በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ክፉዎች የቀራቸው ጊዜ ምን ያህል ነው?

ክፉዎች የቀራቸው ጊዜ ምን ያህል ነው?

ክፉዎች የቀራቸው ጊዜ ምን ያህል ነው?

“[ይሖዋ] ኃጢአተኛውስ ከእርሱ ይልቅ ጻድቅ የሆነውን ሲውጠው ስለ ምን ዝም ትላለህ?”​—⁠ዕንባቆም 1:​13

1. ምድር ከዳር እስከ ዳር የይሖዋን ክብር በማወቅ የምትሞላው መቼ ነው?

 አምላክ ክፉዎችን የሚያጠፋበት ጊዜ ይመጣ ይሆን? የሚመጣ ከሆነስ የምንጠብቀው እስከ መቼ ነው? በመላው ምድር ላይ የሚኖሩ ሰዎች እንደነዚህ ያሉትን ጥያቄዎች ይጠይቃሉ። ታዲያ መልሱን ከየት ማግኘት እንችላለን? በተቀጠረው ዘመን ስለሚፈጸሙ ነገሮች ከተነገሩት በመለኮታዊ መሪነት የተጻፉ ትንቢታዊ ቃላት መልሱን ማግኘት እንችላለን። እነዚህ ትንቢታዊ ቃላት ይሖዋ በቅርብ ጊዜ ውስጥ በክፉዎች ሁሉ ላይ የቅጣት ፍርድ እንደሚፈጽም ያረጋግጣሉ። “ውኃ ባሕርን እንደሚከድን ምድር የእግዚአብሔርን ክብር በማወቅ” የምትሞላው ይህ ከሆነ በኋላ ብቻ ነው። ይህ የተስፋ ቃል የሚገኘው በአምላክ ቅዱስ ቃል በዕንባቆም 2:​14 ላይ ነው።

2. በዕንባቆም መጽሐፍ ውስጥ ተመዝግበው የሚገኙት ሦስቱ መለኮታዊ የቅጣት ፍርዶች ምንድን ናቸው?

2 የዕንባቆም መጽሐፍ የተጻፈው በ628 ከዘአበ ገደማ ሲሆን ይሖዋ አምላክ የሚያስፈጽማቸው ሦስት ተከታታይ የቅጣት ፍርዶች ተመዝግበውበታል። ከእነዚህ ፍርዶች መካከል ሁለቱ ተፈጽመዋል። የመጀመሪያው ይሖዋ በዓመፀኛው የጥንቱ የይሁዳ ብሔር ላይ የተናገረው ፍርድ ነው። ሁለተኛውስ? በጨቋኟ ባቢሎን ላይ የወረደው የአምላክ የቅጣት ፍርድ ነው። ስለዚህ ሦስተኛውም መለኮታዊ ፍርድ መፈጸሙ እንደማይቀር እርግጠኞች የምንሆንበት በቂ ምክንያት አለን ማለት ነው። እንዲያውም ይህ ፍርድ በቅርቡ ይፈጸማል ብለን መጠበቅ እንችላለን። አምላክ በዚህ የመጨረሻ ቀን ለሚኖሩ ቅን ሰዎች ሲል በክፉዎች ሁሉ ላይ ጥፋት ያመጣል። በፍጥነት እየገሰገሰ የሚመጣው “ሁሉን የሚችል አምላክ የጦርነት ቀን” [NW ] የመጨረሻው ዓመፀኛ ከሕልውና ውጭ የሚሆንበት ጊዜ ይሆናል።​—⁠ራእይ 16:​14, 16

3. በዘመናችንም ያሉ ክፉዎች ምን ነገር እንደሚገጥማቸው የተረጋገጠ ነው?

3 የአምላክ ታላቅ የጦርነት ቀን ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ቀርቧል። በዘመናችን ባሉት ክፉዎች ላይ የሚፈጸመው መለኮታዊ ፍርድ በይሁዳም ሆነ በባቢሎን ላይ የተፈጸመውን ፍርድ ያህል የማይቀርና የተረጋገጠ ነው። አሁን ግን በይሁዳ ምድር በዕንባቆም ዘመን እንዳለን አድርገን ለምን አናስብም? በዚያች ምድር ምን እየተደረገ ነው?

