ይሖዋ መጠጊያዬና ኃይሌ ነው
የሕይወት ታሪክ
ይሖዋ መጠጊያዬና ኃይሌ ነው
ማርሴል ፊልቶ እንደተናገረው
“እርሱን ካገባሽ መታሰርሽ አይቀርም።” ይህን ያሏት እኔ ላገባት አስቤ ለነበረችው ሴት ነው። እንዲህ ያሉበትን ምክንያት ልንገራችሁ።
በ1927 ስወለድ የካናዳ ግዛት የሆነችው ኪውቤክ የካቶሊክ እምነት ጠንካራ ይዞታ ነበረች። ከአራት ዓመት ገደማ በኋላ፣ የይሖዋ ምሥክሮች የሙሉ ጊዜ አገልጋይ የሆነችው ሴሲል ዱፈር በሞንትሪያል ከተማ ወደሚገኘው ቤታችን እየመጣች ታነጋግረን ጀመር። ከዚህ የተነሳ አብዛኛውን ጊዜ ጎረቤቶቻችን ይዝቱባት ነበር። እንዲያውም የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት በመስበኳ ምክንያት በተደጋጋሚ እስርና እንግልት ደርሶባታል። በመሆኑም ኢየሱስ “ስለ ስሜም በአሕዛብ ሁሉ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ” ሲል የተናገረው ቃል እውነት መሆኑን ለመገንዘብ ብዙ ጊዜ አልፈጀብንም።—ማቴዎስ 24:9
በዚያን ወቅት ብዙዎች ፈረንሳይኛ ተናጋሪ የሆነ አንድ ካናዳዊ ቤተሰብ የካቶሊክን እምነት ይተዋል ማለት የማይመስል ነገር እንደሆነ ይሰማቸው ነበር። ምንም እንኳ ወላጆቼ የይሖዋ ምሥክሮች ሳይሆኑ ቢቀሩም ብዙም ሳይቆይ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የምታስተምራቸው ትምህርቶች ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር እንደማይስማሙ ተረዱ። ስለዚህ ስምንት ልጆቻቸውን ምሥክሮቹ የሚያትሟቸውን ጽሑፎች እንድናነብ ያበረታቱን ነበር። እንዲሁም ለመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ቁርጥ ያለ አቋም ለወሰድነው ልጆች ድጋፍ ሰጥተውናል።
አስቸጋሪ በሆኑ ጊዜያት ጽኑ አቋም መያዝ
በ1942 ገና ተማሪ እያለሁ ለመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ልባዊ ፍላጎት ማሳደር ጀመርኩ። የይሖዋ ምሥክሮች የጥንቶቹ ክርስቲያኖች የተዉትን ምሳሌ በመከተል በብሔራት መካከል ይካሄድ በነበረው ጦርነት ስለማይካፈሉ በዚያን ወቅት ካናዳ ውስጥ ሥራቸው ታግዶ ኢሳይያስ 2:4፤ ማቴዎስ 26:52) ትልቁ ወንድሜ ሮላንድ በወቅቱ እየተካሄደ በነበረው የዓለም ጦርነት ለመሳተፍ ፈቃደኛ ባለመሆኑ የጉልበት ሥራ ወደሚሠራበት ካምፕ ተልኮ ነበር።
ነበር። (በዚህ ጊዜ አባዬ ጀርመናውያን ምሥክሮች አዶልፍ ሂትለር የሚያካሂደውን ወታደራዊ ዘመቻ ለመደገፍ ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ስለሚደርስባቸው ስቃይ የሚገልጽ አንድ በፈረንሳይኛ የታተመ መጽሐፍ ሰጠኝ። a ጽኑ አቋም በመያዝ ረገድ ምሳሌ ከሚሆኑ ከእነዚህ ደፋር ሰዎች አንዱ መሆኔን ለማሳወቅ ስለተነሳሳሁ በግል መኖሪያ ቤት ይደረጉ በነበሩት የይሖዋ ምሥክሮች ስብሰባዎች ላይ መገኘት ጀመርኩ። ብዙም ሳይቆይ በስብከቱ ሥራ እንድካፈል ግብዣ ቀረበልኝ። ግብዣውን የተቀበልኩት እስር ሊያጋጥመኝ እንደሚችል በመገንዘብ ነበር።
