በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ሲረል ሉካረስ—ለመጽሐፍ ቅዱስ ትልቅ ግምት የነበረው ሰው

ሲረል ሉካረስ—ለመጽሐፍ ቅዱስ ትልቅ ግምት የነበረው ሰው

ሲረል ሉካረስ​—ለመጽሐፍ ቅዱስ ትልቅ ግምት የነበረው ሰው

በ1638 የበጋ ወቅት አንድ ቀን የኦቶማን ግዛት ዋና ከተማ በሆነችው በቁስጥንጥንያ (ዘመናዊቷ ኢስታንቡል ) አቅራቢያ በሚገኘው ማርማራ ባሕር ላይ ዓሣ አስጋሪዎች አንድ አስከሬን ሲንሳፈፍ ዓይተው ደነገጡ። ቀረብ ብለው ሲመለከቱትና ታንቆ የተጣለው ሰው አስከሬን የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን መሪ የሆነው የቁስጥንጥንያ ፓትሪያርክ መሆኑን ሲያውቁ ክው ብለው ቀሩ። በ17ኛው መቶ ዘመን የታወቀ የሃይማኖት ሰው የነበረው የሲረል ሉካረስ አሳዛኝ የሕይወት ፍጻሜ ይህ ነበር።

ሉካረስ የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች ተራው ሰው በሚጠቀምበት ግሪክኛ ቋንቋ ተተርጉመው ወጥተው የማየት ሕልሙ እውን ሳይሆን ሞቷል። ሌላው የሉካረስ ሕልም የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ወደ “ኢቫንጄሊካል ሲምፕሊሲቲ” ስትመለስ ማየት ነበር። ይህ ሕልሙም ቢሆን እውን አልሆነለትም። ለመሆኑ ይህ ሰው ማን ነበር? እነዚህን ሕልሞቹን እውን ለማድረግ ባደረገው ጥረትስ ምን እንቅፋቶች ገጥመውታል?

የትምህርት ማነስ ያስከተለበት ችግር

ሲረል ሉካረስ በቬኒስ ቁጥጥር ስር ባለችው በቀርጤሷ ካንዲያ (በአሁኗ ኢራክሊዮ) በ1572 ተወለደ። ሉካረስ ጥሩ ጭንቅላት የነበረው ሰው ሲሆን በቬኒስና በፓዱዋ ጣሊያን ትምህርቱን ከተከታተለ በኋላ በዚያች አገርና በሌሎች አገሮች ብዙ ተዘዋውሯል። በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ ባለው መከፋፈልና ሽኩቻ የተማረረውና በአውሮፓ እየተካሄደ ባለው የተሐድሶ እንቅስቃሴ የተማረከው ሉካረስ በወቅቱ በካልቪኒዝም እንቅስቃሴ ተጽእኖ ስር የነበረችውን ጄኔቭን ሳይጎበኝ አይቀርም።

ሉካረስ ፖላንድን በጎበኘበት ወቅት በዚያ ያሉ ኦርቶዶክሶች፣ ቀሳውስቱም ሆኑ ምእመናኑ ከትምህርት ማነስ የተነሳ በአሳዛኝ መንፈሳዊ ሁኔታ ላይ ይገኙ እንደ ነበር ተገነዘበ። ወደ እስክንድርያና ቁስጥንጥንያ ሲመለስ ደግሞ ይባስ ብሎ ቅዱሳን ጽሑፎች ይነበቡባቸው የነበሩ አትራኖሶች ከአንዳንዶቹ ቤተ ክርስቲያኖች ተነስተው ሲመለከት በጣም ደነገጠ!

