በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አዳኛችን በሆነው አምላክ ደስ ይበላችሁ

አዳኛችን በሆነው አምላክ ደስ ይበላችሁ

አዳኛችን በሆነው አምላክ ደስ ይበላችሁ

“እኔ ግን በእግዚአብሔር ደስ ይለኛል፤ በመድኃኒቴ አምላክ ሐሴት አደርጋለሁ።”​—ዕንባቆም 3:​18

1. ባቢሎን በ539 ከዘአበ ከመውደቋ በፊት ዳንኤል ስለ ምን ነገር ራእይ ተመልክቷል?

 ባቢሎን በ539 ከዘአበ ከመውደቋ ከአሥር ዓመት በላይ ቀደም ብሎ አረጋዊው ነቢይ ዳንኤል አስገራሚ ራእይ ተመለከተ። ራእዩ በይሖዋ ጠላቶችና እርሱ በሾመው ንጉሥ በኢየሱስ ክርስቶስ መካከል ወደሚደረገው የመጨረሻ ጦርነት የሚመሩት ሁኔታዎች ምን እንደሚመስሉ የሚተነብይ ነበር። ታዲያ ዳንኤል ምን ተሰማው? “እኔም ተኛሁ . . . ስለ ራእዩም አደንቅ ነበር” ብሏል።​—⁠ዳንኤል 8:​27

2. ዳንኤል በራእይ ያየው ግጭት ምንድን ነው? ይህ ጊዜ ስለመቅረቡስ ምን ይሰማሃል?

2 እኛስ? የምንኖረው ዳንኤል ከኖረበት በጣም ሩቅ በሆነ ዘመን ነው! ዳንኤል በራእይ የተመለከተው ግጭት ማለትም አርማጌዶን ተብሎ የሚታወቀው የአምላክ የጦርነት ቀን በጣም ቅርብ መሆኑን ስንገነዘብ እንዴት ይሰማናል? በዕንባቆም ትንቢት ውስጥ የተጋለጠው ክፋት በጣም በመስፋፋቱ ምክንያት የአምላክ ጠላቶች መጥፋታቸው የማይቀር መሆኑን ስንገነዘብ እንዴት ይሰማናል? በትንቢታዊው መጽሐፍ ሦስተኛ ምዕራፍ ላይ ተመዝግቦ የሚገኘውን የመሰለ የዕንባቆም ዓይነት ስሜት ሳይሰማን አይቀርም።

ዕንባቆም የአምላክን ምሕረት ለማግኘት ጸለየ

3. ዕንባቆም የጸለየው ማንን በመወከል ነው? የተናገራቸውስ ቃላት እኛን የሚነኩን እንዴት ነው?

3 ዕንባቆም ምዕራፍ 3 ጸሎት ነው። ቁጥር 1 [NW  ] እንደሚገልጸው ጸሎቱ በሙሾ ወይም በሐዘን እንጉርጉሮ መልክ ተገልጿል። የነቢዩ ጸሎት ስለ ራሱ የቀረበ ይመስላል። እንደ እውነቱ ከሆነ ግን ዕንባቆም የሚናገረው የአምላክን ምርጥ ሕዝቦች ወክሎ ነው። ይህ ጸሎት ዛሬ በመንግሥቱ የስብከት ሥራ ለተጠመዱት የአምላክ ሕዝቦች የላቀ ትርጉም አለው። ይህን በአእምሮአችን ይዘን ዕንባቆም ምዕራፍ 3ን ስናነብ ቃሎቹ ስለወደፊቱ ጊዜ የእርግጠኝነት ስሜት እንዲኖረን ከማድረጋቸውም በተጨማሪ በደስታ እንድንሞላ ያደርጉናል። የዕንባቆም ጸሎት ወይም የሐዘን እንጉርጉሮ አዳኛችን በሆነው ይሖዋ ደስ እንዲለን የሚያደርጉ ጠንካራ ምክንያቶችን ይሰ​ጠናል።

4. ዕንባቆም የፈራው ለምን ነበር? አምላክ ኃይሉን በምን መንገድ እንደሚጠቀምበት እርግጠኞች ልንሆን እንችላለን?