ድፍረት ለማግኘት ከጸለይኩ በኋላ የመጀመሪያዬን በር አንኳኳሁ። በሩን የከፈተችው አንዲት ደግ ወይዘሮ ነበረች። ራሴን ካስተዋወቅሁ በኋላ ‘የእግዚአብሔር መንፈስ ያለበት መጽሐፍ ሁሉ ጠቃሚ ነው’ የሚለውን በ2 ጢሞቴዎስ 3:16 ላይ የሚገኘውን ጥቅስ አነበብኩላት።
“ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ይበልጥ ማወቅ ይፈልጋሉ?” የሚል ጥያቄ አቀረብኩላት።
ሴትዬዋ “አዎ፣ እፈልጋለሁ” ስትል መለሰች።
በዚህ ጊዜ ከእኔ የተሻለ የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት ያላት ሴት ይዤ እንደምመጣ ነገርኳትና በሚቀጥለው ሳምንት አንዲት እህት ይዤ ሄድኩ። ከዚህ የመጀመሪያ ተሞክሮ በኋላ ይበልጥ ትምክህት ያዳበርኩ ሲሆን አገልግሎቱን የምናከናውነውም በራሳችን ኃይል እንዳልሆነ ተገነዘብኩ። ሐዋርያው ጳውሎስ እንደተናገረው አገልግሎቱን የምናከናውነው በይሖዋ እርዳታ ነው። በእርግጥም ‘የኃይሉ ታላቅነት ከእግዚአብሔር እንጂ ከእኛ እንዳልሆነ’ መገንዘባችን በጣም ወሳኝ ነው።—2 ቆሮንቶስ 4:7
ከዚህ በኋላ የስብከቱ ሥራውም ሆነ እስሩ ቋሚ የሕይወቴ ክፍል ሆነ። ለእጮኛዬ “እርሱን ያገባሽው እንደሆነ መታሰርሽ አይቀርም” ማለታቸው ምንም አያስደንቅም! ይሁን እንጂ እንዲህ ዓይነት አጋጣሚዎች ያን ያህል አስቸጋሪ አልነበሩም። ለአንድ ሌሊት እስር ቤት ካደርን በኋላ አብዛኛውን ጊዜ አንድ የይሖዋ ምሥክር ዋስ ሆኖ ያስፈታን ነበር።
ዓበይት ውሳኔዎች
ሚያዝያ 1943 ሕይወቴን ለይሖዋ መወሰኔን በውኃ ጥምቀት አሳየሁ። ከዚያም ነሐሴ 1944 በካናዳ ድንበር አቅራቢያ በሚገኘው በዩ ኤስ ኤ፣ ኒው ዮርክ፣ በፋሎ ለመጀመሪያ ጊዜ በአንድ ትልቅ የአውራጃ ስብሰባ ላይ ተገኘሁ። በስብሰባው ላይ 25, 000 ሰዎች ተገኝተው የነበረ ሲሆን ፕሮግራሙ አቅኚ (የሙሉ ጊዜ አገልጋይ የሆኑ የይሖዋ ምሥክሮች የሚታወቁበት ስም ነው) የመሆን ፍላጎት አሳደረብኝ። ካናዳ ውስጥ በይሖዋ ምሥክሮች ሥራ ላይ ተጥሎ የነበረው እገዳ ግንቦት 1945