ሉካረስ በ1602 ወደ እስክንድርያ ከተመለሰ በኋላ ዘመዱ በነበረው በፓትሪያርክ ሚሊቲኦስ ምትክ መንበረ ፓትሪያርክነቱን ያዘ። ከዚያም በአውሮፓ ከሚገኙ የተሐድሶ ዝንባሌ ካላቸው የሃይማኖት ምሁራን ጋር ደብዳቤ መጻጻፍ ጀመረ። የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን በርካታ የተሳሳቱ የአምልኮ ድርጊቶችን የሙጥኝ ብላ እንደያዘች ከጻፋቸው ደብዳቤዎች በአንዱ ላይ ገልጿል። በሌላ ደብዳቤ ላይ ደግሞ ቤተ ክርስቲያኒቱ በአጉል እምነት ፋንታ “ኢቫንጀሊካል ሲምፕሊሲቲን” መተካትና ቅዱሳን ጽሑፎችን ብቻ እንደ ባለ ሥልጣን አድርጋ መመልከት እንደሚያስፈልጋት ጠበቅ አድርጎ ገልጿል።

በተጨማሪም ሉካረስ የቤተ ክርስቲያን አባቶችን መንፈሳዊ ሥልጣን ኢየሱስና ሐዋርያት ከተናገሯቸው ቃላት ጋር በእኩል ደረጃ የማየቱ ጉዳይ በእጅጉ አሳስቦት ነበር። “ከእንግዲህ ሰው ሠራሽ ወጎች ከቅዱሳን ጽሑፎች እኩል ክብደት እንዳላቸው ሲነገር እየሰማሁ መታገሥ አልችልም” ሲል ጽፏል። (ማቴዎስ 15:​6) በተጨማሪም በእሱ አመለካከት የምስል አምልኮ አደገኛ እንደሆነ ገልጿል። “ቅዱሳንን” አማላጅ አድርጎ ማመን መካከለኛ ሆኖ የሚያገለግለውን ኢየሱስን መሳደብ እንደሆነም ተናግሯል።​—⁠1 ጢሞቴዎስ 2:​5

መንበረ ፓትሪያርኩን በገንዘብ

እነዚህ ሐሳቦች ለሮማ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ከነበረው ጥላቻ ጋር ተዳምረው ጀስዊቶችና ከካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ጋር መዋሃድን የሚደግፉ አንዳንድ ኦርቶዶክሶች ጥላቻና ስደት አስነሱበት። ይህ ተቃውሞ ቢኖርም በ1620 ሉካረስ የቁስጥንጥንያ ፓትሪያርክ ሆኖ ተመረጠ። በዚያን ወቅት የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን መንበረ ፓትሪያርክ በኦቶማን አገዛዝ ቁጥጥር ሥር ነበር። የኦቶማን መንግሥት ገንዘብ ካገኘ አንድን ፓትሪያርክ አውርዶ በምትኩ አዲስ ፓትሪያርክ ይሾማል።

የሉካረስ ቀንደኛ ጠላቶች የሆኑት ጀስዊቶችና ኮንግርጋቲኦ ዴ ፕሮፓጋንዳ ፊዴ (የእምነት ማስፋፊያ ጉባኤ) የተባሉት ከፍተኛ ተደማጭነት የነበራቸውና ሉካረስን በጣም የሚፈሩት ሰዎች ስሙን ማጥፋታቸውንና በእሱ ላይ ማሴራቸውን ሥራዬ ብለው ተያያዙት። “ጀስዊቶች ይህን ዓላማቸውን ከግብ ለማድረስ ያልቆፈሩት ጉድጓድ ያልፈነቀሉት ድንጋይ አልነበረም፤ በተንኮል፣ በስም ማጥፋት፣ በሽንገላ፣ ከሁሉም በላይ ደግሞ የኦቶማን ባለ ሥልጣናትን ልብ በመማረክ ረገድ ውጤታማ ሆኖ ባገኙት በጉቦ ተጠቅመዋል” ሲል ካይሪሎስ ሉካሪስ የተባለው ጽሑፍ ገልጿል። በዚህም የተነሳ በ1622 ሉካረስ ወደ ሮድ ደሴት እንዲወሰድ ከተደረገ በኋላ የአማሲያው ግሪጎሪ መንበረ ፓትሪያርኩን በ20, 000 ጠገራ ብር ለመግዛት ተስማማ። ሆኖም ግሪጎሪ ይህን ገንዘብ መክፈል ሳይችል በመቅረቱ የአድሪያኖፕሉ አንቲመስ መንበረ ፓትሪያርኩን ከገዛው በኋላ ሥልጣኑን በገዛ ፈቃዱ ለቋል። ሉካረስ በሚያስገርም ሁኔታ መንበረ ፓትሪያርኩን መልሶ አገኘ።

