጽፎ አያውቅም። አዲሱን መጽሐፍ ልክ የደረሰኝ ዕለት ምሽት እንዳጋመስኩት ንባቤን አቋርጬ ይሖዋን በጸሎት ለማመስገን ተገድጃለሁ።”​—⁠ማርክ

“ፈጽሞ ያልጠበቅነው ነገር ቢኖር በልጆቻችን ላይ ይህን ያህል ተጽዕኖ ማሳደሩ ነው። ልጆቻችን የአምስትና የሦስት ዓመት ናቸው። . . . ልጆቹ ቀድሞውንም የዳንኤል፣ የአናንያ፣ የሚሳኤልና የአዛርያ ታሪክ የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች መማሪያ መጽሐፌ በተባለው ውስጥ ከሚገኙት በጣም ከሚወዷቸው ታሪኮች መካከል አንዱ ስለነበር የዳንኤል ትንቢት በተባለው መጽሐፍ ውስጥ ያለው አቀራረብ ፈጽሞ ከጠበቅነው በላይ ማርኳቸዋል። ገና ሕፃናት ቢሆኑም እንኳ እንደ እነዚህ ጻድቅ ወጣት ወንዶች መሆን ይፈልጋሉ። እነዚህ ወጣቶች ለልጆቻችን እንዴት ያሉ ግሩም ምሳሌዎች ናቸው! እንዴት ያለ ድንቅ መሣሪያ ነው ያዘጋጃችሁልን! በጣም በጣም እናመሰግናችኋለን!”​—⁠ቤቴል

“እነዚያ ዕብራውያን ወጣቶች የእምነት ፈተና በደረሰባቸው ጊዜ አብሬያቸው ያለሁ ያክል ነው የተሰማኝ። የራሴንም እምነት እንድመረምር አበረታቶኛል። ‘ምን አስተውለሃል?’ የሚለው የክለሳ ሣጥን ጠቅላላ የምዕራፉ ይዘት በልብ ውስጥ እንዲቀረጽ ያደርጋል። ይህን የመሰለ ድንቅ መጽሐፍ ስላዘጋጃችሁልን በድጋሚ አመሰግናችኋለሁ።”​—⁠ሊዲያ