የተነሳ ሲሆን እኔም በቀጣዩ ወር አቅኚነት ጀመርኩ።ይሁን እንጂ በአገልግሎቱ የማደርገው ተሳትፎ እየጨመረ ሲሄድ የዚያኑ ያህል በተደጋጋሚ ታሰርኩ። በአንድ ወቅት ለረጅም ጊዜ ይሖዋን በታማኝነት ካገለገለው ከማይክ ሚለር ጋር በአንድ ክፍል ውስጥ ታስሬ ነበር። የሲሚንቶ ወለሉ ላይ ቁጭ ብለን ተጨዋወትን። ያደረግነው ገንቢ የሆነ መንፈሳዊ ጭውውት ከፍተኛ ብርታት ሰጠኝ። በኋላ ላይ ግን ‘በመካከላችን አለመግባባት የነበረና እርስ በርሳችን የማንነጋገር ቢሆን ኖሮ ምን እንሆን ነበር?’ ብዬ ማሰብ ጀመርኩ። ከዚህ ውድ ወንድም ጋር በእስር ቤት ያሳለፍኩት ጊዜ በሕይወቴ ካገኘኋቸው እጅግ ጠቃሚ ትምህርቶች አንዱን አስተምሮኝ አልፏል። ይህም ወንድሞቻችን የግድ ስለሚያስፈልጉን እርስ በርሳችን ይቅር መባባልና ደጎች መሆን እንዳለብን ነው። ይህ ካልሆነ ግን ሐዋርያው ጳውሎስ “እርስ በርሳችሁ ብትነካከሱና ብትበላሉ እርስ በርሳችሁ እንዳትጠፋፉ ተጠንቀቁ” ሲል የገለጸው ነገር ሊደርስብን ይችላል።—ገላትያ 5:15
መስከረም 1945 ቤቴል ብለን በምንጠራው በካናዳ ቶሮንቶ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ቅርንጫፍ ቢሮ እንዳገለግል ግብዣ ቀረበልኝ። በቤቴል ያለው መንፈሳዊ ፕሮግራም የሚያንጽና እምነት የሚገነባ ነው። በሚቀጥለው ዓመት ከቅርንጫፍ ቢሮው በስተ ሰሜን ወደ 40 ኪሎ ሜትር ገደማ ላይ በሚገኘው የቤቴል እርሻ እንድሠራ ተመደብኩ። ከወጣቷ አን ዎሊኔክ ጋር እንጆሪ በምንለቅምበት ጊዜ አካላዊ ውበቷን ብቻ ሳይሆን ለይሖዋ የነበራትን ፍቅርና ቅንዓት ጭምር አስተዋልኩ። ከዚያም ተዋደድንና ጥር 1947 ላይ ተጋባን።
በቀጣዮቹ ሁለት ዓመታት ተኩል ጊዜ ውስጥ በለንደን፣ ኦንታሪዮና በኋላም ጉባኤ እንዲቋቋም እርዳታ ባበረከትንበት በኬፕ ብሪተን ደሴት በአቅኚነት አገለገልን። ከዚያም በ1949 ሚስዮናውያን ለመሆን ሥልጠና በወሰድንበት የጊልያድ የመጠበቂያ ግንብ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት 14ኛ ክፍል እንድንካፈል ግብዣ ቀረበልን።
በኪውቤክ ያከናወንነው ሚስዮናዊ አገልግሎት
በፊት ከተካሄዱት የጊልያድ ክፍሎች የተመረቁ ካናዳውያን የስብከቱን ሥራ በኪውቤክ እንዲጀምሩ በዚያ ተመድበው ነበር። በ1950 የ14ኛው ክፍል ተማሪዎች ከነበሩ ከሌሎች 25 ተመራቂዎች ጋር ሆነን ከእነርሱ ጋር ማገልገል ጀመርን። እያደገ የሄደው የሚስዮናውያን እንቅስቃሴ በሮማ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን መሪዎች ቆስቋሽነት ከፍተኛ ስደትና የሕዝብ ዓመፅ አስከተለ።
የመጀመሪያው ሚስዮናዊ ምድብ ቦታችን በሆነው በሮይን ከተማ ከደረስን ከሁለት ቀን በኋላ አን ተይዛ በአንድ የፖሊስ መኪና ውስጥ ከኋላ ተቀምጣ ነበር። የመጣችው እምብዛም ፖሊስ ከማይታይባት በካናዳ፣ ማኒቶባ ክልል ውስጥ ከምትገኝ ከአንዲት ትንሽ መንደር ስለነበር ይህ ለእርሷ አዲስ ነገር ነበር። በመሆኑም ፍርሃት አደረባት፤ “እርሱን ካገባሽ መታሰርሽ አይቀርም” ተብሎ የተነገራትም ትዝ አላት። ሆኖም መኪናውን አስነስተው ከመሄዳቸው በፊት ፖሊሶቹ እኔንም አገኙኝና ከአን ጋር መኪናው ውስጥ አስገቡኝ። “አንተን በማግኘቴ ደስ ብሎኛል!” አለች። ይሁን እንጂ “ሐዋርያትም ቢሆን ስለ ኢየሱስ በመስበካቸው ይኸው ደርሶባቸዋል” ብላ በማስታወስ መረጋጋቷ የሚያስደንቅ ነው። (ሥራ 4:1-3፤ 5:17, 18) የዚያን ዕለት ቆየት ብሎ በዋስ ተፈታን።