ቀውጢ የሆነ ምድር

4. ዕንባቆም ምን አስደንጋጭ መልእክት ደረሰው?

4 የይሖዋ ነቢይ የሆነው ዕንባቆም የምሽቱን ቀዝቃዛ አየር እየተነፈሰ በቤቱ ሰገነት ላይ እንደ ተቀመጠ አድርገህ በዓይነ ሕሊናህ ተመልከት። አጠገቡ የሙዚቃ መሣሪያውን አስቀምጧል። (ዕንባቆም 1:​1፤ 3:​19፣ የመጽሐፉ መግለጫ NW ) ይሁን እንጂ ዕንባቆም ንጉሥ ኢዮአቄም ነቢዩን ኦርዮን አስገድሎ አስከሬኑን ክቡራን ባልሆኑ ሰዎች መቃብር እንደጣለው የሚገልጽ አስደንጋጭ ዜና ደረሰው። (ኤርምያስ 26:​23) ኦርዮ በፍርሃት ወደ ግብፅ ሸሽቶ ስለነበር በይሖዋ ላይ የነበረውን ትምክህት አጥፍቶ እንደነበር ምንም አይካድም። ይሁንና ኢዮአቄም ይህንን ዓመፅ የፈጸመው የይሖዋን ክብር ለማስጠበቅ እንዳልሆነ ዕንባቆም ያውቃል። ንጉሡ ለመለኮታዊው ሕግ ካሳየው ፍጹም ንቀት እና ለነቢዩ ኤርምያስም ሆነ ይሖዋን ለሚያገለግሉ ለሌሎች ሰዎች ከነበረው ጥላቻ ይህንን በግልጽ መረዳት ይቻላል።

5. በይሁዳ የነበረው መንፈሳዊ ሁኔታ ምን ይመስላል? የዕንባቆምስ ምላሽ ምን ነበር?

5 ዕንባቆም በአካባቢው ከሚገኙት ቤቶች የሚወጣውን የእጣን ጭስ ይመለከታል። ሰዎቹ ይህን እጣን የሚያጨሱት ይሖዋን ለማምለክ አልነበረም። ክፉው የይሁዳ ንጉሥ ኢዮአቄም ያስፋፋ የነበረውን የሐሰት አምልኮ መፈጸማቸው ነበር። እንዴት ያለ የሚያሳፍር ነገር ነው! ዕንባቆም ዓይኖቹ እንባ አቅርረው እንዲህ በማለት ተማጸነ:- “አቤቱ፣ እኔ ስጮኽ የማትሰማው እስከ መቼ ነው? ስለ ግፍ ወደ አንተ እጮኻለሁ፣ አንተም አታድንም። በደልንስ ስለምን አሳየኸኝ? ጠማምነትንስ ስለ ምን ትመለከታለህ? ጥፋትና ግፍ በፊቴ ነው፤ ጠብና ክርክር ይነሣሉ። ስለዚህ ሕግ ላልቶአል፣ ፍርድም ድል ነሥቶ አይወጣም፣ ኃጢአተኛ ጻድቅን ይከብባልና፤ ስለዚህ ፍርድ ጠማማ ሆኖ ይወጣል።”​—⁠ዕንባቆም 1:​2-4

6. በይሁዳ ሕግም ሆነ ፍትሕ ምን ሆኖ ነበር?

6 አዎን፣ ብዝበዛና ግፍ ተስፋፍቷል። ዕንባቆም በዞረበት ሁሉ ከመከራ፣ ከጠብና ከክርክር ሌላ ነገር አያይም። “ሕግ ላልቶአል” ወይም ኃይል አጥቷል። ፍትሕስ? “ድል ነሥቶ አይወጣም።” አሸናፊ አይሆንም። ከዚህ ይልቅ ‘ክፉዎች’ ንጹሐን ሰዎችን ለመጠበቅ ታስበው የወጡ ሕጋዊ እርምጃዎችን በማጣመም ‘ጻድቁን ይከብባሉ።’ በእርግጥም “ፍርድ ጠማማ” ሆኗል። ተበላሽቷል። እንዴት ያለ አሳዛኝ ሁኔታ ነው!

