በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አንዲት እናት የሰጠችው ጥበብ ያዘለ ምክር

አንዲት እናት የሰጠችው ጥበብ ያዘለ ምክር

አንዲት እናት የሰጠችው ጥበብ ያዘለ ምክር

“ልጄ ሆይ፣ የአባትህን ምክር ስማ፣ የእናትህንም ሕግ አትተው።”​—⁠ምሳሌ 1:​8

ወላጆቻችን ጠቃሚ የሆነ የማበረታቻ፣ የድጋፍና የምክር ምንጭ ሊሆኑ ይችላሉ። የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የሆነው መጽሐፈ ምሳሌ ከእናቱ ‘ክብደት ያለው ምክር’ ስላገኘ ልሙኤል ስለሚባል አንድ ወጣት ንጉሥ ይናገራል። እነዚህ ቃላት በመጽሐፈ ምሳሌ ምዕራፍ 31 ላይ ተመዝግበው የሚገኙ ሲሆን እኛም ይህች እናት ከሰጠችው ጥበብ ያዘለ ምክር መጠቀም እንችላለን።​—⁠ምሳሌ 31:​1 NW

ለአንድ ንጉሥ የሚስማማ ምክር

የልሙኤል እናት ምክሯን ስትጀምር ጉጉታችንን የሚያሳድጉ በርካታ ጥያቄዎች አቅርባለች። “ልጄ ሆይ፣ ምንድር ነው? የሆዴ ልጅ ሆይ፣ ምንድር ነው? የስእለቴ ልጅ ሆይ፣ ምንድር ነው?” ሦስት ጊዜ ደጋግማ ያቀረበችው ልመና ልጅዋ ለምክሯ ትኩረት የመስጠቱ ጉዳይ በጣም እንዳሳሰባት ያሳያል። (ምሳሌ 31:​2) ለልጅዋ መንፈሳዊ ደህንነት ያሳየችው አሳቢነት ዛሬ ላሉ ክርስቲያን ወላጆች ጥሩ ምሳሌ ይሆናቸዋል።

አንዲት እናት የልጅዋን ደህንነት በተመለከተ ከፈንጠዝያና ሥነ ምግባር ከጎደለው አኗኗር ጋር ከሚዛመዱት እንደ መጠጥ፣ ሴትና ዘፈን ከመሳሰሉት የተለመዱ ነገሮች የበለጠ ሊያሳስባት የሚችል ምን ነገር ይኖራል? የልሙኤል እናት ጉዳዩን ሳትሸፋፍን እንዲህ ብላለች:- “ጉልበትህን ለሴቶች አትስጥ።” ሴሰኛነት ‘ነገሥታትን የሚያጠፋ’ እንደሆነ ገልጻለች።​—⁠ምሳሌ 31:​3

ከልክ በላይ መጠጣትም በቸልታ የሚታለፍ ጉዳይ አይደለም። “ለነገሥታት አይገባም፣ ልሙኤል ሆይ፣ ነገሥታት የወይን ጠጅ ይጠጡ ዘንድ አይገባም” በማለት አስጠንቅቃዋለች። አንድ ንጉሥ ሁልጊዜ የሚሰክር ከሆነ ጤናማ በሆነና ባልተዛባ አእምሮ መፍረድ እንዲሁም ‘ሕግን ሳይረሳና የድሀ ልጆችን ፍርድ ሳያጓድል’ እንዴት መግዛት ይችላል?​—⁠ምሳሌ 31:​4-7

ከዚህ በተቃራኒ ንጉሡ ከእንዲህ ዓይነት መጥፎ ምግባሮች በመራቅ ‘በእውነት መፍረድ፤ ለድሀና ለምስኪን መፍረድም’ ይችላል።​—⁠ምሳሌ 31:​8, 9