ይህ ከሆነ ከአንድ ዓመት ገደማ በኋላ አዲስ በተመደብንበት በሞንትሪያል ከቤት ወደ ቤት እያገለገልን ሳለ መንገድ ላይ የረብሻ ድምፅ ሰምቼ ዞር ስል በቁጣ የገነፈሉ ዓመፀኞች ድንጋይ ሲወረውሩ አየሁ። አንና የአገልግሎት ጓደኛዋን ለመርዳት ወደዚያው ሳመራ ፖሊሶች በቦታው ደረሱ። ፖሊሶቹ ዓመፅ የቀሰቀሱትን ሰዎች ከማሰር ይልቅ አንና ጓደኛዋን ያዟቸው! እስር ቤት እያሉ አን ለአዲሷ ምሥክር “በሁሉም ስለ ስሜ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ” የሚሉት የኢየሱስ ቃላት ሲፈጸሙ ማየታቸው እንደሆነ አስታወሰቻት።—ማቴዎስ 10:22
በአንድ ወቅት ኪውቤክ ውስጥ በይሖዋ ምሥክሮች ላይ የቀረቡ ወደ 1, 700 ገደማ ክሶች ውሳኔ ይጠብቁ ነበር። በአመዛኙ የሚቀርብብን ክስ ሕዝብን በመንግሥት ላይ የሚያነሳሱ ጽሑፎች ያሰራጫሉ ወይም ፈቃድ ሳይኖራቸው ጽሑፍ ያድላሉ የሚል ነበር። ከዚህ የተነሳ የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር የሕግ ክፍል በኪውቤክ መንግሥት ላይ የሕግ እርምጃ ወሰደ። ለዓመታት ከዘለቀ የሕግ ፍልሚያ በኋላ ይሖዋ በካናዳ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሁለት ታላላቅ ድሎች እንድናገኝ አስቻለን። በታኅሣሥ 1950 ጽሑፎቻችን በመንግሥት ላይ ዓመፅ ያነሳሳሉ ከሚለው ክስ ነፃ ሆንን። በጥቅምት 1953 ደግሞ ፈቃድ ሳይኖረን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን የማሰራጨት መብታችን ተከበረልን። በመሆኑም ይሖዋ መዝሙር 46:1
በእርግጥ “መጠጊያችንና ኃይላችን፣ ባገኘን በታላቅ መከራም ረዳታችን” መሆኑን በተጨባጭ አስተዋልን።—በኪውቤክ የነበሩት ምሥክሮች ቁጥር በ1945 አቅኚነት ስጀምር ከነበረበት ከ356 ተነስቶ አስደናቂ ጭማሪ በማሳየት ዛሬ ከ24, 000 በላይ ደርሷል! በእርግጥ የመጽሐፍ ቅዱሱ ትንቢት እንደተናገረው ነው:- “በአንቺ ላይ የተሠራ መሣሪያ ሁሉ አይከናወንም፤ በፍርድም በሚነሣብሽ ምላስ ሁሉ ትፈርጂበታለሽ።”—ኢሳይያስ 54:17
በፈረንሳይ ያከናወንነው ሥራ