7. ዕንባቆም ምን ለማድረግ ቆርጧል?

7 ዕንባቆም ቆም ብሎ ሁኔታውን ያሰላስላል። ተስፋ ቆርጦ ይተው ይሆን? በፍጹም አያደርገውም! በአምላክ የታመኑ አገልጋዮች ላይ የደረሰውን ስደት በሙሉ በሐሳቡ ካውጠነጠነ በኋላ ይህ ታማኝ ሰው በይሖዋ ነቢይነቱ ጸንቶ ለመቆም ያደረገውን ቁርጥ ውሳኔ ያድሳል። ዕንባቆም ሞት የሚያስከትልበት ቢሆን እንኳን የአምላክን መልእክት ማወጁን ይቀጥላል።

ይሖዋ ለማመን የሚያዳግት “ሥራ” ይሠራል

8, 9. ይሖዋ የሚያከናውነው ለማመን የሚያዳግት “ሥራ” ምንድን ነው?

8 ዕንባቆም አምላክን የሚያዋርዱትን ሐሰተኛ ሃይማኖተኞች በራእይ ተመልክቷል። ይሖዋ ምን እንደሚላቸው አዳምጡ:- “እናንተ የምትንቁ ሆይ፣ . . . እዩ፣ ተመልከቱ፣ ተደነቁ።” አምላክ ለእነዚህ ክፉ ሰዎች ለምን እንዲህ እንዳለ ዕንባቆም ሳይገርመው አይቀርም። ወዲያው ግን ይሖዋ “አንድ ቢተርክላችሁ ስንኳ የማታምኑትን ሥራ በዘመናችሁ እሠራለሁና” ሲላቸው ይሰማል። (ዕንባቆም 1:​5) እንዲያውም ‘ይህን ሊያምኑ የማይችሉትን ሥራ’ የሚሠራው ይሖዋ ራሱ ነው። ግን ይህ ሥራ ምንድን ነው?

9 ዕንባቆም በምዕራፍ 1:​6-11 ላይ የሚገኙትን ተጨማሪ ቃላት በትኩረት ያዳምጣል። ይህ መልእክት የራሱ የይሖዋ ስለሆነ ማንም የሐሰት አምላክ፣ ማንም በድን ጣዖት መልእክቱ እንዳይፈጸም ሊያግደው አይችልም። “እነሆ፣ የእነርሱ ያልሆነውን መኖሪያ ይወርሱ ዘንድ በምድር ስፋት ላይ የሚሄዱትን መራሮችንና ፈጣኖችን ሕዝብ ከለዳውያንን አስነሣለሁ። እነርሱ የሚያስፈሩና የሚያስደነግጡ ናቸው፤ ፍርዳቸውና ክብራቸው ከራሳቸው ይወጣል። ፈረሶቻቸውም ከነብር ይልቅ ፈጣኖች ናቸው፣ ከማታም ተኩላ ይልቅ ጨካኞች ናቸው፤ ፈረሰኞቻቸውም ይንሳፈፋሉ፣ ከሩቅም ይመጣሉ፣ ለመብልም እንደሚቸኩል ንስር ይበርራሉ። ሁሉም ለግፍ ሥራ ይመጣሉ፣ ፊታቸውንም እንደ ምሥራቅ ነፋስ ያቀናሉ፤ ምርኮኞችንም እንደ አሸዋ ይሰበስባሉ። በነገሥታት ላይ ያላግጣሉ፣ መሳፍንትም ዋዛ ሆነውላቸዋል፤ በምሽጉ ሁሉ ይስቃሉ፣ አፈሩንም ከምረው ይወስዱታል። የዚያን ጊዜም እንደ ነፋስ አልፎ ይሄዳል፣ ይበድልማል፣ ኃይሉንም አምላክ ያደርገዋል።”

10. ይሖዋ እነማንን አስነሣ?