4 ቀደም ባሉት ሁለት ርዕሶች ውስጥ እንደተመለከትነው በዕንባቆም ዘመን በይሁዳ ምድር የነበረው ሁኔታ በጣም መጥፎ ነበር። ይሁን እንጂ አምላክ ይህ ሁኔታ እንዲቀጥል አይፈቅድም። ይሖዋ ቀደም ሲል እንዳደረገው ሁሉ እርምጃ መውሰዱ አይቀርም። ነቢዩ “አቤቱ፣ ዝናህን ሰምቼ ፈራሁ፤ አቤቱ፣ . . . ሥራህን” ሲል መጮሁ አያስደንቅም። ምን ማለቱ ነበር? ‘የይሖዋ ዝና’ የተባለው አምላክ በቀይ ባሕር፣ በምድረ በዳና በኢያሪኮ እንዳደረጋቸው ስለመሳሰሉት ታላላቅ ሥራዎች የሚገልጸው በጽሑፍ የሠፈረ ታሪክ ነው። ዕንባቆም እነዚህን ሥራዎች አሳምሮ ያውቅ ነበር። አሁንም ይሖዋ በጠላቶቹ ላይ ይህን ታላቅ ኃይሉን እንደሚያሳይ ማወቁ አስፈራው። እኛም በዛሬው ጊዜ ያለውን የሰው ልጅ ክፋት ስንመለከት ይሖዋ ጥንት እንዳደረገው አሁንም እርምጃ እንደሚወስድ እናውቃለን። ታዲያ ይህ ያስፈራናልን? እንዴታ! ቢሆንም እንደ ዕንባቆም በማለት እንጸልያለን:- “አቤቱ፣ በዓመታት መካከል ሥራህን ፈጽም፤ በዓመታት መካከል ትታወቅ፤ በመዓት ጊዜ ምሕረትን አስብ።” (ዕንባቆም 3:​2) አምላክ በቀጠረው ጊዜ “በዓመታት መካከል” ተአምራዊ ኃይሉን ሥራ ላይ ያውላል። በዚያ ጊዜ ለሚወዱት ምሕረትን ለማሳየት ያስብ ዘንድ ጸሎታችን ነው!

ይሖዋ እየገሰገሰ ነው!

5. አምላክ ‘ከቴማን የመጣው’ እንዴት ነበር? ይህስ ስለ አርማጌዶን ምን የሚጠቁመው ነገር አለ?

5 ይሖዋ የእርሱን ምሕረት ለማግኘት ለምናቀርበው ጸሎት መልስ ሲሰጥ ምን ነገር ይከሰታል? መልሱን ዕንባቆም 3:​3, 4 ላይ እናገኛለን። በመጀመሪያ ነቢዩ “እግዚአብሔር ከቴማን፣ ቅዱሱም ከፋራን ተራራ ይመጣል” ይላል። ቴማንና ፋራን በጥንቱ ነቢይ በሙሴ ዘመን እስራኤላውያን ወደ ከነዓን ሲጓዙ በምድረ በዳ መንገዳቸው ያለፉባቸው ቦታዎች ናቸው። ያ ታላቅ የእስራኤል ሕዝብ በሚጓዝበት ጊዜ ይሖዋ ራሱ ምንም ነገር ሳያግደው ወደፊት በመገስገስ ላይ እንዳለ ያህል ነበር። ሙሴ ከመሞቱ ከጥቂት ጊዜ በፊት “እግዚአብሔር ከሲና መጣ፣ በሴይርም ተገለጠ፤ ከፋራን ተራራ አበራላቸው፣ ከአእላፋትም ቅዱሳኑ [መላእክቱ] መጣ” ብሎ ነበር። (ዘዳግም 33:​2) ይሖዋ በአርማጌዶን በጠላቶቹ ላይ በሚዘምትበት ጊዜም ምንም ነገር የማያግደው ኃይሉ በተመሳሳይ ሁኔታ ይገለጣል።

6. አስተዋይ ክርስቲያኖች ከአምላክ ክብር በተጨማሪ ምን ነገርም ያያሉ?