ሉካረስ ያገኘውን ይህን አዲስ አጋጣሚ በመጠቀም አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉምና ሃይማኖታዊ ትራክቶች በማሳተም የኦርቶዶክስ ቀሳውስትንና ምእመናንን ለማስተማር ቆርጦ ተነሳ። ይህንም ዓላማውን ለማሳካት አንድ የማተሚያ መሣሪያ በእንግሊዝ አምባሳደር ሽፋን ወደ ቁስጥንጥንያ እንዲገባ ዝግጅት አደረገ። ሆኖም ሰኔ 1627 መሣሪያው ቁስጥንጥንያ ሲደርስ የሉካረስ ጠላቶች ለፖለቲካ ዓላማ ይጠቀምበታል ሲሉ ከሰሱት። በመጨረሻም መሣሪያው ከጥቅም ውጭ እንዲሆን አስደረጉ። አሁን ሉካረስ በጄኔቭ የሚገኝ ማተሚያ መጠቀም ግድ ሆነበት።

የክርስቲያን ቅዱሳን ጽሑፎች ትርጉም

ሉካረስ ለመጽሐፍ ቅዱስና መጽሐፍ ቅዱስ ላለው የማስተማር ኃይል የነበረው የላቀ ግምት የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ለተራው ሰው ይበልጥ እንዲዳረስ የማድረግ ምኞት በውስጡ እንዲቀጣጠል አድርጓል። በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፉት የመጀመሪያዎቹ የግሪክኛው መጽሐፍ ቅዱስ ቅጂዎች የተጻፉበት ግሪክኛ ቋንቋ ማንም ሰው በቀላሉ አንብቦ የሚረዳው መሆኑ እንዳከተመለት ተገንዝቦ ነበር። ስለዚህ የሉካረስ የመጀመሪያ ተልእኮ የግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች በእሱ ዘመን ወደሚነገረው ግሪክኛ ቋንቋ እንዲተረጎሙ ማድረግ ነበር። መጋቢት 1629 ማክሲመስ ካሊፖልተስ የተባለ አንድ ምሁር መነኩሴ ሥራውን ጀመረ። የጥንቱ ቅጂ የቱንም ያህል የማይገባ ቢሆንም ቅዱሳን ጽሑፎችን መተርጎም ተገቢ አይደለም ሲሉ ብዙዎቹ ኦርቶዶክሶች ተቃወሙ። ሉካረስ የእነሱን ተቃውሞ ለማብረድ ሲል ትንሽ ማስታወሻ ብቻ በመጨመር የመጀመሪያው ቅጂና አዲሱ ትርጉም በአምድ ተከፍሎ ጎን ለጎን እንዲታተም አደረገ። ካሊፖሊተስ ትርጉሙን እንደ ጨረሰ ስለ ሞተ የማጣሪያ ንባቡን ያደረገው ራሱ ሉካረስ ነበር። ይህ ትርጉም ሉካረስ በ1638 ከሞተ በኋላ ብዙም ሳይቆይ ለኅትመት በቃ።