10 ከልዑል አምላክ የተሰጠ እንዴት ያለ ትንቢታዊ ማስጠንቀቂያ ነው! ይሖዋ አረመኔውን የባቢሎን ብሔር፣ ከለዳውያንን ሊያስነሳባቸው ነው። ‘በምድር ስፋት’ ላይ በሚያደርገው ግስጋሴ ብዙ፣ ብዙ መኖሪያዎችን ይወርራል። እንዴት ያለ የሚያስፈራ ነገር ነው! የከለዳውያኑ ጭፍራ ‘የሚያስፈራና የሚያስደነግጥ’ በፍርሃት የሚያርድ ነው። ለራሱ የሚበጀውን ሊታጠፍ የማይችል ሕግ ያወጣል። ‘ፍርዳቸው ከራሳቸው ይወጣል።’

11. የባቢሎን ኃይል በይሁዳ ላይ ያደረገውን ዘመቻ እንዴት ትገልጸዋለህ?

11 የባቢሎን ፈረሶች ከነብር ይልቅ የፈጠኑ ናቸው። ፈረሰኞቹ በሌሊት ለአደን ከተሰማሩ የተራቡ ተኩላዎች ይበልጥ የሚያስፈሩ ናቸው። ለመሄድ እየተቁነጠነጡ ‘በኮቴያቸው መሬቱን ይቆፍራሉ።’ ሩቅ ከሆነው አገራቸው ከባቢሎን ተነስተው ወደ ይሁዳ ያቀናሉ። የሚጓጓለትን ምግብ ለማግኘት እንደሚበር ንሥር ከለዳውያን እንደ መብል በሆነላቸው ሕዝብ ላይ ድንገት ዘልለው ጉብ ይላሉ። ይህ ግን በጥቂት ወታደሮች ብቻ የሚደረግ ለአጭር ጊዜ የሚቆይ ወረራ ነውን? ፈጽሞ አይደለም! ምድሪቱን በሙሉ ለማውደም በጣም ትልቅ ሠራዊት ሆነው “ሁሉም ለግፍ ሥራ ይመጣሉ።” በጉጉት ስሜት ተውጠው እንደ ምሥራቅ ነፋስ በከፍተኛ ፍጥነት በስተ ምዕራብ ወደሚገኙት ወደ ይሁዳና ወደ ኢየሩሳሌም ይጋልባሉ። የባቢሎን ጭፍሮች በጣም ብዙ እስረኞችን ስለሚያግዙ ‘ምርኮኞችን እንደ ባሕር አሸዋ ይሰበስባሉ።’

12. የባቢሎናውያኑ ዝንባሌ ምን ነበር? ይህ የማይበገር ጠላት ‘በደለኛ’ ሆኖ የተገኘውስ እንዴት ነው?

12 አንዳቸውም ቢሆኑ የድል አድራጊነት ግስጋሴውን ሊገቱ ስላልቻሉ የከለዳውያኑ ጭፍራ በነገሥታት ላይ ይስቃል፣ በከፍተኛ ባለሥልጣኖችም ላይ ያላግጣል። ባቢሎናውያን ‘የአፈር ክምር’ ሠርተው ማጥቃት ሲጀምሩ ምሽግ የተባለው ሁሉ ወዲያው ስለሚፈርስ ‘በምሽጎች ሁሉ ላይ ይስቃል።’ ይህ የማይጋፉት ጠላት ይሖዋ በቀጠረው ቀን “እንደ ነፋስ ያልፋል።” በይሁዳና በኢየሩሳሌም ላይ ጥቃት ሲሰነዝር በአምላክ ሕዝቦች ላይ ጉዳት ማድረሱ ስለሆነ ‘በደል’ ይሆንበታል። የከለዳውያን ጦር አዛዥ እንደ አውሎ ነፋስ ፈጣን የሆነ ድል ከተቀዳጀ በኋላ ‘ይህን ኃይል ያገኘነው ከአምላካችን ነው’ ብሎ ይፎክራል። ግን ምንኛ ተሳስቷል!