6 ዕንባቆም በመቀጠል እንዲህ ይላል:- “[የይሖዋ] ክብሩ ሰማያትን ከድኖአል፣ ምስጋናውም ምድርን ሞልቶአል። ፀዳሉም እንደ ብርሃን ነው።” እንዴት ያለ የሚያስደንቅ ትዕይንት ነው! እርግጥ ነው፣ ሰዎች ይሖዋ አምላክን አይተው በሕይወት ሊኖሩ አይችሉም። (ዘጸአት 33:​20) ሆኖም የአምላክ ታማኝ ሕዝቦች ክብሩንና ግርማውን ሲያስቡ የልባቸው ዐይን ማየት ከሚችለው በላይ ይሆንባቸዋል። (ኤፌሶን 1:​18) አስተዋይ ክርስቲያኖች ደግሞ ከይሖዋ ክብር በተጨማሪ የሚያዩት ሌላ ነገር አለ። ዕንባቆም 3:​4 ሲደመድም “ጨረር ከእጁ ወጥቶአል ኃይሉም በዚያ ተሰውሮአል” ይላል። አዎን፣ ይሖዋ የኃይልና የጉልበት ምሳሌ በሆነው በቀኝ እጁ እርምጃ ሊወስድ እንደተዘጋጀ እንመለከታለን።

7. የአምላክ የድል ግስጋሴ በእርሱ ላይ ለሚያምፁት ምን ማለት ይሆናል?

7 የአምላክ የድል ግስጋሴ በእርሱ ላይ ለሚያምፁ ጥፋት ማለት ነው። ዕንባቆም 3:​5 እንዲህ ይላል:- “ቸነፈር በፊቱ ይሄዳል፣ የእሳትም ነበልባል ከእግሩ ይወጣል።” እስራኤላውያን ወደ ተስፋይቱ ምድር ዳርቻ ቀርበው በነበረበት በ1473 ከዘአበ ብዙዎች ዝሙት በመፈጸምና ጣዖት በማምለክ በአምላክ ላይ ዓምፀዋል። በዚህም ምክንያት ከ20, 000 የሚበልጡ ሰዎች ከአምላክ በተላከ ቸነፈር ተገድለዋል። (ዘኁልቁ 25:​1-9) በቅርቡ ይሖዋ “ሁሉን በሚችለው አምላክ ታላቅ የጦርነት ቀን” በሚዘምትበት ጊዜ በእርሱ ላይ የሚያምፁ ሁሉ በተመሳሳይ የኃጢአታቸውን ብድራት ያገኛሉ። እንዲያውም አንዳንዶቹ ቃል በቃል በቸነፈር ሊመቱ ይችላሉ።​—⁠ራእይ 16:​14, 16

8. በ⁠ዕንባቆም 3:​6 መሠረት የአምላክ ጠላቶች ምን ይጠብቃቸዋል?