ሉካረስ ያን ሁሉ ጥንቃቄ አድርጎ የነበረ ቢሆንም ይህ ትርጉም በብዙዎቹ ጳጳሳት ዘንድ ተቃውሞ አስነስቷል። በዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም መቅድም ላይ ያለው ሐሳብ ሉካረስ ለአምላክ ቃል ምን ያህል ፍቅር እንደነበረው በግልጽ ያሳያል። ሰዎች በሚግባቡበት ቋንቋ የቀረቡት ቅዱሳን ጽሑፎች “ከሰማይ እንደ መጣ ጣፋጭ መልእክት” ናቸው ሲል ጽፏል። ሰዎች “ከጠቅላላው [የመጽሐፍ ቅዱስ] ይዘት ጋር በሚገባ እንዲተዋወቁ” ከመከረ በኋላ “መለኮታዊ ምንጭ ባለውና ቅዱስ በሆነው ወንጌል አማካኝነት ካልሆነ በስተቀር . . . እምነትን የሚመለከቱ ነገሮችን በትክክል” ማወቅ የሚቻልበት ሌላ ምንም መንገድ የለም ሲል ተናግሯል።​—⁠ፊልጵስዩስ 1:​9, 10

ሉካረስ መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናትንና የጥንቱን ቅጂ መተርጎምን የሚከለክሉ ሰዎችን አጥብቆ አውግዟል። “ምንም ሳይገባን የምንናገር ወይም የምናነብ ከሆነ ቃላትን ለነፋስ እንደ መበተን ይሆናል” ሲል ተናግሯል። (ከ1 ቆሮንቶስ 14:​7-9 ጋር አወዳድር።) በመቅድሙ ላይ ያለውን ሐሳብ ሲደመድም እንዲህ ብሏል:- “ሁላችሁም ይህን መለኮታዊ ምንጭ ያለው ቅዱስ ወንጌል በገዛ ቋንቋችሁ ስታነቡ ከወንጌሉ ሙሉ ጥቅም ለማግኘት ጣሩ . . . አምላክም መልካሙን ጎዳናችሁን ይበልጥ እያበራላችሁ ይሂድ።”​—⁠ምሳሌ 4:​18

“ከንፌሽን ኦቭ ፌይዝ”

ሉካረስ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም እንዲጀመር ካደረገ በኋላ ሌላም ድፍረት የሚጠይቅ እርምጃ ወስዷል። በ1629 ከንፌሽን ኦቭ ፌይዝ የሚል መጽሐፍ በጄኔቭ አሳተመ። በኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን በሥራ ላይ ይውላሉ ብሎ የሚያምንባቸውን የራሱን ሐሳቦች የያዘ መጽሐፍ ነበር። ከንፌሽን “የኦርቶዶክስን የሥርዓተ ቅስና ትምህርት ትርጉም የለሽ ያደረገ እንዲሁም ምሥሎችን ለአምልኮ መጠቀምን ያጣጣለና ለቅዱሳን ልመና ማቅረብ ከጣዖት አምልኮ ተለይቶ የሚታይ አለመሆኑን ያጋለጠ ነው” ሲል ዚ ኦርቶዶክስ ቸርች የተባለው መጽሐፍ ገልጿል።

ከንፌሽን 18 አንቀጾችን የያዘ ነው። ሁለተኛው አንቀጽ ቅዱሳን ጽሑፎች በአምላክ መንፈስ አነሳሽነት የተጻፉ እንደሆኑና ከቤተ ክርስቲያን ይበልጥ ሥልጣን ያላቸው እነሱ እንደሆኑ ይገልጻል። “ቅዱስ ጽሑፉ ከአምላክ የተሰጠን እንደሆነ እናምናለን። . . . ቅዱስ ጽሑፉ ቤተ ክርስቲያን ካላት ሥልጣን የበለጠ እንደሆነ እናምናለን። በመንፈስ ቅዱስ መማር በሰው ከመማር ፈጽሞ የተለየ ነገር ነው።”​—⁠2 ጢሞቴዎስ 3:​16