ተስፋ ለማድረግ የሚያስችል ጠንካራ መሠረት

13. ዕንባቆም ተስፋና ትምክህት ሊኖረው የቻለው እንዴት ነው?

13 አሁን ዕንባቆም ስለ ይሖዋ ዓላማ ተጨማሪ እውቀት በማግኘቱ ተስፋው በልቡ ውስጥ ማደግ ጀመረ። በትምክህት ስለተሞላ ይሖዋን የሚያወድስ ቃል አሰማ። ነቢዩ በ⁠ዕንባቆም 1:​12 [NW ] ላይ ተመዝግቦ እንደሚገኘው “አቤቱ ይሖዋ፣ አንተ ከጥንት ጀምሮ ያለህ አይደለህምን? አቤቱ አምላኬና ቅዱሴ ሆይ፣ አንተ አትሞትም” አለ። በእርግጥም ይሖዋ አምላክ “ከዘላለም እስከ ዘላለም” ነው።​—⁠መዝሙር 90:​1, 2

14. ከሃዲዋ ይሁዳ ምን ዓይነት ጎዳና ተከትላለች?

14 ነቢዩ ከአምላክ የተቀበለውን ራእይ መለስ ብሎ በማሰብና ራእዩ ባስገኘለት ማስተዋል በመደሰት “አቤቱ ለፍርድ ሠርተኸዋል፣ ለተግሣጽም አድርገኸዋል” በማለት ይቀጥላል። አምላክ በከዳተኞቹ አይሁዳውያን ላይ የጥፋተኝነት ፍርድ ስለፈረደባቸው ከይሖዋ የሚመጣባቸውን ተግሳጽና ከባድ ቅጣት ሊቀበሉ ነው። እሱን አለታቸው፣ ብቸኛ ምሽጋቸው፣ መጠጊያቸውና መዳኛቸው ሊያደርጉ ይገባቸው ነበር። (መዝሙር 62:​7፤ 94:​22፤ 95:​1) ከዳተኞቹ የይሁዳ መሪዎች ግን ወደ አምላካቸው ከመቅረብ ይልቅ ማንንም የማይጎዱትን የይሖዋን አምላኪዎች መጨቆናቸውን ቀጠሉ።

15. የይሖዋ ‘ዓይኖች ክፉን እንዳያዩ ንጹሕ ናቸው’ የተባለው በምን መልኩ ነው?

15 ይህ ሁኔታ የይሖዋን ነቢይ በእጅጉ አሳዝኖታል። በዚህ ምክንያት “ዓይኖችህ ክፉ እንዳያዩ ንጹሐን ናቸው፣ ጠማምነትንም ትመለከት ዘንድ አትችልም” በማለት ተናገረ። (ዕንባቆም 1:​13) አዎን፣ በእርግጥም ‘የይሖዋ ዓይኖች በጣም ንጹሐን በመሆናቸው’ ጠማማነትን ሊመለከት ወይም በሌላ አባባል ክፉ አድራጎትን ዝም ብሎ ሊመለከት አይችልም።

16. በ⁠ዕንባቆም 1:​13-17 ላይ ተመዝግቦ የሚገኘውን ሐሳብ ጠቅለል አድርገህ የምትገልጸው እንዴት ነው?

