በኔዘርላንድ የሚኖሩትን ሁሉንም ዓይነት ሰዎች መርዳት
የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ሪፖርት
በኔዘርላንድ የሚኖሩትን ሁሉንም ዓይነት ሰዎች መርዳት
አብርሃም ልዩ እምነት የነበረው ሰው ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ እንደተናገረው አብርሃም ‘በተጠራ ጊዜ’ የአምላክን ቃል በመታዘዝ ‘ወዴት እንደሚሄድ ሳያውቅ ወጥቷል።’ አብርሃም መላ ቤተሰቡን ይዞ በመጓዝ በቀጣዮቹ አንድ መቶ ዓመታት ‘ቃል በተገባለት አገር እንደ መጻተኛ በእምነት ተቀምጧል።’—ዕብራውያን 11:8, 9 NW
ዛሬም በተመሳሳይ ብዙ የይሖዋ ምሥክሮች ይበልጥ እርዳታ በሚያስፈልግበት ቦታ ለማገልገል ሲሉ ወደ ሌላ አገር መሄድ የሚያስከትለውን ተፈታታኝ ሁኔታ ለመጋፈጥ ፈቃደኛ ሆነዋል። ሌሎች ደግሞ ወደ አገራቸው ለመጡ የውጭ አገር ዜጎች መመሥከር እንዲችሉ ሌላ ቋንቋ ተምረዋል። የሚከተሉት ምሳሌዎች እንደሚያሳዩት 15 ሚልዮን ከሚያክሉት ነዋሪዎች መካከል ከሌሎች አገሮች የመጡ አንድ ሚልዮን ሰዎች በሚገኙባት በኔዘርላንድ የሚታየው ይህ ጥሩ መንፈስ “ሥራ የሞላበት ትልቅ በር” ከፍቷል።—1 ቆሮንቶስ 16:9
□ ቀድሞ የኩንግ ፉ አሠልጣኝ የነበረው ባራም በመካከለኛው ምሥራቅ ከምትገኝ አገር የመጣ ነው። እዚያ ከመጣ በኋላ መጽሐፍ ቅዱስና አንዳንድ የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ጽሑፎች አገኘ። በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ባራም እውነትን ማግኘቱን ተገነዘበ። እርሱና ሚስቱ ጥናት ጀመሩ። ሆኖም የመጽሐፍ ቅዱስ አስተማሪያቸው የእነርሱን ቋንቋ መናገር አለመቻሉ ችግር ፈጥሮባቸው ነበር። ይግባቡ የነበረው በምልክት ሲሆን “በእጅ በእግራቸው” የማውራት ያህል እንደነበር ያስታውሳሉ። ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ባራምና ሚስቱ በትውልድ ቋንቋቸው የሚመራ ጉባኤ አገኙ፤ ከዚያም ፈጣን እድገት አደረጉ። አሁን ባራም የተጠመቀ ምሥክር ሆኗል።
□ የደች ተወላጅ የሆኑ አቅኚ ባልና ሚስት በአንድ የገበያ አዳራሽ አጠገብ ቆሞ የነበረን ኢንዶኔዥያዊ ቀርበው አነጋገሩ። ባልና ሚስቱ በራሱ ቋንቋ ሲያነጋግሩት ተደሰተ። ከዚያም ቤቱ ሄደው ለማነጋገር ዝግጅት አደረጉ። የማሕፀን ሕክምና ትምህርት በተከታተለባት በሩስያ ከ20 ለሚበልጡ ዓመታት መኖሩን ተገነዘቡ። በአምላክ መኖር እንደማያምን ቢናገርም ባዋለደ ቁጥር “ሰውነታችን ምንኛ ድንቅ ነው! እንዴት ያለ ተዓምር ነው!” እያለ ይገረም ነበር። መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት ተስማማና ብዙም ሳይቆይ ለሰው ዘር የሚያስብ ፈጣሪ መኖሩን አምኖ ተቀበለ። (1 ጴጥሮስ 5:6, 7) አሁን የተጠመቀ ወንድም ሆኖ አምስተርዳም በሚገኘው የኢንዶኔዥያ ቋንቋ ተናጋሪ ጉባኤ ያገለግላል።
□ በዓለም ላይ ካሉት ግዙፍ የባሕር ወደቦች አንዱ ወደሚገኝበት ወደ ሮተርዳም በየቀኑ ለሚመጡት የተለያየ ቋንቋ የሚናገሩ ሰዎች በመስበክ ረገድ አንድ የአቅኚዎች ቡድን የተዋጣለት ሆኗል። ይህ ቀናተኛ የሰባኪዎች ቡድን ባደረገው እንቅስቃሴ የተነሳ አንድ ካፒቴን፣ አንድ የባሕር መኮንንና ቀድሞ አጃቢ ወታደር የነበረን ሰው ጨምሮ በርከት ያሉ መርከበኞች እውነትን ተቀብለዋል። አሁን እነርሱም የአምላክን መንግሥት ምሥራች በዓለም ዙሪያ በማሰራጨቱ ሥራ እየተካፈሉ ነው።—ማቴዎስ 24:14
በሌሎች የዓለም ክፍሎች እንዳሉት ሁሉ በኔዘርላንድ የሚገኙት የይሖዋ ምሥክሮችም የዘላለሙን ምሥራች ለእያንዳንዱ ብሔር፣ ነገድ፣ ቋንቋና ወገን በማወጅ ረገድ የበኩላቸውን ድርሻ ለማበርከት ቁርጥ ውሳኔ አድርገዋል።—ራእይ 14:6