በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በመጽናት የሚገኝ ስኬት

በመጽናት የሚገኝ ስኬት

በመጽናት የሚገኝ ስኬት

በዛሬው ጊዜ ጽናት እምብዛም የሚታይ ባሕርይ አይደለም። ብዙ ሰዎች ስኬት ማግኘት አለማግኘትህ የተመካው በትክክለኛው ቦታና በትክክለኛው ጊዜ ላይ በመገኘትህ እንጂ በጽናት ላይ አይደለም የሚል እምነት አላቸው። ዳሩ እነርሱ ምን ያድርጉ? የዜና ማሠራጫዎች በጥቂት ጥረትና አነስተኛ ገንዘብ የፈለግኸውን ነገር ሁሉ ማግኘት ትችላለህ በሚል የማስታወቂያ መፈክር የተሞሉ ናቸው። ጋዜጦችም በአንድ ጀንበር ስለተሳካላቸውና ትምህርታቸውን እንደጨረሱ ቱጃር ስለሆኑ ብልህ የንግድ ሰዎች የሚገልጹ ታሪኮችን በየጊዜው ያወጣሉ።

የጽሑፍ አምድ አዘጋጅ የሆኑት ሌነርድ ፒትስ እንዲህ ሲሉ ቅሬታቸውን ገልጸዋል:- “የብልጠት ጉዳይ ነው የሚል አስተሳሰብ በተጠናወተው ኅብረተሰብ ውስጥ በጣም ቀላል እንደሆነ ተደርጎ ይታያል። . . . ማንኛውም ሰው ዘዴው ከገባው፣ ችሎታው ካለው ወይም አምላክ ከረዳው ሊያገኘው እንደሚችል ተደርጎ ይታሰባል።”

ጽናት ምንድን ነው?

መጽናት ማለት ‘መሰናክል ወይም እንቅፋት ቢኖርም እንኳ አንድን ዓላማ፣ ሁኔታ ወይም ተግባር የሙጥኝ ብሎ ዳር ማድረስ’ ማለት ነው። መከራን እየተጋፈጡ በቁርጠኝነት ወደፊት መግፋት፣ አቋምን አለማላላት፣ ተስፋ አለመቁረጥ ማለት ነው። መጽሐፍ ቅዱስ የዚህን ባሕርይ አስፈላጊነት ጎላ አድርጎ ይገልጻል። ለምሳሌ ያህል የአምላክ ቃል እንዲህ ሲል ማሳሰቢያ ይሰጠናል:- “አስቀድማችሁ የእግዚአብሔርን መንግሥት . . . [“ሳታቋርጡ፣ NW  ] ፈልጉ፣” “መዝጊያን [“ሳታቋርጡ፣ NW  ] አንኳኩ፣ ይከፍትላችሁማል፣” “በጸሎት ጽኑ” እንዲሁም “መልካሙንም [“አጥብቃችሁ፣” NW  ] ያዙ።”​—⁠ማቴዎስ 6:​33፤ ሉቃስ 11:​9፤ ሮሜ 12:​12፤ 1 ተሰሎንቄ 5:​21

የጽናት አንዱ በጎ ጎን ማጋጠማቸው የማይቀረውን እንቅፋቶችን መቋቋም መቻሉ ነው። ምሳሌ 24:​16 እንዲህ ይላል:- “ጻድቅ ሰባት ጊዜ ይወድቃልና፣ ይነሣማል።” (በሰያፍ የጻፍነው እኛ ነን።) ጽኑ የሆነ ሰው ችግር ወይም ሽንፈት ሲገጥመው ‘ተሽመድምዶ’ ከመቅረት ይልቅ ‘ይነሣል፣’ ‘ይቀጥላል፣’ እንዲሁም እንደገና ይሞክራል።

ይሁን እንጂ ብዙዎች ሊገጥማቸው የሚችለውን ችግርና ሽንፈት ለመጋፈጥ ዝግጁ አይደሉም። የመጽናት ፍላጎት በውስጣቸው ስላላዳበሩ በቀላሉ እጃቸውን ይሰጣሉ። ጸሐፊው ሞርሌ ኮላጋን እንዳሉት ከሆነ “ብዙ ሰዎች ለሚገጥማቸው ሽንፈት ምላሽ የሚሰጡት ራሳቸውን በሚጎዳ መንገድ ነው። ስለ ራሳቸው በማዘን ይቆዝማሉ፣ ሰዉን ሁሉ ተወቃሽ ያደርጋሉ፣ ይመረራሉ እንዲሁም . . . ተሽመድምደው ይወድቃሉ።”