16 ስለዚህም በዕንባቆም አእምሮ ውስጥ አሳሳቢ ጥያቄዎች ተቀሰቀሱ። እንዲህ ሲል ጠይቋል:- “አታላዮችንስ ለምን ትመለከታለህ? ኃጢአተኛውስ ከእርሱ ይልቅ ጻድቅ የሆነውን ሲውጠው ስለምን ዝም ትላለህ? ሰዎችንም እንደ ባሕር ዓሣዎች፣ አለቃም እንደሌላቸው ተንቀሳቃሾች ለምን ታደርጋቸዋለህ? ሁሉን በመቃጥን ያወጣል፣ በመረቡም ይይዛቸዋል፣ በአሽክላውም ውስጥ ያከማቻቸዋል፤ ስለዚህ ደስ እያለው እልል ይላል። እድል ፈንታው በእነርሱ ሰብታለችና፣ መብሉም በዝቶአልና ስለዚህ ለመረቡ ይሠዋል፣ ለአሽክላውም ያጥናል። ስለዚህ መረቡን ይጥላልን? አሕዛብንም ዘወትር ይገድል ዘንድ አይፈራምን?”​—⁠ዕንባቆም 1:​13-17

17. (ሀ) ባቢሎናውያን ይሁዳንና ኢየሩሳሌምን በማጥፋት የአምላክን ዓላማ ያስፈጸሙት እንዴት ነው? (ለ) ይሖዋ ለዕንባቆም የሚገልጽለት ነገር ምንድን ነው?

17 ባቢሎናውያን ይሁዳንና ዋና ከተማዋን ኢየሩሳሌምን የሚያጠቁት የራሳቸውን ፍላጎት ለማሟላት ነው። አምላክ ታማኝ ባልሆኑ ሕዝቦቹ ላይ የጽድቅ ፍርዱን እንዲፈጽሙ መሣሪያ አድርጎ እንደተጠቀመባቸው አያውቁም። ዕንባቆም አምላክ የቅጣት ፍርዱን ለማስፈጸም በክፉዎቹ ባቢሎናውያን የተጠቀመበትን ምክንያት ለመረዳት ለምን አስቸጋሪ ሆኖ እንዳገኘው ለመገንዘብ አያዳግትም። እነዚህ ጨካኝ ከለዳውያን የይሖዋ አምላኪዎች አይደሉም። የሰው ልጆችን ተጠምደው ከሚበሉ ‘ዓሣዎችና ተንቀሳቃሾች’ ለይተው አይመለከቱም። የዕንባቆም ግራ መጋባት ለረዥም ጊዜ አይቆይም። ይሖዋ ብዙም ሳይቆይ ባቢሎናውያን በስግብግብነት በመመዝበራቸውና በአሰቃቂ ሁኔታ ደም በማፍሰሳቸው ቅጣት መቀበላቸው እንደማይቀር ለነቢዩ ይገልጥለታል።​—⁠ዕንባቆም 2:​8

ይሖዋ የሚናገራቸውን ተጨማሪ ቃላት ለማዳመጥ መዘጋጀት

18. በ⁠ዕንባቆም 2:​1 ላይ ከተንጸባረቀው የነቢዩ አመለካከት ምን ትምህርት እናገኛለን?

18 አሁን ግን ዕንባቆም ይሖዋ የሚነግረውን ተጨማሪ ቃል ለማዳመጥ ይጠባበቃል። ነቢዩ በቁርጠኝነት “በመጠበቂያዬ ላይ እቆማለሁ፣ በአምባ ላይም እወጣለሁ፤ የሚናገረኝንም፣ ስለ ክርክሬም የምመልሰውን አውቅ ዘንድ እመለከታለሁ” ብሏል። (ዕንባቆም 2:​1) ዕንባቆም አምላክ እርሱን እንደ ነቢይ ተጠቅሞ የሚናገረውን ቃል ለመስማት በጣም ጓጉቷል። ዕንባቆም፣ ይሖዋ አምላክ ክፋትን የማይታገሥ አምላክ ስለመሆኑ ባለው እምነት ምክንያት ክፋት ለምን አሸንፎ እንደሚኖር ለመረዳት ቢቸገርም አስተሳሰቡን ለማስተካከል ዝግጁ ነው። እኛስ? አንዳንድ የክፋት ድርጊቶች ለምን ዝም ተብለው እንደሚታለፉ ለመረዳት በምንቸገርበት ጊዜ በይሖዋ አምላክ ጻድቅነት ላይ ያለን ትምክህት ሚዛናችንን እንዳናጣና እርሱን እንድንጠባበቅ ሊያደርገን ይገባል።​—⁠መዝሙር 42:​5, 11

19. አምላክ ለዕንባቆም በተናገረው ቃል መሠረት አስቸጋሪ በነበሩት አይሁዳውያን ላይ ምን ነገር ደረሰ?