8 አሁን የሠራዊት ጌታ ይሖዋ የሚያደርገውን ነቢዩ በሥዕላዊ ቃላት ሲገልጽ እንስማ። ዕንባቆም 3:​6 ላይ እንዲህ እናነባለን:- “[ይሖዋ አምላክ] ቆመ፣ ምድርንም አወካት፤ ተመለከተ፣ አሕዛብንም አናወጠ፤ የዘላለም ተራሮች ተቀጠቀጡ፣ የዘላለምም ኮረብቶች ቀለጡ፣ መንገዱ ከዘላለም ነው።” በመጀመሪያ ይሖዋ የጦር ሜዳውን እንደሚቃኝ ጄኔራል ‘ቀጥ ብሎ ይቆማል።’ ጠላቶቹ በፍርሃት ይንቀጠቀጣሉ። የተቃወማቸው ማን እንደሆነ ይመለከቱና ደንግጠው በፍርሃት ይዘላሉ። ኢየሱስ “የምድር ወገኖች ሁሉ ዋይ ዋይ” የሚሉበት ጊዜ እንደሚመጣ ትንቢት ተናግሯል። (ማቴዎስ 24:​30) ምንም ማድረግ በማይችሉበት ጊዜ ይሖዋን ማንም ሊቃወም እንደማይችል ይገነዘባሉ። እንደ ‘ዘላለም ተራሮች’ ወይም እንደ ‘ዘላለም ኮረብቶች’ የማይናወጡ መስለው ይታዩ የነበሩ ሰብዓዊ ድርጅቶች ፍርስርሳቸው ይወጣል። በዚህ ጊዜ ‘ከዘላለም እንደነበረው’ የአምላክ መንገድ ይሆናል። ማለትም ጥንት እንዳደረገው ያደርጋል።

9, 10. በ⁠ዕንባቆም 3:​11-17 ላይ የተመዘገቡት ነገሮች ምን ያስታውሱናል?

9 ይሖዋ በጠላቶቹ ላይ ‘ተቆጥቶአል።’ ይሁን እንጂ በታላቁ ጦርነቱ ወቅት የሚጠቀምባቸው የጦር መሣሪያዎች ምን ይሆናሉ? ነቢዩ የሚሰጠውን መግለጫ አዳምጡ:- “በቃልህ እንደ ማልህ መቅሠፍትህን አወጣህ፤ ቀስትህንም ገተርህ፤ ምድርን ሰንጥቀህ ፈሳሾችን አወጣህ። ተራሮች አንተን አይተው ተጨነቁ፤ የውኃ ሞገድ አልፎአል፤ ቀላዩም ድምፁን ሰጥቶአል፣ እጁንም ወደ ላይ አንሥቶአል። ፍላጾችህ ከወጡበት ብርሃን የተነሣ፣ ከሚንቦገቦገውም ከጦርህ ፀዳል የተነሣ፣ ፀሐይና ጨረቃ በመኖሪያቸው ቆሙ።”​—⁠ዕንባቆም 3:​7-11

10 በኢያሱ ዘመን ይሖዋ ፀሐይና ጨረቃ ቀጥ ብለው እንዲቆሙ በማድረግ የኃይሉን ታላቅነት በአስደናቂ ሁኔታ አሳይቷል። (ኢያሱ 10:​12-14) ይሖዋ ይህንኑ ኃይሉን በአርማጌዶን እንደሚጠቀምበት የዕንባቆም ትንቢት ያስታውሰናል። ይሖዋ በ1513 ከዘአበ በቀይ ባሕር ተጠቅሞ የፈርኦንን ሠራዊት ባጠፋ ጊዜ በምድር ቀላያት ላይ ያለውን ሥልጣን አሳይቷል። ይህ ከሆነ ከአርባ ዓመት በኋላ እስከ አፉ ጢም ብሎ ይጎርፍ የነበረው የዮርዳኖስ ወንዝ እስራኤላውያን ወደ ተስፋይቱ ምድር በድል አድራጊነት እንዳይገቡ ለማገድ ሳይችል ቀርቷል። (ኢያሱ 3:​15-17) በነቢይቱ ዲቦራ ዘመን የወረደው ኃይለኛ ዝናብ የእስራኤላውያን ጠላት የነበረውን የሲሳራን የጦር ሠረገሎች ጠራርጎ ወስዷል። (መሳፍንት 5:​21) ይሖዋ በአርማጌዶን ጦርነትም በእነዚሁ ኃይሎች ማለትም በጎርፍ፣ በኃይለኛ ዝናብና በጥልቅ ባሕሮች በተመሳሳይ ሁኔታ ሊጠቀም ይችላል። በተጨማሪም ነጎድጓድና መብረቅ በእጁ እንዳለ ጦር ወይም በፍላጻዎች እንደተሞላ ኮሮጆ ናቸው።

11. ይሖዋ ታላቅ ኃይሉን ሲጠቀም ውጤቱ ምን ይሆናል?