ምንም እንኳ ክርስቲያን ወጣቶች በዛሬው ጊዜ “ነገሥታት” ባይሆኑም የልሙኤል እናት የሰጠችው ጥበብ ያዘለ ምክር ዛሬም ወቅታዊ ነው። እንዲያውም ዛሬ ያለው ጠቀሜታ ባይበልጥ! በዛሬው ጊዜ አልኮል መጠጦችን ያላግባብ መጠጣት፣ ሲጋራ ማጨስና የፆታ ብልግና መፈጸም በወጣቶች ዘንድ ተስፋፍቶ ይገኛል። በመሆኑም ክርስቲያን ወጣቶች ወላጆቻቸው የሚሰጧቸውን ‘ክብደት ያለው ምክር’ በትኩረት መከታተላቸው እጅግ አስፈላጊ ነው።

ልባም ሚስት

እናቶች ወደ ጉልምስና ዕድሜ እየተጠጉ ስላሉት የወንዶች ልጆቻቸው የወደፊት ትዳር ማሰባቸው ተገቢ ነገር ነው። የልሙኤል እናት ቀጥሎ ትኩረት ያደረገችው አንዲት ልባም ሚስት ልታሟላቸው በሚገቡ ባሕርያት ላይ ነው። አንድ ወጣት ከዚህ አስፈላጊ ጉዳይ አንጻር የአንዲትን ሴት ሁኔታ መገምገሙ እንደሚጠቅመው የታወቀ ነው።

ቁጥር 10 “ልባም ሴት [“ሚስት፣” NW  ]” በቀላሉ በማይገኝና በከበረ ዕንቁ ተመስላለች። በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን ዕንቁ ለማግኘት ከፍተኛ ጥረት ማድረግ ይጠይቅ ነበር። በተመሳሳይ መንገድ ልባም ሚስት ማግኘትም ጥረት ይጠይቃል። አንድ ወጣት በችኮላ ወደ ትዳር ዓለም ከመግባት ይልቅ ምርጫ ለማድረግ በቂ ጊዜ መውሰዱ የተገባ ይሆናል። ከዚያም በብዙ ጥረት ያገኘውን ነገር ከፍ አድርጎ መመልከቱ የማይቀር ነው።

ልሙኤል ልባም ሚስትን በተመለከተ “የባልዋ ልብ ይታመንባታል” ተብሎ ተነግሮታል። (ምሳሌ 31 ቁጥር 11) በሌላ አባባል ሚስቱ ለእያንዳንዱ ጉዳይ የእርሱን ፈቃድ ማግኘት እንዳለባት አድርጎ ማሰብ የለበትም። እርግጥ፣ የትዳር ጓደኛሞች ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቁ ግዢዎችን ወይም ልጆች ማሳደግን የመሳሰሉ ከባድ ውሳኔዎች ከማድረጋቸው በፊት መመካከር አለባቸው። በእነዚህ መስኮች የሐሳብ ልውውጥ ማድረጋቸው በመካከላቸው የጠበቀ ትስስር እንዲኖር አስተዋጽኦ ያደርጋል።

እርግጥ ልባም የሆነች ሚስት የምታከናውናቸው ብዙ ነገሮች አሉ። ከምሳሌ 31 ቁጥር 13 እስከ 27 ላይ በየትኛውም ዘመን የሚኖሩ ሚስቶች ቤተሰባቸውን ለመጥቀም ሲሉ ሊሠሩበት የሚችሉ ምክርና መሠረታዊ ሥርዓት ተዘርዝሯል። ለምሳሌ ያህል የልብስና የቤት ዕቃዎች ዋጋ እያሻቀበ ባለበት ጊዜ ልባም ሚስት ቤተሰቧ ምቹና የሚያስከብር ልብስ እንዲኖረው በእጅዋ ለመሥራትና ያላትን በቁጠባ ለመጠቀም ትጥራለች። (ምሳሌ 31 ቁጥር 13, 19, 21, 22) ቤተሰቡ ለምግብ የሚያወጣውን ወጪ ለመቀነስ ብላ የቻለችውን ራሷ ታበቅላለች እንዲሁም በጥንቃቄ ትሸምታለች።​—⁠ቁጥር 14, 16