መስከረም 1959 እኔና አን በፈረንሳይ ፓሪስ በሚገኘው ቤቴል እንድናገለግል ግብዣ ቀረበልን። እዚያም የኅትመት ሥራ የበላይ ተመልካች ሆኜ ተመደብኩ። እኛ እስከመጣንበት እስከ ጥር 1960 ድረስ ጽሑፎች የሚታተሙት በአንድ የንግድ ማተሚያ ቤት ነበር። በዚያን ጊዜ ፈረንሳይ ውስጥ መጠበቂያ ግንብ ታግዶ ስለነበር መጽሔቱን የምናትመው በባለ 64 ገጽ ቡክሌት መልክ በወር አንዴ ነበር። ቡክሌቱ የይሖዋ ምሥክሮች የውስጥ ቡሌቲን በመባል ይታወቅ የነበረ ሲሆን በወሩ ውስጥ በጉባኤ የሚጠኑትን ርዕሶች ይዞ ይወጣ ነበር። ከ1960 እስከ 1967 በነበረው ጊዜ ውስጥ በፈረንሳይ በስብከቱ ሥራ የሚሳተፉት ቁጥር ከ15, 439 ወደ 26, 250 አድጓል።
በመጨረሻ አብዛኞቹ ሚስዮናውያን እንደገና ወደ ሌሎች አገሮች የተመደቡ ሲሆን አንዳንዶቹ ፈረንሳይኛ ተናጋሪ ወደሆኑ የአፍሪካ አገሮች፣ ሌሎች ደግሞ ወደ ኪውቤክ እንዲመለሱ ተደረገ። አን ጥሩ ጤንነት ስላልነበራትና ቀዶ ሕክምናም ያስፈልጋት ስለነበር ወደ ኪውቤክ ተመለስን። ለሦስት ዓመታት የሕክምና ክትትል ካደረገች በኋላ ጤንነቷ ተመለሰላት። በዚህ ጊዜ እኔ መንፈሳዊ ማበረታቻ ለመስጠት በየሳምንቱ አንድ ጉባኤ እየጎበኘሁ በወረዳ አገልጋይነት እንድሠራ ተመድቤ ነበር።
በአፍሪካ ያከናወንነው ሚስዮናዊ ሥራ
ከጥቂት ዓመታት በኋላ በ1981 አሁን የኮንጎ ዲሞክራቲክ ሪፑብሊክ ተብላ በምትጠራው በዛየር በሚስዮናዊነት እንድናገለግል አዲስ ምድብ ሲደርሰን በጣም ተደሰትን። ሕዝቡ ድኻ የነበረ ከመሆኑም በላይ ብዙ ስቃይ ይደርስበት ነበር። እዚያ ስንደርስ 25, 753 ምሥክሮች የነበሩ ሲሆን ዛሬ ግን ቁጥራቸው አድጎ ከ113, 000 በላይ ሆኗል። እንዲሁም በ1999 የክርስቶስ ሞት መታሰቢያ ላይ የተገኙት 446, 362 ነበሩ!
በ1984 መንግሥት አዲስ ቅርንጫፍ ቢሮ የምንሠራበት ወደ 200 ሄክታር የሚደርስ መሬት ሰጠን። ከዚያም ታኅሣሥ 1985 በዋና ከተማው በኪንሻሳ ከበርካታ የዓለም ክፍል የመጡ 32, 000 ልኡካን የተገኙበት አንድ ብሔራት አቀፍ የአውራጃ ስብሰባ ተደረገ። ከዚያ በኋላ በቀሳውስት አነሳሽነት የደረሰብን ተቃውሞ በዛየር የምናከናውነውን ሥራ አስተጓጎለብን። መጋቢት 12, 1986 ኃላፊነት የነበራቸው ወንድሞች የዛየር የይሖዋ ምሥክሮች ማኅበር ሕገወጥ መሆኑን የሚያሳውቅ ደብዳቤ ተሰጣቸው። በሥራችን ላይ የተጣለው ይህ አጠቃላይ እገዳ በወቅቱ የአገሪቱ ፕሬዚዳንት በነበሩት በሟቹ በሞቡቱ ሴሴ ሴኮ ፊርማ የጸደቀ ነበር።
እነዚህ ነገሮች የተከሰቱት በድንገት ስለሆነ “ብልህ ሰው ክፉን አይቶ ይሸሸጋል፤ አላዋቂዎች ግን አልፈው ይጐዳሉ” የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር በሥራ ማዋል ነበረብን። (ምሳሌ 22:3) ኪንሻሳ ውስጥ ጽሑፎቻችንን ለማተም ወረቀት፣ ቀለም፣ ፊልም፣ ማተሚያ ፕሌትና ኬሚካሎች ከውጭ አገር የምናስገባበት ዘዴ ፈጠርን። በተጨማሪም ጽሑፍ የምናሰራጭበት የራሳችን የሆነ መዋቅር ዘረጋን። አሠራራችን መልክ ከያዘ በኋላ የምንጠቀምበት ዘዴ ከመንግሥት የፖስታ አገልግሎት በተሻለ ሁኔታ መሥራት ጀመረ!