ይህ በጣም የሚያሳዝን ነው። ፒትስ እንደተናገሩት “የሚደርስብን ፈተና አንድ ዓላማ እንደሚያከናውን ማለትም ከችግሩ አንድ ትልቅ ነገር ልንማር እንደምንችል እንረሳለን።” ይህ ትልቅ ትምህርት ምንድን ነው? ሐሳባቸውን ሲያጠቃልሉ እንዲህ ብለዋል:- “[አንድ ሰው] ሽንፈት ሞት ወይም እስከ ወዲያኛው መሸነፍ ማለት እንዳልሆነ ይማራል። ብስለት ያገኛል። ወደፊት ለሚገጥመው ነገር ዝግጁ ይሆናል።” መጽሐፍ ቅዱስ በአጭሩ “በድካም ሁሉ ልምላሜ ይገኛል” ይላል።​—⁠ምሳሌ 14:​23

እርግጥ አንድ ዓይነት እንቅፋት ከገጠመን በኋላ እንደገና ተነስቶ መቀጠል ሁል ጊዜ ቀላል አይሆንም። አንዳንድ ጊዜ የሚገጥሙንን እንቅፋቶች ለመወጣት የምናደርገውን ጥረት የሚያከሽፉ መስለው የሚታዩ ተፈታታኝ ሁኔታዎች ይገጥሙናል። ወዳለምነው ግብ ከመቅረብ ይልቅ ጭራሽ እየራቅን የምንሄድ መስሎ ሊታየን አልፎ ተርፎም ከእይታ እንደተሰወረ ሆኖ ሊሰማን ይችላል። አንዳንድ ጊዜ ከአቅማችን በላይ እንደሆነ፣ ብቁ እንዳልሆንን ሊሰማን እንዲሁም ተስፋ ልንቆርጥና ጭንቀት ውስጥ ልንገባ እንችል ይሆናል። (ምሳሌ 24:​10) ይሁንና መጽሐፍ ቅዱስ “ባንዝልም በጊዜው እናጭዳለንና መልካም ሥራን ለመሥራት አንታክት” በማለት ያበረታታናል።​—⁠ገላትያ 6:​9፣ በሰያፍ የጻፍነው እኛ ነን።

እንድንጸና ሊረዳን የሚችለው ነገር ምንድን ነው?

በመረጥነው ጎዳና ለመጽናት የሚረዳን የመጀመሪያው ነገር የማያስቆጩና ሊደረስባቸው የሚችሉ ግቦች ማውጣት ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ ይህን ነገር በሚገባ ተገንዝቦ ነበር። ለቆሮንቶስ ሰዎች እንዲህ ብሏቸዋል:- “እኔ ያለ አሳብ እንደሚሮጥ ሁሉ እንዲሁ አልሮጥም፣ ነፋስን እንደሚጐስም ሁሉ እንዲሁ አልጋደልም።” ጳውሎስ ጥረቱ የተሳካ እንዲሆን ከፈለገ ትኩረቱን በሩጫው የመጨረሻ መስመር ላይ እንደሚያደርግ ሯጭ ግልጽ ሆኖ የሚታይ ግብ ሊኖረው እንደሚያስፈልግ ተረድቶ ነበር። “በእሽቅድምድም ስፍራ የሚሮጡት፣ ሁሉ እንዲሮጡ ነገር ግን አንዱ ብቻ ዋጋውን እንዲቀበል አታውቁምን? እንዲሁም ታገኙ ዘንድ [“በዚህ መልክ፣” NW  ] ሩጡ” ሲል አጥብቆ አሳስቧል። (1 ቆሮንቶስ 9:​24, 26) ይህንን ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?

ምሳሌ 14:​15 “ብልህ ግን አካሄዱን ይመለከታል” ይላል። ወዴት እያመራን ነው? እንዲሁም በምን በኩል ማስተካከያ ማድረግ ያስፈልገናል? እያልን ራሳችንን በመጠየቅ በሕይወታችን ውስጥ የቀየስናቸውን ስልቶች በየጊዜው እንደገና መገምገሙ ጥበብ ይሆናል። ማከናወን የምንፈልገው ነገር ምን እንደሆነና ያንን ማድረግ የፈለግነው ለምን እንደሆነ በአእምሮአችን ውስጥ በግልጽ ማስቀመጣችን በጣም አስፈላጊ ነው። የመጨረሻ ግባችን ምን እንደሆነ በአእምሮአችን ውስጥ በግልጽ ከሳልን ተስፋ የምንቆርጥበት አጋጣሚ የጠበበ ነው። በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፈው ምሳሌ ‘የእግርህ መንገድ እንዲቀና አካሄድህም ሁሉ እንዲጸና’ “ዓይኖችህ አቅንተው ይዩ” በማለት አጥብቆ ይመክራል።​—⁠ምሳሌ 4:​25, 26