ይህች ሴት ‘የሀኬትን እንጀራ’ እንደማትበላ ግልጽ ነው። በትጋት ትሠራለች፤ የቤቷንም ሥራ በተቀላጠፈ ሁኔታ ታደራጃለች። (ምሳሌ 31 ቁጥር 27) “ወገብዋን በኃይል ትታጠቃለች።” ይህም አድካሚ የሆነ ሥራ ለመሥራት ትዘጋጃለች ማለት ነው። (ምሳሌ 31 ቁጥር 17) ሥራዋን የምትጀምረው ገና ሳይነጋ ነው። መሽቶ እያለም በትጋት መሥራትዋን አታቆምም። ለሥራዋ የምትጠቀምበት መብራት ሁልጊዜ የሚበራ ያህል ነበር።​—⁠ቁጥር 15, 18

ከሁሉም በላይ ልባም የሆነች ሚስት መንፈሳዊ ሰው ነች። ለአምላክ ጤናማ ፍርሃት አላት፤ የምታመልከውም ጥልቅ አክብሮትና አምልኮታዊ ፍርሃት በታከለበት መንገድ ነው። (ምሳሌ 31 ቁጥር 30) በተጨማሪም ልጆቿ ተመሳሳይ ነገር እንዲያደርጉ በማሰልጠን ረገድ ባልዋን ትረዳዋለች። ምሳሌ 31 ቁጥር 26 “በጥበብ” ልጆችዋን እንደምታስተምርና “የርኀራኄም ሕግ በምላስዋ” እንዳለ ይናገራል።

ልባም የሆነ ባል

ልሙኤል ልባም የሆነችን ሚስት ለመማረክ ራሱ ልባም የሆነ ባል የሚያሟላቸውን ኃላፊነቶች አሟልቶ መገኘት ይኖርበታል። የልሙኤል እናት ከእ​ነዚህ አንዳንዶቹን ጠቅሳለታለች።

አንድ ጥሩ ባል “በአገር ሽማግሌዎች” ዘንድ መልካም ስም ይኖረዋል። (ምሳሌ 31:​23) ይህም ባለ ሙያ፣ ሐቀኛ፣ ታማ​ኝና ፈሪሃ አምላክ ያለው ሰው ይሆናል ማለት ነው። (ዘጸአት 18:​21፤ ዘዳግም 16:​18-20) ከዚህ የተነሳ ከፍተኛ ቦታ ያላቸው ሰዎች በከተማው ጉዳይ ላይ ለመምከር በሚሰበሰቡበት “በበር የታወቀ” ይሆናል። አም​ላክን የሚፈራ ሰው ነው በሚል ‘ለመታወቅ’ ከበቃ ምክንያታዊና ‘በአገሩ’ ከሚኖሩ ሽማግሌዎች ጋር በስምምነት የሚሠራ መሆን አለበት። አገር የሚለው ቃል አንድን አውራጃ ወይም አካባቢ ሊያመለክት ይችላል።

የልሙኤል እናት ከራሷ ተሞክሮ በመነሳት እንደሚሆን የታወቀ ነው፣ ወደፊት ሚስቱ ለምትሆነው ሴት አድናቆት ማሳየቱ ያለውን ጠቀሜታ ለልጅዋ አሳስባዋለች። በዚህ ምድር ላይ የእርሷን ያህል የሚቀርበው ሰው አይኖርም። በመሆኑም በሰዎች ሁሉ ፊት “መልካም ያደረጉ ብዙ ሴቶች አሉ፣ አንቺ ግን ከሁሉ ትበልጫለሽ” ሲል በንግግሩ የሚንጸባረቀውን ጥልቅ ስሜት ገምቱ።​—⁠ምሳሌ 31:​29

ልሙኤል እናቱ የሰጠችውን ጥበብ ያዘለ ምክር ከፍ አድርጎ እንደተመለከተው ግልጽ ነው። ለምሳሌ ያህል ምሳሌ 31 ቁጥር 1 ላይ እናቱ የተናገረችው ቃል የራሱ እንደሆነ አድርጎ መናገሩን እናነባለን። በመሆኑም እርሷ የሰጠችውን ‘እርማት’ ተቀብሎ ከምክሩ ጥቅም አግኝቷል። እኛም ይህ ‘ክብደት ያለው ምክር’ የያዘውን መሠረታዊ ሥርዓት በሕይወታችን ውስጥ በተግባር በማዋል ተጠቃሚዎች እንሁን።

[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ልባም ሚስት ‘የሀኬትን እንጀራ’ አትበላም