በሺዎች የሚቆጠሩ ምሥክሮች ታሰሩ፤ አብዛኞቹም ጭካኔ በተሞላበት መንገድ ተደበደቡ። ሆኖም ከጥቂቶች በስተቀር የደረሰባቸውን ሥቃይ በጽናት ተወጥተዋል፤ ታማኝነታቸውንም ጠብቀዋል። እኔም ታስሬ ስለነበር ወንድሞች እስር ቤት ውስጥ የነበሩበትን አሰቃቂ ሁኔታ ለማየት ችያለሁ። ብዙ ጊዜ ሕዝብ ደኅንነትና ባለሥልጣኖች ከየአቅጣጫው ጫና ይፈጥሩብን ነበር፤ ይሁን እንጂ ይሖዋ ምንጊዜም መውጫ ቀዳዳ አዘጋጅቶልናል።—2 ቆሮንቶስ 4:8
በአንድ ነጋዴ መጋዘን ውስጥ ወደ 3, 000 ካርቶን ገደማ ጽሑፍ ደብቀን ነበር። መጨረሻ ላይ ግን ከሠራተኞቹ አንዱ ጉዳዩን ለሕዝብ ደኅንነት አሳወቀና ነጋዴው ተያዘ። እነርሱ ወደ እስር ቤት ሲያመሩ እኔ ደግሞ በራሴ መኪና ስሄድ ድንገት መንገድ ላይ ተገጣጠምን። ነጋዴው ጽሑፉን ለማስቀመጥ ከእርሱ ጋር የተዋዋልኩት እኔ መሆኔን ነገራቸው። ፖሊሶቹ አስቆሙኝና በዚህ ሰውዬ መጋዘን ውስጥ ሕገወጥ ጽሑፍ በማስቀመጤ በመወንጀል ስለ ጉዳዩ ጠየቁኝ።
“መጽሐፉ በእጃችሁ ይገኛል?” ስል ጠየቅኋቸው።
“ምን ጥያቄ አለው” ሲሉ መለሱልኝ።
“ማየት እችላለሁ?” ስል ጠየቅኋቸው።
አንድ ቅጂ ሰጡኝ። ከዚያም ውስጠኛው ገጽ ላይ “በመጠበቂያ ግንብ የመጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር በዩናይትድ ስቴትስ የታተመ” የሚለውን አሳየኋቸው።
“እጃችሁ ላይ ያለው መጽሐፍ የአሜሪካ ንብረት እንጂ የዛየር አይደለም። የአገሪቱ መንግሥት እገዳ የጣለው ደግሞ በዛየር በሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ማኅበር ሕጋዊ ኮርፖሬሽን ላይ እንጂ በዩናይትድ ስቴትስ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር ላይ አይደለም። ስለዚህ በእነዚህ ጽሑፎች ምክንያት ችግር ውስጥ እንዳትገቡ በጣም መጠንቀቅ ያለባችሁ ይመስለኛል” ስል አሳሰብኳቸው።
እኔን ለማሰር የሚያስችል የፍርድ ቤት ትእዛዝ ስላልያዙ በነፃ ለቀቁኝ። የዚያን ዕለት ማታ ሁለት የጭነት መኪናዎች ይዘን ሄደን ጽሑፉን ከመጋዘኑ አነሳን። ባለሥልጣኖቹ በሚቀጥለው ቀን መጥተው መጋዘኑን ባዶ ሆኖ በማግኘታቸው በጣም ተናደዱ። በዚህ ጊዜ እኔን ለማሰር የሚያስችል የፍርድ ቤት ትእዛዝ አውጥተው ስለነበር እኔን ለማግኘት ፍለጋ ላይ ነበሩ። ካገኙኝ በኋላ መኪና ስላልነበራቸው እኔ ራሴ እየነዳሁ ወደ እስር ቤት ሄድኩ! መኪናዬን እንወርሳለን ከማለታቸው በፊት ይዟት እንዲሄድ አንድ ሌላ ምሥክር አብሮኝ መጣ።
ስምንት ሰዓት ከፈጀ ምርመራ በኋላ ከአገር እንድባረር ወሰኑ። ሆኖም ታግዶ ያለውን የዛየር የይሖዋ ምሥክሮች ማኅበር ቋሚ ንብረቶች ለመሸጥ ከመንግሥት የተቀበልኩትን የውክልና ደብዳቤ ፎቶ ኮፒ አሳየኋቸው። በዚህ ምክንያት በቤቴል የማከናውነውን ሥራ እንድቀጥል ተፈቀደልኝ።