ስምንተኛውና አሥረኛው አንቀጽ ኢየሱስ ክርስቶስ ብቸኛው መካከለኛ፣ ሊቀ ካህንና የጉባኤ ራስ መሆኑን ይገልጻል። “ኢየሱስ ክርስቶስ በአባቱ ቀኝ እንደተቀመጠና እዚያም ሆኖ ስለ እኛ እንደሚማልድ፣ እውነተኛና ሕጋዊ ሊቀ ካህን እንዲሁም መካከለኛ መሆኑን እናምናለን” በማለት ሉካረስ ጽፏል።​—⁠ማቴዎስ 23:​10

አሥራ ሁለተኛው አንቀጽ ደግሞ ቤተ ክርስቲያን ሐሰቱን ከእውነት መለየት ተስኗት ልትባዝን ትችላለች፤ ሆኖም በታማኝ አገልጋዮች ጥረት የመንፈስ ቅዱስ ብርሃን ወደ ትክክለኛው መንገድ ሊመልሳት እንደሚችል ይገልጻል። ሉካረስ በ18ኛው አንቀጽ ላይ መንጽሔ ጨርሶ የሌለ ነገር መሆኑን ሲገልጽ “መንጽሔ የሚባለው ልብ ወለድ ሐሳብ ተቀባይነት እንደሌለው ግልጽ ነው” ብሏል።

ከንፌሽን ተጨማሪ ክፍል [appendix] ብዙ ጥያቄዎችንና መልሶቻቸውን ይዟል። ማንም ታማኝ ሰው ቅዱሳን ጽሑፎችን ማንበብ እንዳለበትና አንድ ክርስቲያን የአምላክን ቃል ሳያነብ ከቀረ ጉዳት እንደሚደርስበት ጠበቅ አድርጎ ገልጿል። ከዚያም አዋልድ መጻሕፍትን ማስወገድ እንደሚገባ አክሎ ገልጿል።​—⁠ራእይ 22:​18, 19

አራተኛው ጥያቄ “ምስሎችን እንዴት ልንመለከታቸው ይገባል?” ይላል። ሉካረስ መልሱን ሲሰጥ እንደሚከተለው ብሏል:- “‘በላይ በሰማይ ካለው፣ በታችም በምድር ካለው፣ ከምድርም በታች በውኃ ካለው ነገር የማናቸውንም ምሳሌ፣ የተቀረጸውንም ምስል ለአንተ አታድርግ። አትስገድላቸው፣ አታምልካቸውምም [ዘጸአት 20:​4, 5]’ በማለት በግልጽ ከሚናገሩት መለኮታዊ ምንጭ ካላቸው ቅዱሳን ጽሑፎች ተምረናል። እኛ ማምለክ ያለብን ፍጥረትን ሳይሆን የሰማይና የምድር ፈጣሪና ሠሪ የሆነውን ስለሆነ አምልኮ ልናቀርብ የሚገባን ለእሱ ብቻ ነው። . . . ለምስሎች የሚቀርብ አምልኮና ቅዳሴ በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ . . . የተከለከለ እንደ መሆኑ መጠን እኛም አንቀበለውም። ምክንያቱም ከፈጣሪ ይልቅ የተለያዩ ሥዕሎችን፣ ምስሎችንና ፍጥረታትን የምናመልክ ከሆነ ይህን ትእዛዝ ልንዘነጋው እንችላለን።”​—⁠ሥራ 17:​29

ሉካረስ እሱ በኖረበት የመንፈሳዊ ጨለማ ዘመን ሁሉንም ስህተት ማስተዋል ባይችልም a መጽሐፍ ቅዱስ በቤተ ክርስቲያን ሃይማኖታዊ ትምህርቶች ላይ ሥልጣን እንዲኖረውና ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስን ትምህርቶች እንዲማሩ ለማድረግ ያደረገው ጥረት የሚያስመሰግን ነው።