19 አምላክ ለዕንባቆም የተናገረውን ቃል በመጠበቅ ባቢሎናውያን ይሁዳን እንዲወሩ በማድረግ ከመንገዳቸው የሳቱትን አይሁዳውያን ቀጥቷል። በ607 ከዘአበ ኢየሩሳሌምንና መቅደስዋን ካጠፉ በኋላ ሽማግሌ፣ ወጣት ሳይሉ ብዙዎቹን ገድለው ብዙዎችን ወደ ግዞት ወስደዋል። (2 ዜና መዋዕል 36:​17-20) ታማኝ አይሁዳውያን ቀሪዎች ከበርካታ ዓመታት የግዞት ኑሮ በኋላ ከባቢሎን ወደ ትውልድ አገራቸው ተመልሰው ቤተ መቅደሱን በድጋሚ ሠሩ። ይሁን እንጂ ከዚያም በኋላ ቢሆን አይሁዳውያኑ ለይሖዋ ታማኝ አልሆኑም። በተለይ የኢየሱስን መሲሕነት ለመቀበል እምቢተኞች በሆኑ ጊዜ ይህንኑ አቋማቸውን አንጸባርቀዋል።

20. ጳውሎስ ኢየሱስን አንቀበልም ማለታቸውን በማስመልከት ዕንባቆም 1:​5ን የተጠቀመበት እንዴት ነው?

20 በሐዋርያት ሥራ 13:​38-41 መሠረት ሐዋርያው ጳውሎስ በአንጾኪያ ይኖሩ ለነበሩ አይሁድ ኢየሱስን መካድና ቤዛዊ መሥዋዕቱን ማቃለል ምን ውጤት እንደሚያስከትል ተናግሯል። ጳውሎስ ዕንባቆም 1:​5ን ከግሪክኛው የሰፕቱጀንት ትርጉም ጠቅሶ እንዲህ በማለት አስጠነቀቀ:- “እንግዲህ:- እናንተ የምትንቁ፣ እዩ ተደነቁም ጥፉም፤ አንድ ስንኳ ቢተርክላችሁ የማታምኑትን ሥራ በዘመናችሁ እኔ እሠራለሁና ተብሎ በነቢያት የተነገረው እንዳይደርስባችሁ ተጠንቀቁ።” ጳውሎስ በጠቀሰው መሠረት የሮማ ሠራዊት በ70 እዘአ ኢየሩሳሌምንና ቤተ መቅደሷን ባጠፋ ጊዜ ዕንባቆም 1:​5 ለሁለተኛ ጊዜ ፍጻሜውን አግኝቷል።

21. አምላክ ባቢሎናውያንን በመጠቀም ኢየሩሳሌም እንድትጠፋ በማድረግ የሠራውን “ሥራ” በዕንባቆም ዘመን የነበሩት አይሁዳውያን የተመለከቱት እንዴት ነበር?

21 በዕንባቆም ዘመን ይኖሩ ለነበሩት አይሁዶች ባቢሎናውያን ኢየሩሳሌምን እንዲያጠፉ ያደረገው የአምላክ “ሥራ” ሊታሰብ የማይችል ነበር። ምክንያቱም ኢየሩሳሌም የይሖዋ አምልኮ የሚካሄድባትና ይሖዋ የቀባው ንጉሥ የሚቀመጥባት ከተማ ነበረች። (መዝሙር 132:​11-18) ከዚያ በፊት በኢየሩሳሌም ላይ ጥፋት ደርሶ አያውቅም። ቤተ መቅደሷ ተቃጥሎ አያውቅም። የዳዊት ተወላጆች ንጉሣዊ ዙፋን ተገልብጦ አያውቅም። ይሖዋ እንደነዚህ ያሉ ነገሮች እንዲፈጸሙ ይፈቅዳል ብሎ ማሰብ ፈጽሞ ሊታመን የማይችል ነገር ነበር። አምላክ ግን ይህን የመሰለ አስደንጋጭ ነገር እንደሚፈጸም በዕንባቆም በኩል አስጠነቀቀ። የተነገረውም ትንቢት በትክክል እንደተፈጸመ ታሪክ ያረጋግጣል።