11 በእርግጥም ይሖዋ ታላቅ ኃይሉን በሚሰነዝርበት ጊዜ በጣም የሚያስፈራ ይሆናል። ሌሊቱ ወደ ቀን እንደሚለወጥና ቀኑ ደግሞ ከፀሐይ ብርሃን እጅግ የደመቀ እንደሚሆን የዕንባቆም ቃላት ያመለክታሉ። ይህ ስለ አርማጌዶን በመንፈስ አነሳሽነት የተነገረው ትንቢታዊ መግለጫ ምሳሌያዊም ሆነ ቃል በቃል የሚፈጸም አንድ ነገር የተረጋገጠ ነው። ይሖዋ ድል ያደርጋል፣ ከጠላቶቹ አንዱም ቢሆን ሊያመልጥ አይችልም።

የአምላክ ሕዝቦች የተረጋገጠ መዳን!

12. አምላክ በጠላቶቹ ላይ ምን እርምጃ ይወስዳል? ይሁን እንጂ እነማን ይድናሉ?

12 ነቢዩ፣ ይሖዋ በጠላቶቹ ላይ ስለሚያመጣው ጥፋት የሚሰጠውን መግለጫ ይቀጥላል። ዕንባቆም 3:​12 ላይ እንዲህ እናነባለን:- “በምድር ላይ በመዓት ተራመድህ፤ አሕዛብን በቁጣ አሄድሃቸው።” ቢሆንም ይሖዋ በጅምላ አያጠፋም። የሚድኑ ሰዎች ይኖራሉ። ዕንባቆም 3:​13 “ሕዝብህን ለመታደግ፣ የቀባኸውንም ለማዳን ወጣህ” ይላል። አዎን፣ ይሖዋ የታመኑ ቅቡዓን አገልጋዮቹን ያድናል። በዚያን ጊዜ የዓለም የሐሰት ሃይማኖት ግዛት የሆነችው የታላቂቱ ባቢሎን ጥፋት ሙሉ በሙሉ ይጠናቀቃል። ዛሬ ግን ብሔራት ንጹሑን አምልኮ ከምድር ገጽ ለማጥፋት እየሞከሩ ነው። በቅርቡ የይሖዋ አገልጋዮች በማጎግ ጎግ ጭፍሮች ጥቃት ይደርስባቸዋል። (ሕዝቅኤል 38:​1–39:​13፤ ራእይ 17:​1-5, 16-18) ታዲያ ይህ ሰይጣናዊ ጥቃት ይሳካ ይሆን? በፍጹም አይሳካም! ይህን በሚያደርጉበት ጊዜ ይሖዋ ጠላቶቹን በቁጣ ተነስቶ በውድማ ላይ እንዳለ እህል በእግሩ ያደቃቸዋል። በመንፈስና በእውነት የሚያመልኩትን ግን ያድናል።​—⁠ዮሐንስ 4:​24

13. ዕንባቆም 3:​13 ፍጻሜውን የሚያገኘው እንዴት ነው?