ከንፌሽን የተባለው መጽሐፍ ወዲያው እንደወጣ በሉካረስ ላይ እንደገና የተቃውሞ ማዕበል አገረሸ። በ1633 ሲረል ኮንታሪ የተባለው የቤሪያ (የአሁኗ አሌፖ) አቡን የሆነው በጀስዊቶች የሚደገፈውና ቀንደኛ የሆነው የሉካረስ ጠላት መንበረ ፓትሪያርኩን ለማግኘት ከኦቶማኖች ጋር በዋጋ ለመደራደር ሞክሮ ነበር። ሆኖም ኮንታሪ የተጠየቀውን ገንዘብ መክፈል ሳይችል በመቅረቱ መንበረ ፓትሪያርኩን ለማግኘት የነበረው እቅድ ከሽፎበታል። ሉካረስ ሥልጣኑን እንደያዘ ቀጠለ። በቀጣዩ ዓመት የተሰሎንቄው አታናሲየስ ይህን ሥልጣን ለማግኘት 60, 000 ጠገራ ብር ከፈለ። ሉካረስ እንደገና መንበረ ፓትሪያርኩን እንዲለቅ ተደረገ። ሆኖም በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ወደ ሥልጣኑ እንዲመለስ ተደረገ። ያኔ ሲረል ኮንታሪ 50, 000 ጠገራ ብር አቀረበ። ሉካረስ ወደ ሮድ ደሴት እንዲወሰድ የተደረገው በዚህ ጊዜ ነበር። ሆኖም ከስድስት ወራት በኋላ ጓደኞቹ ወደ ሥልጣኑ እንዲመለስ ማድረግ ችለው ነበር።

ሆኖም በ1638 ጀስዊቶችና ኦርቶዶክስ ደጋፊዎቻቸው ሉካረስን የኦቶማን መንግሥትን በመክዳት ወንጀል ከሰሱት። በዚህ ጊዜ ሱልጣኑ ሉካረስ እንዲገደል አዘዘ። ከዚያም ሉካረስ በቁጥጥር ስር እንዲውል ከተደረገ በኋላ በግዞት እንደሚወሰድ አስመስለው ሐምሌ 27, 1638 በአንዲት ትንሽ ጀልባ አሳፍረው ወሰዱት። ጀልባዋ ወዲያው ጉዞ እንደ ጀመረች አንቀው ከገደሉት በኋላ አስከሬኑን ባሕሩ ዳርቻ ቀበሩት። እንደገና ደግሞ ቆፍረው አውጥተው ወደ ባሕሩ ወረወሩት። ዓሣ አስጋሪዎች ያገኙት በዚህ ጊዜ ነበር፤ ከዚያም ወዳጆቹ ወስደው ቀበሩት።

ከዚህ የምናገኘው ትምህርት

አንድ ምሁር “የሉካረስ አንዱ ተቀዳሚ ዓላማ በአሥራ ስድስተኛው እንዲሁም በአሥራ ሰባተኛው መቶ ዘመን መጀመሪያ ላይ በጣም አነስተኛ የነበረውን የቀሳውስቱንም ሆነ የሕዝቡን የእውቀትና የትምህርት ደረጃ ከፍ እንዲል ማድረግ ነበር። ይህ ደግሞ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ነገር ነው” ሲሉ ገልጸዋል። ሉካረስ ያሰበው ግብ ላይ እንዳይደርስ በርካታ እንቅፋቶች አግደውታል። አምስት ጊዜ ከመንበረ ፓትሪያርኩ እንዲወርድ ተደርጓል። ከሞተ ከሠላሳ አራት ዓመት በኋላ በኢየሩሳሌም የሚገኝ ሲኖዶስ የሉካረስ አመለካከት መናፍቅነት ነው ሲል አውግዞታል። ቅዱሳን ጽሑፎችን “ማንበብ የሚገባቸው አስፈላጊውን ምርምር ካደረጉ በኋላ የመንፈስን ጥልቅ ነገሮች መረዳት ወደሚችሉበት ደረጃ የደረሱ ሰዎች ናቸው እንጂ ማንም ተራ ሰው ተነስቶ ሊያነበው አይገባም” በማለት ተናግረዋል። በእነርሱ አባባል ማንበብ የሚችሉት የተማሩት ቀሳውስት ብቻ ናቸው።

