በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ስኬታማ ለመሆን የሚያስችለው ቁልፍ ምንድን ነው?

ስኬታማ ለመሆን የሚያስችለው ቁልፍ ምንድን ነው?

ስኬታማ ለመሆን የሚያስችለው ቁልፍ ምንድን ነው?

አዲስ ነገር የመሥራት ከፍተኛ ጉጉት የነበራቸው ሁለት ወጣቶች በሠሩት ለየት ያለ መሣሪያ ላይ ወሳኝ የሆነ ሙከራ ለማድረግ በዝግጅት ላይ ነበሩ። ከየት መጣ ሳይባል ኃይለኛ ነፋስ መጥቶ ይህንን ጥንቃቄ የሚጠይቅ መሣሪያ ወደ ሰማይ ካነሳ በኋላ መልሶ ከመሬት ጋር በማላተም ስብርብሩን አወጣው። ወጣቶቹ ተስፋ ቆርጠው ባሉበት ቆመው ቀሩ። በስንት ጥንቃቄ የደከሙለት ሥራቸው የእንጨትና የብረታ ብረት ክምር ብቻ ሆኖ ቀረ።

ኦርቨል እና ዊልበር ራይት በአየር ላይ የሚበር ማሽን ለመሥራት ባደረጉት ሙከራ በጥቅምት 1900 የገጠማቸው ይህ ወሽመጥ የሚቆርጥ ችግር የመጀመሪያቸው አልነበረም። ይህንን ሙከራ በማድረግ የተወሰኑ ዓመታት አሳልፈውና ለዚህም ሲሉ በርካታ መጠን ያለው ገንዘብ አፍስሰው ነበር።

በመጨረሻ ግን ጽናታቸው ፍሬ አፍርቷል። እነዚህ ወንድማማቾች ታኅሣሥ 17, 1903 ዩ ኤስ ኤ ውስጥ በሰሜን ካሮላይና በምትገኘው በኪቲ ሃውክ ለ12 ሰኮንዶች ብቻ አየር ላይ የቆየውን የመጀመሪያ በሞተር የሚሠራ ማሽን ማብረር ችለው ነበር። አየር ላይ የቆየበት ጊዜ ዛሬ ከሚደረጉት በረራዎች አንጻር ሲታይ አጭር ቢሆንም የዓለምን ታሪክ እስከ ወዲያኛው ለመለወጥ ግን በቂ ነበር!

አብዛኛዎቹ ሙከራዎች መሳካት አለመሳካታቸው ባመዛኙ የተመካው ያለመሰልቸት በሚደረግ ጥረት ላይ ነው። አንድን አዲስ ቋንቋ አቀላጥፎ መናገርም ሆነ አንድ ሙያ መማር ወይም ደግሞ ወዳጅነት ማዳበር አብዛኛዎቹ ከፍ ያለ ግምት የሚሰጣቸው ነገሮች ያላሰለሰ ጥረት የሚጠይቁ ናቸው። ጸሐፊው ቻርለስ ቴምፕልተን እንደሚሉት “ከአሥር እጅ ዘጠኙ ስኬት ማግኘታቸው ከአንድ ነገር ጋር በቀጥታ የተያያዘ ነው። ይኸውም ጠንክሮ መሥራት ነው።” የጽሑፍ ዓምድ አዘጋጅ የሆኑት ሌነርድ ፒትስ ጁኒየር እንዲህ ይላሉ:- “ስለ ተሰጥዎ እናወራለን። ዕድልን እናመሰግናለን፣ ነገር ግን ብዙውን ጊዜ ሊረሱ የማይገባቸውን ጠንክሮ መሥራትንና በመካከል የሚገጥሙ እንቅፋቶችን እንዲሁም ብዙ ሰዓት መድከምን እንዘነጋለን።”

ይህም መጽሐፍ ቅዱስ ከረጅም ጊዜ በፊት “የትጉ እጅ ትገዛለች” ሲል ከተናገረው ነገር ጋር ይስማማል። (ምሳሌ 12:​24) ትጋት ማለት በምናደርገው ጥረት መጽናት ማለት ነው። ለመሥራት ያቀድነውን ነገር ከዳር ማድረስ ከፈለግን ይህን ማድረጋችን አስፈላጊ ነው። ጽናት ምንድን ነው? ግባችንን ከዳር ለማድረስ መጽናት የምንችለው እንዴት ነው? መጽናት የሚኖርብንስ በምን ነገር ነው? እነዚህ ጥያቄዎች በሚቀጥለው ርዕስ ውስጥ መልስ ያገኛሉ።

[በገጽ 3 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

U.S. National Archives photo