13 በክፉዎች ላይ የሚደርሰው ፍጹም ጥፋት በሚከተሉት ቃላት ተገልጸዋል:- “[ይሖዋ፣ አንተ] የኃጢአተኛውን ቤት ራስ ቀጠቀጥህ፤ መሠረቱን እስከ አንገቱ ድረስ ገለጥህ።” (ዕንባቆም 3:​13) ይህ “ቤት” በሰይጣን ዲያብሎስ ቁጥጥር የተቋቋመው ክፉ ሥርዓት ነው። ሙሉ በሙሉ ይወድማል። ‘ራሱ’ ወይም ፀረ አምላክ የሆኑ መሪዎች ይቀጠቀጣሉ። መላው መዋቅር ከአናት እስከ መሠረቱ ይደረመሳል። ከዚያ በኋላ ሊኖር አይችልም። እንዴት ያለ እፎይታ ይሆናል!

14-16. በ⁠ዕንባቆም 3:​14, 15 መሠረት የይሖዋ ሕዝቦችና ጠላቶቻቸው ምን ይደርስባቸዋል?

14 በአርማጌዶን ጦርነት የይሖዋን “ቅቡዕ” ለማጥፋት የሚሞክሩ ሁሉ በትልቅ ግራ መጋባት ውስጥ ይወድቃሉ። በዕንባቆም 3:​14, 15 መሠረት ነቢዩ ለአምላክ እንዲህ ይላል:- “የአለቆችን ራስ በገዛ በትራቸው ወጋህ፤ እኔን ይበትኑ ዘንድ እንደ ዐውሎ ነፋስ መጡ፤ ችግረኛውን [“የተጠቃውን፣” NW  ] በስውር ለመዋጥ ደስታቸው ነው። ፈረሶችህን በባሕር፣ በብዙ ውኆችም ላይ አስረገጥህ።”

15 ዕንባቆም “[አለቆች] እኔን ይበትኑ ዘንድ እንደ ዐውሎ ነፋስ መጡ” ያለው ስለ ይሖዋ ቅቡዓን አገልጋዮች ነው። ብሔራት መንገድ ላይ አድፍጠው እንደሚዘርፉ ሽፍቶች ይሖዋን የሚያመልኩትን ለማጥፋት ይነሣሉ። እነዚህ የአምላክና የሕዝቡ ጠላቶች እንደሚሳካላቸው በመተማመን ‘ደስ ይሰኛሉ።’ ታማኝ ክርስቲያኖች እንደ ‘ተጠቃ’ ሰው ደካማ መስለው ይታያሉ። ፀረ አምላክ ኃይሎች ጥቃታቸውን መሰንዘር በሚጀምሩበት ጊዜ ግን ይሖዋ በገዛ ራሳቸው መሣሪያ እንዲጠፉ ያደርጋል። የገዛ ራሳቸውን መሣሪያ ወይም “በትር” በራሳቸው ተዋጊዎች ላይ ያነጣጥራሉ።

16 ይሁን እንጂ በቅርቡ የሚከናወን ተጨማሪ ነገር አለ። ይሖዋ ከሰብዓውያን የበለጠ ኃይል ባላቸው መንፈሳዊ ኃይሎች በመጠቀም በጠላቶቹ ላይ የሚያደርሰውን ጥፋት ወደ ፍጻሜ ያመጣል። በኢየሱስ ክርስቶስ በሚመሩት የሰማያዊ ጭፍሮቹ “ፈረሶች” ‘በባሕሩና በብዙ ወኆች’ ላይ ማለትም ተነዋዋጭ በሆኑት ሰብዓውያን ጠላቶቹ ላይ በድል አድራጊነት ይዘምታል። (ራእይ 19:​11-21) በዚያ ጊዜ ክፉዎች ከምድር ላይ ይወገዳሉ። እንዴት ያለ ታላቅ የመለኮታዊ ኃይልና ፍትሕ መግለጫ ነው!

የይሖዋ ቀን ቀርቧል!

17. (ሀ) ዕንባቆም የተናገራቸው ቃላት ፍጻሜያቸውን ያገኛሉ የሚል ትምክህት ሊኖረን የሚችለው ለምንድን ነው? (ለ) የይሖዋን ታላቅ ቀን ስንጠባበቅ የዕንባቆም ዓይነት ዝንባሌ ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?