ግብህ ምን እንደሆነ ለይተህ ካወቅህ በኋላ ቀጣዩ እርምጃ እዚያ ላይ መድረስ የምትችለው እንዴት እንደሆነ መመርመር ነው። ኢየሱስ እንዲህ ሲል ጠይቋል:- “ከእናንተ ግንብ ሊሠራ የሚወድ ለመደምደሚያ የሚበቃ ያለው እንደ ሆነ አስቀድሞ ተቀምጦ [ኪ]ሳራውን የማይቈጥር ማን ነው?” (ሉቃስ 14:​28) ከዚህ መሠረታዊ ሥርዓት ጋር በሚስማማ መንገድ አንድ የአእምሮ ጤና ባለሙያ እንዲህ ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል:- “ስኬታማ ስለሆኑ ሰዎች ያስተዋልኩት አንድ ነገር ቢኖር በሕይወታቸው ውስጥ በምክንያትና በውጤት መካከል ያለውን ዝምድና በግልጽ የሚረዱ ሰዎች መሆናቸውን ነው። ስኬታማ የሆኑ ሰዎች አንድ ነገር ከፈለጉ ያንን ለማግኘት አስፈላጊ የሆኑትን እርምጃዎች ሁሉ መውሰድ እንዳለባቸው ይገነዘባሉ።” ማግኘት የምንፈልገውን ነገር ለማግኘት የምንወስዳቸውን እርምጃዎች በሙሉ በግልጽ መረዳታችን በግባችን ላይ እንድናተኩር ይረዳናል። እንዲሁም ምናልባት አንድ ዓይነት እንቅፋት ቢያጋጥመን እንኳ እንደገና ተነስተን ወደፊት ለመጓዝ ይረዳናል። ኦርቨል እና ዊልበር ራይት ስኬታማ እንዲሆኑ የረዳቸው መሠረታዊ ነገር ይህ ነበር።

በመሆኑም አንድ ዓይነት እንቅፋት ሲገጥምህ አዎንታዊ በሆነ መንገድ ለማየትና አንድ ነገር ተምረህ የምታልፍበት ተሞክሮ እንደሆነ አድርገህ ለመመልከት ሞክር። ሁኔታውን በመመርመር ስህተትህ ምን ላይ እንደነበር አስተውል። ከዚያም ስህተቱን አርም ወይም ለድክመትህ መፍትሔ ፈልግ። ‘አሳብ በምክር ስለምትጸና’ ከሌሎች ጋር መወያየቱ ይጠቅማል። (ምሳሌ 20:​18) በየጊዜው የምታደርገው ጥረት ቀስ በቀስ የተሻለ ችሎታና ክህሎት እንድታዳብር ስለሚረዳህ በመጨረሻ ስኬታማ እንድትሆን አስተዋጽኦ ይኖረዋል።

ለጽናት በጣም አስፈላጊ የሆነው ሦስተኛው እርምጃ ደግሞ አለማሰለስ ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ “በደረስንበት በዚያ እንመላለስ” ሲል አጥብቆ አሳስቧል። (ፊልጵስዩስ 3:​16) አንድ አስተማሪ እንዳሉት ከሆነ “አንድን ነገር መጠኑን ጠብቆ ሳያሰልሱ ለረጅም ጊዜ ማከናወን ያለው ጥቅም ከፍተኛ ነው።” ስለ ኤሊና ጥንቸል በሰፊው የሚነገረው የኢሰፕ ተረት ይህን ጉዳይ ግልጽ ያደርገዋል። ኤሊ ከጥንቸል አንጻር ስትታይ በጣም ቀርፋፋ ብትሆንም ውድድሩን አሸንፋለች። ለምን? ምክንያቱም ኤሊ ራሷን በመገሰጽ ያለማቋረጥ በውድድሩ በመቀጠሏ ነው። ውድድሯን ከማቋረጥ ይልቅ የምትችለውን ያህል እየሮጠች የመጨረሻውን መስመር እስክታልፍ ድረስ በዚያው ቀጥላለች። አንድ የተደራጀና በጀመረው መልክ መመላለሱን የሚቀጥል ሰው የማያቋርጥ ዕድገት ስለሚያደርግ ውስጣዊ ስሜቱ አይጠፋም። ከዚህም የተነሣ ውድድሩን አያቋርጥም ወይም ከውድድሩ አይባረርም። አዎን፣ ሽልማትህን እንድታገኝ ‘በዚህ መልክ ሩጥ።’