ዛየር ውስጥ ሥራችን ላይ ተጥሎ የነበረው እገዳ የሚያስከትለው ጫና እያለ ለአራት ዓመታት ካገለገልኩ በኋላ ጨጓራዬ ቆስሎ መድማት ጀመረ። ሕክምና ለማግኘት ወደ ደቡብ አፍሪካ መሄድ እንዳለብኝ ተወሰነና በዚያ ያለው ቅርንጫፍ ቢሮ ጥሩ እንክብካቤ ስላደረገልኝ ከበሽታው ዳንኩ። በዛየር ባገለገልንባቸው ስምንት ዓመታት ፈጽሞ የማይረሳና አስደሳች ተሞክሮ ካሳለፍን በኋላ በ1989 ወደ ደቡብ አፍሪካ ቅርንጫፍ ቢሮ ተዛወርን። በ1998 ወደ ትውልድ አገራችን የተመለስን ሲሆን ከዚያን ጊዜ ጀምሮ እንደገና በካናዳ ቤቴል እያገለገልን ነው።
ላገኘሁት የአገልግሎት መብት አመስጋኝ ነኝ
በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ያሳለፍኳቸውን 54 ዓመታት መለስ ብዬ ስመለከት የወጣትነት ጉልበቴን ለይሖዋ ውድ አገልግሎት በማዋሌ እርካታ ይሰማኛል። ምንም እንኳ አን ብዙ ፈታኝ ሁኔታዎችን በጽናት ማሳለፍ የነበረባት ቢሆንም በነበሩን እንቅስቃሴዎች በሙሉ ጥሩ ደጋፊ ነበረች እንጂ የምታማርር አልነበረችም። አንድ ላይ ሆነን ብዙዎች ይሖዋን ወደማወቅ ደረጃ እንዲደርሱ የመርዳት መብት አግኝተናል፤ አብዛኞቹ በሙሉ ጊዜ አገልግሎት በመካፈል ላይ ናቸው። የእነርሱ ልጆች አልፎ ተርፎም የልጅ ልጆች የሆኑት አንዳንዶች ታላቁን አምላካችንን ይሖዋን ሲያገለግሉ ማየት እጅግ ያስደስታል!
ይሖዋ ከሰጠን መብቶችና በረከቶች ጋር ሊወዳደር የሚችል ይህ ዓለም የሚሰጠን አንድም ነገር እንደሌለ እርግጠኛ ነኝ። እርግጥ በጽናት ያሳለፍናቸው ብዙ ፈተናዎች ነበሩ፤ ሆኖም ሁሉም በይሖዋ ላይ ያለንን እምነትና ትምክህት እንድንገነባ ረድተውናል። በእርግጥ ይሖዋ የብርታት ምንጭና መጠጊያ እንዲሁም በጭንቅ ጊዜ ቶሎ የሚደርስ ደጋፊ ሆኖልናል።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a መጽሐፉ ክሮይትጹግ ጌይግን ዳስ ክርስትንቱም (ክርስትናን ለመደምሰስ የተደረገ ተጋድሎ) በሚል ርዕስ መጀመሪያ በጀርመንኛ የታተመ ነበር። መጽሐፉ ወደ እንግሊዝኛ ባይተረጎምም በፈረንሳይኛና በፖሊሽ ግን ተተርጉሟል።
[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በ1947 አብረን በአቅኚነት ስናገለግል፤ በዛሬው ጊዜ ከአን ጋር
[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በዛየር ያገኘናቸው ሰዎች ለመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ፍቅር ነበራቸው