የሃይማኖት መሪዎች የአምላክ ቃል ለመንጎቻቸው እንዳይደርስ ከመከላከል ቦዝነው አያውቁም። ስሕተትና መጽሐፍ ቅዱሳዊ ያልሆኑ አንዳንድ አመለካከቶቻቸውን ለማጋለጥ የሚደረገውንም ሙከራ በኃይል አፍነው ለማስቀረት ይጥራሉ። የሃይማኖታዊ ነፃነትና የእውነት ዋነኛ ጠላቶች መሆናቸውን አስመስክረዋል። እንዲህ ያለው ሁኔታ እስከ ዘመናችን ድረስ መዝለቁ የሚያሳዝን ነው። ቀሳውስት የሚጠነስሱት ሴራ ሐሳብን የመግለጽ ነፃነትን የሚያፍን ሆኖ ሲገኝ ምን ሊከሰት እንደሚችል የሚያሳይ ነው።

[የግርጌ ማስታወሻ]

a ከንፌሽን በተባለው መጽሐፉ ሥላሴን፣ ዕድል አስቀድሞ ተወስኗል የሚለውን ትምህርትና የነፍስን አለመሞት የሚደግፍ ሐሳብ አስፍሯል። ሁሉም ግን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትምህርቶች አይደሉም።

[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

ሉካረስ መጽሐፍ ቅዱስ በቤተ ክርስቲያን ሃይማኖታዊ ትምህርቶች ላይ ሥልጣን እንዲኖረውና ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስን ትምህርቶች እንዲማሩ ያደረገው ጥረት የሚያስመሰግን ነው

[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

ሉካረስ እና የአሌክሳንድሪነስ ኮዴክስ

በብሪታንያ ቤተ መጻሕፍት ውስጥ እንደ ዕንቁ ከሚታዩት ነገሮች አንዱ የአምስተኛው መቶ ዘመን እዘአ የመጽሐፍ ቅዱስ ቅጂ የሆነው የአሌክሳንድሪነስ ኮዴክስ ነው። መጀመሪያ ላይ ነበሩት ተብሎ ከሚገመተው 820 ገጾቹ ውስጥ 773 የሚሆኑት ተጠብቀው ቆይተዋል።

ሉካረስ የግብጿ እስክንድርያ ፓትሪያርክ በነበረበት ወቅት ከፍተኛ የመጻሕፍት ስብስብ ነበረው። በቁስጥንጥንያ ፓትሪያርክ ሆኖ በተሾመበት ወቅት የአሌክሳንድሪነስን ኮዴክስ ይዞ ሄዶ ነበር። ለእንግሊዙ ንጉሥ ለጀምስ አንደኛ በስጦታ መልክ እንዲሰጥለት በ1624 በቱርክ ለነበረው የብሪታንያ አምባሳደር ሰጥቶት ነበር። ከሦስት ዓመት በኋላ የዙፋኑ ወራሽ ለሆነው ለቻርልስ አንደኛ ተሰጥቷል።

የንጉሡ ሮያል ቤተ መጻሕፍት በ1757 ለብሪታንያ መንግሥት ተሰጥቶ ነበር። እናም ይህ ግሩም ኮዴክስ በአሁኑ ጊዜ በአዲሱ የብሪታንያ ቤተ መጻሕፍት በጆን ሪትብላ የሥዕል አዳራሽ ውስጥ ይገኛል።

[ምንጭ]

Gewerbehalle, Vol. 10

From The Codex Alexandrinus in Reduced Photographic Facsimile, 1909

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

Bib. Publ. Univ. de Genève