የማያስቆጩ ግቦች ማውጣት

እርግጥ ጽናታችን ዋጋማ እንዲሆን ካስፈለገ የምናወጣቸው ግቦች የማያስቆጩ መሆን አለባቸው። ብዙ ሰዎች ደስታ የማያመጡ ነገሮችን ያሳድዳሉ። ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል:- “ነገር ግን ነጻ የሚያወጣውን ፍጹሙን ሕግ ተመልክቶ የሚጸናበት፣ ሥራንም የሚሠራ . . . በሥራው የተባረከ [“ደስተኛ፣” NW ] ይሆናል።” (ያዕቆብ 1:​25) አዎን፣ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተዘረዘረውን የአምላክ ሕግ ማጥናት ምንም የማያስቆጭ ግብ ነው። ለምን? ዋነኛው ምክንያት የአምላክ ሕግ በእርሱ ፍጹምና ጻድቅ በሆነ የአቋም ደረጃ ላይ የተመሠረተ በመሆኑ ነው። ፈጣሪ እንደመሆኑ መጠን ለፍጥረታቱ የሚበጃቸውን ነገር ያውቃል። በመሆኑም የአምላክን መመሪያዎች በመማርና በሕይወታችን ውስጥ እነዚያን ተግባራዊ በማድረግ ብንጸና ይህን የመሰለው ጽናት ደስታን እንደሚያስገኝልን ምንም ጥርጥር የለውም። ምሳሌ 3:​5, 6 ላይ “በፍጹም ልብህ በእግዚአብሔር ታመን፣ . . . በመንገድህ ሁሉ እርሱን እወቅ፣ እርሱም ጎዳናህን ያቀናልሃል” የሚል ቃል ተገብቶልናል።

በተጨማሪም ስለ አምላክና ስለ ኢየሱስ ማወቅ “የዘላለም ሕይወት” እንደሚያስገኝ ኢየሱስ ተናግሯል። (ዮሐንስ 17:​3) የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት በዚህ የነገሮች ሥርዓት ‘የመጨረሻ ቀናት’ እንደምንኖር ይጠቁመናል። (2 ጢሞቴዎስ 3:​1-5፤ ማቴዎስ 24:​3-13) በቅርቡ የአምላክ መንግሥት ማለትም ጽድቅ የሰፈነበት መስተዳድሩ በምድር ነዋሪዎች ላይ ግዛቱን ያሰፍናል። (ዳንኤል 2:​44፤ ማቴዎስ 6:​10) ይህ መስተዳድር ይህ ነው የማይባል ሰላምና ብልጽግና የሰፈነበት እንዲሁም ታዛዥ የሰው ልጆች በሙሉ ደህንነት የሚያገኙበት ዘመን ያመጣል። (መዝሙር 37:​10, 11፤ ራእይ 21:​4) ሥራ 10:​34 ‘አምላክ ለሰው ፊት አያዳላም’ ይላል። አዎን፣ ሁሉም ሰው ይህ መንግሥት የሚያመጣቸው ጥቅሞች ተቋዳሽ እንዲሆን ተጋብዟል!

መጽሐፍ ቅዱስ ጥበብ የሞላበትና ትርጉም ያዘለ ጥንታዊ መጽሐፍ ነው። ይህን መጽሐፍ መረዳት ጊዜና ጥረት ይጠይቃል። ይሁን አንጂ በአምላክ እርዳታ እንዲሁም እውቀት ለማግኘት በምናደርገው ፍለጋ ከጸናን በግልጽ ልንረዳው እንችላለን። (ምሳሌ 2:​4, 5፤ ያዕቆብ 1:​5) የተማርነውን ነገር ሥራ ላይ ማዋል ፈታኝ ሊሆንብን እንደሚችል አይካድም። በአስተሳሰባችን ወይም በልማዳችን ላይ ማስተካከያ ማድረግ ያስፈልገን ይሆናል። ወዳጆቻችን ወይም የቤተሰባችን አባላት ለእኛ በማሰብ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናታችንን ይቃወሙ ይሆናል። ስለዚህ ጽናት የግድ አስፈላጊ ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ አምላክ ‘በመልካም ሥራ ለሚጸኑ ሰዎች’ የዘላለም ሕይወትን እንደሚሰጥ ያሳስበናል። (ሮሜ 2:​7) የይሖዋ ምሥክሮች እዚህ ግብ ላይ መድረስ ትችል ዘንድ ሊረዱህ ፈቃደኛ ናቸው።

ስለ አምላክና ስለ እርሱ ፈቃድ በመማር እንዲሁም የተማርከውን ሥራ ላይ በማዋል ከጸናህ ስኬታማ እንደምትሆን እርግጠኛ ሁን።​—⁠መዝሙር 1:​1-3

[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ስለ አምላክና ስለ ፈቃዱ በመማር ከጸናህ ስኬታማ ትሆናለህ

[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

Culver Pictures