አምላክ በዘመናችን የሚያከናውነው ለማመን የሚያዳግት “ሥራ”

22. ይሖዋ በዘመናችን የሚያከናውነው ለማመን የሚያዳግት “ሥራ” ምንድን ነው?

22 ዛሬም ይሖዋ ለማመን የሚያዳግት “ሥራ” ይሠራ ይሆን? ለተጠራጣሪዎች የማይታመን መስሎ ቢታይም ማድረጉ እንደማይቀር እርግጠኞች ሁኑ። በዚህ ወቅት ግን ይሖዋ የሚፈጽመው ለማመን የሚያዳግት ሥራ በሕዝበ ክርስትና ላይ የሚደርሰው ጥፋት ነው። ሕዝበ ክርስትና እንደ ጥንቷ ይሁዳ አምላክን አመልካለሁ ትበል እንጂ በእጅጉ ነቅዛለች። ይሖዋ በቅርብ ጊዜ ውስጥ እያንዳንዱ የሕዝበ ክርስትና ሃይማኖታዊ ርዝራዥ የሐሰት ሃይማኖት ግዛት ከሆነችው ‘ከታላቂቱ ባቢሎን’ ጋር ተጠራርጎ እንዲጠፋ ያደርጋል።​—⁠ራእይ 18:​1-24

23. የአምላክ መንፈስ ዕንባቆም ቀጥሎ ምን እንዲያደርግ አነሳስቶታል?

23 ኢየሩሳሌም በ607 ከዘአበ ከመጥፋቷ በፊት ይሖዋ ለዕንባቆም ያዘጋጀው ተጨማሪ ሥራ ነበር። አምላክ ለዚህ ነቢይ ምን የሚነግረው ነገር ይኖር ይሆን? ዕንባቆም የሙዚቃ መሣሪያውን አንስቶ ለይሖዋ የሐዘን እንጉርጉሮውን እንዲያሰማ የሚያነሳሳው ነገር ሊሰማ ነው። ከዚያ በፊት ግን የአምላክ መንፈስ ነቢዩ ትንቢታዊ ወዮታዎች እንዲያሰማ ይገፋፋዋል። በእርግጥ፣ እነዚህ አምላክ በቀጠረው ጊዜ ፍጻሜያቸውን እንደሚያገኙ የተነገረላቸው ትንቢታዊ ቃላት ያላቸውን ጥልቅ ትርጉም ማስተዋል እንፈልጋለን። እንግዲያስ የዕንባቆምን ትንቢት በትኩረት እንከታተል።

ታስታውሳለህ?

• በዕንባቆም ዘመን በይሁዳ የነበረው ሁኔታ ምን ይመስል ነበር?

• ይሖዋ በዕንባቆም ዘመን ያከናወነው ለማመን የሚያዳግት “ሥራ” ምን ነበር?

• ዕንባቆም ለተስፋ መሠረት የሚሆን ምን ነገር ነበረው?

• አምላክ በዘመናችን የሚያከናውነው ለማመን የሚያዳግት “ሥራ” ምንድን ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አምላክ ክፋት ሲስፋፋ እያየ ዝም ማለቱ ዕንባቆምን አስገርሞት ነበር። አንተንስ?

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ዕንባቆም ይሁዳ በባቢሎናውያን እጅ መከራ እንደምትቀምስ ተንብዮአል

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕ]

በአርኪኦሎጂ የተገኘው በ607 ከዘአበ የጠፋችው የኢየሩሳሌም ፍርስራሽ