በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አካላቸው ትንሽ፣ ልባቸው ትልቅ

አካላቸው ትንሽ፣ ልባቸው ትልቅ

አካላቸው ትንሽ፣ ልባቸው ትልቅ

ቁመትህ 76 ሴንቲ ሜትር ብቻ ቢሆን ኖሮ ከዚህ በፊት ለማታውቃቸው ሰዎች ስለ አምላክ መንግሥት እንዴት አድርገህ ትናገር ነበር? ላውራ ልትነግርህ ትችላለች። ዕድሜዋ 33 ዓመት ሲሆን ቁመቷ ግን 76 ሴንቲ ሜትር ብቻ ነው። እርሷና የ24 ዓመት ዕድሜና 86 ሴንቲ ሜትር ቁመት ያላት ማሪያ የተባለችው እህቷ የሚኖሩት በኢኳዶር፣ ኪቶ ውስጥ ነው። በክርስቲያን አገልግሎት እየተካፈሉ ሳለ የሚያጋጥሟቸውን እንቅፋቶች ሲናገሩ እንስማ።

“ወደ አገልግሎት ክልላችንና ወደ ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች የሚወስደንን አውቶቡስ ለመያዝ ግማሽ ኪሎ ሜትር በእግር እንጓዛለን። ከዚህኛው አውቶቡስ ወርደን ሌላ ሁለተኛ አውቶቡስ ለመያዝ ተጨማሪ ግማሽ ኪሎ ሜትር በእግር እንጓዛለን። የሚያሳዝነው ደግሞ በዚህ መንገድ ላይ አምስት ኃይለኛ ውሾች አሉ። ፈረስ አክለው ስለሚታዩን ውሾች በጣም ያስፈሩናል። ውሾቹ ከመጡብን ለማባረር ዱላ እንይዛለን። ዱላውን ወደ ቤት ስንመለስም እንድንጠቀምበት አውቶቡስ ከመሳፈራችን በፊት መንገዱ ዳር ደብቀነው እንሄዳለን።

“አውቶቡስ ላይ ወጥቶ መሳፈር ለእኛ በጣም አስቸጋሪ ነው። በቀላሉ ለመሳፈር እንድንችል አውቶቡስ ማቆሚያው አካባቢ ባለ የተከመረ ቆሻሻ ላይ እንቆማለን። አንዳንዶቹ ሾፌሮች አውቶቡሱን አስጠግተው ያቆሙልናል፤ አንዳንዶቹ ደግሞ አያስጠጉልንም። በዚህ ጊዜ ከሁለታችን ረዘም ያለው አጠር ያለውን በመርዳት እንሳፈራለን። ሁለተኛውን አውቶቡስ ለመያዝ ተሽከርካሪ የሚበዛበት አንድ አውራ ጎዳና የግድ ማቋረጥ ይኖርብናል። ይህ ደግሞ አጫጭር እግሮች ላሉን ለእኛ በጣም አስቸጋሪ ነው። ቁመታችን አጭር ስለሆነ ተለቅ ያለ የጽሑፍ ቦርሳ መያዝ ችግር ነው። የቦርሳውን ክብደት ለማቅለል ስንል በኪስ የሚያዝ መጠን ያለው መጽሐፍ ቅዱስ እንይዛለን እንዲሁም የምንይዘውን የጽሑፍ ብዛት መጠን እንቀንሳለን።

“ከልጅነታችን ጀምሮ የማያውቀን ሰው የለም። ጎረቤቶቻችን ሰዎችን ቀርበን ማነጋገር እንቸገር እንደነበር ያውቃሉ። ስለዚህም በራቸውን አንኳኩተን ስናነጋግራቸው በጣም ይገረማሉ። ብዙውን ጊዜም በደንብ ያዳምጡናል። ሆኖም ከዚህ በፊት ወደማያውቁን ሰዎች ቤት ስንሄድ ድንክነታችን ትኩረታቸውን ስለሚስበው ለመልእክታችን የሚገባውን ያክል ትኩረት ሰጥተው አያዳምጡንም። ሆኖም ይሖዋ እንደሚወደን ማወቃችን በወንጌላዊነቱ ሥራ ለመቀጠል የሚያስችለንን ብርታት ሰጥቶናል። በተጨማሪም በ⁠ምሳሌ 3:​5, 6 ላይ ማሰላሰላችን ድፍረት ሰጥቶናል።”

በላውራ እና በማሪያ ላይ እንደታየው አካላዊ እክል ቢኖርም በጽናት መቀጠሉ አምላክን ያስከብራል። ሐዋርያው ጳውሎስ ‘የሥጋው መውጊያ’ ይኸውም ያለበት አካላዊ እክል ሳይሆን አይቀርም እንዲወገድለት ጸልዮ ነበር። ሆኖም አምላክ “ጸጋዬ ይበቃሃል፣ ኃይሌ በድካም ይፈጸማልና” በማለት መልሶለታል። አዎን፣ አምላክን ማገልገል እንችል ዘንድ ያለብን አካላዊ እክል የግድ መወገድ አያስፈልገውም። ሙሉ በሙሉ በአምላክ ላይ መታመን ሁኔታችን የፈቀደልንን ያህል የተሻለ ነገር እንድናደርግ ሊረዳን ይችላል። ጳውሎስ ‘የሥጋውን መውጊያ’ የተመለከተው በዚህ መንገድ ስለነበረ “ስደክም ያን ጊዜ ኃይለኛ ነኝ” ለማለት ችሏል። (2 ቆሮንቶስ 12:​7, 9, 10) ከጥቂት ዓመታት በኋላ ጳውሎስ “ኃይልን በሚሰጠኝ በክርስቶስ ሁሉን እችላለሁ” በማለት ጽፏል።​—⁠ፊልጵስዩስ 4:​13

በዘመናችንም አምላክ ራሳቸውን ለእርሱ በወሰኑ ወንዶች፣ ሴቶችና ልጆች አማካኝነት አስደናቂ ሥራዎችን በማከናወን ላይ ይገኛል። ከእነዚህ መካከል የተወሰኑት በተለያየ ምክንያት አካላዊ እክል አለባቸው። በአምላክ መንግሥት ሥር መለኮታዊ ፈውስ እንደሚያገኙ ተስፋ የሚያደርጉ ቢሆንም በእርሱ አገልግሎት ለመሳተፍ ምንም ዓይነት ጥረት ሳያደርጉ እንዲሁ ቁጭ ብለው ከችግሮቻቸው የሚገላገሉበትን ጊዜ አይጠባበቁም።

አንድ ዓይነት አካላዊ እክል አለብህ? አይዞህ! ጳውሎስ፣ ላውራ እና ማሪያ እንዳሳዩት ዓይነት እምነት ልታሳይ ትችላለህ። በጥንት ጊዜ ለነበሩት ታማኝ ወንዶችና ሴቶች እንደተባለው ሁሉ ለእነርሱም “ከድካማቸው በረቱ” ሊባልላቸው ይችላል።​—⁠ዕብራውያን 11:​34

[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ማሪያ

ላውራ

[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ላውራ አውቶቡስ ላይ እንድትወጣ ማሪያ ስትረዳት

[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

“ውሾች ፈረስ አክለው ስለሚታዩን በጣም ያስፈሩናል”

ከታች:- ላውራ እና ማሪያ እንዲሁም መጽሐፍ ቅዱስ የሚያስጠኗቸው ሰዎች