17 የዕንባቆም ቃላት በቅርቡ ፍጻሜያቸውን እንደሚያገኙ እርግጠኞች ልንሆን እንችላለን። አይዘገዩም። ይህን በማወቅህ አንተ በግልህ እንዴት ይሰማሃል? ዕንባቆም የጻፈው በመንፈስ ተመርቶ እንደነበረ አስታውስ። ይሖዋ እርምጃ ይወስዳል፣ ይህ በሚሆንበት ጊዜ ደግሞ በምድር ላይ ትልቅ ትርምስ ይፈጠራል። ነቢዩ እንደሚከተለው ማለቱ አያስደንቅም:- “እኔ ሰምቻለሁ፣ ልቤም ደነገጠብኝ፤ ከድምፁ የተነሣ ከንፈሮቼ ተንቀጠቀጡ፤ መንቀጥቀጥ ወደ አጥንቶቼ ውስጥ ገባ፤ በስፍራዬ ሆኜ ተናወጥሁ፤ በሚያስጨንቁን ሕዝብ ላይ እስኪመጣ ድረስ የመከራን ቀን ዝም ብዬ እጠብቃለሁ።” (ዕንባቆም 3:​16) ዕንባቆም መረበሹ የሚጠበቅ ነገር ነው። ግን እምነቱ ተናውጧል? በምንም ዓይነት! የይሖዋን ታላቅ ቀን ዝም ብሎ ለመጠበቅ ፈቃደኛ ነበር። (2 ጴጥሮስ 3:​11, 12) የእኛስ ዝንባሌ ይህ አይደለምን? ምንም ጥርጥር የለውም! የዕንባቆም ትንቢት እንደሚፈጸም ሙሉ እምነት አለን። እስከዚያ ጊዜ ድረስ ግን በትዕግሥት እንጠብቃለን።

18. ዕንባቆም መከራ እንደሚመጣ ቢጠብቅም ምን ዓይነት ዝንባሌ ነበረው?

18 ጦርነት በድል አድራጊዎቹ ላይ ሳይቀር ችግርና መከራ ያስከትላል። የምግብ እጥረት ሊያጋጥም፣ ንብረት ሊወድም ይችላል። የኑሮ ደረጃ ዝቅ ሊል ይችላል። እንዲህ ያለው ሁኔታ በእኛ ላይ ቢደርስ ምን ይሰማናል? ዕንባቆም እንደሚከተለው በማለት ጥሩ ምሳሌ የሚሆን ዝንባሌ አሳይቷል:- “ምንም እንኳ በለስም ባታፈራ፣ በወይንም ሐረግ ፍሬ ባይገኝ፣ የወይራ ሥራ ቢጎድል፣ እርሾችም መብልን ባይሰጡ፣ በጎች ከበረቱ ቢጠፉ፣ ላሞችም በጋጡ ውስጥ ባይገኙ፣ እኔ ግን በእግዚአብሔር ደስ ይለኛል። በመድኃኒቴ አምላክ ሐሤት አደርጋለሁ።” (ዕንባቆም 3:​17, 18) ዕንባቆም መከራ፣ ምናልባትም ረሐብ እንደሚደርስ ጠብቋል። ቢሆንም መዳን በሚያገኝበት በይሖዋ መደሰቱን አላቆመም።

19. ብዙ ክርስቲያኖች ምን መከራ አለባቸው? ይሁን እንጂ በሕይወታችን ውስጥ ለይሖዋ አንደኛውን ቦታ ከሰጠነው ስለ ምን ነገር እርግጠኞች መሆን እንችላለን?

19 ዛሬም፣ ይሖዋ በክፉዎች ላይ የሚያደርገው ጦርነት ገና ከመጀመሩ በፊት እንኳን በከባድ ችግር ውስጥ የሚኖሩ ብዙዎች ናቸው። ኢየሱስ በንጉሣዊ ክብር ‘መገኘቱን ከሚያሳዩት ምልክቶች’ መካከል ጦርነት፣ ረሐብ፣ የምድር መናወጥና ቸነፈር እንደሚኖር ተንብዮአል። (ማቴዎስ 24:​3-14፤ ሉቃስ 21:​10, 11) በርካታ የእምነት ባልደረቦቻችን በኢየሱስ ትንቢት መፈጸም ምክንያት ብዙ ጉዳት በደረሰባቸው አገሮች ስለሚኖሩ በዚሁ ምክንያት ብዙ መከራ ይደርስባቸዋል። ሌሎቹ ደግሞ ወደፊት ተመሳሳይ መከራ ይደርስባቸው ይሆናል። ለብዙዎቻችን ከመጨረሻው ቀን በፊት ‘በለስ አያፈራልን’ ይሆናል። ይሁን እንጂ እነዚህ ነገሮች የሚሆኑበትን ምክንያት እናውቃለን። ይህ ደግሞ ኃይል ይሰጠናል። ከዚህም በላይ ብቻችንን አልተተውንም። ኢየሱስ “ነገር ግን አስቀድማችሁ የእግዚአብሔርን መንግሥት ጽድቁንም ፈልጉ፣ ይህም ሁሉ ይጨመርላችኋል” በማለት ቃል ገብቶልናል። (ማቴዎስ 6:​33) ይህ ከችግር ነፃ የሆነ ኑሮ እንደምንኖር ዋስትና የሚሰጥ ባይሆንም በሕይወታችን ይሖዋን ብናስቀድም እንደሚጠብቀንና እንደሚያስብልን ዋስትና ይሰጠናል።​—⁠መዝሙር 37:​25

20. ጊዜያዊ መከራ ቢኖርብንም ቁርጥ ውሳኔያችን ምን ለማድረግ መሆን ይኖርበታል?

20 ስለዚህ ምንም ዓይነት ጊዜያዊ መከራ ቢደርስብን በይሖዋ የማዳን ኃይል ያለንን እምነት አናጣም። በአፍሪካ፣ በምሥራቅ አውሮፓና በሌሎች አገሮች የሚኖሩ ብዙ ወንድሞቻችን የሚኖሩት በከባድ መከራ ውስጥ ቢሆንም ‘በይሖዋ መደሰታቸውን አላቆሙም።’ እኛም እንደነርሱ ማድረጋችንን አናቁም። ‘የኃይላችን’ ምንጭ ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ እንደሆነ አስታውስ። (ዕንባቆም 3:​19) ፈጽሞ አይተወንም። አርማጌዶን መምጣቱ አይቀርም፣ አምላክ ቃል የገባለት አዲስ ዓለም ደግሞ ተከትሎት እንደሚመጣ የተረጋገጠ ነው። (2 ጴጥሮስ 3:​13) በዚያ ጊዜ “ውኃ ባሕርን እንደሚከድን ምድር የእግዚአብሔርን ክብር በማወቅ ትሞላለች።” (ዕንባቆም 2:​14) ያ አስደናቂ ጊዜ እስኪደርስ ግን የዕንባቆምን አርዓያ እንከተል። ‘አዳኛችን በሆነው አምላክ በይሖዋ መደሰታችንን እንቀጥል።’

ታስታውሳለህን?

• የዕንባቆም ጸሎት ሊነካን የሚችለው እንዴት ነው?

• ይሖዋ እየገሰገሰ ያለው እንዴት ነው?

• የዕንባቆም ትንቢት ስለ መዳን ምን ይላል?

• የይሖዋን ታላቅ ቀን መጠባበቅ ያለብን ምን ዓይነት ዝንባሌ በመያዝ ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አምላክ በአርማጌዶን ወቅት በክፉዎች ላይ ምን ኃይል እንደሚጠቀም ታውቃለህ?